በApril 24, 2012 ዓ.ም የዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ዕትም ላይ ዝነኛው ድምጻዊ ተሾመ አሰግድ “በጠራራ ጸሐይ ተዘረፍኩ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፍረደኝ” ሲል ድምጻዊ ጎሳዬ ቀለሙ (ጃኪ ጎሲ) ካለፈቃዴ “የኔ አካል” የሚለውን ተወዳጅ ዘፈኔን ወስዶ ተጫውቷል በተቃውሞ ነበር። ከጊዜ በኋላ ድምጻዊ ጃኪ ጎሲ በጆሲ ሾው ላይ በመቅረብ “ከዚህ በኋላ ተሾመ ይህን ዘፈን የኔ ነው ብሎ መጠየቅ አይችልም፤ ለዜማና ግጥም ደራሲዎቹ ከፍዬበታለሁ” ሲል ተናግሮ እንደነበርም ይታወሳል።
ጃኪ ወደ ሰሜን አሜሪካ ሲመጣ ይታየው የተባሉ ጸሐፊ “ድምጻዊ ጎሳዬ ቀለሙ (ጃኪ ጎሲ) ከተሾመ አሰግድ ለወሰደው ዘፈን ይቅርታ ይጠይቅ ይሆን? ወይስ ማን አለብኝነት ያልፈዋል?” ሲሉ ተሾመ ከዚህ ቀደም የሰጠውን ቃለምልልስ በመጥቀስ አስተያየት ጽፈው ነበር። ወደ ኢትዮጵያ ሙዚቃ ኮከብነት እየተጓዘ የሚገኘው ጃኪ ይህን አስተያየት በብልህነት የተመለከተው ይመስላል። በዚህም መሠረት ትናንት በዋሽንግተን ዲሲ ባደረገው የመጀመሪያው የሰሜን አሜሪካ ኮንሰርቱ ላይ ሰው ባልጠበቀው ሁኔታ ዝነኛውን ድምጻዊ ወደ መድረክ በማምጣት አብሮት “የኔአካል” የሚለውን ተወዳጅ ዘፈን ካቀነቀኑ በኋላ ድምጻዊ ጃኪም ካለፍቃዱው ወስዶ በመስራቱ ይቅርታ ጠይቋል። ጨምሮም ዘፈኑን የሰራው ከመውደዱ የተነሳ እንደሆነ ገልጿል። አርቲስት ተሾመ አሰግድም “እዚህ ሃገር ሰንመጣ መንገዱን ያሳየን ሰው አልነበረም። ጥረታችን የቀድሞ ሙዚቃኞቻችን ውለታ እንዲህ በቀላል እንዳይረሳ ሙዚቃዎቹን ስትጫወቱ በፈቃድ ጥያቄ ጠይቃችሁ ተጫወቱ። [የኔ አካል] ከኔ በበለጠ ጃኪ ተጫውቶታል። አብልጦ ነው የተጫወተው፤ ሞቅ አድርጉለት” ብሎ አርቲስቱም ይቅርታውን ተቀብሏል። ጃኪም የሕዝብ ድምጽን ማድመጡ፤ ከምንም በላይ ይህን ስመጥር አርቲስት በመድረክ ጋብዞ እንዲታወስ በማድረጉ ዘ-ሐበሻ አድናቆቷን በዚህ አጋጣሚ እየገለጸች፤ አንባቢዎች በዘ-ሐበሻ የተጀመረው የጃኪና የተሾመ ጉዳይ መቋጨቱን በዚህ አጋጣሚ እንገልጻለን። መልካም የሥራ ዘመን ለሁለቱም።
የይቅርታውን ስነስርዓት ቪዲዮ ይመልከቱ
የግርጌ ማስታወሻ ጥቂት ስለስመጥሩ አርቲስት ተሾመ አሰግድ፦
በኢትዮጵያ ስመ-ጥር ከሆኑ ድምጻዊያን መካከል የሆነውና ብዙዎች “ኢትዮጵያዊው ስቲቭ ዎንደር” የሚሉት ተሾመ አሰግድ በኢትዮጵያ አቆጣጠር በመስከረም ወር 1945 ተወልዶ በተወለደ በ5 ወሬ ዓይነ ስውር መሆኑን በዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ቁጥር 2 ላይ በሰጠው ቃለ ምልልስ መናገሩ ይታወሳል። የመጨረሻ ካሴቱን ካወጣ 17 ዓመት ያለፈው ይህ ድምጻዊ እስካሁን ስንት ካሴቶችን ሰርተሃል በሚል ጥያቄ አቅርበንለት “ጥቂት ካሴቶችን አውጥቻለው:: ትዝታና ባቲ በሚባለው የሙዚቃ ቅኝት በፊሊፕስ አሳታሚነት በ1960ዎቹ አንድ ሸክላ አውጥቼ ነበር:: ከዛ በተረፈ ያልተሳካለት አንድ ካሴት ሰርቼ ነበር:: ከዛ ወዲህ ግን ጅቡቲ ለ5 አመታት ከቆየው በሗላ ከሮሀ ባንድ ጋር በመሆን ‘የኩባያ ወተት”ን ሰራሁኝ:: ይበልጥ ከሕዝብ ጋር ያስተዋወቀኝም ይሄ ሥራ ነው:: በሌላ በኩል ከነራሄል ዮሐንስ; አሰፉ ደባልቄ እና ኬኔዲ መንገሻ ጋር አንድ ካሴት; እንዲሁም ከማርታ አሻጋሪ; በዛወርቅ አስፋው እና ኤልያስ ተባባል ጋር በመሆን አንድ ኮሌክሽን ሰርቼ ነበር:: በራሴ በኩል 2ኛውን ሙሉ ካሴቴን “ደርባባዬ’ን አውጥቼ ነበር:: ብዙም በሕዝብ ዘንድ አልገባም:: ግን አልፎ አልፎ ሰዎች ያውቁታል::” ሲል መልሷል።