Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ኦቦ ዓለማየሁ አቶምሳ እንዴት በምግብ መመረዝ ሊሞቱ ይችላሉ? –በምግብ መመረዝ የሚከሰቱ 4ቱ ገዳይ በሽታዎች

$
0
0

የምግብ መመረዝ ለበርካታ ሰዎች የሞት መንስኤ ሲሆን ይስተዋላል፡፡ በቅርቡ እንኳ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ አለማየሁ አቶምሳ በምግብ መመረዝ እንደሞቱ ሲነገር እንሰማለን፡፡ ውድ አዘጋጅ፤ የምግብ መመረዝ እንዴት ይከሰታል? በምን ያህል ጊዜስ ይገድላል? ሰዎች በምግብ ተመረዙ ሲባል ምን ማለት ነው? የምግብ መመረዝ አይነቶች ስንት ናቸው? በምግብ መመረዝ የተጠቃ ሰው የመዳን ተስፋስ ይኖረዋል? ሰዎች በምግብ የሚመረዙት ባለማወቅ ነው ወይስ ሆን ተብሎ በሰዎች በተቀነባበረ ዘዴ? የምግብ መመረዝ ችግር በእኛ ሀገር Food Poison የሚባለው ነው ወይስ ይለያል? በዓለማችን በምግብ መመረዝ ለሞት ወይም ለህመም የተዳረጉ ሰዎችስ ይኖሩ ይሆን?
በጥቅሉ የምግብ መመረዝ ችግርን በሚመለከት ለሌሎች ትምህርት ሊሰጥ በሚችል መልኩ ማብራሪያ ብትሰጡኝ ደስተኛ ነኝ፡፡
ጫላ ዋቆ ከሚኒያፖሊስ

Alemayehu Atomsa
ከዶ/ር ዓብይ ዓይናለም የተሰጠ ምላሽ፦

በእንግሊዝኛው Food poisoning ወይንም Food borne illness ተብሎ የሚጠራው የምግብ መመረዝ በሽታ ሰዎች የተመረዘ ወይም በባክቴሪያ፣ በቫይረስና በፓራሳይቶች የተጠቃ ምግብን በሚመገቡበት ጊዜ የሚከሰትና ሰዎችን ከቀላል በሽታ አንስቶ እስከ ሞት ሊያደርስ የሚችል ህመም ነው፡፡ ይህ በሽታ ምግቡ በሚመረትበት ጊዜ ወይንም በቤት ውስጥ በሚበስልበት ጊዜ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ወደ ውስጡ በሚገቡ መርዛማ ነገሮች ምክንያት ሊከሰት የሚችል ነው፡፡
ሰዎች በምግብ መመረዝ በሚጠቁበት ጊዜ ትውከት (nausea)፣ ማቅለሽለሽና ተቅማጥ (vomiting or diarrhea) ወዲያውኑ የሚከሰቱ ምልክቶች ናቸው፡፡ እነኚህ ምልክቶች ደግሞ ምግቡን ከተመገብን በሰዓታት ጊዜ ውስጥ የሚታዩ ናቸው፡፡ በእርግጥ ብዙውን ጊዜ የምግብ መመረዝ ቀላል እና ያለ አንዳች የህክምና ክትትል ሊወገድ የሚችል ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ ከባድና የረዥም ጊዜ የህክምና ክትትልን የሚጠይቁ ናቸው፡፡ እንደተወሰደው መርዛማ ንጥረ ነገር ህመሙ ስር እየሰደደ እስከ ሞትም ሊያደርስ የሚችል ነው፡፡

የምግብ መመረዝን የሚያስከትሉ ነገሮች

በመላው ዓለም በየጊዜው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በምግብ መመረዝ በሽታ ይጠቃሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ ለምግብ ደህንነትና ንፅህና ከፍተኛ ትኩረት በሚሰጡ በአውሮፓና በአሜሪካ ውስጥ በሚገኙ ሀገሮች ውስጥ በዚህ ችግር የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ለበሽታው በዋነኛነት የሚጠቀሰው ምክንያት ደግሞ የምግብ በመርዛማ ነገሮች መበከል (contaminated food) ነው፡፡
የምግብ መመረዝ የተለያዩ ህመሞችን ያስከትላል
- የጨጓራ ህመም (upset stomach)
- የሆድ መነፋት (abdominal cramps)
- ማቅለሽለሽና ተውከት (nausea and vomiting)
- ተቅማጥ (diarrhea)
- ትኩሳት (fever)
- የሆድ ድርቀት (dehydration)
በምግብ መመረዝ ምክንያት ከሚከሰቱ የህመም አይነቶች ውስጥ የሚጠቀሱ ሲሆኑ ህመሞቹም እንደ ሰውነታችን መመረዝ ቀላል እና ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡

ባክቴሪያ እና ቫይረስ

ባክቴሪያ እና ቫይረስ የምግብ መመረዝን ከሚያስከትሉት ነገሮች ውስጥ በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የህመሙ ምልክትና የፅናቱ መጠን ምግቡ እንደተበከለበት ባክቴሪያ ወይም ቫይረስ መጠንና አይነት ሊለያይ ይችላል፡፡

ፓራሳይትስ (ጥገኛ ህዋሳት)

ፓራሳይቶች በሆድ ውስጥ የሚፈጠሩና ምግብን እና ደህንነትን ከሌሎች ህዋሳት በመውሰድ የሚኖሩ ጥገኛ ህዋሳት ናቸው፡፡ እነኚህ ህዋሳት ደግሞ የምግብ መመረዝን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ በጥናት ተረጋግጧል፡፡ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከዋናዎቹ ምግብ ወለድ ጥገኛ ህዋሳት መካከል ባለ አንድ ሴል ህዋስ (protozoa) ክብ ህዋሳት (roundaxnmt) እና የኮሶ ትሎች (topwarm) ይገኙበታል፡፡

መርዛማ ንጥረ ነገሮች

በእርግጥ ብዙውን ጊዜ የምግብ መመረዝ የሚከሰተው በባክቴሪያ፣ በቫይረስ እና በፓራሳይትስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አልፎ አልፎም ቢሆን በተፈጥሮ ወይም በኬሚካል መርዛማ ነገሮች ምግብ ውስጥ መጨመር የተነሳ አደገኛና ገዳይ የምግብ መመረዝ ሊከሰት ይችላል፡፡

አለርጂ

አንዳንድ ሰዎች ለተለያዩ ምግቦች ባላቸው አለርጂነት የተነሳ የምግብ መመረዝ ችግር ሊከሰትባቸው ይችላል፡፡ ብዙውን ጊዜ ለአለርጂነት ከሚያጋልጡት የምግብ አይነቶች መካከል ለውዝ፣ ወተት እና እንቁላል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ከባድ የምግብ መመረዝ
በአሜሪካ ውስጥ ከስድስት ሰዎች መካከል አንዱ በየዓመቱ በምግብ መመረዝ ችግር ይጠቃል፡፡ ይህም ማለት 48 ሚሊዮን አሜሪካውያን በየዓመቱ የዚህ ችግር ሰለባዎች ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ይህም ሆኖ አብዛኛዎቹ ሰዎች ህመሙ ብዙም ጉዳት ሳያስከትልባቸው ያለ ህክምና ክትትል ወይም በቀላል ህክምና ይፈወሳሉ፡፡ ይህም ሆኖ ጥቂቶችና ህመሙ ከፍተኛ ህመም ሊያስከትልባቸውና እስከሞትም ሊያደርሳቸው እንደሚችል ተረጋግጧል፡፡ በምግብ መመረዝ ምክንያት ከሚከሰቱና እስከ ሞት ሊያደርሱ ከሚችሉ ህመሞች መካከል የሚከተሉት በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡

1. የኩላሊት በሽታ

ሄሞላይቲክ ዩሪሚክ ሲንድሪም (Hemolytic uremic syndrome (HUS)) በምግብ መፈጨት ሂደት ውስጥ መርዛማ ነገሮች ሲፈጠሩና ቀይ የደም ሴሎች በሚድሙበት ጊዜ የሚከሰት አደገኛ በሽታ ነው፡፡ በሽታው አደገኛ የሚሆነው በኩላሊት ላይ ቁስለትን የሚያስከትል በመሆኑ ነው፡፡ HUS የሚከሰተው ኢ-ኮሊ (E-coli) በተባሉት የባክቴሪያ አይነቶች ምክንያት ነው፡፡ ሄሞላይቲክ ዩሬሚክ ሲንድረም ብዙውን ጊዜ ህፃናትን የሚያጠቃ ቢሆንም በአዋቂዎች ላይ የሚከሰትና ኩላሊትን የሚያጠቃ የህመም አይነት ነው፡፡

strong>2. የአጥንት መገጣጠሚያ በሽታ (Chronic Arthritis)

ሺጌሳ ወይንም ሳላሞኔላ በተሰኙት ህመሞች የተጠቁ ሰዎች አንዳንዴ በአጥንት መገጣጠሚያዎቻቸው ላይ ህመም ሊሰማቸው ይችላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እነኚህ ሰዎች የአይን እብጠት እና ሽንት በሚሸኑበት ጊዜ የህመም ስሜት ይሰማቸዋል፡፡ ይህ የህመም አይነት የሚከሰተው በአጥንት መገጣጠሚያዎች አካባቢ በሚፈጠር የህመም ስሜት (reactive arthritis) ምክንያት ነው፡፡ ይህ ህመም እንደ ሁኔታው ለወራት ወይንም ለዓመታት ሊዘልቅ የሚችል ሲሆን ስር የሰደደ የአጥንት መገጣጠሚያ አካባቢ ችግርን ሊያስከትል የሚችል ነው፡፡ ህመሙ አንዴ ከተከሰተ በህክምና ለመዳንም ያስቸግራል፡፡
3. የአዕምሮና የነርቭ ችግር
የምግብ መመረዝን የሚያስከትሉ የባክቴሪያ ዝርያዎች (Listeria) ወዲያውኑ ካልተወገዱ የአንጎል ገለፈትን በማጥቃት Meningitis የተባለውን አደገኛ አእምሮ ነርቭ ህመም ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ አንድ ጨቅላ ህፃን ገና እንደተወለደ በሊስቴሪያ ባክቴሪያዎች ከተጠቃ የህፃኑ የወደፊት እጣ ፈንታ የአእምሮ ህመም (mental retardation) በሚጥል በሽታ፣ የአካል መሽመድመድ፣ አይነ ስውርነት፣ ወይም መስማት የተሳነው ሊሆን ይችላል፡፡

ጉሌይን ቤር ሲንድረም (Guillain Bare Syndrome) የሰውነታችንን ነርቭ የሚያጠቃ የህመም አይነት ነው፡፡ ይህ በሽታ የሚከሰተው ደግሞ የሰውነታችን ተፈጥሯዊ በሽታን የመከላከል ሲስተም የራሳችንን ነርቭ በሚያጠቃበት ጊዜ ነው፡፡ ይህ የህመም አይነት ከፍተኛ የህክምና ክትትልን የሚጠይቅና በጊዜው መፍትሄ ካላገኘ የአካል መሽመድመድንና አልፎም ተርፎ ህልፈተ ህይወትን ሊያስከትል የሚችል ነው፡፡

በአሜሪካ ውስጥ በየዓመቱ 3,000 የሚሆኑ ሰዎች ከምግብ መመረዝ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ህመሞች ምክንያት ይሞታሉ፡፡ ከእነኚህ ሟቾች ውስጥ 88 በመቶ የሚሆኑት የህመማቸው ምክንያት ሳልሞኔላ፣ ቶክስፕላዝማ፣ ሊስቴሪያ፣ ኖርቫይርስ እና ካምፓይሎባክተር ተብለው የሚጠሩት ህዋሳት ናቸው።
ሌሎች ሞትን የሚያስከትሉና ምግብ ወለድ የሆኑ የህመም አይነቶችም አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህልም ጥሬ ዓሣን በመመገብ ምክንያት የሚከሰተውን ቫይብሮ ኢንፌክሽን የተባለውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህ የህመም አይነት የደም ዝውውር ሂደትን በመመረዝ እስከ ሞት ሊያደርስ የሚችል ነው፡፡ በዚህ በሽታ ከሚጠቁ ሰዎች መካከል ግማሽ ያህል የሚሆኑት እንደሚሞቱና ህመሙም አጣዳፊና በሁለት ቀናቶች ውስጥ የሚገድል እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡
4. በምግብ መመረዝ የተጠቁ ታዋቂ ሰዎች
ባክቴሪያ ድሃ ሆነ ሀብታም፣ የተማረ ይሁን ያልተማረ፣ ታዋቂ ይሁን አንዳችም እውቅና የሌለው ሰው በአጠቃላይ ለማንኛውም የሰው አይነት ደንታ የሌለው ህዋስ ነው፡፡ አንድ ሰው ሆን ተብሎ የተመረዘም ይሁን በተለያየ ምክንያት በባክቴሪያ፣ በቫይረስ በፓራሳይት ወይም በመርዛማ ንጥረ ነገሮች የተሞላ ምግብን ከተመገበ ይታመማል፣ ህመሙ በቀላሉ ሊድን አሊያም እስከ ሞት ሊያደርሰውም ይችላል፡፡ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ታዋቂ ሰዎች በምግብ መመረዝ ከተጠቁት ዝነኞች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

- ክራንቤረስ የተባለው ታዋቂ የሙዚቀኞች ቡድን በማርች 2012 አንደኛው ዘፋኝ በምግብ መመረዝ በመጠቃቱ ምክንያት በአውስትራሊያ ሊያቀርብ የነበረውን ዝግጅቱን ለመሰረዝ ተገዷል፡፡
- ዝነኛው ድምፃዊ ኤልተን ጆን በዚሁ በሽታ በመጠቃቱ ምክንያት በፌብርዋሪ 20 2012 በላስ ቬጋስ ሊያቀርብ የነበረውን ዝግጅት ሰርዞታል፡፡
- የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት የነበሩት ኒኮላስ ሳርኮዚ ወንድ ልጅ የሆነው ፔሪ ሳርኮዚ በምግብ መመረዝ ምክንያት በጃንዋሪ 26 2012 በብላክ ሲ ከተማዋ ኦዴሳ ውስጥ ሆስፒታል ገብቶ ነበር፡፡
- የሀገረሰብ ሙዚቃ አቀንቃኟ ኬሊ ፒክለር በጃንዋሪ 2012 በአሪዞና ፍኒክስ ከተማ ውስጥ የምግብ መመረዝ ህመም አጋጥሟት ነበር፡፡
- ሌላዋ የሀገረሰብ ሙዚቃ አቀንቃኟ ሚራንዳ ለምበርቶ በጃንዋሪ 2012 በተመሳሳይ መንገድ በአደገኛ የምግብ መመረዝ ተጠቅታ ነበር፡፡ ‹‹ለሞት ተቃርቤ ነበር›› የሚል የትዊተር መልዕክቷን ያስተላለፈችው ሚራንዳ ህመሙ የጀመራት ‹‹ሽሪምና›› የተሰኘ የዓሣ አይነት በመመገቧ ምክንያት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
- የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኙ ጆይ ጆፐስ በዲሴምበር 2011 በተመሳሳይ ችግር ተጠቅቶ በአስቸኳይ ወደ ሆስፒታል ለመሄድ ተገድዶ ነበር፡፡
- ራፐሩ ዲ.ኤም ኤክስ በጃንዋሪ 25 2012 በምግብ መመረዝ ተጠቅቶ ሆስፒታል ገብቶ ለመታከም ተገዷል፡፡ በDMX ችግሩ የተከሰተው ሸሪምፕ የተባለውን የዓሣ አይነት በመመገብ ምክንያት እንደሆነም በወቅቱ ተጠቅሶ ነበር፡፡
- በኦክቶበር 2011 ዝነኛው የሮክ ሙዚቃ አቀንቃኝ ስቲቨን ቴይለር በምግብ ወለድ ህመም ተጠቅቶ በመንገድ ላይ በመውደቁ በአስቸኳይ ወደ ሆስፒታል ተወስዶ ነበር፡፡
- የቼልሲው የመሀል ሜዳ ኮከብ ፍራንክ ላምፓርድ ባለቤት የሆነችው እና ‹‹Dancing on Ice›› የተሰኘውን የቴሌቪዥን ሾው የምታቀርበው ክርስቲን ብሊክሊ በቅርቡ በምግብ መመረዝ ተጠቅታ ሆስፒታል ተወስዳ ነበር፡፡ ለእሷም ህመም በምክንያትነት የተጠቀሰው ‹‹ሽሪምፕ›› የተሰኘው የዓሣ አይነት ነው፡፡
- በዲሴምበር 5 2011 የቀድሞው ብራዚላዊ የእግርኳስ ኮከብ ሶቅራትስ በ57 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ቀደም ሲል በተመገበው የተመረዘ የበሬ ሥጋ ምክንያት ለረዥም ጊዜ በሆስፒታል ውስጥ የህክምና እርዳታ ከተደረገለት በኋላ ነው፡፡
ወደኛ ሀገር ስንመለስ ደግሞ ነፍሱን ይማረውና ዝነኛው ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ በተለያዩ ወቅቶች ከስራው ጋር በተያያዘ የምግብ መመረዝ አጋጥሞት እንደነበር ይነገራል፡፡
ውድ ጫላ፡- ከላይ በመጠኑ ለማብራራት እንደሞከርነው የምግብ መመረዝ በሽታ በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰትና እንደ ሁኔታው እስከ ህልፈተ ህይወት ሊያደርስ የሚችል የህመም አይነት ነው። ምግብ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ በሆነ ምክንያት ሊመረዝ እና የሰውን አካል ሊጎዳ ይችላል፡፡ ባክቴሪያ፣ ቫይረስ፣ ፓራሳይትስ የተባሉት ህዋሳቶችና መርዛማ ንጥረ ነገሮች ምግብን መርዛማ ከሚያደርጉት ነገሮች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

በእርግጥ በምግብ መመረዝ ከሚጠቁት ሰዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ ያለ አንዳች ህክምና ወይንም ቀለል ባለ የህክምና ክትትል የሚወገዱ ናቸው፡፡ ለህልፈተ ህይወት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥርም ቢሆን ቀላል አይደለም፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>