በ ዘሪሁን ሙሉጌታ
ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) በሀገሪቱ በሚታዩ ወቅታዊ ችግሮች ላይ መንግስት እየወሰደ ያለውን የኃይል እርምጃ በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ መጥራቱን አስታወቀ።
የመድረክ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንዳሻው ትናንት ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት ሰላማዊ ሰልፉ በመጪው እሁድ ግንቦት 3 ቀን 2006 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑን አስታውቀዋል። የሰላማዊ ሰልፉ ዓላማ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ሰላማዊ ተቃውሞዎች ላይ መንግስት የኃይል ምላሽ እየሰጠ በመሆኑና የፖለቲካ ምህዳሩም እየጠበበ በመምጣቱ መንግስት የዜጎችን ሕገ-መንግስታዊ መብቶች አክብሮ ተቃውሞዎችን በሰለጠነ አግባብ እንዲያስተናግድ ግፊት ለማድረግ ነው ብለዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን በቀጣይ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲስተካከልና በመጪው ዓመት የምርጫ ዝግጅት ለማድረግ መንግስትን ለድርድር ዝግጁ እንዲሆን ለማስገደድ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ጥላሁን የሕዝብ መፈናቀልና በኦሮምያ አካባቢ የተነሱ ተቃውሞዎች መንግስት የሕዝብን ጥያቄ በቸልታ የማየት ውጤት መሆኑን ለመግለፅ ነው ሲሉ አስረድተዋል። በአጠቃላይ ሰልፉ ላይ የሰብአዊ፣ የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ላይ የሚያተኩር እንደሆነም አስረድተዋል።
ሰላማዊ ሰልፉን ለማካሄድ ሁለት አማራጮች ማቅረባቸውን አቶ ጥላሁን የገለፁ ሲሆን፤ የመጀመሪያው ፓርቲው ዋና ጽ/ቤት ከሚገኝበት ስድስት ኪሎ ተነስቶ በፒያሳ በኩል ወደ ድላችን ሐውልት እንዲሁም ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ስድስት ኪሎ ከሚገኘው የመድረክ ዋና ጽ/ቤት ተነስቶ በቀድሞ ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ አድርጎ በአራት ኪሎ አደባባይ በማለፍ ወደ መስቀል አደባባይ መሆኑን ተናግረዋል። ለሰላማዊ ሰልፉ እውቅና ለማግኘት ለአዲስ አበባ አስተዳደር በትናንትናው ዕለት የማመልከቻ ደብዳቤ መቅረቡንና ምላሽ ከአስተዳደሩ እየጠበቀ መሆኑን ጠቅሰዋል። ጎን ለጎን ሰልፉን የሚያደራጅ አካል ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል። በሰልፉም ላይ እስከ 50 ሺህ ሰው እንደሚሳተፍ እንጠብቃለን ሲሉ ጨምረው ገልፀዋል።