ምኒልክ ሳልሳዊ
በዚህ ሳምንት አትክሮት ማግኘት ከሚፈልጉ ወገኖቻችን በዋነኝነት በኩዌት የሚኖሩ እና በስራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ናቸው:: ባሳለፍነው ቀናት በዋና ዜናነት በአገሪቱ የስፖርት ሚኒስትር መኖሪያ ቤት ውስጥ የምትሰራ ኢትዮጵያዊቷ የቤት ሰራተኛ የአሰሪዋን ሴት ልጅ ገላለች ተብሎ የተዘገበውን ዜና ተከትሎ ኢትዮጵያውያን በስጋት ላይ ሲሆኑ እንዲሁም ተከራካሪ የዜግነት መብታቸውን የሚያስከብር ኤምባሲ መጥፋቱ እና በኤምባሲው የሚፈጸመውን ደባ በከፊል ለማየት እንሞክራለን::
በአሁኑ ወቅት በኩዌት ለኢትዮጵያውያን ነገሮች ሁሉ አስቀያሚ እና አስቸጋሪ እየሆኑ እንደሆን ለኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ቅርብ የሆነ ኢትዮጵያዊ ገልጿል::ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደረጉ በደሎች ተከራካሪ የመንግስት አካል እና የኤምባሲ ሰው መጥፋቱ ለአሁኑ ወንጀል መፈጸም እና ስጋት መንስኤ እንደሆነ ጠቁሟል::በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሱ በደሎች እና ከአሰሪዎቻቸው እና ከቀጣሪ ድርጅቶች ጠፍተው የሚመጡ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሃገራቸው መመለስ ሲገባው ከደላሎች ጋር በመመሳጠር ሌላ ስራ በማስገባት ችግሩ እንዲሰፋ ያደረገው እምባሲው እና ሆዳም ዲፕሎማቶቹ ናቸው ሲል ይኸው የኮሚኒቲው ሰው ገልጿል::ኢትዮጵያውያን በኩዌት እስር ቤት እየተሰቃዩ ከፍተኛ ወጪ ከኤምባሲው እና ከኮሚኒቲው በማውጣት ደግሰው በመጨፈር ላይ በነበሩበት ሰአት ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠማቸው ሲሆን ወገኖቻችን በእስር ቤት እየተሰቃዩ ለምን እንዲህ አይነት ድግስ ይደገሳል:: አስፈላጊውን ወጪ በማድረግ ወደ ሃገራቸው የሚመለሱ ይመለሱ ያሉ ወገኖችን የተለያየ የኤምባሲ ትብብር በመከልከል ወደኤምባሲው በር እንዳይደርሱ በማገድ ከፍተኛ የሆነ የግል ጥቅምን ያማከለ በደል እየተፈጸመ መሆኑን የኮሚኒቲው ሰው አጫውቶናል::ለማንም ተደግሶ የማያውቅ ኮሚኒቲው የኢትዮጵያ ሆኖ እያለ ለሌሎች ኢትዮጵያውያን እና ግለሰቦች ሳያገለግል የትግራይ ልማት ማህበር አላማን ሲያስተምር ይውላል ሲሉ አባላቱ ይተቹታል:: የታሰሩትን ለጊዜው ተወት አድርጓቸው እና የሃገራችንን መልካም ገጽታ እናስተዋውቅ እያሉ ለዜጎች አትኩሮት በመንፈግ አሁን ላለንበት ስጋት አብቅተውናል ሲሉ ኢትዮጵያውያን በማማረር ይናገራሉ::
ኮሚኒቲው ሲቋቋም ለታሰሩ እና ለተቸገሩ መፍትሄ ይሆናል ተብሎ የነበረ ቢሆንም በስሙ መካከል ህዳሴ የሚል ቃል በመጨመር ቢሮውን ከነበረበት ቦታ ወደ ኤምባሲው ውስጥ በማዘዋወር ፖለቲካ እየሰበከ ኢትዮጵያውያንን ረስቷል ሲሉ ይናገራሉ::ሌላው ነገር ይላሉ ኢትዮጵያውያኑ ማንኛውንም ደብዳቤ በኤምባሲውም ይሁን በኮሚኒቲው ማህተም ተደግፎ ቢጻፍ በኩዌት ውስጥ ተቀባይነት የለውም ሲሉ ይገልጻሉ::የመኖሪያ ፈቃድ ለማሳደስ በእጃችን ፓስፖርት እያለ ፓስፖርቱን ለመቀበል የኩዌት መኖሪያ ፈቃድ የሚያድሰው አካል ብዙ መጉላላት እና ወከባ እንደሚፈጽምባቸው እና ይህንንም ለኤምባሲው ሪፖርት ቢደረግ የራሳችሁ ጉዳይ የሚል ዘለፋ አዘል መልስ እንደሚሰጡ ታውቋል::
በግድያ ወንጀል ተጠርጥራ የተያዘችው ኢትዮጵያዊት ተከትሎ የመኖሪያ መታወቂያዎች እንዲታደሱ መደረግ የጀመረ ሲሆን ካሁን በፊት NON KUWAITI የሚል ሲጻፍ የነበረ ሲሆን በኣሁን ሰአት ለኢትዮጵያውያን በተለየ መልኩ Ethiopian ኢትዮጵያዊ የሚል መጻፍ የተጀመረ መሆኑ ታውቋል::
የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ምንም መከራከር የማይችል እና በመኪና ተገጭተው የሞቱ ታንቀው ራሳቸውን ከፎቅ ወርውረው የሞቱ ኢትዮጵያውያን ደብዛቸው እና የሞት ጉዳያቸው እንዳይነሳ ኮሚኒቴው በመሸፋፈን ለችግር እየዳረገን ነው ሲሉ በኮሚኒው ላይ አማረዋል::በ17 አመቷ ወደ ኩዌት የገባችው እና በአሁን ሰአት የ22 አመት ወጣት የሆነችው በግድያ ተጠርጥራ የተያዘችው ኢትዮጵያዊት በአሰሪዎቿ ልጆች የተደፈረች መሆኗን ለኤምባሲው ቅርብ የሆነ ግለሰብ ተናግሯል::ግድያውን ከመፈጸሟ በፊት በልጁ የተደፈረች እና ይህንን ጉዳይ ለሴት ልጂቷ ብትናገር የሚሰማት ያጣት እና የደበደቧት መሆኗን እና ይህንን ተከትሎ ወንጀሉን ፈጽማው ይሆናል የሚሉ ግምቶች በስፋት ይነገራል::
በኢምባሲው ውስጥ የሚደረገው ከፍተኛ በደል በኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ሲሆን በኤምባሲው ውስጥ ከ400 እስከ 500 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን የሚገኙ ሲሆን: ከፍተኛ የሆነ መጉላላት እየደረሰባቸው ለኣእምሮ ጉዳት ለጭንቀት ለድብርት እና ለእብደት መዳረጋቸውን የገለጹ ሲሆን በኤምባሲው ውስጥ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ያለ ሲሆን ኤምባሲው ግን በድግስ እየተንበሸበሸ ኮሚኒቲው በየድህረገጹ የፌሽታ ፎቶዎችን በመርጨት ከፌሽታው ጀርባ ግን የኢትዮጵያውያን ሞት እና ሰቆቃ ለእይታ እንዳይበቃ እያደረገ ሲሆን አንድም ቀን የሞቱ እና የተበደሉ ኢትዮጵያንን ቦታ ሳይሰጥ የኢትዮጵያውያን መብት እና ነጻነት ሳያስከብሩ በአደባባይ ስንገላታ እያዩን ያላግጡብናል ያመናጭቁናል ከፖሊስ ጋር ይተባበሩብናል በማለት አቤቱታቸውን የሚሰማ አካል እንዳላገኙ እና በስጋት አጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸውን ኢትዮጵያውያን ተናግረዋል:: ተጨማሪ ዘገባዎች ካሉ እንመለሳለን::