· ተጠርጣሪዎቹን ለመያዝ የታሰበው ከአቶ መለስ ህልፈት በፊት ነው
· ተጨማሪ እርምጃ እንደሚወሰድ ኮሚሽነሩ ፍንጭ ሰጥተዋል
· በተጠርጣሪዎቹ ላይ የተወሰደው እርምጃ ታስቦበት እንጂ
በግርግር አይደለም ብለዋል
በዘሪሁን ሙሉጌታ
የፌዴራል የስነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዓሊ ሱሌይማን ሰሞኑን በድንገት በቁጥጥር ስር በዋሉት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ባለሀብቶችን በተመለከተ በጥንቃቄ የተሞላ መግለጫ ሰጡ።
በመግለጫው ላይ በርካታ ጋዜጠኞች ተገኝተው ለኮሚሽነሩ በርካታ ጥያቄዎች ለማቅረብ ቢፈልጉም ጋዜጣዊ መግለጫው በአጭሩ እንዲከናወን ተደርጓል። በዚሁ ጥንቃቄ በተደረገበት መግለጫ ላይ ኮሚሽነር ዓሊ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ጥናትና ክትትል ሲደረግ የቆየው ከሁለት ዓመት በፊት አቶ መለስ በህይወት በነበሩበት ወቅት መሆኑን አረጋግጠዋል። ኮሚሽኑ በቀጣይም እርምጃ እንደሚወስድ ፍንጭ የሰጡ ሲሆን በተጠርጣሪዎቹ ላይ የተወሰደው እርምጃ ታስቦበት እንጂ “በቱማታ” አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።
ችግሩ የቆየ ከሆነ አሁን ለምን እርምጃ ተወሰደ ተብለው የተጠየቁት ኮሚሽነሩ ሲመልሱ፤ “ጠመንጃ የያዘ ሰው “ኮሽ” ባለ ቁጥር አይተኩስም” እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው ጉዳዮች ነበሩ። ከነዚህም ውስጥ ደግሞ የዜጎችን ሕገ-መንግስታዊ መብት ሳይነካ በቂ ማስረጃ መሰብሰብ በማስፈለጉ ነው” ብለዋል። ሙስናም ቀጣይ ትግል በመሆኑ እርምጃው ዘግይቷል ሊባል አይቻልም ሲሉ ተናግረዋል። በሌሎችም መስሪያቤቶች ክትትሉ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።
“ትልልቅ የመንግስት ኃላፊዎችን መያዝ ድፍረቱ ከዬት ተገኘ?” ለሚለው የጋዜጠኞች ጥያቄ ኮሚሽነሩ ሲመልሱ ከዚህ በፊትም ትላልቅ የመንግስት ኃላፊዎች ክስ ሲመሰርት መቆየቱን ጠቅሰው የኮሚሽኑ ትኩረት ወንጀሉ ላይ እንጂ ግለሰቦቹ ላይ አለመሆኑን ተናግረዋል።
በቂ ማስረጃ ካላችሁ ለምን ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቅ አስፈለጋችሁ ለተባሉት ኮሚሽነሩ ሲመልሱ ይዞ ለመመርመር የሚያበቃ ማስረጃ እና ለፍርድ ቤት አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ የተለያዩ በመሆኑ ነው ብለዋል።
በቁጥጥር ስር ከዋሉ ተጠርጣሪዎች መካከል ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ ለምን አሰራችሁ? ተብለው ኮሚሽነሩ ቢጠየቁም ያለመከሰስ መብት ሊነሳ ይችላል በሚል ብዙም ግልፅ ያልሆነ መልስ ሰጥተዋል።
ተጠርጣሪዎቹን ለመያዝ የባለሥልጣናት የሐብት ምዝገባው አግዟችኋል ወይ ለተባሉት “አግዞናል” በሚል አጭር መልስ ሰጥተዋል። ወደፊትም በግብር ጉዳይ ላይ ኮሚሽኑ ያተኩራል ብለዋል። እርምጃው የፖለቲካ ጉዳይ ስለመሆኑም ተጠይቀው በሀገራችን ብቻ ባይሆን በሌሎች አገሮችም የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን ሲያዙ ጉዳዩ “ፖለቲካ ነው” መባሉ አይቀርም። ወደፊት የፖለቲካ ኬዝ እንዳልሆነ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ እናሳያለን በማለት በአጭሩ መልሰዋል።
ከሀገር ውጪ ስለኮበለለ ሀብትም ተጠይቀው ለጊዜው አስፈላጊ አይደለም። ነገር ግን በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ተጋግዘን እንሰራለን ሲሉ መልሰዋል።¾ (ምንጭ ሰንደቅ ጋዜጣ የዛሬ ዕትም)