በአዲስ አበባ የሚሰራጨው ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ራድዮ እንደዘገበው የመብራት መቆራረጥ ያማረረው በአዲስ አበባ የሽሮሜዳ አካባቢ ነዋሪዎች ሰልፍ ወጡ።
ራድዮው እንዳነጋገራቸው ነዋሪዎች ገለጻ በአካባቢው የሚኖረው ሕዝብ በተደጋጋሚ ለሚመለከተው አካል ስሞታ ቢያቀርቡም መፍትሄ ባለማግኘታቸው ስልፍ ለመውጣት ምክንያት ሆኗቸዋል። ሰልፈኞቹ በተደጋጋሚ የሚያጋጥመውን እና ብልጭ ድርግም ከማለት ጀምሮ ለቀናት ጭራሹኑ እስከመጥፋት በሚደርሰው የኤሌክትሪክ ሃይል መማረራቸውን ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በመገኘት ነው በተቃውሞ ሰልፍ ድምጻቸውን ሲያሰሙ ውለዋል ያለው ራድዮ ጣቢያው የሚመለከታቸውን የስራ ሃላፊዎች በማግኘት ምላሻቸውን ለመስማት የተደረገው ጥረት አልተሳካልኝም ሲል ዘግቧል።
በሌላ በኩል በተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥን በመማረር በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የተለያዩ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ድምጻቸውን ለማሰማት የወጡ ሰልፈኞች ምላሸ ሳይሰጣቸው “ተበተኑ” በሚል ትእዛዝ እንዲበተኑ እንደሚደረግ ሸገር የዘገበ ሲሆን የሽሮሜዳ አካባቢ ነዋሪዎችም የሬድዮ ጣቢያው ጋዜጠኞች በቦታው ከመድረሳቸው በፊት እንዲበተኑ መደረጉን ነው አስታውቋል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የትራንስፖርት፣ የውሃ፣ የመብራት፣ የቴሌኮምዩኒኬሽን፣ የጋዝ እና የሌሎችም እጥረቶች ሕዝቡን እያማረሩት ከእለት ተእለት እንቅስቃሴው እየገደቡት ይገኛሉ።