Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የስፖርት ጋዜጠኞች የተያያዙት ማዝናናት ወይስ ማዘናጋት?

$
0
0
 በግሬስ አባተ
cbአሁን ባለንበት ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሁሉም ነገር በሚባል ሁኔታ ጮክ ተብለው የሚወሩት ሁለቱ ነገሮች ናቸው፡፡ አንደኛው የአውሮፓ እግር ኳስ ሲሆን ሁለተኛው ፆታዊ ግንኙነትን የተመለከቱ ርዕሶች ናቸው፡፡  በዚህ ፅሁፍ ለመዳሰስ  የፈለኩት በአውሮፓ እግር ኳስ  ዙሪያ የመገናኛ ብዙሃንን ያልተገደበ አስተዋዋቂነት ወይም ቲፎዞነት ወይም የማራገብ  ሁኔታ መመልከት፤ እንዲሁም የዚህ ማራገብ አስፈላጊነቱ ለምን እንደሆነ መግለፅ  ይሆናል፡፡
ለመነሻ ያህል በአዲስ አበባ ካሉት የራዲዮ ፕሮግራሞች እንኳን ብንጀምር ምን ያህል ሰአት ለአውሮፓ እግር ኳስ እንደሚሰጡ መታዘብ ይቻላል፡፡ ከሌሎች የራዲዮ ፕሮግራሞች አንፃር አብዛኛውን የአየር ሰአት ተሰጥቶት የሚለፈፈው የእስፖርት ፕሮግራም ነው፡፡  በአዲስ አበባ ካሉት ኤፍ ኤም ራዲዮኖች፤ በእንግሊዝኛ ከሚተላለፈው አፍሮ ኤፍ ኤም  በተስተቀር አብዛኛው ለእግር ኳስ የሚሰጡት የአየር ሰአት ከፍ ያለ ነው፡፡  እንዲሁ ለእግር ኳስ አልኩ እንጂ ይህም ለሃገር ውስጥ ከሚሰጠው የአየር ሰአት ጋር ሲነፃፀር ሰማይና መሬት መሆኑን ዘወትር የምንታዘበው ነው፡፡ ያንበሳው ድርሻ  ለማንችስተርና ለአርሰናል፤ለባርሳና ማድሪድ ወ.ዘ.ተ ይሰጣል፡፡ እዚህ ላይ የአገር ውስጡን ስፖርት እንዲሁ ለቅንነት ያህል ገለፅኩት እንጂ ከማንችስተር እና አርሰናል አንፃር  የአየር ሰአት ያገኛል ለማለት እንኳ አያስደፍርም፡፡
ለምሳሌ ያህል የራዲዮኖቹን አነሳው እንጂ በጋዜጣ የሚታተሙትን እድሜ ጠገቦቹን ኢትዮ ስፖርት፣ ወርልድ ስፖርት፣ዘ-ገነርስ… እማ  95% የሚሆነው የጋዜጣቸው ሽፋን ለአውሮፓ እግር ኳስ እንደሚሰጡ ግልፅ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ማለትም በህትመትና በራዲዮ ካሉት በተጨማሪ  ብቸኛው ኢቲቪ(ለነገሩ አሁን ኦሮሚያ ቲቪም የአውሮፓን እግር ኳስን በማስተላለፍ ከኢቲቪ ጋር እኩል እየተጋ ይገኛል፡፡) በነፃ በማስተላለፍ ጠመቃውን እያሳለጡት ይገኛሉ፡፡ አንድ አይነት አካሄድ የሚስተዋልበት ይህ የአውሮፓ እግር ኳስ የጠመቃ አካሄድ ጥርጣሬን ካጫረብኝ ሰንበትበት ብሏል፡፡  እንዳልኩት ሱፐር እስፖርት በክፍያ ኢቲቪና ኦሮሚያ ቲቪ በነፃ በድምፅ እና ምስል የሚያስተላልፉት ሲሆን በራዲዮን በኩል እነ መሰለ መንግስቱ ከሱፐር ስፖርቶቹ ጋዜጠኞች በላይ ሰፊ የአየር ሰአት ወስደው በቀጥታ ያስተላልፋሉ፡፡ ሸገር ኤፍ ኤም ላይም እንዲሁ በየሳምንቱ የሚተላለፍ ፕሮግራም እንዳለ ይታወቃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የየጨዋታዎቹን ውጤት ተከትሎ ትንታኔ የሚሰጡ ጋዜጠኖች ቁጥራቸው የትየሌሌ ነው፡፡ ለዚህ ይመስላል የአውራምባ ታይምሱ አቤል አለማየሁ በአንድ መፅሃፉ ‹‹አንተ ብቻ የስፖርት ጋዜጠና ሁን›› ሲል የጊዜውን ሁኔታ የገለፀው፡፡
በየቀኑ የሚሰጡትን የእግር ኳስ የትንታኔ ሰአቶች እንኳን ትተን በሳምንት የሚሰጠውን የቀጥታ ስርጭት ብንመለከት ጉዳዩ ምን ያህል እየተሰራበት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ለምሳሌ ‹‹እግር ኳስን በራዲዮ ተመልከቱ›› የሚለውን የመሰለን ፕሮግራም ለአብነት ብንወስድ በየሳምንቱ ለአንድ ጨዋታ  በትንሹ 90 ደቂቃ የቀጥታ ጨዋታው + ከጨዋታው በፊት 30 ደቂቃ + 30 ከጨዋታው በሁዋላ ያለውን ብንወስድ በድምሩ በሳምንት 2:30 ይወስዳል፡፡ ይህ በወር ሲመታ፣ በአመት ሲመታ ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል አስቡት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ   ከውጤትና ከጨዋታ በፊትና በኋላ ያሉትን ትንታኔዎች የወሰድን እንደሆነ ከአፍሮ ኤፍ ኤም ውጪ በቀን እያንዳንዱ ራዲዮን በትንሹ 2:00 የአየር ሰአት ለአውሮፓ እግር ኳስ ይሰጣል፡፡ ይህን በሳምንት እንዲሁም በወር ሲመታ አስቡት ምን ያህል እንደሆነ!
የእኔ መከራከሪያ ለምን ስፖርት ተወራ አይደለም፡፡  ጉዳዬ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት ላይ መነሳትም አይደለም፡፡ እርግጥ ነው መናገር መብታቸው ነው፡፡ ስለ ዋይኒ ሩኒ፣ሜሲ፣ሮናልዶ  እድሜ እና ክብደት እንዲሁም ቁመት መናገር ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት ነው ከተባለ መቼስ ምን ይደረጋል፡፡ ጥያቄዬ ስለምን ይህን ያህል የአየር ሰአት ተሰጥቶት ሊወራ ቻለ ነው? ይህንን የሚያግዝ በተጨባጭ ኢትዮጵያ ውስጥ ምን አለ ነው? መቼም አድማጭም ተመልካችም ያለው የአውሮፓ እግር ኳስን ነው፤ የሚል ቀልድ አዘል አስተያየት  አይቀርብም አይባልም፡፡ ይህ ቁጥር ነጋ ጠባ እያሻቀበ እንዲሄድና ወጣቱ ስለ ራሱ የወደፊት ሁኔታ ከመጨነቅ ይልቅ ስለ ማንችስተርና አርሰናል እንዲጨነቅ ነጋ ጠባ የሚለፈለፍለት ስለምን ይሆን? መቼም ከዚህ ጀርባ አንድ ድብቅ ሴራ እንዳለ ግልፅ ነው፡፡
ለዚህም ማጠናከሪያ የሚሆነን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአለም ወንጫ ማጣሪያ ላይ የተከሰተው  ድርጊት  ነው፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ቡድን ሁለት ቢጫ ካርድ ያየ ተጫዋች አላግባብ አሰልፏል ተብሎ 3 ነጥብ እንደተቀነሰበት ሰምተናል፡፡ እዚህ ላይ  መነሳት ያለበት የስፖርት ጋዜጠኞች ድርሻ ነው፡፡ የኛ የስፖርት ጋዜጠኞች ምን ይሰራሉ? የነ ሩኒን ፣ የነቫምፐርሲን፣ የነሮናልዶን ወ.ዘ.ተ ከእግር ጫማቸው እስከ እራስ ፀጉራቸው ሲለፈልፉልን ስለምን ስለአገራቸው እግር ኳስ ቢያንስ በ90 ደቂቃ ውስጥ የተመዘዘውን ቢጫ ካርድ መዝግበው  መያዝ  አቃታቸው? የአርሰናሉ ኮሶሎኒ በሁለት ቢጫ ካርድ ምክንያት በሚቀጥለው ጨዋታ አይሰለፍም፣ ሜሲ እዚህ አገር ተወልዶ እንትን በምትባል መንደር አድጎ ቁመቱ ይህን ያህል ክብደቱ ይህን ያህል የሚሉን የስፖርት ጋዜጠኞች ስለምን የኛን ቡድን የ 90 ደቂቃ ቢጫ እንኳ መቁጠር አቃጣቸው ብለን ስንጠይቅ ሴራው ፍንትው ብሎ ይታየናል፡፡ በማስታወቂያ በኩል ያለውን ብንመከት ድርጅቶች ስፖንሰር የሚያደርጉት የእስፖርት ፕሮግራሞችን 90% ያለፈ መሆኑን ሌሎች ፕሮግራሞች ባንፃሩ የማስታወቂያ ድርቅ ሲመታቸው እንመለለከታለን፡፡ ምነው ይህን ያህል እዚህ አገር ሳናውቀው ኳስ ተዘርቶ ኳስ መታጨድ ተጀመረ እንዴ?
ምንአልባት በደምብ አልገለፅኩት ይሆናል አንጂ አሁን ያለው ሁኔታ እጅግ አስከፊ ወደ ሆነ አዘቅት ውስጥ የሚከተን ይሆናል፡፡ አንድ ታዳጊ አገር ያውም ከድህነትና ከችጋር ያልተላቀቀች አገር ውስጥ የተማሩና ገና የመጀመሪያ ደረጃ ትምርታቸውን ያልጨረሱ አፍላ ወጣቶች ሳይቀሩ በአውሮፓ እግር ኳስ ተጠምደው ነጋ ጠባ የሚያሳስባቸው የክለቦቹ መሸነፍና ማሸነፍ ሲሆን ወዴት እየሄድን እንደሆነ እና ሴራው ግቡን እየመታ መሆኑን እንረዳለን፡፡ በየመስሪያ ቤቱ ስለ አውሮፓ እግር ኳስ  ሲከራከሩ ከፍ ሲልም  ሲደባደቡ መመልከት ብዙም የሚያስደንቅ አይደለም፡፡ ተማሪዎችም በእረፍት ግዜያቸው ሰብሰብ ብለው ሲያወሩ የሚሰሙት   ስለ እግር ኳስ ከሆነ አመታት ተቆጠሩ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች ሳይቀሩ የመጀመሪያው ወሬያቸው ስለተሰጣቸው የቤት ስራ ሳይሆን ስለ ማታው ጨዋታ ከሆነ ቆየ፡፡ ገና 10 እና 11 አመት ያልሆናቸው ልጆች ስለምን  ስለ አርሰናል እና ማንችስተር ነጥብ መጣል እንዲሁም ስለ ተጫዋቾች ጉዳት እንዲጨነቁ ተፈረደባቸው?
 ገና ከወዲሁ ትውልዱን በአንድ አይነት አካሄድ የመቅረፅ ሴራ… ከፍ ያለውንም እንዲዝናና ሳይሆን መሬት ላይ ያለውን  እውነት እንዳያይ ማዘናጋት የስፖርት ጋዜጠኖች ድርሻ ከሆነ ቆየ፡፡  ጋዜጠኞቹም ገንዘብ እስካገኙ ድረስ  የትውልዱ እጣ ፋንታ ግድ የሚሰጣቸው እንዳልሆነ አሳይተውናል እያሳዩንም ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ እነሆ ማን ነው ይችን አገር የሚረከባት? መቼም 4-4-2 አሰላለፍ  በስነ-ምግባርና በእውቀት የታነፀ ትውልድ ለመቅረፅ ቀርቶ ቤተሰብን ለመምራት እንኳ አያገለግልምና የትውልዱ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው፡፡ ምን ብናረግ ትውልዱን ከዚህ አይነት አፍዝዝ አደንዝዝ ሴራ ማውጣት እንችላለን? የሚለው የሁሉም የአገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ  ድርሻ በመሆኑ፤ ለዚህ ሴራ መክሸፍ የበኩላችንን በማድረግ ትውልዱን ልናድነው ይገባል፡፡
ግሬስ አባተ

Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>