ግርማ ካሳ
Muziky68@yahoo.com
ግንቦት 6 ቀን 2005 ዓ.ም
በዳያስፖራ ቀንደኛ የኢሕአዴግ ደጋፊና የኢሕአዴግ ደጋፊዎች አስተባባሪ የሚባሉት፣ የሲቪሊቲ ፓልቶክ ክፍል ዋና አድሚን፣ አቶ ብርሃኑ ዳምጤ (አባ መላ) ከአዉራምባ ታይምሱ ዳዊት ከበደ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ አደመጥኩ። አባ መላ ጠንካራ ትችት በኢሕአዴግ ላይ ሰንዝረዋል። ይሄም ብዙዎችን ሳያስገርም አልቀረም። «አባ መላ፣ አራዳ ነዉ፤ ወያኔ ሊወድቅ ሲል ፍሬቻ አብሮቶ ታጠፈ» ያሉም አሉ። ፡) ፡) እኔ ግን ብዙ አላስገረመኝም። አባ መላን ጨምሮ በርካታ የኢሕአዴግ ደጋፊዎች ገዢዉን ፓርቲ የሚደግፉት በሚደረጉ የልማት እንቅስቃሴዎች እንጂ፣ በዴሞክራሲና በሰብአዊ መብት መከበር ረገድ ብዙ ቅሬታዎች እንደነበሯቸው ስለማወቅ።
አባ መላን ጨምሮ በርካታ የሲቪሊቲ ክፍል አድሚኖች፣ ገዢዉን ፓርቲ ይደግፉ እንጂ፣ ገዢዉ ፓርቲ በሚያደርጋቸው የተሳሳቱ ተግባራት ላይ ተቃዉሟቸውን ያሰሙበት ጊዜ ጥቂት አይደለም። ኢሕአዴግ በልማቱ ረገድ የሚያደርገዉን እየደገፉ፣ በዲሞክራሲና በሰብአዊ መብት ረገድ የሚደረጉትን ስህተቶች ግን ብዙ ጊዜ ሲቃወሙ ሰምቻቸዋለሁ። ፓርቲዉ እንዲያሻሻል፣ አንዳንድ ጎጂ ፖሊሲዎቹንም እንዲቀይር፣ ዉስጥ ዉስጡን ግፊት ሲያደርጉ የነበሩ ናቸው።
አንድ ምሳሌ ልጥቀስ። ከአራት አመታት በፊት ሰኔ ወር 2001 ዓ.ም ላይ ነዉ። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በግፍ የታሰረችበት ወቅት። አቶ ስብሐት ነጋ በሲቪሊቲ ፓልቶክ ክፍል እንግዳ ሆነው ይቀርባሉ። በወ/ት ብርቱካን መታሰር ደስተኛ ያለሆኑትና ለመፈታቷ አጥብቀዉ ዉስጥ ለዉስጥ ሲታገሉ የነበሩት አባመላ፣ በገዢዉ ፓርቲ ላይ ያለቸዉን ተቃዉሞ በይፋ ገለጹ። ብዙ ታዳሚ ባለበት፣ አቶ ስብሃት ነጋን የሚከተለዉን ጠየቁ ፡
«አንዳንድ ጊዜ ከኢሕአዴግ በኩል፣ በዳያስፖራዉ የኢሕአዴግን ደጋፊዎች ሁሉ ሳይቀሩ፣ criticise የሚያደርጉት popular ያልሆኑ ነገሮችን ትወስዳላቹህ። አላስፈላጊ የሆነ። ለምሳሌ በቅርቡ በብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የተወሰደዉ እርምጃ ምንም እንኳን ጥፋት አጥፍታለች ቢባልም ቴክኒካሊ፣ አስፈላጊ ያልሆነ confrontation ነዉ። ብዙ የምንሰራዉ፣ እንደ አገር የምንሰራዉ ብዙ ነገር አለ። በሕግ አንጻር ሁሉን ነገር እንደ ሌጦ መተርጎም የለብንም። ሌሎች moral values የሕዝብ አስተያየት የመሳሰሉ ነገሮችን ግምት ዉስጥ አስገብቶ ማየት ይገባል። የአንድ ጠንካራ መንግስት መለኪያዉ እርሱ ነዉ ብለን እናምናለን። ምን አልባት እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች፣ implication ያላቸዉን ጉዳዮች avoid ለማድረግ በኢሕአዴግ በኩል አንዳንድ ድክመት አለ። በሕዝብ ታዋቂ የሆኑ፣ በጥሩም ሆነ በመጥፎ ተወዳጅነት ያላቸዉ የሙዚቃ ሰዉ ሊሆን ይችላል። ስፖርተኛ ሊሆን ይችላል። ወይም የፖለቲካ ሰዉ። በተለይ የብርቱካን ጉዳይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ዉስጥ እርስዎም እንደሚያወቁት፣ የሴቶች ታጋዮች ሚና በጣም በጣም ትንሽ ነዉ። በተቃዋሚም እንኳን ብትሆን «በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ እታገላለሁ» ብላ የገባች እስከሆነች ድረስ፣ በአምጽ የሚታገሉትን ተቃዉመን፣ ጠመንጃ ከሻቢያ ጋር አንስተዉ ግለሰቦችን ለመግደል፣ ተቋሞችን ለማፍረስ፣ የሚንቀሳቀሱትንም እያወገዝን፣ በሰላም «አገሬ ዉስጥ ሕግና ሕገ መንግስት አለ። መንግስትን ፊት ለፊት እታገላለሁ» ብሎ የገባዉንም ኃይል እኩል treat ማድረግ የለብንም። በተለይ ሴት በመሆኗ፣ የልጅ እናትም በመሆኗ፣ በኢትዮጵያ ዉስጥ የሴቶችን ሚና ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ እምነት አለዉ ብዬ ስለማምን፣ ኢሕአዴግ በእንደዚህ አይነት ሰዎች ላይ የምትወስዱት እርምጃ በምንም መልክ defend ልናደርግ፣ justify ልናደርግ እያቃተን ነዉ። ከእንደዚህ አይነት unpopular ድርጊት መቼ ነዉ ኢሕአዴግ የሚገደበዉ? ይሄን ጉዳይ በቅርቡ ለመፍታት የታሰበ ነገር አለ ወይ ?»[1]
አንድ የሕወሃት ታጋይ የነበረ ወዳጅ አለኝ። በእስረኞች መታሰር ዙሪያ ያለኝን ምሬት አደመጠና እንዲህ አለኝ «ወንድሜ ግርማ፣ አንተ በምትለው እስማማለሁ። ኢሕአዴግ ዉስጥ ብዙ ችግር አለ። እኔ ጦርነት ላይ ጓደኞቼ ሲሞቱ አይቻለሁ። በርሃ ገብተን የታገልነው ግፍን በመቃወም ነዉ። አሁን ግፍ በሕዝብ ላይ እንዲሰራ አንፈልግም። ኢሕአዴግ ለዉጥ ማድረግ አለበት። ኢሕአዴግ ማሻሻያ እንዲያደርግ ሁላችንም እንጣር። አንዳንች አንዳችንን እንደጠላት በማየት ሳይሆን ለአገራችን የጋራ ጥቅም አብረን እንስራ» ነበር ያለኝ። እኔም ተስማማሁ።
እንግዲህ እነዚህ የሚያሳዩት ብስለት ከማጣት የተነሳ፣ የኢሕአዴግ ደጋፊዎችን ሁሉ በአንድ ጨፍልቆ ማየት ትክክል እንዳልሆነ ነዉ። በጣም ብዙ የኢሕአዴግ ደጋፊዎች፣ ኢሕአዴግ የሚያደርጋቸውን የልማት እንቅስቃሴች እየደገፉ በዴሞክራሲና በሰብአዊ መብት መከበር ዙሪያ ለዉጦች እንዲደረጉ፣ ዉስጥ ዉስጡን ግፊት የሚያደርጉ አሉ። በባለስልጣናቱ «እናሻሽላለን፣ ድክመታችን እናርማለን …» እየተባሉ፣ ከዛሬ ነገ መሻሻሎች ይመጣሉ በሚል ሲጠባበቁ የነበሩ ናቸው። ለዚህም ነዉ አብዛኞቻችን «በኢሕአዴግ ዉስጥ ለዉጥ እንዲመጣ ለማድረግ ከኢሕአዴግና ከደጋፊዎቹ ጋር መሰዳደብ ሳይሆን በጨዋነት መነጋገር አለብን። በኢሕአዴግ ዉስጥ ለዉጥ ለማምጣት የሚሰሩ ኢሕአዴጎችን ማበረታታ አለብን» ስንል የነበረዉ። ይሄ ጥረታችንም ነዉ «ወያኔ» ሲያስብለን የነበረዉ።
በነአባመላ እንዳየነዉ፣ የብዙ የኢሕአዴግ ደጋፊዎች ትእግስት እየተሟጠጠ የመጣ ይመስለኛል። በተለይም በሰብአዊ መብት መከበርና በዴሞክራሲ ዙሪያ፣ እንኳን መሻሻል ሊኖር፣ እየበሳስበት መምጣቱን፣ በፓርቲዉ ያሉ የበሰሉ ሰዎች ወደ ጎን እየተገፉ በአንጻሩም የጫካ አስተሳሰብ ያላቸዉ፣ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝንም አላሰራም ያሉ፣ የአስተሳሰብ እንጭጮች አይለው መዉጣታቸውን እና ኢሕአዴግ በራሱ ሰዎች ከሕዝብ ጋር በየጊዜው እየተጋጨ፣ በዉስጡ እየተሸረሸረ አደገኛ ሁኔታ ላይ መሆኑን የታዘቡ ይመስላል። የታቀዱ የልማት እንቅስቃሴዎች ከግቡ እንዲደርሱ፣ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ፣ የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ.፣ የታሰሩ የሕሊና እስረኞች እንዲለቀቁ፣ ከሙስሊሞች ጋር ያለዉ ችግር በሰላም እንዲፈታና በአገራችን እርቀ ሰላም እንዲወርድ ለማድረግ፣ ኢሕአደግ ዉስጥ ያሉ እንክርዳዶች መወገድ እንዳለባቸው የተረዱ ይመስላል።
በመሆኑም በኢሕአዴግን ዉስጥ ያሉ ስልጣን የጨበጡ አክራሪዎችን ለመታገል፣ ከወሬ ያለፈ፣ አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ጀምረዋል። ከፍተኛ ገንዘብ የማሸሽ እንቅስቅሴ እየተደረገ እንዳለ የጠቆሙት፣ የሲቪሊቲ አድሚኖች በዴንቨርና በዲሲ፣ 1 ዶላር በ27 ብር እንደሚመነዘር፣ አገር ቤት ያሉ አንዳንድ ግለሰቦችም እስከ 1 ሚሊዮን ዶላር ወደ ዉጭ ለማሸሽ፣ በአገር ቤት 27 ሚሊዮን ብር ለመክፈል እየሞከሩ እንደሆነ ይናገራሉ።
በአሜሪካና በካናዳ እንዲሁም በለንደን ፣ በዚያ መኖር ከጀመሩ አንድ አመት ባልሞላቸው ሰዎች የተገዙ ከ300 ሺህ ዶላር በላይ የሚያወጡ በርካታ ቤቶች ፣ (ሃብታሞች በሚኖሩባት በኦሬንጅ ካዉንቲ ካሊፎርኒያ ብቻ የታወቁ፣ ወደ አራት የሚሆኑ ቪላ ቤቶች) እንዲሁም የተከፈቱ በርካታ ቢዝነሶች እንዳሉ ያስረዱት የሲቪሊቶ ክፍል አድሚኖች፣ እነዚህን ከሕዝብ በተዘረፈ ገንዘብ፣ የተገዙ ቤቶችንና ቢዝነሶችን በተመለከተ ያሰባሰቧቸው፣ በፎቶ ግራፍ ላይ የተመረኮዘ መረጃዎች በቅርብ ጊዜ ዉስጥ ይፋ እንደሚያደርጉ አሳዉቀዋል። (በነገራችን ላይ የሕወሃት ነባር ታግይ ያልኩት ከላይ የጠቀስኩት ወዳጄ የሚኖረዉ፣ እየሰራ፣ እንደማንኛዉም ሌላው ኢትዮጵያዊ መለስተኛ በሆነ አፓርተማ ዉስጥ ነው። የ300 ሺህ ዶላር ቤት አልገዛም። ስለዚህ የሕወሃት/ኢሕአዴግ ደጋፊ ሁሉ ገንዘብ በልቷል፣ ሰላይ ነዉ ወዘተረፈ የሚል የተሳሳተ አስተያየት አይኑረን። ስንከስ በስሜት ሳይሆን በመረጃ ይሁን። እንሰልጠን።)
ይህ የተዘረፈዉን የሕዝብ ገንዘብ ለማስመለስ በ«ኢሕአዴግ ደጋፊዎች» የሚደረገዉን ጥረት፣ አገሩን በሚወድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሊደገፍ ይገባዋል ባይ ነኝ። ይህ መልካም እንቅስቃሴ፣ ትምህርት ሆኖን፣ ዜጎችን «ወያኔ፣ ሆዳም» እያሉ የመስደብ አመላችንን አቁመን፣ «በምንስማማባቸው ነጥቦች ከኢሕአዴግ ደጋፊዎች ጋር አብረን መስራት መልመድ» አለብን እላለሁ።
በርካታ የኢሕአዴግ ደጋፊዎች ፣ እኛ እንዲኖር የምንፈልገዉን መልካም ለዉጥ፣ በኢሕአደግ ዉስጥ ይፈልጋሉ። የሕሊና እሥረኞች በሙሉ እንዲፈቱ ይፈልጋሉ። የዲሞክራሲ ስርዓት እንዲገነባ ይፈልጋሉ። እርቀ ሰላም እንዲወርድ ይፈልጋሉ። አሁን በአገዛዙ እየተደረገ ያለዉ የልማት እንቅስቃሴ እንዲቀጥልም ይፈልጋሉ።
እንግዲህ ለመልካም ለዉጥ፣ ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ ለእርቅ ፣ ለሰላም፣ ለልማት አብረናቸው የማንሰራበት ምክንያት የለም። የሚያሳዝነው አሁን ስልጣን ከበስተጀርባ የጨበጡትና በኢሕአዴግ ዉስጥም ችግር የፈጠሩት ጥቂት ጨካኝ፣ ዘረኛና ክፉ ባለስልጣናት መሆናቸው ነዉ። «EPRDF is controlled by hateful elements» [2]በሚል በቅርብ ጊዜ ይሄንኑ እዉነታ ለማንጸባርቅ ሞክሪያለሁ።
ለምሳሌ ጋዜጣኛ ተመስገን ዳሳለኝ እንደዘገበዉ፣ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ እንዲሁም አቶ ደመቀ ብርሃኑ፣ እነ እስክንድር ነጋ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ይፈልጋሉ። ዶር ቴዎድሮስ አዳኖም እና ከሃላፊነታቸው የተሰናበቱት፣ በአዲስ አበባ ከተማ በሰሩት ሥራ የማከበራቸው፣ አቶ አርከበ እቁባይ ተመሳሳይ አመለካከት እንዳላቸው ፣ ካሉኝ አንዳንድ መረጃዎችም ፍንጭ ለማግኘት ችያለሁ። ፕሬዘዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፣ የአጼ ኃይለስላላሴ ሃዉልት በአፍሪካ ሕብረት ከጋናዉ ንክሩማ ጎን እንዲቆም ደብዳቤ ጽፈዋል።
ነገር ግን ለእስረኞች መፈታትም ሆነ ለአጼ ኃይለስላሴ ሃዉልት መሰራት፣ መሰናክል የሆኑት፣ እነ እስክንድርን «መለስ ዜናዊ አደገኛ ብሎ አስሯቸዋል። እዚያዉ ቃሊቲ ይበስብሱ» የሚሉ ፣ እነ ደምቀ ብርሃኑን አላሰራም ያሉ፣ ሚሊተሪዉንና ደህንነቱን የሚቆጣጠሩ፣ እፍኝ የማይሞሉ ጥቂት ግለሰቦች ናቸው። እርግጠኛ ነኝ አብዛኛዉ የኢሕአዴግ ደጋፊ፣ እነ አባመላ እንዳደረኩት፣ ከተነሳ፣ በአጭር ጊዜ ዉስጥ እነዚህ እፍኝ የማይሞሉ እፉኞች ታሪክ ይሆናሉ።
ምንም እንኳን በነአባ መላ እያየን ያለነዉ አስደሳች ዜና ቢሆንም፣ የተቀረዉ የተቃዋሚ ኃይል ግን የበለጠ እራሱን ማደራጀት ይጠበቅበታል። ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት በኢሕአዴግ ዉስጥ ለዉጥ እንዲመጣ መጠበቁ፣ ለዚያም መስራቱ ተገቢ ቢሆንም፣ ያንን ብቻ ጠበቆ ግን ቁጭ ብሎ መቀመጥ ትልቅ ስህተት ነዉ። የተቃዋሚዉ ኃይል እራሱን ከመቼዉም ጊዜ በበለጠ ፣ በቲቪና በስብሰባዎች ቀርቦ ከማዉራትና፣ መግለጫዎች ከማውጣት ያለፈ፣ በተጨበጡ ስራዎች ዙሪያ እራሱን የማሰማራት እንቅስቃሴ ይጠበቅበታል። ለዚህም ነዉ እንደ አንድነት ፓርቲና መኢአድ ያሉ፣ አገር ቤት ያሉ ድርጅቶች ሆነ፣ ከአገር ዉጭ የሚገኙ፣ እንደ ሽግግር መንግስት ምክር ቤትና አዲሱ የኦሮሞ ዴሞክራሲያ ግንባር ያሉ ድርጅቶች፣ እንዲሁም ኢትዮጵያዉያን ሁሉ፣ አገር ቤት ያለዉ የሰማያዊ ፓርቲ፣ ግንቦት 17 ቀን 2005 ዓ.ም በአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ ፊት ለፊት በጠራዉ የሰላማዊ ሰልፍና ከግንቦት 15 እስከ ግንቦት 17፣ ጥቁር አልባሳት በመልበስ፣ ለሚደረገዉ የሰላማዊ ተቃዉሞ ወቅታዊ ጥሪ፣ ሕዝባዊ ምላሽ መስጠት ያለባቸው። ማንም ይጠራዉ ማንም፣ መልካም እስከሆነ ድረስ መደገፍ አለበት። የምንፈልገዉ በአገራችን ለዉጥ እንዲመጣ እንጂ ድርጅት አምላኪዎች አይደለንም። (በዚህ ረገድ እንደ ቃሌ ፓልቶክ ክፍል፣ ኢትዮጵያ ሪቪው፣ ዘሃበሻ፣ ኢኤም.ኤፍ የመሳሰሉ ድህረ ገጾች፣ እንዲሁም ኢሳት፣ ይሄንን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማገዝ እያደረጉ ያሉትን ጥረት ለማበረታት እወዳለሁ። በዚህ ጉዳይ በሰፊዉ የምመለስበት ይሆናል። እስከዚያም በቸር እንሰብት።