ታዋቂው የስነጽሁፍ ሰውና ኮሜዲያን በእውቀቱ ስዩም በፌስቡክ ገጹ በእስር ላይ ስለሚገኙት የዞን 9 ጦማሪያን የሚከተለውን አስፍሯል።
ነጻነትና ፍትህ በሌሉበት አገር ውስጥ የልማት አውታሮችን መገንባት የት ለመድረስ ነው?የባቡር ሀዲድ ግንባታ ሳይ ፣የሚመጣብኝ እንደ አይሁድ በባቡር ታጭቀው ወደ መግደያ ጣቢያ የሚጓጓዙ ዜጎችን ነው፡፡የኤሌክትሪክ ግንባታ ሳይ የሚመጣብኝ የኤሌክትሪክ መግደያ ወንበር ነው፡፡የሚቆፈር ነገር ሳይ ድቅን የሚልብኝ የጅምላ መቃብር ነው፡፡
የዞን ዘጠኝ ጀግኖች ብረሳችሁ ታሪክ ይርሳኝ፡፡ባንድ በኩል የዘመናችሁ ተካፋይ በመሆኔ ኩራት ይሰማኛል፡፡በሌላ በኩል፣ የመከራችሁ ተካፋይ ባለመሆኔ ሐፍረቱን አልችለውም፡፡ያም ሆኖ‹‹በሉ እናንተም ሂዱ እኛም ወደዛው ነው፡፡ወትሮም መንገደኛ ፊትና ኋላ ነው›› የሚለው የዓለሙ አጋ የበገና እንጉርጉሮ ባጸደ-ነፍስ ላሉት ብቻ ሳይሆን ባጸደ-ወህኒ ላሉትም ይሆናል፡፡ስሜቴን እንዴት መግለጽ እንዳለብኝ አላቅም፡፡የገላውድዮስ ዜና- መዋእል ጸሐፊ በዚህ ሰዓት የሚሰማኝ ስሜት ከምእተ አመታት በፊት ተሰምቶት ነበር፡፡
መዓልትኒ ኮነ ሌሊተ፣ዘኢነአምሮ ወጽልመት ዘኢልማድ መጽአ
ወደፈነ እንስሳ ወሰብአ
(ቀኑ ሌሊት ሆነና፣ ወጋገኑ ተሰደደ
እንግዳ ጨለማ መጣ፣ጠባዩ ያልተለመደ
ሰውን፣ እንስሳን ጋረደ)