እብሪተኛ የመንግስት ታጣቂዎች ለሚቀጥፉት የሰው ህይወት መንግስት ተጠያቂ የሚሆነው መቼ ነው?
ከዳዊት ሰለሞን
የመንግስት ታጣቂዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ደማቸው በትንሽ በትልቁ እየፈላ ሲቪል ዜጎችን የሚጨርሱበት አጋጣሚ ከቀን ቀን እየጨመረ ነው፡፡
የባህር ዳሩን ዘግናኝ እልቂት ለጥቆ ቂርቆስ ቤ/ክ አካባቢ ሁለት ሰዎችን በጥይት በመምታት የወሲብ ደምበኛው እንደነበረች የተነገረላትን ሴት ሲገድል አብሯት የነበረውን ማቁሰሉ አይዘነጋም፡፡የታክሲ ሹፌሩ አልጭንህም ስላለው የታጠቀውን ሽጉጥ በመምዘዝ ለፍቶ አዳሪውን በአጭር አስቀርቶታል፣አራት ኪሎ ቤተ መንግስት አቅራቢያ በሚሄድ መኪና የተርከፈከፈ ጥይት ስንቱን እንዳስቀረ እግዜር ይወቀው ፡፡በየአካባቢው እንዲህ አይነት ዘግናኝ ዜናዎችን መስማት አዲስ አይደለም፡፡
ከትናንት በስቲያ በላፍቶ ክፍለ ከተማ አቦ ማዞሪያ አካባቢ በምስሉ የምትመለከቷቸውን የሶስት ልጆች ወላጆች እብሪተኛው ታጣቂ በጥይት በመደብደብ ገድሏቸዋል፡፡ ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡እሰየው ነው ፡፡ግን በቃ?እነዚያን ሶስት ህጻናት ማን ነው የሚያሳድጋቸው?ግለሰቡን አምኖ ክላሽ ያስታጠቀው አካል የማይጠየቀውስ እስከመቼ ነው?
መንግስት የመኪና አሽከርካሪዎች የሶስተኛ ወገን ኢንሹራንስ እንዲገቡ እያስገደደ መሆኑ በመኪኖቹ አደጋ ለሚደርስበት ሰው አንዳች ነገር ነውና ይበረታታል፡፡መንግስት በነካ እጁ የሚያስታጥቃቸው ሰዎች ለሚያደርሱት የመብት ጥሰት ኢንሹራንስ ይግባ!!!በእኔ እምነት ስለ ተገደሉት ወላጆችና ወላጅ አልባ ስለሆኑት ልጆች መጮህ የሁላችንም ግዴታ ነው።