ረፖርተር
መጋቢት 22, 2006 ዓ.ም
በአዲስ ከንቲባና ነባር ካቢኔ ሥራውን የጀመረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰባተኛ ወሩን ይዟል፡፡
አስተዳደሩ የቆየባቸው ሰባት ወራት የሥራ ክንውን የከተማውን ነዋሪዎች ብሶትና ችግር የፈታ ሳይሆን፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ጐልተው የታዩበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ከ2001 ዓ.ም. እስከ 2005 ዓ.ም. ለአምስት ዓመታት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን በከንቲባነት ሲመሩ ከነበሩት አቶ ኩማ ደመቅሳ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤትን ቁልፍ የተረከቡት አቶ ድሪባ ኩማ፣ የከተማውን ነዋሪዎች ሲያንገሸግሻቸው የቆየውን የመልካም አስተዳዳር እጦት ችግር በመጠኑም ቢሆን ይፈቱታል የሚል ግምት ተሰጥቶዋቸው እንደነበር ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ የከተማው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ ነዋሪዎቹ ቅድሚያ ግምት የሰጡት ዝም ብለው ሳይሆን በፌዴራል መንግሥት ጭምር ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት ያለባቸው በዋናነት፣ የመልካም አስተዳደር እጦትና የሙስና ጉዳዮች በመሆናቸው ጭምር ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ለሚጠይቋቸው የመብትም ሆነ ሌሎች ጥያቄዎች ተገቢ የሆነ ምላሽ ማግኘት ባለመቻላቸው፣ የመልካም አስተዳደር እጦትን በማንሳት ጠዋት ማታ ሲያማርሩ መክረማቸው የአደባባይ ሚስጥር መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ ይገልጻሉ፡፡
የከተማውን ነዋሪዎች ብሶትና የዕለት ከዕለት ምሬት የተሰማቸው በሚመስል ሁኔታ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ተክተው የተመረጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም ትኩረት ሰጥተው ከሚንቀሳቀሱባቸው የሥራ ዘርፎች መካከል በዋነኛነት የጠቀሷቸው የመልካም አስጸዳደር እጦትንና ሙስናን መዋጋት እንደነበር ነዋሪዎች ያስታውሳሉ፡፡
ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ ከንቲባ መሾሙን ተከትሎ፣ በአስተዳደሩ መዋቅር ላይ ለውጥ ተደርጐ የአገልግሎት አሰጣጥ ለውጥ ያመጣል የሚል ግምትም ነበር፡፡ አስተዳደሩም ለውጥ ለማምጣት ቆርጦ የተነሳ በሚመስል ሁኔታ ለሰው ኃይሉ ግምገማዊ ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በሥልጠናውም 500 ከፍተኛ አመራሮች፣ 3,000 መካከለኛ አመራሮችና 52 ሺሕ ሠራተኞች ተሳትፈዋል፡፡
መሬትና መሬት ነክ ይዞታዎች
የሙስና መፈንጫ ናቸው ተብለው ከተፈረጁ አራት ዘርፎች መካከል አንዱና ዋነኛው መሬትና መሬት ነክ ይዞታዎች ዘርፍ ነው፡፡ በተለይ የቀድሞው ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ የአስተዳደሩን ሥልጣን ከተረከቡበት ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ በዘርፉ ማሻሻያ ለማድረግ ብዙ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡
ከተሠሩት ሥራዎች መካከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ዘርፍን መዋቅር መለወጥ፣ የሰው ኃይሉን ማሟላትና ለሥራው ብቁ ማድረግ ነው፡፡ የሕግ ክፍተቶችን ለመሙላት ደግሞ የፌዴራል መንግሥት የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ አዋጅ በኅዳር ወር 2004 ዓ.ም. ወጥቷል፡፡ በዚህ አዋጅ መነሻነት በርካታ ደንቦችና መመርያዎች በአስተዳደሩ ወጥተዋል፡፡
በዚህ መሠረት አስተዳደሩ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ከማቋቋሙም በተጨማሪ፣ በሥሩ የግንባታ ፈቃድ አሰጣጥና ክትትል ባሥልጣን፣ የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት፣ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲና የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ኤጀንሲ መሥሪያ ቤቶች እንዲቋቋሙ ተደርጓል፡፡
እነዚህ መሥሪያ ቤቶች የሚመሩባቸው ሕግጋትና ልዩ ልዩ የሕግ ማዕቀፎች ከመውጣታቸውም በተጨማሪ የሰው ኃይል እንዲሟላላቸው ተደርጓል፡፡
ከአቶ ኩማ ደመቅሳ ሥልጣኑን የተረከቡት አቶ ድሪባ ኩማ የሥልጣን ዘመን፣ የመሬት ዘርፍ በተቀመጠው ዕቅድ መሠረት ቢደራጅም ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ሁኔታ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ነዋሪዎች ቅሬታ ማንሳታቸው አልቀረም፡፡
በመሬት ተቋማት ላይ እየቀረቡ ከሚገኙ ቅሬታዎች መካከል ከዓመታት በፊት የቀረቡ የመሬት ጥያቄዎች ምላሽ አለማግኘታቸው፣ ለአገር ይበጃሉ የተባሉ ፕሮጀክቶች የሚያቀርቡት የማስፋፊያ ቦታ ጥያቄዎች አለመስተናገዳቸው፣ ለዓመታት ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎች ላይ ዕርምጃ አለመወሰዱ፣ ለጥቃቅን ጉዳዮች ሳይቀር ውሳኔ የሚሰጥ አመራር መጥፋት የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሰነድ አልባ ይዞታዎች ካርታ አሰጣጥ የተጓተተ መሆኑና ለተነሺዎች የሚሰጠው ካሳ ፍትሐዊ አለመሆኑ ከሚነሱ ችግሮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
አስተዳደሩ እነዚህን ችግሮች በተመለከተ ያለው አቋም በሕግ መሠረት ሊስተናገዱ የማይችሉ ናቸው የሚል ነው፡፡ አለፍ ሲልም ‹‹ችግሩን ተገንዝበናል፣ የኅብረተሰቡን ቅሬታ እንደ ግብዓት ወስደናል…›› የሚል መሆኑን ጥያቄያቸው ያልተመለሰላቸው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ የሊዝ ሕጉ በዋነኛነት መሬት የሚቀርበው በጨረታ አግባብ ነው ይልና የከተማው ከንቲባ ግን ፋይዳ ያለው ፕሮጀክት ነው ብለው ካመኑ ለካቢኔ ቀርቦ በልዩ ሁኔታ ሊስተናግድ እንደሚችል ይገልጻል፡፡
ነገር ግን ፋይዳ አላቸው ተብለው በልዩ ሁኔታ ይስተናገዳሉ የሚባሉት ፕሮጀክቶች በግልጽና በዝርዝር ባለመቀመጣቸው፣ የመሬት ቢሮ ሠራተኞች የሚቀርቡላቸውን ጥያቄዎች ለማስተናገድ ዝግጁዎች እንዳይሆኑ አድርጓል ሲሉ የሕግ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
በዚህ ምክንያት የከተማው የሊዝ ማስፈጸሚያ መመርያና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የሊዝ አዋጅ ብዙም ሥራ ላይ ሳይውሉ እንዲሻሻሉ መመርያ መሰጠቱ እየተነገረ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ባለሀብቶች ቀደም ሲል የቀረቡት የመሬት ጥያቄዎች ሊስተናገዱ ባመቻላቸው ቅሬታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡
የከንቲባው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሚያስኬዱ አንዳንድ ነገሮች መኖራቸውን፣ የሊዝ አዋጁና የሊዝ አዋጅ ማስፈጸሚያ የትርጉም ችግር ከመጣ እንደሚሻሻል ጠቅሰው፣ የመሬት አቅርቦትን በተመለከተ ግን አስተዳደሩ ትኩረት አድርጎ የነበረው ለኮንዶሚኒየምና ለ40/60 ቤቶች የሚያስፈልጉ ቦታዎችን ማቅረብ ነው፡፡ ለጨረታ የሚቀርቡ መሬቶችን በማዘጋጀት በኩል የተወሰኑ መጓተቶች እንደነበሩና በሚቀጥሉት ወራት ለጨረታ የሚቀርቡ ቦታዎች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አቶ አሰግድ ተናግረዋል፡፡ አስተዳደሩ በዓመቱ መጀመርያ ላይ 1,200 ሔክታር መሬት ለሊዝ ጨረታ እንደሚያቀርብ ገልጾ ነበር፡፡ ነገር ግን በእስካሁኑ ቆይታ የዚህን ዕቅድ ሩብ እንኳ ለገበያ አለማቅረቡን በርካታ ሰዎች ይናገራሉ፡፡
በመሬት ዘርፍ ችግር የነበሩ ጉዳዮችን የቀድሞ አስተዳደር ቅርፅ አስይዞታል የሚሉ በርካታ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችና ባለሀብቶች፣ ከከንቲባ ድሪባ ኩማ በርካታ አገልግሎቶች ቢጠብቁም እንዳልተሳካላቸው እየገለጹ ነው፡፡
ውኃ
አስተዳደሩ በግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙ ጥሩ እየተሠራ መሆኑን የገለጸው አንዱ ንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦትን በሚመለከት ነው፡፡ ንፁህ የመጠጥ ውኃ ጥልቅ ጉድጓዶችን በመቆፈርና ግድቦችን በማስፋፋት እንደሚያቀርብ ገልጿል፡፡ አስተዳደሩ ውኃን በሚመለከት በስድስት ወራት ውስጥ የሠራውን ግልጽ ሆኖ በሚታይ ሁኔታ ባያስቀምጥም፣ በጥቅሉ በበጀት ዓመቱ እየሠራቸው ያሉትንና ሊሠራቸው ያቀዳቸውን ተናግሯል፡፡ በበጀት ዓመቱ በአቃቂ 19 ጥልቅ ጉድጓዶችን እየቆፈረ መሆኑንና 80 ሺሕ ሜትር ኩብ ውኃ ማምረቱን በሪፖርቱ ቢገልጽም ወደ ሥርጭት አልገባም፡፡ በለገዳዲ ደግሞ 11 ጥልቅ ጉድጓዶችን መቆፈር መጀመሩንና ሲጠናቀቅ 40 ሺሕ ሜትር ኩብ ውኃ ማምረት እንደሚጀምር ይናገራል፡፡ የድሬ ግድብን በማሻሻልና የለገዳዲ ማጣሪያን በማስፋፋት የውኃን ምርት ወደ 195 ሺሕ ሜትር ኩብ ለማሳደግ እየሠራ መሆኑንም በሪፖርቱ ገልጿል፡፡
በአጠቃላይ አስተዳደሩ የውኃ ምርትን በማሳደግ በኩል ከፍተኛ የሆነ ሥራ እየሠራና የጀመራቸው የጉድጓድ ቁፈራ፣ ግድብ ማስፋፋትና የክረምት ውኃ ጥበቃን በሚመለከት በኩራት እየተናገረ ቢሆንም፣ በከተማው ውስጥ እየታየ ያለው እውነታ ግን የተገላቢጦሽ መሆኑን ሁሉም ነዋሪዎች ይስማሙበታል፡፡
በከተማው በተለይ ባለፉት አራትና አምስት ወራት ውስጥ የውኃ ችግር በከፍተኛ ሁኔታ ምሬት እየፈጠረ ነው፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት የውኃ እጥረት ያለባቸው የከተማው አካባቢዎች ዳገታማ ቦታዎችና ከማሠራጫ ጣቢያዎች ርቀው የሚገኙ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ግን ከማዕከል አካባቢዎች ጀምሮ የውኃ ችግር ከፍተኛውን ቦታ ይዞ ይገኛል፡፡ የመሠረተ ልማቶች መስፋፋት ለውኃ እጥረት በምክንያትነት ቢጠቀሱም፣ ነዋሪዎች ግን አይስማሙም፡፡ አዲስ አበባ ከተማ እየሰፋች መሆኗን ሁሉም ነዋሪዎች የማይክዱት ሀቅ ነው፡፡ ነገር ግን ከከተማው መስፋፋት ጋር ተያይዞ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራባቸው ከሚገቡ ነገሮች አንዱና ዋነኛው በቂ የውኃ ምርት ማቅረብ ላይ መሆኑን አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የከተማው የውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ባልደረባ ይናገራሉ፡፡ ባለሥልጣኑ በንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦትና ፍሳሽ ማስወገጃ ሥራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚናገረውና ለመንቀሳቀስ የሚሞክረው በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ወራትና በበጀት መዝጊያ ወቅት መሆኑን ሠራተኛው ይናገራሉ፡፡
የበጀት ዓመቱ ሲጀመር በተለይ ውኃ የማይደርስባቸው ቦታዎች ይመረጡና ቅድሚያ ተሰጥቶ እንዲሠሩ በሚል ብዙ ገንዘብ ወጪ እንደሚደረግ የሚናገሩት ሠራተኛው፣ ፕሮጀክቶቹ ከጅምር ቁፋሮ ሳያልፉ በኃላፊዎች የወረቀት ላይና የዓውደ ጥናት ፕሮፓጋንዳ ታጅበው በጀት ዓመቱ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል፡፡ በጀት ዓመቱ ሊዘጋ ወር ሲቀረው፣ በተለይ ፍሳሽ ለማስወገድ በሚል የክረምቱን ጭቃ የሚያባብሱ ቁፋሮዎች በየመኖሪያ ሠፈሮች ይቆፈሩና የተረፈው በጀት እንዲጣጣ እንደሚደረግም አክለዋል፡፡ ይኼ አሠራር የተለመደና አሁንም መልኩን ቀይሮ የተለያዩ ሰበቦች እየተደረደሩ፣ ማለትም የመንገድ ሥራ፣ የባቡር ሀዲድ ዝርጋናታና ሌሎችም ምክንያቶች እየቀረቡ የኅብረተሰቡ ንፁህ የመጠጥ ውኃ የማግኘት ችግር ተባብሶ መቀጠሉን አውስተዋል፡፡
የባለሥልጣኑ ባልደረባ እንደገለጹት፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ንፁህ የመጠጥ ውኃ እጦት ከቀናት አልፎ ወራትንም እያስቆጠረ መሆኑን እየገለጹ ናቸው፡፡ በወረቀት ላይ በሚቀርብ ሪፖርት ብቻ የከተማውን የንፁህ መጠጥ ውኃ ችግር ለመፍታት የጉድጓድ ቁፋሮና የግድብ ማስፋፋት ሥራ እያከናወነ ባለበት ሁኔታ፣ ችግሩ ከ25 እስከ 30 ዓመታት የሚወገድበትን ፕሮጀክት ዘርግቶ እየሠራ መሆኑን በስድስት ወራት ያቀረበውን የአፈጻጸም ሪፖርት ነዋሪዎች ውድቅ አድርገውታል፡፡
የቤቶች ልማት ፕሮግራም
አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰበት መሆኑን ከሚናገርባቸው ተቀዳሚ ተግባራት መካከል የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር መቅረፍ ይገኝበታል፡፡ በመሆኑም በከንቲባ ኩማ ዘመን የተጀመሩና ያልተጠናቀቁ 95 ሺሕ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ማጠናቀቅና በበጀት ዓመቱ የ65 ሺሕ ቤቶችን ግንባታ ለማስጀመር መሆኑንም መናገሩ ይታወሳል፡፡ በመሆኑም በ2003 ዓ.ም. የተጀመሩ 17,171 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታን 92 በመቶ ማጠናቀቁን ጠቁሟል፡፡ በ2004 በጀት ዓመት ደግሞ በማስፋፊያና መልሶ ማልማት በ16 የተመረጡ ቦታዎች 44,709 ነባር የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ግንባታ እያፋጠነ መሆኑንም በስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸሙ ላይ አስታውቋል፡፡ ለሌሎች ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች 33,593 ቤቶችን ግንባታ እያፋጠነ መሆኑንና ለ40/60 ቁጠባ ቤቶች ተመዝጋቢዎች በአራት ሳይቶች እየገነባ መሆኑን በሪፖርቱ አካቷል፡፡
የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ግንባታ በሚመለከት አስተዳደሩ በቅርቡ የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጠበትን የ50 ሺሕ ቤቶች ግንባታ ጨምሮ በጥሩ ሁኔታ እየሠራ መሆኑንና የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሆነ፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከመናገር አላረፈም፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤትን በሚመለከት የሚናገሩትና አስተዳደሩ ‹‹እየሠራሁ ነው›› የሚለው ግን የሚጣጣምና የሚገናኝ አይደለም፡፡
የመኖሪያ ቤትን ችግር ለመቅረፍ በሚል የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ጽንሰ ሐሳብ የተጀመረው በ1996 ዓ.ም. ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ የከተማው ከንቲባ በነበሩበት ዘመን መሆኑ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ተጋግሎ በነበረው የምርጫ 97 የምረጡኝ ቅስቀሳ ተከትሎ የመጣው የጋራ ቤቶች ግንባታ ምዝገባ፣ በአብዛኛው የከተማ ነዋሪዎች ብዙም ትኩረት አልተሰጠውም ነበር፡፡ ቢሆንም ግን በወቅቱ ከ453 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች መመዝገባቸው ይታወሳል፡፡ ለተከታታይ ዘጠኝ ዓመታት ድጋሚ ምዝገባ ሳይደረግ፣ በ1996 ዓ.ም. ብቻ ለተመዘገቡ ቤት ፈላጊዎች አንድ መቶ ሺሕ ያልሞሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከሰባት ጊዜ በላይ በዕጣዎች፣ ከዕጣ በተጨማሪም በልማት ምክንያት ለሚነሱ ነዋሪዎችና በትዕዛዝ ለተሰጣቸው ሰዎች ተከፋፍለዋል፡፡ በ2005 ዓ.ም. መጨረሻ ወራት ላይ በተደረገው ዳግም ምዝገባ ከ800 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች ሊመዘገቡ ችለዋል፡፡ አስተዳደሩ ምዝገባውን በአራት የተለያዩ ፕሮግራሞች ከፋፍሎ አካሂዷል፡፡ 10/90፣ 20/80፣ 40/60 እና የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት በሚል፡፡
በመኖሪያ ቤት ችግር የሚሰቃዩ ነዋሪዎች ከሚያገኙት ገቢ ላይ በየወሩ እንዲቆጥቡ በመገደዳቸው ኑሮን የከፋ ቢያደርግባቸውም፣ አማራጭ ስለሌላቸው ከልጆቻቸው የትምህርት ቤት ክፍያ፣ ከቤት ኪራይና ከቀለባቸው አብቃቅተው መቆጠቡን ተያይዘውታል፡፡ ቀደም ብሎ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት የተመዘገቡ ነዋሪዎች አስተዳደሩ በቅርቡ በዕጣ እንደሚያከፋፍል ቃል የገባውን የጋራ መኖሪያ ቤት እየጠበቁ ቢሆንም፣ አስተዳደሩ ግን ቃሉን አልጠበቀም፡፡
በዳግም ምዝገባው (ከሐምሌ እስከ ነሐሴ 2005 ዓ.ም.) ለነባር ተመዝጋቢዎች ከ17 ሺሕ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በዕጣ እንደሚከፋፈሉ፣ በድጋሚ በሚያዝያ ወር 2006 ዓ.ም. እንደሚያከፋፍል የተናገረውን ቃል በማጠፍ፣ ዕጣው የሚወጣው በሰኔ ወር ነው በማለቱ ነዋሪዎች ‹‹ድሮም እነሱን ማመን›› በማለት ቅሬታቸውን በተለያዩ አጋጣሚዎች እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ ሌላው አስተዳደሩ በልማት ምክንያት ለሚነሱ ነዋሪዎች የኮንዶሚኒየም ቤት ለመስጠት ቃል የገባ ቢሆንም፣ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ባለመጠናቀቁ በዕቅዱ መሠረት እየሄደ አለመሆኑን የከንቲባው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰግድ አምነዋል፡፡
በመሀል ከተማ በሚገኙ ቦታዎች ላይ ይገነባሉ በሚል በ40/60 ፕሮግራም የበርካታ ቤት ፈላጊዎችን ቀልብ ለመሳብ ፈልጐ የነበረው አስተዳደሩ፣ ያሰበውን ያህል ተመዝጋቢ ባለማግኘቱ በአራት ሳይቶች ላይ እየገነባ ከመሆኑ ባለፈ ብዙም የተሳካ ነገር ሲያደርግ አይስተዋልም፡፡ አዋጭነቱም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ በመሆኑ የ40/60 ተመዝጋቢዎች በማኅበር ከተደራጁት ውስጥ እንዲካተቱ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ግፊት እያደረገ መሆኑም ይሰማል፡፡ በማኅበር ተደራጅቶና መሬት ወስዶ ለመሥራት የተጀመረው ፕሮግራምም የተፈለገውን ያህል እንደልሆነ እየተነገረ ነው፡፡ በአጠቃላይ አስተዳደሩ በቤቶች ልማት ፕሮግራም ላይ እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ ባለፉት ስድስት ወራት ከወረቀት ላይ ያለፈ አርኪ ሥራ አለመሥራቱን ያመለክታል፡፡
የቴሌኮምና የኤሌክትሪክ መቆራረጥ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የቴሌኮምና የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ኤሌክትሪክ በተደረጋሚ ከመቆራረጡም በላይ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ለቀናት እየጠፋ መሆኑ የኅብረተሰቡ የዕለት ከዕለት ችግር ሆኗል፡፡
ኤሌክትሪክ በሚቆራረጥበት ወቅት ውኃና የቴሌኮም ኔትወርክ አብረው የሚቋረጡ በመሆናቸው ኅብረተሰቡ ለከፋ ቀውስ እየተጋለጠ ይገኛል፡፡ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ በማይኖርበት ወቅት ጭምር ውኃና ቴሌኮም የሚቋረጡ በመሆናቸውም ችግሩን አባብሶታል፡፡
ይህንን ችግር የከተማው ነዋሪዎች በሰፊው የሚያነሱት በመሆኑ፣ አስተዳደሩ ከሁለቱ የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጋር በጋራ ለመሥራት ኮሚቴ አዋቅሯል፡፡
ከንቲባ ድሪባ ኩማ ባቀረቡት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ይህንን ጉዳይ ጠቅሰዋል፡፡ የከንቲባው ሪፖርት እንደሚለው በኤሌክትሪክና በቴሌኮም ላይ የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡
የመጀመርያው የከተማው መልሶ ማልማትና ግዙፍ የልማት እንቅስቃሴ በሚካሄዱባቸው አካባቢዎች የመሠረተ ልማት (ኤሌክትሪክ፣ ውኃና ቴሌኮም) መስመሮች ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡
እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ከሁለቱ ተቋሞች ጋር የጋራ ሥራ መጀመሩ፣ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ (ቤንች ማርክ) በመነሳት የተለያዩ የማሻሻያ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
የከንቲባው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰግድ እንደገለጹት በየ15 ቀኑ በጋራ መድረኩ ውይይት ይደረጋል፡፡ እስካሁን ድረስ የቴሌኮም ችግርን ለመፍታት በ400 ቦታዎች ላይ የቴሌኮም አንቴናዎች መትከያ ያስፈልጋል ተብሎ፣ 327 ቦታዎችን አስተዳደሩ መስጠቱንና ቀሪዎቹ በሕንፃዎች አናት ላይ የሚተከሉ በመሆናቸው ኢትዮ ቴሌኮም ከሕንፃ ባለቤቶች ጋር እየተነጋገረበት መሆኑ ተወስቷል፡፡
የኤሌክትሪክ መቆራረጥን ለማስቀረትም የኤሌክትሪክ መስመሮችና ማስፋፊያ ጣቢያዎችን አቅም ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አቶ አሰግድ አክለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኢኮኖሚያዊና በማኅበራዊ ዘርፎች በርካታ ቅሬታዎች እየቀረቡበት ይገኛሉ፡፡ የኅብረተሰቡን ቅሬታ መሠረት በማድረግ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት፣ በየወሩ ከኅብረተሰቡ ጋር የሚገናኝበትን አሠራር ከታህሳስ 15 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ መዘርጋቱን አስታውቆ ነበር፡፡
በዚህ መድረክ በየጊዜው ኅብረተሰቡ በርካታ አንገብጋቢ ጥያቄዎችን ያለማቋረጥ ከማንሳቱም በላይ፣ የአስተዳደሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ችግሩን ከመሠረቱ ለማድረቅ እየሠሩ መሆናቸውን ከመናገር አልተቆጠቡም፡፡
ነገር ግን ከጥቃቅን እስከ ትላልቅ የሚነሱት ችግሮች ከመፍታት ይልቅ ይበልጥ እየተተበተቡ መሄዳቸውን በተለያዩ መድረኮች እየተገለጹ ነው፡፡ በዚህም የከተማው ነዋሪዎች እርካታ እንዲያገኙ ማድረግ አልተቻለም፡፡
ነዋሪዎች እንደሚሉት ለችግሮቹ ሁሉ ቁልፍ የሆነው የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች በባለቤትነት ስሜት ሥራዎችን መሥራት አለመቻላቸው፣ ከአቶ ኩማ ጋር የከረመው አሮጌው ካቢኔ እንዳለ ሳይነካ ከአቶ ድሪባ ጋር እንዲቀጥል መደረጉ በምክንያትነት እየተጠቀሰ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበርካታ ችግሮች የተተበተበ በመሆኑ መዋቅራዊ ለውጥና በሙያ የበለፀገ የሰው ኃይል ሥምሪት ወሳኝ መሆኑን ነዋሪዎች በአፅንኦት ይገልጻሉ፡፡