ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ(አንድነት) የተሰጠ መግለጫ
የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መስሪያ ቤት እ.ኤ.አ በ2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ተፈፀሙ ያላቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሪፖርት ተመልክተነዋል፡፡ በሪፖርቱ የተካተቱት የመብት ጥሰቶች አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ በተደጋጋሚ ያጋለጣቸው እና ከፍተኛ ትግል እያደረግንባቸው የሚገኙ አስከፊ ተግባራት እንደሆኑ ቢታወቅም የቆምንለት ዓላማ እና እየታገልነው ያለው ስርዓት በሌሎች ዘንድም ድርጊቱ የታወቀ መሆኑን ያረጋገጥንበት ነው፡፡ የዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ በሪፖርቱ ያካተታቸው እንደተጠበቁ፣ የተፈጸሙ እና እየተፈጸሙ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከዚያም የላቁ እንደሆኑ አንድነት በተጨባጭ ያውቃል፡፡
የኢህአዴግ መንግሥት ዜጎችን በማፈን፣ ሚዲያዎችን በመዝጋት፤ ለህግ የበላይነት ቁብ በማጣት፤ ድብቅ በሆኑ እስር ቤቶች ዜጎችን በማጎር፤ በጥርጣሬ ያዝኳቸው የሚላቸውን ዜጎች በራሳቸው ላይ እንዲመሰክሩ በማስገደድ፤ በማሰቃየት፤ በማስፈራራት፤ በመግደልና አስገድዶ ከሀገር በማሰደድ የተመሰከረለት ነው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከገዥው የኢህአዴግ መንግሥት የተለየ አመለካከት ያላቸውና ስርዓቱን የሚተቹ ዜጎች የመከራ ገፈት የሚጋቱባት ሀገር እንደሆነች መቀጠሏም ከዜጎቿም ሆነ ከዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ የተሰወረ አይደለም፡፡
ቀደም ሲል በግፍ ታስረው ከሚገኙት የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አንዷለም አራጌ እና ናትናኤል መኮንንን ከመሳሰሉ ብርቱ ሰላማዊ ታጋዬቻችን በኋላ እንኳን በቅርቡ የፓርቲያችን የቀድሞ ዋና ፀሐፊና የአሁኑ የብሔራዊ ም/ቤት አባል የሆኑት አቶ አስራት ጣሴ ሃሳባቸውን በመጽሔት ጽፈዋል ተብለው ለእስር መዳረጋቸው የስርዓቱ አፋኝነት መቋጫ ያጣ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ሌላኛው አባላችን አቶ አለማየሁ ለፌቦ ከፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ማግስት ጀምሮ ወደ ደቡብ ክልል ሲመለሱ የፓርቲ አባል በመሆናቸው ብቻ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለ27 ቀናት መታሰራቸው፤ በኦሮሚያ በደቡብ እና በሰሜናዊት ኢትዮጵያ በተለየ ሁኔታ አባሎቻችን በአመለካከታቸው ብቻ ከስራ እየተፈናቀሉ መሆኑ፤ ጋዜጠኞች እና የሙስሊሙ ማህበረሰብ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ዛሬም በእስር ላይ መሆናቸው፤ ከዚህ በተጨማሪ ሙስና፤ የመሬት ቅርምት፤ የዜጎች መፈናቀል እና ህገ ውጥ አሰራር በበኩሉ ከስርዓቱ ጋር የተገነባ መሆኑ ሀቅ ነው፡፡
በሪፖርቱ የተዘረዘሩትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መድገም ባያስፈልግም በዚህች ሀገር የተንሰራፋው ህገ ወጥነት ይቀየር ዘንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ የሲቪክ ተቋማት፤ ድፕሎማቲክ ማህበረሰቡ እና የሚመለከተቸው አካላት ህጋዊ በሆነ ሁኔታ በመንግሥት ላይ ጫና እንዲያሳድሩ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ይህ ሁሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ባለበት ‹‹ጤነኛ እንደሆነ መንግሥት ›› ራሱን ለመቁጠር እንደሚያስቸግረው እንረዳለን፡፡ በመሆኑም የፖለቲካ ምህዳሩን ለሁሉም እኩል በማድረግ፤ የፀረ ሽብር፤ የፕሬስ፤ የበጎ አድራጎት እና ማህበራት ማደራጃ፤ ህጎችን በመቀየር፤ የሊዝ አዋጁን እና በተሻሻለው የወንጀለኛ መቅጫ የተካተተውን የፕሬስ ነጻነት የሚገፋ አንቀጽ በመሰረዝ፤ ከዴሞክራሲና የፍትሕ ተቋማት ላይ እጁን በማንሳት ከሚመጣበት የህዝብ ቁጣም ሆነ የታሪክ ተወቃሽነት ቢያመልጥ መልካም ነው እንላለን፡፡ አንድነት፣ በሀገራችን ያሉትን የፖለቲክ ችግሮች በዉይይት ለመፍታት በኢሕአዴግ እና በተቃዋሚዎች መካከል ሁሉም አሸናፊ የሆኑበትና ቅንነት ያለበት ውይይት እንዲደረግ፣ ፍላጎት እንዳለው በተደጋጋሚ በገለጸው መሰረት፣ ኢሕአዴግ ወደ መሃል ሜዳ መጥቶ ለዉይይት እንዲዘጋጅም እንጠይቃለን።
በሪፖርቱ የተዘረዘሩ እና ሌሎችም የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በሚመለከት ግን በተለይ የተወካዮች ምክር ቤት፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮምሽንና የእንባ ጠባቂ ተቋማት ከፓርቲ ወገንተኝነት በፀዳ መልኩ መርምረውና አጣርተው የመብት ጥሰት የፈጸሙትን የመንግስት አካላት ለፍትህ ማቅረብ ግዴታቸው መሆኑን አንድነት ፓርቲ ያሳውቃል፡፡
ከሁሉም በላይ ዋነኛ የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆናችሁ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ ያላችሁ መላው የሀገራችን ዜጎች ሰፊው ህዝብ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት እንጂ ከጥቂት አምባገነን መሪዎች መብት የሚለምን አለመሆኑን በመገንዘብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ስርዓቱን ለመታገል በአንድ ድምጽ ከጎናችን እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
የአሜሪካ መንግሥትም ቢሆን አንዲህ ዓይነቱን ከአሜሪካ ባህልና እሴት ጋር የሚቃረኑ ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተደጋጋሚ በየዓመቱ ሪፖርት ከማውጣት ባሻገር ትርጉም ያለው ጫና በማሳደር ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን ለዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብት መከበር ሊቆም ይገባል ብለን እናምናለን፡፡
ዘለዓለማዊ ክብር ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን!!!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
የካቲት 26 ቀን 2006 ዓ.ም
አዲስ አበባ