አሁን አሁን የኢትዮጵያ የሙዚቃ ጉዞ እጅግ እየቀዘቀዘና እድገቱ እምብዛም የማይታይበት እየሆነ የመጣ እንደሆነ በርካታ ነባር ድምፃውያን፣የግጥምና ዜማ ደራሲዎችና የሙዚቃ አፍቃሪያን እየገለፁ ይገኛሉ፡፡
ምክንያታቸው ደግሞ የሁሉም ማለት ይቻላል ሙዚቃ ሳትጠራቸው ወቅቱና ገንዘቡን ብቻ ያገኙ በርካታ ወጣቶች ወደሙዚቃው በመግባታቸውና ለግጥሙና ዜማው እምብዛም የማይጨነቁ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው መታየት የሚፈልጉ በብዛት መምጣታቸው የሙዚቃውን እድገት ቁልቁል ያስኬደው ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች በሁለተኛ ደረጃ ያስቀመጡት ምክንያት የኮፒ ራይት ጥሰት ሲሆን ነባርና የብዙ የሙዚቃ አፍቃሪያን ቀልብን ገዝተው የዘለቁ ድምፃውያን ካሴቶቻቸውን ቶሎ ቶሎ ባለማውጣታቸውና አንዳንዶቹም ከነአካቴው ከሙዚቃው በመራቃቸው የሙዚቃ እድገቱን አስተጓጉሎታል ይላሉ፡፡
አዳዲስና ወጣት ድምፃውያን በብዛት እየመጡ ነው፡፡ አብዛኞቹ ታዲያ የነባር ድምፃውያንን ሙዚቃ ዳግሞ በመጫወት ድምፃቸውን እያሟሹ ዘፋኞች ለመሆን በቅተዋል፡፡ ምን ያህልም እንደተሳካላቸው ፍርዱን ለሙዚቃው አፍቃሪ እንተዋለን፡፡
ከነዚህ የነባር ድምፃውያን ሙዚቃዎች ተጫውተው ከተሳካላቸው ድምፃውያን መካከል አንዱ ብዙአየሁ ደምሴ አንዱ ነው ብንል ማጋነን አይሆንብንም ምክንያቱም ከአራት ዓመታት በፊት የታዋቂውን ድምፃዊ ሙሉቀን መለሰን ዘፈኖች ሙሉ ካሴት በመስራት የሙዚቃ አፍቃሪያንን አስደምሟልና ነው፡፡ በዚህ አልበሙ አብዛኛው የሙዚቃ አፍቃሪ ከሙሉቀን ያልተናነሰ ብቃት እንዳለው መስክረው ለታል፡፡ ምንም እንኳ “አስፈቅጃለሁ” “አላስፈቀደኝም” በሚል ያለመግባባት በሁለቱ ድምፃውያን መካከል ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም በኋላም በሰይፉ ፋንታሁን አማካኝነት ሊታረቁ ንደቻሉ ሰምተናል፡፡ በዚህ ካሴቱ በርካታ ነባርና አዳዲስ ድምፃውያን አድናቆትን ችረውታል፡፡ ትንሽ ዝምድና ከድምፃዊው ጋር ያለው ቴዲ አፍሮ ሳይቀር ምስክርነቱን የሰጠበት አጋጣሚ ነበር፡፡
ከሁለት ወራት በፊት ዜማ አማን በተባለ ከበርካታ ድምፃውያን ጋር በአማኑኤል ይልማ የተዘጋጀው ካሴት ላይ ባወጣቸው ሁለት ዘፈኖች በርካታ አድናቆትን ተችሮት ነበር፡፡ ከአንድ ወር በፊት የራሱን ሁለተኛ ካሴት “ሳላይሽ” በሚል መጠሪያ በናሆም ሪከርድስ አማካኝነት ከሚኖርበት ካናዳ አድናቂዎቹ አበርክቷል፡፡ በዚህም የራሱን የአዘፋፈን ስልት እንዲሁም ከአንድ የሙሉቀን መለሰ ዘፈን በስተቀር ሁሉም አዲስ ግጥምና ዜማ በማቅረቡ እጅግ ተወዶለታል፡፡ ካሴቱም በወጣ በአጭር ቀናት በብዙ ሺህ ኮፒዎች እንደተሸጡለት ተነግሯል፡፡
አሁንም በበርካታ መዝናኛ ስፍራዎችና በተለያዩ ቦታዎች የዚህን ድምፃዊ ሙዚቃዎች መደመጥን ቀጥለውበታል፡፡ በዚህም እጅግ እንደተሳካለት መመስከር ይቻላል፡፡ ብዙአየሁ ደምሴ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ሲሆን ከአንድ ዓመት በላይ በካናዳ እየኖረ ይገኛል፡፡ ከመላው ዓለም የኮንሰርት ጥሪ እየቀረበለት ያለው ወጣቱ ድምፃዊ ምናልባትም ከፋሲካ በኋላ ጥሪውን ተቀብሎ ኮንሰርቶችን ሊያቀርብ እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ የነባር ድምፃዊያንን ሙዚቃ በመጫወት በርካታ ድምፃውያን የራሳቸውን ችሎታ ሳያሳዩ ተውጠው የቀሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ነገር ግን ብዙዓየሁ ደምሴ በመጀመሪያ አልበሙ ተጠቅሞበት የነበረውን ሙሉቀን መለሰን በመተው በራሱ የአዘፋፈን ስታይል ጥሩ ካሴት ለአድማጩ አበርክቷል፡፡ ይህም ወጣቱን በእጅጉ ያስመሰግነዋል፡፡ በዚህ በያዝነው 2ዐዐ6 ዓ.ም ከሸዋንዳኝ ኃይሉ ካሴት በኋላ የአድማጭን ቀልብ ገዝቶ እስከ አሁን የቆየውና በእጅጉ እየተደመጠ ያለው “ሳላይሽ” የብዙዓየሁ ደምሴ ካሴት ነው በዚህም አንቀላፍቶ የነበረውን የኢትዮጵያ የሙዚቃ ጉዞ መነቃቃትን
ፈጥሮለታል ለማለት ይቻላል፡፡ ብራቮ ብዙዓየሁ!!
ዘ-ሐበሻ በኪነጥበብ ዙሪያ የሚሰጡ አስተያየቶችን ለማስተናገድ ሁሌም ዝግጁናትና ይሳተፉ።