ቅዳሜ ኤፕሪል 19 ቀን 2014 የትንሣኤ ቅዳሴ በዓል ከምሽቱ 6 ሰዓት ጀምሮ በሚኒሶታው ደብረሰላም መድሃኔዓለም ቤተክርስቲያን እንደሚደረግ ለሰላም እና ለአንድነት የቆሙ ምዕመናን ገለጹ። ምእመናኑ ለዘ-ሐበሻ በላኩት መግለጫ መሠረት አንዳንድ ከወያኔ መንግስት ጋር ያደሩና በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ የገቡ ፖለቲከኛ ግለሰቦች በደብረሰላም መድሃኔዓለም ቤ/ክ የቅዳሴ ስነስርዓት እንደማይኖርና ቅዳሴ በሌላ ቦታ እንደሚደረግ በቴክስት መልዕክትና በበራሪ ወረቀት የሚገልጹት ከእውነት የራቀ ነው።
የቤተከርሲቲያኑ ጉዳይ ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ እስከሚወሰንና በፍርድ ቤትም የማንም ፓትሪያርክ ስም በጠቅላላ ጉባኤ እስከሚወሰን ድረስ እንዳይጠራና ማንም እንዳይጋበዝ በጊዜያዊነት አግዶ እያለ በዚህ መሃል አንዳንድ የቤተክርስቲያኒቱ ካህናት “የአቡነ ማቲያስን ስም ካልጠራን አንቀድስም” በሚል ለቤተክርስቲያኑ ደብዳቤ መጻፋቸውን የሚገልጹት አስተያየት ሰጪዎች ‘በትንሣኤ በዓል ቤተክርስቲያኑን ጥለው መሄዳቸው ለሰላም እና ለአንድነት አለመቆማቸውን ያሳያል፤ እንዲሁም ቤተክርስቲያኑን ለመበተን ቆርጠው መነሳታቸውን በግልጽ የሚያሳይ ነው ሲሉ ይተቻሉ።
ምንም እንኳ ምዕመናኑን ለማሳሳት የትንሣኤ ቅዳሴ ከደብረሰላም መድሃኔዓለም ቤ/ክ ውጭ ይደረጋል በሚል እየተነገረ ያለው ነገር ደብረሰላምን ለመከፋፈል የሚደረግ ሴራ እንደሆነ ምእመናኑ እንዲገነዘብ ያሳሰቡት ለሰላም እና ለአንድነት የቆሙት ምዕመናን ሕዝቡ እየተነዛ ያለውን በደብረሰላም መድሃኔዓለም ቤ.ክ ቅዳሴ አይኖርም አሉባልታ ወደኋላ በመተው በቤተክርስቲያኑ በሃይማኖት አባቶች ስርዓተ ቅዳሴ ስለሚደረግ በደመቀ ሁኔታ የትንሣኤን በዓል እንዲያከበር ጥሪ ቀርቧል።
የደብረሰላም መድሃኔዓለም ቤ/ክ አድራሻ 4401 Minnehaha Ave. S Minneapolis, MN 55406 USA እንደሆነ ይታወቃል።
ለጊዜው ወደ አባ ሃይለሚካኤል ስልክ ደውለን የርሳቸውን ሃሳብ ለማካተት ያደረግነው ጥረት ባይሳካም ከሁሉም ወገን ተጨማሪ መረጃዎች ካሉ ይዘን ለመቅረብ እንሞክራለን።