ከዳዊት ሰለሞን
ባሳለፍነው ሳምንት ታላቁ ሩጫ ባዘጋጀው የሴቶች ውድድር ላይ በመሳተፍ ተቃውሞ በማሰማታቸው ለእስር የተዳረጉት ሰባት ሴቶችና ተባባሪ ተደርገው የታሰሩ ሶስት ወንዶች ዛሬ በነበራቸው ቀጠሮ መሰረት ቀበና በሚገኘው ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር፡፡
ታሳሪዎቹ በአንድ ፖሊስ ጣብያ ውስጥ የከረሙ ቢሆንም ፖሊስ ወደ ፍርድ ቤቱ በመጀመሪያ ያመጣው ወንዶቹን ነበር፡፡ሴቶቹ ለሰዓታት ዘግይተው በሩጫው ወቅት ለብሰውት የነበረውን ባለ ሙሉ ቢጫ ቀለም ቲ ሸርት እንደለበሱ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡
ዳኛው ከተሰየሙ በኋላ ከሳሽን በመወከል የቀረቡ ሁለት ፖሊሶች ‹‹ምርመራችንን ባለማጠናቀቃችን ተጨማሪ የሰባት ቀን የምርመራ ግዜ ይፈቀድልን››በማለት ጠይቀዋል፡፡የተከሳሾች ጠበቃ(የጋዜጠኛ ርዕዮት ወላጅ አባት አቶ አለሙ ጎቤቦ) ፖሊስ ደምበኞቼን በእስር ለማቆየት ካለው ፍላጎት እንጂ ወንጀሉ ተፈጸመ የተባለው በአደባባይ በመሆኑ ተጨማሪ ምርመራ አያስፈልገውም ስለዚህ ደምበኞቼ ጉዳያቸውን በውጪ ሆነው እንዲከራከሩ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብታቸውን ያክብርልኝ››በማለት ተከራክረዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ የመናገር እድል እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ሲፈቀድላቸው ‹‹ሲቪል የለበሱ ሰዎች እየመጡ በሌሊት ጭምር ከታሰሩበት ቤት እንዲወጡ በማድረግ እንገድላችኋለን፣ከአሸባሪዎች ጋር መስራታችሁን አቁማችሁ አብራችሁን ስሩ፣በመጥረጊያ አናትሽን ብልሽ የሚደርስልሽ አይኖርም››የሚሉ ማስፈራሪያዎችን እንዳደረሱባቸው በመግለጽ ዋስትና ይሰጠን ሲሉ አቤት ብለዋል፡፡
ፖሊሶቹ በተከሳሾች የቀረበው ሐሰት መሆኑን በመግለጽ ‹‹ሴቶቹ ለምሳሌ ወደዚህ ለመምጣት የቆዮት የለበሱትን ቲሸርት እንዲለውጡ ሲነገራቸው እምቢ በማለታቸው ነው፡፡ በመኪና ላይ ይጨፍሩ ነበር፡፡እስር ቤት ውስጥም ሌሎች እስረኞችን ያነሳሳሉ ››ብለዋል፡፡
ቲሸርቱ በፍርድ ቤት እንዳይለበስ ያልታገደ በመሆኑ መልበስ መብታቸው ነው ያሉት አቶ አለሙ ‹‹ደምበኞቼን ፖሊስ በፈለገው ጊዜ ሊያገኛቸው የሚችል በመሆኑ በእስር መቆየታቸው ተገቢ አይደለም››ብለዋል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጡት ዳኛው ‹‹ፖሊስ የእስረኞቹን መብት ማክበር ግዴታው ነው ስለዚህ የተባለው ነገር እንዳይደገም በማለት የዋስትና መብታቸውን ሳይጠብቁ ለፖሊስ ተጨማሪ አራት ቀን በመፍቀድ ተጠርጣሪዎቹ ወደ ፖሊስ ጣብያ እንዲመለሱ አዘዋል፡፡