Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

አበበ ተካ፡ ሀገሩን በሴት ፍቅር የለወጠው ድምፃዊ

$
0
0

abebe teka
ሳምሶን አብ
(በቁም ነገር መጽሔት ቅጽ 13 ቁጥር 178 ግንቦት 2006 ታትሞ የወጣ)

በሀገራችን ጥቂት የሙዚቃ አልበም አሣትመው እጅግ ከፍተኛ ተወዳጅነት ካተረፉ ድምፃውያን መካከል አንዱ ነው አበበ ተካ፡፡ በተለየ የአዘፋፈን ስልቱና ሙዚቃን በእውነተኛ ስሜት ተውጦ በማቀንቀኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም ቀልብ ሳቢ አቀራረቡ በ1989 ዓ.ም የዓመቱ ምርጥ ድምፃዊ ተብሎ የወርቅና የገንዘብ ሽልማት ማግኘት ችሏል፡፡ በእርግጥ ከአዘፋፈን ችሎታው በላይ የዘፈኖቹ በጥልቀት ፍቅርን የመግለፅ አቅምም ከሠው ልብ ውስጥ በቀላሉ መግባት የሚችሉ ሥራዎች እንዲኖሩት ሣይረዱት አልቀሩም፡፡ መድረክ ላይ ዓይኖቹን ጨፍኖ በታላቅ ተመስጦ ሲያቀነቅን የድምፃዊው ልብ ክፉኛ በፍቅር የተጎዳ መሆኑ ከፊቱ ላይ ይነበብ ነበር፡፡ ፍቅር አቅልጦ ቀጥቅጦ የሠራው ድምፃዊ ነው፡፡ በወቅቱ ኑሮን ለማሸነፍ ከአጠገቡ የራቀችው የፍቅር አጋሩ የዘፈኖቹ ዋና ተዋናይ ነበረች፡፡ እነ ‹‹ሠው ጥሩ››፣ ‹‹ምንድነው ቀለበት››፣ ‹‹በይ ካልረሣሽኝ›› እና ‹‹ አገሯ ወዲያ ማዶ›› የመሣሠሉት ድንቅ ሥራዎች የፍቅሩ ትሩፋቶች ናቸው፡፡

በፍቅሯ ጨርቁን መጣሉ፤ በናፍቆቷ መብሠልሠሉ፣ ከእርሷ በመለየቱ ‹‹ቀኑም ጨለማ ሌሊቱም ጨለማ›› የሆነበት መምሠሉ ከኃያል ጭንቀቱ የተፀነሡ ጊዜ አይሽሬ ሙዚቃዎች በግጥምና ዜማ ደራሲዎች እገዛ ለአድናቂዎቹ ጆሮ እንዲደርሱ ምክንያት ሆነ፡፡ አዎ ምናልባትም ከድምፃውያን መካከል የአበበ ተካን ያህል ለፍቅር ታላቅ መስዋዕትነት የከፈለ ያለ አይመስልም፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ህይወትን መለወጥ በጣም ከባድ ነው፡፡ እርሷም ኑሮዋን ለማሻሻል ነው ከሀገር የወጣችው›› የሚለው ትሁቱ አፍቃሪ የተሠበረ ልቡን በዜማ ብቻ እያስታመመ ፍቅረኛው እስከምትመጣ ለመጠበቅ አልወደደም፡፡ እናም እርሷን ፍለጋ ተሠደደ፡፡ ከሀገር ሀገርም ተንከራተተ፡፡ በተጭበረበረ ፓስፖርት በተሠኘ ምክንያትም በአሜሪካ አንድ እስር ቤት ለአምስት ዓመት በእስር አሣለፈ፡፡ ከዚህ ሁሉ መስዋዕትነት በኋላ ምኞቱ ሞልቶ እንደ ዓይኑ ብሌን የሚሳሳላትን ሴት ከእቅፉ አስገባ፤ በትዳር ተጣመሩ፡፡ ልጆችም አፈሩ፡፡ሶስት ጉልቻ ቆመ፡፡

ዛሬ አበበ የወደዳትን ሴት አግብቶ የሞቀ ትዳር ከጀመረ ረጅም ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የሙዚቃው አድናቂዎች ግን የምንወዳቸውን ሌሎች ሥራዎቹን ማግኘት የህልም ያህል ርቆናል፡፡ አበበ ሙዚቃን በትዳሩ ሳይለውጣት አልቀረም፡፡ ለነገሩ የሠው ልጅ እውነተኛ ችሎታ የሚገለጠው በማጣቱ ዘመን ነው ይባላል፡፡ አበበ ፍቅር ያጣ ጊዜ ድንቅ ሙዚቃዎችን ሰርቷል፡፡ ዛሬ ፍቅርን ሲጠግብ ሙዚቃው ቦታ ያጣ ይመስላል፡፡ እንጂማ ሠው እንዴት ከአሥራ አምስት ዓመታት በላይ አድናቂዎቹን ዘንግቶ ይኖራል? ለብዙ አርቲስቶቻችን ያልተመለሠው ‹የአሜሪካ ጅብ›› አበበን ከበላው ረጅም ዓመት አስቆጥሯል፡፡ እነ ‹‹ሠው ጥሩ››፣ እነ ‹‹ወፍዬ››፣ እነ ‹‹ምንድነው ቀለበት›› ተተኪ የማፍራት አቅማቸው መንምኗል፡፡ አዎ አበበ ሙያውን በትዳር ሸጧል፡፡ እንጂማ ከአሥራ አምስት ዓመት በላይ በሆነ ጊዜ እንኳን አንድ አልበም፤ አንዲት ሀገርስ ትሠራ የለም? ታዲያ አበበን ምን ነካው?
የተጣልን ያህል ለሚሠማን አድናቂዎቹ የእርምታህል የለቀቃት ነጠላ ዜማ በቅርቡ በዩቲዩብ ድረገፅ ተጭና እየተመለከትን ነው፡፡ እንደ ማይክል ቦልተን ፍቅርን ጥሩ አድርጎ ለማዜም የተፈጠረ የሚመስል አንደበቱ አሁን ተራውን ለሀገሩ ሰጥቷል፡፡

‹የፍቅር ገዳም የውበት ፍሬ››
ይናፍቀኛል ከአንቺ ማደሬ››
እያለ ያንቆለጳጵሳትም ይዟል፡፡ አበበ የዛሬ እጦቱ ሴት አይደለችም፡፡ ዛሬ ሀገሩን ነው ያጣው፡፡ ፍቅረኛውን ተከትሎ ጥሏት የሄደችው ሀገር ዛሬ የልቡ ሲሞላ ትናፍቀው ጀምራለች፡፡ እናም ውሎ አድሮ በለቀቀው ነጠላ ዜማለ፡-
‹‹ሁሌም ሀገሬን ምድሬን ይለኛል
ሂድ ይለኝና ሆድ ይብሠኛል
አፈር መሬቱም ይናፍቀኛል
ገራገር ህዝቡም ፍቅሩ ይገድለኛል›› እያለ ድለላ የሚመስል ነገር ጀምሯል፡፡

የማለቃቀስ ስልት ባለው በዚህ ዘፈን አበበ ተካ ወደ ሀገሩ እንዳይገባ ማዕቀብ ተጥሎበት ስሞታውን ለሌሎች የሚያሠማ ነው የሚመስለው፡፡ ታዲያ ይህን የድምፃዊውን በቁጭት መብሠልሠል ስመለከት ታዲያ ለምን ወደ ሀገሩ አይመጣም ብዬ ነበር ራሴን የጠየቅኩት፡፡ ለነገሩ ሠው ሀገር ሆኖ ‹‹ሀገሬ ናፈቅሽኝ ልሙትልሽ ልቀበርልሽ›› አይነት ዘፈኖችን ማቀንቀን ሌሎችም ድምፃውያን የበሉበት ሙድ ነው፡፡ አሜሪካ እቅፍ ውስጥ ተቀምጦ ስለ ኢትዮጵያ ‹‹ምድረ ገነትነት›› ማቀንቀን የብዙ ድምፃውያን ልማድ ሆኗል፡፡ አበበ ተካም ገና ወደ ሀገሩ የመመለሱ ደመና እንኳ ሣይታይ
‹‹ይናፍቀኛል መች ያስተኛኛል
ሀገሬን ሀገሬን ይለኛል››
ማለቱ የዚሁ ልክፍት አንድ አካል ነው፡፡ እንጂማ ፍቅረኛውን ፍለጋ ወደ ማያውቃት አሜሪካ የሄደ ሠው የናፈቀውን ህዝብ ፍለጋ ወደ ወጣበት ሀገር መመለስ ባልራቀው ነበር፡፡ ‹‹ያለቃቀሰላትን›› የፍቅር አጋር ዕድለኛ ሆኖ አግኝቷት ሶስት ጎጆ አቁሟል፡፡ ታዲያ መልሶ ላጣት ሀገሩ ‹‹ሌላ ለቅሶ››
ለምን አስፈለገው? ሀገሩ እንደሁ የትም አልሄደችም፡፡ ትላንት ጥሏት የሄደችበት ቦታ ነው ያለችው፡፡ እንዲያውም ከውጪ የሚመጡ ኢትዮጵያውያንን እጅ ስሞ የመቀበል አባዜ ስለተጠናወታት ተንከባክባው ለማኖር አትሠንፍም ነበር፡፡ ታዲያ አበበ ተካ የእውነት ‹‹ሁሌም ሀገሬን ይለኛል›› የሚለን ከልቡ ከሆነ ለምን ወደ ሀገሩ አይመለስም? አንዲትሴት ለመፈለግ ያልሠነፈ ጉልበት እንዴት ሀገርን ያህል የማትጠፋ ግዑዝ አካል መፈለግ ይከብደዋል?

በርግጥ ይሄ የብዙ ድምፃውያኖቻችን ችግር ነው፡፡ ሀገራቸውን ለቅቀው ይወጡናየሌላትን ሁሉ ቅድስና ሠጥተው በዘፈን ያንቆለጳጵሷታል፡፡ ለሀገር የምታስቡ ከሆነ ሆድ የሚያስብስ ዘፈናችሁን ትታችሁ ምናለበት ሆድ የሚሞላ ሥራ ብትሠሩ? የሆነች ገንዘብ አዋጥቶ ኢትዮጵያውያንን የሚረዳ የበጎ አድራጎት ድርጅት ማቋቋምምኮ አንድ መልካም ተግባር ነው፡፡ ለዘፈኑ ከሆነማ ታላላቆቹ ድምፃውያን እነ አልፋ ብሎንዴም ለኢትዮጵያ ዘፍነዋል፡፡ ስለዚህ ‹‹ሀገሬን ሀገሬን ይለኛል›› ማለት ወይ እየሰጡ ወይ እየመጡ ነው እንጂ እንዲሁ ‹‹ሀገሬን ሀገሬን›› ለማለትማ እዚህ ያለነውስ መች አነስን?


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles