ዘ-ሐበሻ ከጥቂት ሳምንታት በፊት መምህር ግርማ ወንድሙ በደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤ/ክ እንዳያጠምቁ መታገዳቸውን መዘገቧ ይታወሳል። ዛሬ ከአዲስ አበባ የደረሰን ዜና እንደሚያመለክተው ደግሞ አዲስ አበባ የሚገኘው ጠቅላይ ቤተ ክህነት የአጥማቂውን እግድ እንዳጸና ገልጿል። በአነጋጋሪነታቸው የቀጠሉት መምህር ግርማ እንዳያጠምቁ መታገዳቸው ከተሰማ በኋላ ም ዕመናን የተለያዩ አስተያየቶችን ሲሰነዝሩ ቆይተዋል።
ጠ/ቤተክህነቱ ግንቦት 2 ቀን 2005 ለ:-
- ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
- ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ ልዩ ጽ/ቤት
- ለአስተዳደር መምሪያ
- ለሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
- ለምሥራቅ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት
- ለፌዴራል ጉዳዮች ጽ/ቤት
- ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን
- ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት
- ለአ/አ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን
- ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ
- ለአ/አ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ
- ለቂርቆስ ክ/ከ ፍትሕ ጽ/ቤት
ግልባጭ አድርጎ በጻፈው የእግዳ ማጽኛ ደብዳቤ ላይ መምህሩን “አጥማቂ ነኝ ባይ” ሲል ገልጿቸዋል። ደብዳቤውን እንደወረደ ያንብቡት።
ጉዳዩ፡- በአስቸኳይ አጥማቂ መምህር ግርማ ወንድሙ በደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ሰ/ጉ/ጽ/ቤት በቁጥር 339/ቀ/አ/ቤ/ክ በ28/8/2005 ዓ.ም የተሰጠው እገዳ መ/ፓ/ጠ/ጽ/ቤት ያጸናው ስለመኾኑ ይመለከታል፤
መ/ር ግርማ ወንድሙ ሰባኬ ወንጌልና አጥማቂ ነኝ፤ የማዳን ፈውስ አለኝ በማለት በሕገ ወጥ መንገድ እስከ አሁን ድረስ በደብሩ እያጠመቁ ይገኛሉ፡፡
ይኹንና በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከ1993 ዓ.ም እስከ 2002 ዓ.ም ድረስ በየወቅቱ በሕገ ወጥ መንገድ የማዳን ፈውስ አለኝ በማለት ሕዝበ ክርስቲያኑን በየደብሩ ቅጽር ግቢ በማሰባሰብ የሚያጠምቁትን በተመለከተ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
ከቤተ ክርስቲያኗ ቀኖና ሥርዐት ውጭ በሚፈጸም ስብከትና ጥምቀት፤
የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ሳይፈቅዱ የሚሰጥ የወንጌልና ጥምቀት አገልግሎት መስጠትን በተመለከተ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነ ቢኾንም በሥርዐተ አልበኝነት በተለያዩ ቦታዎች የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ሲጣስ ይታያል፡፡
በመኾኑም መምህር ግርማ ወንድሙ በደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ የሚፈጽሙት ሕገ ወጥ የማጥመቅ ሥርዐትና የወንጌል አገልግሎት መኾኑን እየገለጽን የእምነታችን ተከታይ ሕዝበ ክርስቲያኑ ከዚህ እግድ ጋራ በተያያዘ የጸጥታ ችግር እንዳይገጥመው የሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት ጥብቅ ክትትል በማድረግ ውሳኔውን ተግባራዊ እንዲያደርግ እያሳሰብን የሚመለከታቸው የመንግሥት የጸጥታ አካላትም የቤተ ክርስቲያኒቱን ውሳኔ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ አስፈላጊው ትብብር እንዲያደርጉልን በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡
ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን::