Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ጃዋር ነበር የሚለው፣ አሁን ግን የኦሮሞ ተማሪዎችም ደገሙት –ኦሮሚያ የኦሮሞዎች ናት (ናኦሚን በጋሻዉ)

$
0
0

ናኦሚን በጋሻዉ
naomibegashaw@gmail.com

 

በዉጭ አገር የሚኖሩ የኦሮሞ ብሄረተኖች፣ በዶር መራር ጉዲና የሚመራዉን ኦፌኮ ጨምሮ በርካታ የኦሮሞ ድርጅቶች እና አንዳንድ የኦሮሞ ሜዲያዎች ያቀረቡትን ጥሪ በመቀበልና አዲሱን የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን በመቃወም ፣ የኦሮሞ ተማሪዎች በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ተቃዉሞ ማሰማታቸው በስፋት ተዘግቧል።

መቅደም ያለበትን ላስቀድም። ተማሪዎቹ ጥያቄዎቻቸዉን ያነሱት ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ነው። በፌደራል ፖሊስ የደረሰባቸው ድብደባ ልብን የሚያቆስል ከመሆኑም ባሻገር  መወገዝ አለበት። በዚህ ጉድያ ላይ፣  ሌላ አቋም ይዞ የሚከርከር ካለ፣ ለሰብአዊነት ደንታ የሌለው ሰዉ ነው ብዬ ከማለፍ ዉጭ ብዙ የምለው አይኖረኝም።

የኦሮሞ ድርጅቶች ሆነ ተማሪዎች አዲሱን ማስተር ፕላን የተቃወሙበት ሁለት ጥንድ ምክንያቶች ሊኖሯቸው ይችላል ብዬ አስባለሁ። አንደኛው፣ በልማት ስም የኦሮሞ ገበሬዎች አግባብ በሌለው መልኩ መፈናቀል የለባቸውም የሚል ነው።

በልማት ስም፣ ወይንም የአንድ ቋንቋ ተናገሪ በመሆናቸው ምክንያት ሰላማዊ ዜጎችን የማፈናቀሉ ተግባር፣  ላለፉት ሃያ አመታት በአገራችን በስፋት ሲታይ የነበረ አሳዛኝ ክስተት ነው። እነዚህ የኦሮሞ ድርጅቶች፣  የኦሮሞ ገበሬዎች ለምን ተፈናቀሉ በሚል አሁን እየተከራከሩና እየጻፉ እንዳሉት፣ በኦሮሚያ ዉስጥ «ይሄ አገራችሁ አይደለም እየተባሉ» ዜጎች ሲባረሩና የዘር ማጽዳት ወንጀል ሲፈጸምባቸው፣ በሌሎች የኢትዮጵያ ግዛቶች በልማት ስም ቤቶች ሲፈርሱ»  ለምን ብለው ድምጻቸውን አሰምተውን ቢሆን ኖሮ ለነርሱ የበለጠ ከበሬታ ይኖረን ነበር።

የኦሮሞ ገበሬዎች በኦሮሚያ ዉስጥ በጂማ፣ በኢሊባቡር፣ በወለጋና  በመሳሰሉት   በኦሮሚያ ክልል መንግስት ተፈናቅለው መሬታቸው ለባለ ሃብቶች የተሰጠበት ሁኔታ  እንዳለ እናውቃለን። ገበሬዎቹን ሆነ ሌሎች ዜጎችን የማፈናቀል ተግባር፣ ከኦሮሞነት ጋር፣ ወይንም በአዲስ አበባ ስር ከመሆን ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። ዜጎችን በቅያቸው የማፈናቀሉ ጉዳይ መንግስት ከሚከተለው የመሬት ፖሊሲ ጋር የተገናኘ ነው። መሬት የመንግስት እስከሆነ ድረስ በኦሮሚያ ክልል አስተዳደሪ ትእዛዝ ይሁን፣ በአዲስ አበባ ከንቲባ ትእዛዝ ፣ ዜጎች በግፍ ፣ በቂ ካሳ ሳይከፈላቸው እንዳይፈናቀሉ የሚገታ ምንም ነገር የለም። ስለዚህ የሚበጀው ፣ የኦሮሞ ገበሬዎችን ጨምሮ ማንኛዉም ዜጋ የመሬት ባለቤት እንዲሆኑ መታገሉ ነው።

ሁለተኛው ተቃዉሞ የተሰማበት ምክንያት፣  በቀጥታ ተቃዉሞ እያሰሙ ካሉ የኦሮሞ ተማሪዎች ጋር በሃሳብ የሚያላትመኝ ጉዳይ ሆኖ ነው ያገኝሁት። «ኦሮሚያ የኦሮሞዎች ናት። ፊንፊኔ የኦሮሞዎች ናት»  የሚለው መፈክራቸው ፣ እጅግ በጣም መርዛማ ከመሆኑም የተነሳ አገሪቷን ወደ ከፋ የዘር ጦርነት የመዉሰድ አቅም ያለው ነው። ይህ አይነቱ ፖለቲካ ከዉጭ በነጃዋር ሞሃመድ እየተጠነሰሰ ሲሠራበት የነበረና፣ በየድህረ ገጹና ሶሻል ሜዲያዉ የተረጨ  ሲሆን  ይኸው ዉጤቱም በመጠኑም ቢሆን በአንዳንድ የኦሮሞ ተማሪዎች ሲንጸባረቅ ለማየት እየቻልን ነው። ይህ መርዝ በአስቸኳይ እንዲመክን ካልተደረገ፣ በኦሮሞዎች እና በአማራዎች፣ በኦሮሞዎች እና በጉሙዞች፣ በኦሮሞዎችና በሶማሌዎች፣ በኦሮሞዎች እና ከፊቾዎች …መካከል የዘር ግጭት በስፋት ሊሰራጭ ይችላል። ይህም ደግሞ በዋናነት የኦሮሞ ማህበረሰብን ከሌላው ጋር በማጋጀት ፣ በማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያመጣል።

ይህ አይነቱን ፖለቲካ ፊት ለፊት መጋፈጥና መቃወም ያስፈልጋል። ከአሁን ለአሁን የተቃወሙት አገዛዙን  ነው በሚል፣ ዝም ተብለው ሊታለፉ አይገባም።

«ኦሮሚያ የኦሮሞዎች ብቻ ናት። ኦሮሚያ እየተወረረች ነው ! ፊንፊኔ የኦሮሚያ ናት…» የመሳሰሉትን  ከፋፋይና ጠባብ መፈክሮች ሲያሰሙ የሰማናቸው እነዚህ የኦሮሞ ተማሪዎችና በዉጭ ያሉ የኦሮሞ አክራሪዎች፣ ከገበሬዉ የሰብአዊ መብት ይልቅ፣  ከሃያ አመታት በፊት በኦነግ እና በሕወሃት በኃይል በሕዝቡ ላይ የተጫነዉን የኦሮሚያ ካርታ፣ መለወጡ ያሳሰባቸው ነው የሚመስለኝ። ከአሁን ለአሁን አዲስ አበባ ከሰፋች፣ ማስተር ፕላኑ ከጸደቀ፣ ኦሮሚያ ለሁለት ትከፈላለች የሚል ፍርሃት ሳይገባባቸው እንዳልቀረ ነው። ምናልባትም ኦሮሚያ ሬፑብሊክን የመመስረት እድላችንን ያጨልምብናል የሚልም ስጋት ሊኖራቸውም ይችላል።

ነገር ግን አንድ የዘነጉት ነገር አለ። አብዛኞቻችን ዝም ስንልላቸው፣ እነርሱ የሚጩኹት ጩኸት የበለጠ ተሰሚነት ያገኝ እየመሰላቸው ነው። አዲስ አበባ ዋና ከተማችን ናት። ማስተር ፕላን ኖረም አልኖረም አዲስ አበባ ትሰፋለች። እስከአሁንም የሰፋችው ማስተር ፕላን ኖሮ አይደለም። አዲስ አበባ ኦሮሞዉ፣ ሱማሌዉ፣ ትግሬው፣ አማራዉም ፣ ድብልቁም ..ሁሉም ያለ ፍርሃትና ያለ ሰቀቀን የሚኖሩባት ከተማ ናት። አዲስ አበባ በኦሮሚያ እንዳሉሌሎች ከተሞች፣ ኦሮሞዎች ብቻ የሚመረጡበትና የሚመርጡባት፣ ሌሎች በሰቀቀን እንደ ሁለተኛ ዜጋ የሚኖሩባት፣ አፓርታይድ የሰፈነባት ከተማ አይደለችም። አዲስ አበባ የሁሉም ናት። ሕዝቡ ከሁሉም አቅጣጫ በአዲስ አበባ መኖር ይፈልጋል። በዘረኝነት አጥር መታጠር አይፈልግም። መሻሻል ይፈልጋል። ወደ አዲስ አበባም ይጎርፋል። በዚህም ምክንያት አዲስ አበባ አደገች። የሕዝቧም ቁጥር ጨመረ።

በቅርብ ጊዜ ዉጥ ናዝሬት እና አዲስ አበባ ፣ አዲስ አበባ እና ደብረ ብርሃን፣ አዲስ አበባና ወሊሶ፣ አዲስ አበባና አምቦ ይገጥማሉ ተቦ ይጠበቃል። ከአዲስ አበባ ናዝሬት ያለው ሰፊ መንገድ ተጠናቋል። በኢኮኖሚና በሕዝብ ለሕዝብ ትስስር አኳያ ካየነው ፣ አዲስ አበባ እና አዳማ ገጥመዋል ማለት ይቻላል።  አዲስ አበአ እየኖሩ ናዝሬት የሚሰሩ፣ ናዝሬት እየኖሩ አዲስ አበባ የሚሰሩ ቁጥራቸው እየበዛ ነው። በቦሌ ያለው ኤርፖርት ብቃት ስለሌለው ፣ አዲስ አይሮፕላን ማረፊያ በቴሲ ከተማ ሊሰራ ነው። ቴሲ፣ ሰበታን አልፎ በአዲስ አበባ እና በወሊሶ መሃከል ያለች ናት። ኤርፖርቱ ሲጠናቀቅ ፣ የዚያኑ ያህል የኢኮኖሚክ እንቅስቃሴውም ያድጋል። አካባቢዉ ከአዲስ አበባ ጋር ትስስሩ የበለጠ እየጨመረ ይመጣል። ይሄም ደግሞ የሆነው በማስተር ፕላኑ ምክንያት አይደለም። የሕዝብ እንቅስቃሴ ነው። የሕዝብ እንቅስቃሴን ደግሞ በአዲስ አበባ ዙሪያ እንደ በርሊን ግንብ አይነት ፣ ካልተሰራ ማቆም አይቻልም። እነርሱ የሕዝብን እድገት ማፈን፣ ህዝቡን በዘር አጥር አሸገው ማስቀመጥ ቢፈልጉም፣ ህዝቡ ግን አይሰማቸው። ተሸናፊ የሚሆኑት እነርሱ እርሳቸው ናቸው። (በነገራችን ላይ የዉሸት አፈታሪክ ላይ ተመርኩዘው የአኖሌን የጥላቻ ሃዉልት የገነቡ፣ ነገ የአዲስ አበባን ግንብ እንገባ ቢሉ የሚያስደንቅ አይሆንም)

እንግዲህ «አዲስ አበባ ለምን አደገች፣ ተወረርን» የሚለውን ጠባብ አመለካከት መያዝ ሳይሆን  የሚያዋጣዉ፣ «አዲስ አበባ በምታድግበት ጊዜ ሁሉንም በጠቀመና ፍትሃዊነት ባለዉ መልኩ ይሁን» በሎ መከራከሩ ነው። በተለይም ከላይ እንደገለጽኩት መሬት የመንግስት ነው በሚል ዜጎችን በኃይል የማፈናቀል  ተግባር እንዲቆም አስፈላጊዉን ግፊትና ጫና ማሳደሩ በጣም አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ይህ የዘር ወይንም የጎሳ ጉዳይ ሳይሆን የሰብአዊ መብት ጉዳይ ነው።

የኦሮሞ ተማሪዎችንም ሆነ ድርጅቶች የኦሮሚያ የዘር ጠባብ ጥያቄዎችን ማንገብ አቁመው፣ የሰብአዊ መብት ጥያቄዎች ያንግቡ እላለሁ። ያኔ እኛም ከጎናቸው እንቆማለን። አሁን ግን «ኦሮሚያ ለኦሮሞዎች» ካሉ መንገዱን ጨርቅ ያርግላቸው። እነርሱን ከማንም በላይ  የምንታገልና የምንቃወም እንጂ የምንደግፍ አንሆንም። አዲስ አበባ የሁላችንም ናት። ቡራዪ፣ ሰበታ፣ ለገጣፎ፣ አምቦ፣ ወለጋ፣ ኢሊባቡር የሁላችንም ናቸው።

 

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>