Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የመደብ ወይስ የብሄር ጭቆና?! (ከአብርሃ ደስታ)

$
0
0

እንዲህ ተጠይቋል
“ባለፉ ስርዓታት የነበረ የማሕበረ ፖለቲካ መዋቅር የመደብ የትግል (ጭቆና) መሰረት ያደረገ ነበር ወይስ ብሄር?”
ባለፉ ስርዓታት ጭቆና ነበረ (አሁንም አለ)። በኢትዮጵያ ታሪክ በህዝብ የተመረጠ ህዝብን ለማገለግል የተነሳ መንግስት አልነበረም (የለም)። ስለዚህ ጭቆና አለ። ጭቆናው ምን መሰረት ያደረገ ነው? ብሄር ወይስ መደብ? በኔ እምነት ጭቆናው ከሁለቱም ዉጭ ነው። በኢትዮጵያ የመደብ ጭቆና አልነበረም (የለም)፤ የብሄር ጭቆናም አልነበረም (የለም)። የነበረው (አሁንም ያለው) ጭቆና የኤሊት (Elite) ጭቆና ነው።
እስካሁን ድረስ የመደብ ፖለቲካ የለንም። የመደብ ፖለቲካ ከሌለ የመደብ ጭቆናም የለም። የብሄር ጭቆናም አልነበረም፣ የለም፣ ሊኖርም አይችልም። የመደብ ጭቆና ግን ለወደፊቱ ሊኖር ይችላል።
ያለፉ የኢትዮጵያ ገዥዎች ስልጣን ለመያዝ እንዲሁም በስልጣን ለመቆየት ሲሉ በህዝቦች ላይ በደል አድርሰዋል። በደል ሲያደርሱ ብሄር ወይ መደብ መሰረት አድርገው አይደለም። መደብ ጭራሽኑም አልነበረም፣ የለም። ብሄር ነበር፤ ግን ጭቆናው ብሄር መሰረት ያደረገ ሳይሆን ስልጣን መሰረት ያደረገ ነበር፣ ነው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ Class Based Or Nation Based Struggle ሳይሆን Elite vs People Based Power Struggle ነው።
ገዥዎች ስልጣን መያዝና እስከ ህልፈታቸው በስልጣን መቆየት ይፈልጋሉ። ለስልጣናቸው ሲሉ ታድያ ይደግፈናል የሚሉትን የሕብረተሰብ ክፍል ይጠቅማሉ፤ ለስልጣን አደጋ ነው በሚሉት ህዝብ ወይ ግለሰብ ደግሞ ጉዳት ያደርሳሉ፤ ስልጣናቸውን ለማጠናከር። ግን በፖለቲካ አንድን የሕብረተሰብ ክፍል መጥቀም አይቻልም፣ ይከብዳልና። ስለዚህ በሕብረተሰቡ ስም የተወሰኑ ግለሰቦች እንዲጠቀሙ ይደረጋል። ግለሰቦቹ ሲጠቀሙ የመጡበትን ሕብረተሰብ እንደተጠቀመ ተድርጎ ይታሰባል: ለፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ሲባል። ህብረተሰቡ በስልጣን ላይ ያለ ስርዓት “የኛነት” ስሜት ያሳድራል። ለዚህም ፕሮፓጋንዳ ይሰራል። ምክንያቱም የተወሰኑ ግለሰቦች ብቻ ነው መጥቀም የሚቻለው። ለስልጣን የሚረዳው ግን አብዛኝው ህዝብ ነው። ተጠቃሚ ግለሰቦች ታማኝ የስርዓቱ አገልጋዮች ይሆናሉ። በነሱ ታማኝነት ስርዓቱ ዕድሜው ያራዝማል።
ለስልጣን አደጋ የሚሆን ግለሰብ ወይ ማሕበረሰብ ደግሞ የጥቃት ዒላማ ይሆናል። የስልጣን ዒላማ የሚሆነው በመደቡ አልነበረም (በመደቡ ዒላማ ሊደረግ ይችላል ግን መደብ አልነበረም)። በብሄሩም አልነበረም። በግዜው ካልተመቱ የስልጣን ስጋት ይሆናሉ የተባሉትን ግለሰቦች ወይ የሕብረተሰብ ክፍሎች ይጠቃሉ፤ ብሄራቸው ምን ይሁን ምን። ግን በኢትዮጵያ ታሪክ አንዳንድ ብሄሮች የከፋ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ለምን? በብሄራቸው ምክንያት? አይደለም። ለስርዓቱ ታማኝ አይደሉም፤ ስጋት ይሆናሉ ስለተባሉ ብቻ ነው።
በኢትዮጵያ ታሪክ የመጎዳትም የመጠቀምም መስፈርት ብሄር ወይ መደብ አይደለም፤ የፖለቲካ ታማኝነት (Political Patrimonial-ism) ነው። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ልምድ መሰረት የፖለቲካ ታማኝነት የሚገናኘው ከብሄር ጋር ነው። ሙሉ በሙሉ ባይባልም አንድ ዓይነት ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች የበለጠ ይተማመናሉ (ምክንያቱም ፖለቲካችን መርህ መሰረት ያደረገ ሳይሆን ስሜት መሰረት ያደረገ ነው። በስሜት መነዳት ደግሞ አለመሰልጠን ነው)። አማርኛ ተናጋሪ ስልጣን ከያዘ አማርኛ የሚናገረውን (ሌላ ቋንቋ ከሚናገር) የበለጠ ያምናል። ኦሮምኛ ተናጋሪ ኦሮሞን የበለጠ ያምናል። ትግርኛ ተናጋሪ ትግራዋይን የበለጠ ያምናል። በዚህ መሰረት አማራኛ ተናጋሪ ስልጣን ሲይዝ አማራዎችን ያስቀድማል (ለስልጣኑ ሲል)። ሌሎች ደግሞ ቅሬታ ያድርባቸዋል። ከዛ ለስርዓቱ ታማኝ አይሆኑም። ታማኝ ካልሆኑ በጠላትነት ይፈረጃሉ። በጠላትነት ሲፈረጁ ተጎጂ ይሆናሉ። እነዚህ የስርዓቱ ተጠቃሚ የሚደረጉ ታማኞች ግለሰቦች ናቸው። ብሄር ሙሉ ተጠቃሚ ማድረግ አይቻልምና። ተጎጂዎች ግን ብሄር ሙሉ ወይ የሀገር ህዝብ በሙሉ ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ ተጠቃሚዎች ታማኝ ግለሰቦች ናቸው። ተጎጂዎች ግን ብሄር ሊሆኑ ይችላሉ። አንድን ብሄር ሌላኛው ብሄር እየበደለ ነው ይባላል። በዳዮቹ ግን ኤሊቶች (elites) ናቸው። ይህን ነገር ጉዳዩ የብሄር ጭቆና ያስመስለዋል። የብሄር ጭቆና ሊኖር ግን አይችልም።
ስለዚህ ባለፉ ስርዓታት (አሁንም ጭምር) በህዝቦች የሚደርስ በደል አለ። ይህንን በደል ብሄሮች የሚፈጥሩት አይደለም። ያለው በደል በብሄሮች ላይ የተፈፀመ የelites በደል ነው። ኦሮሞዎች የተበደሉ ኦሮሞ ስለሆኑ አልነበረም። ለተመሰረተው ስርዓት ተቀብለው አሜን ብለን እንዲገዙ ለማድረግ የተቃጣ ጥቃት ነው የተፈፀመባቸው። ስለዚህ ጥቃቱ ስልጣን መሰረት ያደረገ ነው። ዒላማው የፖለቲካ ታማኝነትን መሰረት ያደረገ ነው።
አማርኛ ተናጋሪ ንጉሶች ታማኝ ባልሆነ ማንም ሰው እርምጃ ይወስዳሉ። ለዚህም ነው በሁሉም ህዝቦች (አማራን ጨምሮ) በደል የደረሰው። ትግርኛ ተናጋሪ ገዥዎች ታማኝ ባልሆነ ማንኛውም ሰው እርምጃ ይወስዳሉ፤ ለስልጣን ሲሉ። ምሳሌ ህወሓት የትግራይ ልጆች በሆኑ እነ ስየ አብርሃ፣ አውዓሎም ወልዱ፣ አስገደ ገብረስላሴና ሌሎች ታጋዮች ላይ መጥፎ እርምጃ የወሰደው እነኚህ ሰዎች ትግርኛ ተናጋሪ ስላልነበሩ አይደለም። ለስርዓቱ ታማኝ ስላልሆኑ እንጂ።
ስለዚህ በኢትዮጵያ ምድር የደረሰውን እንዲሁም እየደረሰ ያለው ጭቆና ብሄር ወይ መደብ መሰረት ያደረገ ሳይሆን የፖለቲካ ታማኝነት መሰረት ያደረገ ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያውያን ጭቆና የብሄር ወይ የመደብ ሳይሆን የፖለቲካ ነው።
It is so!!!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>