Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ሌሎችም ከደሴ አስተዳዳሪዎች ይማሩ ! ግርማ ካሳ

$
0
0

11ባህር ዳር እንደተደረገው፣  ትላንት መጋቢት 28 ቀን፣  በደሴ ከተማ ፣  ከስድሳ ሺሆች በላይ የተገኙበት ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ተደርጓል።  የሰልፉን ሁኔታ የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን ስንመለከት አልፎ አልፎ፣  ሰማያዊ የለበሱ የፖሊስ አባላትን ተመልክተናል። በፖሊስና በሰልፈኞች መካከል ግብግቦች አልተፈጠሩም። የተወረወረ ጠጠር የለም። የተሰበረ ንብረት የለም። የተጎዳ፣ የቆሰለ ወይንም የሞተ ዜጋ የለም። ሰልፉ በሰላም ተጀምሮ ነው በሰላም ያለቀው። እንዲህ አይነት ሰልፍ ደስ ያሰኛል።

 

ለዚህም በዋናናት የደሴን ሕዝብ ላመሰግን እወዳለሁ። ኢትዮጵያዊ ጨዋነቱን እና ሰላማዊነቱን ነው በድጋሚ ያስመሰከረው። ፈርቶና አንገቱን ደፍቶ መቀመጥ ይችል ነበር። ነገር ግን ፍርሃትን አዉልቆ፣ ከአንገቱ ቀና ብሎ፣ የግፍ ቀንበርን ተቃወመ።  በአደባባይ ድምጹን በማሰማት ጀግንነቱን አሳየ። እኔም፣ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ፣ ሌሎች ኢትዮጵያዉያንን በመቀላቀል፣  በደሴ ሕዝብ መኩራቴን መግለጽ እወዳለሁ።

 

በሁለተኛ ደረጃ የአንድነት ፓርቲ አመራር አባላት እና ደጋፊዎችን እንዳመሰግን ይፈቀድልኝ። ሕዝብ የሚያደራጀው ድርጅት ከሌለ ለመንቀሳቀስ፣ አይቻልም ባይባልም፣ ከባድ ነው የሚሆንበት። የአንድነት ፓርቲ በዚህ ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ነው።

 

የአንድነት ፓርቲ ከአገዛዙ ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚ ነን ከሚሉትም በርካታ ቀስቶች ሲወረወሩበት እንደነበረ የሚታወቅ ነው። ዉጭ ተቀምጠው ብዙ የሚያወሩ ፣ ብዙ ብለዋል። ነገር ግን አንድነቶች፣ ዋጋ እየከፈሉ፣ ቲዮሪ እየደረደሩ ማውራት ሳይሆን፣ ትግል ማለት ምን ማለት እንደሆነ በተግባር እያስመሰከሩ ናቸው። ከደሴና አካባቢው ሕዝብ ጋር ሆነው፣ እያነቁትና እየቀሰቀሱት፣ ሕዝቡ ደፍሮ ድምጹን እንዲያሰማ ማድረግ መቻላቸው ትልቅ ነገር ነው። ከዚህ የበለጠስ ምን አለ ? ለዉጥ ሊያመጣ የሚችለው እኮ ሕዝቡ ብቻ ነው !

በሶስተኝነት፣ አዎን፣ የደሴን አስተዳደር ላመሰግን እወዳለሁ። አንዳንዶች «መስራት ያለባቸውን ስለሰሩ ለምን ይመሰገናሉ ?» ሊሉ ይችላሉ። ልክ ነው፣  ሕግን አክብረዉ፣ ዜጎች ሰለማዊ ሰልፍ እንዲያደርጉ መፍቀድ ስራቸው ነው። ነገር ግን እንደ አዲስ አበባ ፣ ባሌ/ሮቢ ፣ መቀሌ……ካሉ፣ ሕገ-መንግስቱን ንቀዉ የዜጎችን መብት በመጋፋት ሰላማዊ ሰልፎ እንዳይደረጉ ከሚያግዱ አስተዳደሮች ጋር፣ የደሴ አስተዳደር ሲነጻጸር በጣም የተሻለ ሆኖ ነው የተገኘው። በጎን ሕግን እንዲያፈርሱ የሚደረግባቸውን ጫና ተቋቁመው፣ ሕግን ማክበሩን መምረጣቸው ያስመሰግናቸዋል።

 

በቅርቡ እንደተከታተልነው፣ አንድነት ፓርቲ በአዲስ አበባ ሰልፍ እንደሚያደርግ ባሳወቀ ጊዜ ፣ አስተዳደሩ ሕግ ወጥ ደብዳቤዎችን በመጻፍ ለሰልፉ እውቅና አልሰጥም ብሎ እንደነበረ ይታወቃል። ከዘጠኝ ወራት በፊት፣ የሚሊዮኖችም ድምጽ ለነጻነት፣ ክፍል አንድ፣ እንቅስቃሴ ወቅት፣ አሁንም የአንድነት ፓርቲ በመቀሌ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ቅስቀሳዎች አድርጎ፣ ሰልፉ  ነገ ሊደረግ ዛሬ፣  «መቀሌን እንኳን አንድነት ቅንጅትም አልደፈራትም» በሚል፣ የአንድነት መራር አባላትን በማሰርና የቅስቀሳ መኪናዎችን በማገት፣ የመቀሌ የሕወሃት አስተዳዳሪዎች ሰልፉ እንዲጨናገፍ ማድረጋቸው በወቅቱ ተዘግቧል። በባሌ/ሮቢ በተመሳሳይ ሁኔታ፣ የቅስቀሳ ዘመቻ ተደርጎ፣ የሰልፉ ቀን በጠዋቱ፣  ሰልፍ ከተደረገ ከፍተኛ ደም መፋሰስ ይኖራል የሚል ዛቻ በመሰጠቱ፣ ለሕዝብ ደህንነት ሲባል ሰልፍ እንዳይቀጥል የተደረገበት ሁኔታም ነበር። ታዲያ ደሴዎች አስር እጥፍ አይሻሉም ?

እንግዲህ ሌሎች የአገራችን ባለስልጣናት፣ ከደሴ አስተዳደር ይማሩ እላለሁ። «ፖሊሶች ፣ ዜጎችን የሚደበድቡና የሚያወኩ፣ የጥቂት የአገዛዙ ባለስልጣናት አገልጋዮች የሆኑ፣ ሕዝብን የሚያስጨንቁ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ የሚሰነዝሩ፣ በሕገ መንግስቱ የተደነገጉ ሕጎችን የሚሸረሽሩ ሳይሆን፣ በደሴ ሰልፍ እንዳየነው፣  ከሕዝብ ጋር እየሄዱ፣  ሕግና ስርዓትን እያስጠበቁ፣  ሕዝብ የሚያገልግሉና ለሕግ የሚገዙ ይሁኑ» እላለሁ።

 

ለአገራችን የሚያዋጣዉ ሁላችንም በሕግ ፊት እኩል ስንሆን ነው። ባለስልጣናት ሕግን ካከበሩ አገር ሰላም ይሆናል። በደሴ እንዳየነው ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች በሰላም ተጀመሮ በሰላም ይጠናቀቃል። እንግዲህ ሁላችንም ለሕግ ተገዥዎች ሆነን አገራችን በፍቅር እንገባ።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>