Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የሞረሽ እንቅስቃሴ ላልተገለጸለን አንዳንድ ነጥቦች

$
0
0

ከሞረሽ ደጋፊ፣ ረቡዕ ሰኔ ፫ ቀን ፪ሺህ፮ ዓ.ም.

moresh
ሞረሽ ወገኔ በወያኔ ዘረኛ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ እቅድና እንቅስቃሴ መሠረት፣ በአገራችን በኢትዮጵያ በአማራ ጎሳ ላይ በየአቅጣጫው እየደረሰ ባለው መጠነ ሰፊ ጉዳት ምክንያት ብሶት የወለደው ድርጅት ነው። በሀገራችን ታሪክ ብዙ ሳንጓዝ «አምባገነን» የሚባለው የወታደራዊው ደርግ የግዛት ዘመን ሳይቀር፣ ጎሳዎችን ሳይለይ በፖለቲካ አመለካከት ምክንያት ኢትዮጵያውያንን በግድያ ንብረታቸውንም ለመንግሥት በማድረግና በመውረስ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰባቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። የአማራው ጎሳ አባላት እንደሌሎች ኢትዮጵያውያን ተጠቂ የነበሩ መሆናቸው የሚካድ አይደለም። በኢሕአፓም ሆነ በሌሎች የተቃውሞ ትግሎች የተሳተፉ፣ መስዋዕትነት የከፈሉ፣ በደርግ በኩልም በመሆን በተቃዋሚዎቹ ዒላማ ተደርገው የተገደሉ የዚሁ ጎሳ አባላት ብዙ ናቸው። ከዚያ በፊት የነበረውንም የቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት «ፍትሐዊ አይደለም» ብለው ከተነሱት የእንቅስቃሴ መሪዎችና ሰለባዎች ውስጥ ከአማራው ጎሳ የተወለዱ፣ ብዙ ለፍትሕ የቆሙ እንደነበሩ፣ ወያኔዎች ሳይቀር ይመሰክራሉ። ለአብነትም እነ የንዋይ ወንድማማቾች ብርጋዴር ጄኔራል መንግሥቱ እና ግርማሜ ንዋይ፣ ዋለልኝ መኮንን እና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ «የኢትዮጵያ አስተዳደር ትክክል አይደለም» በሚል መስዋዕትነትን የከፈሉ ከአማራ ጎሳ የተወለዱ ኢትዮጵያውያኖች እንጂ «አማራ ነን» በሚል የተንቀሳቀሱ አልነበሩም።


ወያኔዎች በኢትዮጵያ ውስጥ በቁጥር አናሳ መሆናቸውን ስለሚገነዘቡ፣ በስልጣን ይቀናቀነኛል የሚሉትን ወገን ሌሎችን አስተባብሮ ማጥቃት እንደ ስትራተጂ የሚጠቀሙበት ነው። በመሆኑም በኢትዮጵያ ተፈጥረው ለነበሩ ችግሮች ብቻ ሳይሆን ያልነበረ ችግርን እንደነበረ አድርጎ፣ ለዚህም የአማራውን ጎሳ ተጠያቂ ማድረግ፣ የአጭር ጊዜ ፍላጎቱን እንደሚያሳካለት በማሰብ ነው። ስለሆነም በትላልቅ ጎሳዎችም ሆነ በአናሳ ጎሳዎች እንዲጠላና ዘመቻ እንዲካሄድበት፣ ከፍተኛ የሆነ የጥፋት ሥራ ሠርቷል። የዋህ የሆኑ የዚህ የወያኔ እኩይ የሆነ አስተሳሰብ ሰለባ የሆኑ ጎሳ አባላትም ለዘመናት አብረዋቸው የኖሩ የአማራ ጎሳ ተወላጂ የሆኑ ጎረቤቶቻቸው ላይ ከ«ውጡልን» አንስቶ እስከ ግድያ የሚደርሱ ብዙ በደሎች ሲደርስባቸው በጥቃቱ በመተባበር ወይም ዝም በማለት አሳልፈዋል፣ ወይም በማሳለፍም ላይ ናቸው። ይህንን በአማራው ጎሳ ላይ ያነጣጠረ ጭፍን ጥላቻ ማንኛውም ፍትሕን የሚሻ ዜጋ ሁሉ ሊቃወመውና ሊያስቆመው ይገባ ነበር። ሆኖም ግን ወያኔ አገሪቱን ከተቆጣጠረ ጀምሮ በአማራው ጎሳ ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት በተጠናከረ መልኩ ሲፈጸም እናያለን።


በተደራጀ ኃይል ጥቃት የሚደርስባቸው ተጠቂዎች ከሚደርስባቸው ጥቃት ሲሸሹና የመጠቃት ፍራቻ ሲኖራቸው በጋራ መከላከልን መሻት ተፈጥሯዊ ክስተት ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ዘርን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ አደረጃጀት መኖር እንደሌለበት የሞረሽ ወገኔ መሥራቾች ጠንቅቀው ያውቃሉ። የፖለቲካ ድርጅቶች ዘርን መሠረት ሲያደርጉ የእድገት ደረጃን ያለማወቅና ሰዎችን አንድ የሚያደርጋቸው ቀለማቸው፣ ቋንቋቸው ወይም ባህላቸው ብቻ ሳይሆን አመለካከታቸው መሆኑን አለመገንዘባቸውን የሚያሳይ ነው። የሞረሽ መሥራቾች የወያኔን የጎሳ ፖለቲካ ቢቀበሉት ኖሮ ቀደም ብለው የፖለቲካ ድርጅት በመሠረቱ ነበር። ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ መጠበቅም ባላስፈለገ ነበር።


ሞረሽ እንደ መርህ በየትም ቦታ የተረገጠች ፍትሕን ትክክል አይደለም ብሎ ያምናል፣ እንዲስተካከልም ድምጽ ያሰማል። በመሆኑም በኦሮሞም፣ በጋምቤላም፣ በሶማሌም፣ በትግሬም ወይም በሌሎች ጎሳዎች በገዢውም ሆነ በሌላ ሥልጣን ፈላጊ ቡድን የሚደርሰውን ጥቃት ሁሉ አጥብቆ ይቃወማል። ሞረሽ ኢትዮጵያ የብዙ ጎሳዎች ደሴት እንደመሆኗ መጠን አንዱ ጎሳ ተጎድቶ ወይም አንዱ ጎሳ የሌለበት ኢትዮጵያ አትኖርም ብሎ ያምናል። ስለሆነም የአማራ ጎሳ የሌለባት ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ አትባልም፣ የኦሮሞ ጎሳ የሌለባት ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ አትባልም፣ የትግሬ ጎሳ የሌለባት ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ አትባልም እንዲሁም ሌሎች ጎሳዎች የሌሉባት ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ አትባልም። በመሆኑም አንዱ ሲበደል ተበዳዩ ብቻ ሳይሆን ሌላውም ሁሉ ቁጭቱን ሊገልጽና ድርጊቱን ሊቃወመው ይገባል። ያ ሲሆን የሚፈራው ሥልጣን የያዘው ሳይሆን ሕዝብ ይሆናል ማለት ነው። ትክክለኛው ፍርሀትም ይሄው ነው።


ሞረሽ በዚህ መርሁ የማንኛውም ጎሳ አባላት በግልም ይሁን በቡድን መበደል የተቃውሞ ድምጹን አጉልቶ ያሰማል። ሌሎች ጎሳዎች በዛ ያሉ ድምጽ የሚያሰሙ ቡድኖችና ድርጅቶች ቢኖሯቸውም የአማራው ጎሳ ግን በታላቁ የኢትዮጵያ ልጅ በፕሮፌሰር አሥራት ተጀምሮ ከነበረው መአሕድ በስተቀር ለጎሳው አቤቱታ የሚያሰማ፣ እየደረሰበት ያለውን ጉዳት የሚቃወም፣ የተሰባሰበ ቡድን የለውም። በሌላ በኩል ግን በወያኔ መንግሥት አስተባባሪነት በአማራው ጎሳ ላይ በየቦታው እየደረሰ ያለው ጉዳትና ጥቃት ለመለካት የሚያስቸግር ነው። በመሆኑም ሞረሽ ወገኔ በአማራው ጎሳ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማሳወቅ አቅሙ የፈቀደውን ትግል የሚያደርግ ከመሆኑም በተጨማሪ ሌሎች አግባብነት ያላቸው መንገዶችን በመጠቀም በደል የሚፈጽሙትና የሚያስፈጽሙትን ከሕግ ፊት ለማቅረብ የበኩሉን ጥረት ያደርጋል። ሞረሽ ወገኔ ለአማራው የሚመኘውን ሰብአዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሌሎች መብቶች ለማንኛው የሀገሪቱ ጎሳ አባላት እንደሚመኚና ለተፈጻሚነቱም ድምጹን በማሰማት የመታገያ ስልቱ አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋል። በዚህ አጋጣሚ ሞረሽ ሊገልጸው የሚፈልገው ነገር ቢኖር አሁን ባለበት ሁኔታ የሲቪክ ድርጅት እንጂ የፖለቲካ ድርጅት አለመሆኑን ነው። እንደ ሞረሽ እምነት የጥቁሮችን መብት በማስከበር በእንቅስቃሴ ውስጥ ነጮች እንደተሳተፉና መስዋዕትነት እንደከፈሉ ሁሉ የአማራው ጎሳ የሚደርስበትን በደል «አግባብ አይደለም» ለማለትና የሚደርስበትን በደል ለማስቆም የየትኛውም ጎሳ አባላት ተሳትፎ ማድረግ አግባብነት አለው ይላል።


የሀገራችን ታሪክ እንደማንኛውም ሀገር ታሪክ መልካምም መጥፎም ገጽታ ይኖረዋል። የሰው ልጅ የሠራው ሥራ የሚገመገመውም በወቅቱ ባለው መለኪያ እንጂ ዘመናትን አሻግሮ በማይመሳሰሉ ዘመናት ባሉ መለኪያዎች መሆን የለበትም። ያለፈውን መልካም ነገር መሠረት አድርጎ ከተሠሩ ስህተቶች ተምሮ መልካም ነገርን ማምጣትና በእጁ ያለውን የአሁኑን ጊዜ በሚገባ በመጠቀም ወደፊት የሚፈጠር እውነታን መቀየርና የሚጻፍ ታሪክን መልካም እንዲሆን ማድረግ ተገቢ ነው። ይህ ለጋራ ዕድገት የተሻለ ነገርን ያመጣል። ያለፈ አፈ ታሪክ ላይ በማተኮር እድገት አይመጣም። እድገት የሚመጣው በአግባቡ የተተለመ ራዕይ ላይ በማተኮርና ተገቢውን በመተግበር ነው። በጥላቻ እድገት አይመጣም። ጥላቻ የሚያመጣውን ውጤት ለማየት ብዙ መመራመር አያስፈልግም። በዓለም ላይ ያሉ ትላልቅ ችግሮች የጥላቻ ውጤቶች ናቸው። ሞረሽ ይህንን ጠንቅቆ ያውቃል። በአማራው ላይ በወያኔ መሪነት በመጀመሪያ በሌሎች ጎሳዎች ጥላቻ እንዲደርስበት ከዚያም በመቀጠል በንብረቱና በሕይወቱ ላይ ጉዳት እንዲደርስበት ሲደረግ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ተቆጥሯል። ልብ እንበል፥ በእናት ማህጸን ውስጥ ያሉ ያልተወለዱ ጽንሶች፣ ምንም የማያውቁ ሕጻናት ሳይቀር ታርደው እንዲገደሉ ተደርጓል። ሠርተው ከመብላት ውጭ ምንም የፖለቲካ አስተሳሰብና የሥልጣን ፍላጎት የሌላቸው ገበሬዎች ከኖሩበትና ሀብትና ንብረት ከአፈሩበት ቦታ ያለምንም ነገር ባዶ እጃቸውን ተፈናቅለው ቤት አልባ መንገድ ተዳዳሪ ለማኞች እንዲሆኑ ተደርገዋል። ይህንን ድርጊት በተደራጀ መልኩ መቃወምና ማስቆም የግድ ይሆናል። ለዚህም ነው ሞረሽ ወገኔ የአማራ ድርጅት የተቋቋመው። በመሆኑም ሞረሽ በወያኔ የፖለቲካ ፍልስፍና መሠረት የተፈጠረ ሳይሆን በወያኔ እኩይ ሥራ ምክንያት መጠነ ሰፊ የሆነ የጥፋት ዘመቻ እየደረሰበት ያለውን የአማራ ጎሳ ለመታደግ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ የተቋቋመ ነው።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>