(ዘ-ሐበሻ) የወያኔ ሥርዓት ሰሞኑን በህግ ቁጥጥር አውያቸዋለሁ ካላቸው ተጠርጣሪዎቸ ጋር ሲፈለጉ ነበር የተባሉት አቶ ተመስገን ጉልላት ከአዲስ አበባ ወደ ጋምቤላ በመሸሽ ሱዳን ለመግባት ሁኔታዎችን ሲያመቻቹ ሊያመልጡ ሲሉ ተያዙ ሲል የወያኔ ሚድያዎች ሲገልጹ ተጠርጣሪው በእጃቸው የተለያዩ ሰነዶችና 160 ሺህ ብር ይዘው ሊሰወሩ ሲሉ ተይዘዋል ብለዋል።
በተጨማሪም በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ታስረዋል የተባሉት 24 ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ። ዛሬ በዋለው ችሎትም ተጠርጣሪዎቹን በሶስት የክስ መዝገብ በመከፋፈል ፍርድ ቤቱ የተመለከተ መሆኑን የዘገቡት መንግስታዊ ሚድያዎች በእነ መላኩ የክስ መዝገብ ውስጥ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች መካተታቸውን አስታውቀዋል። አንደኛው ተጠርጣሪ አቶ መላኩ ፈንታ ጠበቃ ደንበኛቸው በዋስ ለመለቀቅ ያስችሏቸዋል ያሏቸውን ማስረጃዎች ለፍርድ ቤቱ በቃል ማቅርባቸውም ታውቋል።
የሁሉንም ሀሳብ ያደመጠው ፍርድ ቤቱም በጊዜ ቀጠሮ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ ለነገ ቀጠሮ ይዟል። በተመሳሳይ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር፣ በአስርሺዎች የሚቆጠር ዶላርና ዩሮ ቤታቸው ሲበረበር ተገኘ በተባሉት በነገብረዋህድ የክስ መዝገብ ውስጥ የሚገኙ ተጠርጣሪዎችንና የአቃቢ ህግ መከራከሪያን ያደመጠ ሲሆን መደበኛ የስራ ሰዓት በመጠናቀቁ በጊዜ ቀጠሮው ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለነገ ቀጠሮ ይዟል ሲሉ የመንግስት ሚዲያዎች ዘግበዋል።
በእነመላኩ የክስ መዝገብ ውስጥ የሚገኙ 7 ተጠርጣሪዎች
1.መላኩ ፋንታ
2.እሸቱ ወልደሰማያት
3.መርክነህ አለማየሁ
4.አስመላሽ ወልደማርያም
5.ከተማ ከበደ
6.ስማቸው ከበደ
7.ዶክተር ፍቅሩ ማሩ
ከተከሰሱባቸው ወንጀሎች መካከል ቀረጥና ታክስ በማጭበርበር እንዲሁም አራጣ በማበደር የተከሰሱ ግለሰቦች ክስ ስልጣንን በመጠቀም እንዲቋረጥ በማድረግና በዚህም ያልተገባ ሀብትን መሰብሰብ የሚል ይገኝበታል ።
በእነገብረዋህድ የክስ መዝገብ የተከሰሱት 11 ተጠርጣሪዎች
1.ገብረዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ
2.በላቸዉ በየነ
3.ጥሩነህ በርታ
4.ተስፋዬ አበበ
5.ነጋ ገብረ እግዚአብሄር
6.ምህረተአብ ካሳ
7.ሙሌ ጋሻው
8.አሞኘ ታገለ
9.ኮለኔል ሃይማኖት ታፈሰ
10. ሀብቶም ገብረ መድህን
11. ወይዘሮ ንግስቲ ተስፋዬ
ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ የተከለከለ ሲሚንቶ እንዲገባ ማድረግ ፣ በኮንትሮባንድ የተሰማሩ ግለሰቦችን በማገዝ ፣ ከተጠርጣሪዎች መካከል የሁለቱን ክስ የሚደግፉ ሰነዶችን ማሸሽ የሚል ይገኝበታል ።
በሶስተኛው የናዝሬት ጉምሩክ ባልደረቦች በሆኑት በነ መሀመድ ኢሳ የክስ መዝገብ ውስጥ የሚገኙ 6 ተጠርጣሪዎች
1.መሃመድ ኢሳ
2.ሰመረ ንጉሴ
3.ዘሪሁን ዘውዴ
4.ማር እሸት ተስፋዬ
5.ሙሉቀን ተስፋዬ
6.ዳኜ ስንሻው
የተከሰሱባቸው ወንጀሎች ደግሞ በኮንትሮባንድ የተለያዩ እቃዎች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ማድረግና ያልተገባ ሀብት መሰብሰብ የሚሉ ናቸው።