(ዘ-ሐበሻ) ትናንት ሜይ 31 ቀን 2014 ዓ.ም በሚኒሶታ ከጃኪ ጎሲ ጋር በመሆን የሙዚቃ ኮንሰርቱን ያቀረበው ቴዎድሮስ ታደሰ በተመልካቹ ከፍተኛ አድናቆትን አገኘ። በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ስሙ ከፍ ብሎ የሚነሳው ቴዎድሮስ ታደሰ በሚኒሶታ ባቀረበው የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ ተወዳጅ ዘፈኖቹን ያቀረበ ሲሆን በየዘፈኑ መካከል ሕዝቡ ለድምጻዊው ያለውን ፍቅር እጁን በማውለብለብ፣ በፉጨት፣ በጭብጨባ፣ በመጮህ የገለጸ ሲሆን አንድ ዘፈን ዘፍኖ በጨፈረ ቁጥር ደግሞ ሕዝቡ “ቴዲ… ቴዲ… ቴዲ..” እያለ ስሙን በመጥራት ድምጻዊውን አክብሮት አምሽቷል።
ድምፃዊ ቴዎድሮስ ታደሰ በሰሜን አሜሪካ የተለያዩ ከተሞች እየተዘዋወረ እያቀረበ ያለው የሙዚቃ ኮንሰርት የሚቀጥል ሲሆን በመድረክ እያሳየ ያለው ድንቅ ብቃት ሕዝቡን አስደምሟል። ዘ-ሐበሻ በሙዚቃ ኮንሰርቱ ውስጥ ከነበሩ ታዳሚዎች አስተያየት መረዳት እንደቻለችው ሕዝቡ ለቴዎድሮስ ታደሰ ከፍተኛ ክብርና ፍቅር እንዳለው ነው።
የሙዚቃ ሕይወቱ ከቤተክርስቲያን የሚጀምረው ቴዎድሮስ ታደሰ በቅርቡ አንድ ሲዲ ያወጣ ሲሆን በትናንትናው የሚኒሶታ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ ይህ ሲዲ ሲሸጥ እንደነበር ለማየት ችለናል፡፡
ትናንት በሚኒሶታ ቴዎድሮስ ታደሰ ካቀረባቸው ዘፈኖች መካከል ዘ-ሐበሻ ለአንባቢዎቿ አንዱን ቪድዮ እንደሚከተለው አካፍላለች።