(ዘ-ሐበሻ) ሰማያዊ ፓርቲ ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ የጠራውን ‘የተነጠቁ መብቶቻችንን እናስመልስ” ሰላማዊ ሰልፍ በብዙ አፈና ታጅቦ ማጠናቀቁን ለዘ-ሐበሻ የደረሰው መረጃ አመለከተ። በተደጋጋሚ በዚህ ሳምን በድረገጻችን ላይ እንደዘገብነው የዛሬውን ሰላማዊ ሰልፍ ለማሳካት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት በአዲስ አበባ ከተማ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ወቅት እስር እና እንግልት ሲደርስባቸው ቆይቷል።
ዛሬም መነሻውን ከፓርቲው ጽ/ቤት ተነስቶ በአዋሬ፣ አድዋ ድልድይ፣ ባልደራስ አድርጎ መድረሻው ወረዳ 8 ሜዳ የካ ሚካኤል ታቦት ማደርያ ባደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ፖሊስ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የማንገላታትና የማሸማቀቅ ሥራዎችን ሲሰራ እንደነበር የዘ-ሐበሻ ዘጋቢዎች ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ ያለውን የመብራት እጦት፣ የትራንስፖርት፣ የውሃ እጦት፣ የኔትወርክ እጥረትና ሌሎች የማህበራዊ ቀውሶችን ያስተጋባው የዛሬው የሰማያዊ ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ከተሰሙት መፈክሮች መካከል
“ውሃ ጠማን ውሃ ጠማን”
“ፍትህ ናፈቀን ፍትህ ናፈቀን”
“ውሽት ሰለቸን ውሽት ሰለቸን”
“የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ባስቸኳይ ይፈቱ”
“በቀለ ገርባ አሽባሪ አይደለም”
“ኦልባና ለሌሳ አሽባሪ አይደለም”
“አቡበክር አሸባሪ አይደለም”
“አንዷለም አራጌ አሽባሪ አይደለም”
“እስክንድር ነጋ አሽባሪ አይደለም”
“ናትናኤል መኮንን አሽባሪ አይደለም”
“ርዮት አለሙ ጋዜጠና እንጂ አሽባሪ አይደለችም” የሚሉና ሌሎችም ድምጾች ከሰልፉ ተሳታፊዎች ተደምጠዋል።
በተለይም ተሰላፊው “እኛ ኢትዮጵያኖች አንለያይም፤ እኛ ኢትዮጵያኖች አንድ ነን” የሚሉና “የተነጠቁ መብቶቻችን ይመለሱልን” ሲሉ ጩኸታቸውን ያሰሙ ሲሆን መንግስት የለም ወይ? እያሉም ሲጮኹ ነበር።
በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ንግግር ያደረጉትና በቅስቀሳው ወቅት ታስረው ባለፈው አርብ ማምሻውን የተለቀቁት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ለሰልፈኛው “ወደ ሰልፉ የመጡትን እና ስልፉን ያስተባበሩትን ወጣቶች እና መላውን ባለ መብት ተሳታፊ አመሰግናለሁ። ስርዓቱ በሙስና ተጨማልቋል፡፡ አገራችን አደጋ ላይ ወድቃለች፡፡ ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ሆነን እጣ ፈንታችን እንወስን። በየትኛውም አገር አምባገነን እንዲሁ ለሕዝቡ መብት አይሰጥም። አስፈላጊውን መስዕዋትነት መክፈል አለብን” ብለዋል።
ሊቀመንበሩ ቀጥለውም “ከ19 አመት ጀምሮ እስከ 63 አመት ያሉት አባላትና አመራሮቻችን ታስረዋል፡፡ ክርስቲያኖች፣ ሙስሎሞች ወጣቶች፣ ኢንጅነሮች፣ ሌሎቹም ታስረውብናል። ይህም የኢህአዴግ አምባገነንነት ያሳያል፡፡ ሰማያዊ ለሁሉም የህዝብ ክፍል እንደሚቆምም በዚህ ሰልፍ የታሰሩት አባላትና አመራሮቻችን ማሳያ ናቸው ነው። ክብርና ፍርሃት፣ ማጎብደድ የኢትዮጵያውያን ባህል አይደለም፡፡ ማሸነፍን ያስተማርን ህዝቦች ነን፡፡ ሙስሊም ክርስቲያኑ በጨዋነት አብሮ የሚኖርባት አገር ናት፡፡ እነሱ ግን ይከፋፍሉናል፡፡ አሁን በአዋራጅ ሁኔታ ላይ እንገኛለን። ይህን ለማስቆም ከእነአስፈላጊው መስዋትነት ሌት ተቀን እንሰራለን” በማለት ንግግራቸውን አስመተዋል።