Coalition for Equitable Land Acquisitions and Development in Africa በምህጻረ ቃል CELADA በመባል የሚታወቀው በካናዳ ኦታዋ ውስጥ የተቋቋመ ድርጅት በአፍሪካ እየተኪያሄደ ያለውን የመሬት ቅርምት አስመልክቶ በርካታ የፓርላማ አባላት፣ የተራድኦ ድርጅት ሃላፊዎች የዩኒቨርሲቲ መምህራን በተገኙበት በአፍሪካ በኢንቨስትመንት ስም የሚደረገውን የመሬት ቅርምትና ካናዳ ልትይዘው የሚገባትን ፖሊሲ በተመለከተ በኦታዋ ፌብሩዋሪ 25 ቀን 2014 ዓም የተሳካ ስብሰባ አድርገዋል።
በሚሊየን የሚቆጠሩ በእርሻ የሚተዳደሩ ማህበረሰቦችን አግባብ በሌለው ሁኔታ የማፈናቀሉ ሥራ እጅጉን ተጧጡፎ ያለው በተለይ በአፍሪካ በመሆኑ CELADA የተሰኘው ድርጅት ይህ ጉዳይ አለም አቀፍ ትኩረት ያገኝ ዘንድ የበኩሉን ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። ይህ ድርጅት በተለያየ ተቋማት ውስጥ የሚያገለግሉ ካናዳውያን እንዲሁም ከበርካታ አፍሪካ ሀገራት የመጡና በአህጉሪቱ ውስጥ እየሆነ ያለው ነገር ይመለከተናል የሚሉ ትውልደ አፍሪካ ምሁራንን ጭምር ያካተተ ነው። በዚህ ድርጅት ውስጥ በርካታ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምሁራንም የሚሳተፉበት ሲሆን ከመስራች አባላት አንዱ ታዋቂው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑት አቶ ኦባንግ ሜቶ ናቸው።
የስብሰባው ዓላማ ድርጅቱን ከፓርላማ አባላትና በሀገሪቱ ውስጥ የፖለቲካ ተጽእኖ ማሳደር የሚችሉና አለም አቀፍ እውቅና ካላቸው ካናዳውያን ጋር ማስተዋወቅ ሲሆን። በዋነኛነትም ይህ ህገወጥ የመሬት ነጠቃና ቅርምት በሚደረግባቸው አገሮች ውስጥ የካናዳ ግብር ከፋይ ሕዝብ ገንዘብ ተጨማሪ የመጨቆኛ መሳርያ በመሆን ለአምባገነን መንግስታት እንዳይውል ለሚደረገው እንቅስቃሴ ድጋፍ ማሰባሰብያም ነበር።
ስብሰባውን በንግግር የከፈቱቱ የፓርላማ አባል የተከበሩ ሄለን ላቫንዴር ሲሆኑ ለስብሰባው ዝግጅትና ስኬትም ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ያደረጉ ናቸው። እርሳቸውም የጉዳዩን አሳሳቢነት አጽንኦት ሰጥተው ከተናገሩ በሁዋላ መድረኩን ለመስራችና የወቅቱ ሊቀመንበር ለሆኑት ለፕሮፌሰር ሮይ ኩልፔፐር አስተላልፈዋል። ሮይም የስብሰባውን ተካፋዮች አመስግነው በበኩላቸው ይህ ጅምር ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያስፈልጉባቸውን ጉዳዮች በመዘርዘር የድርጅቱ ማለትም የ CELADA ዓላማና ግብም በመላው አፍሪካ እየተከናወነ ባለው የመሬት ነጠቃና ቅርምት ዙርያ ያጠነጠነ መሆኑን አስረድተው ለእለቱ ተናጋሪዎች እድል ሰጥተዋል።
የመጀመርያው ተናጋሪ እውቁ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የተከበሩ ኦቶ ኦባንግ ሜቶ ሲሆኑ ከንግግራቸው ቀደም ሲልም ጥቂት ደቂቃዎች የሚፈጅ በሊቢያ አማካይነት በማሊ ውስጥ የተደረገው የመሬት ቅርምት የሚያደርሰውን አፍራሽ ተጽእኖ፣ የሕዝቡን ቁጣና ተቃውሞ የሚያመለክት ፊልም እንደ መግቢያ ካሳዩ በሁዋላ የችግሩን ጥልቀትና ውስብስብነት በማስረዳት ኢትዮጵያ ውስጥ እየተከናወነ ያለውንም ነገር በመጥቀስ ካናዳ ልትወስድ የሚገባትን አቋም፣ ሊኖራት የሚገባውን ፖሊሲ በማሳሰብ ንግግራቸውን አብቅተዋል። አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የያዘችው አቋምም የጉዳዩን አሳሳቢነት የሚያመለክት በመሆኑ ካናዳም የምትለግሰውን እርዳታ በዚሁ መነጽር ትመለከተው ዘንድ አሳስበዋል።
የማዳጋስካር ተወላጅዋ የ CELADA አባል የሆኑት ማጊ ራዛፊምህኒ ለበርካታ አመታት ለUNICEF ያገለገሉ ሲሆኑ በማዳጋስካር እየሆነ ያለውን የሀገሪቱ ፖሊሲ አገም ጠቀም የሆኑ እርምጃዎችን ቢወስድም አደጋው የከፋ መሆኑን በመግለጽ እርሳቸውም ተመሳሳይ ጥሪ ለካናዳ ሕዝብና መንግስት አቅርበዋል።
በመሬት ቅርምት ላይ ጠንካራ አቋም በመያዝ በተለያየ መስክ ስኬትን ያገኘው የኦክሰፋም ካናዳ ዳይሬክተር የሆኑት ሮበርት ፎክስ በበኩላቸውም የሁኔታውን አሳሳቢነትና አደገኛነት በመግለጽ መሬትም እንደማንኛውም ሸቀጥ ሊሸጥ ሊለወጥ ይችላል በሚል መርህ ሕዝቡን ማፈናቀልና ሀብት ማጋበስ በሚፈልጉ ሰዎች የገንዘብ ፈሰስና ለሀገራቸው ሕዝብ ደንታም በማይሰጣቸው ባለስልጣኖች ግፍ እየተፈጸመ መሆኑንና አብራርተው ምንም እንኳ ችግሩ ዛሬ የአፍሪካ ቢሆንም ነገ ግን ሁላችንንም የሚያስጨንቅ ጉዳይ መሆኑን መዘንጋት የለብንም ብለዋል። በመቀጠልም መሬትን እንደ ተቀማጭ ሀብት የሚያዩት ከበርቴዎች ትላልቅ የእርሻ መሬቶችን በልማት ስም በመግዛት አጥረው ካለምንም ልማት በመያዝ የመሬት ዋጋ የሚያሻቅብበትንና ከፍተኛ ትርፍ የሚያጋብሱበትን ጊዜ እየጠበቁ ነው በማለት በአፍሪካ ድሀ ገበሬዎች ላይ የሚሰራውን ግፍ ተናግረዋል። ለዚህም ምሳሌያቸው ሞዛምቢክ ነበር። ሞዛምቢክ ውስጥ ለውጭ ባለሃብቶች ከተሰጠው መሬት ውስጥ 70% የሚሆነው ታጥሮ የመሬት ዋጋ ውድ የሚሆንበትን ጊዜ የሚጠብቅ ሸቀጥ ሆኗል ብለው ነበር። በዚህም ምክንያት መልማት ያለበት መሬት በከበርቴዎች ተይዞ ሳለ ሚሊየኖች ግን በረሃብ ያልቃሉ የሚል አንድምታ ያለውን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። እንደ ደቡብ ሱዳን ያለ ገና የጸና መንግስትና ፖሊሲ የሌለበት ሃገር ውስጥ በሀገሪቱ ውስጥ መልማት ካለበት መሬት ውስጥ 10% በውጭ ኢንቨስተሮች ተይዟል።
ይህ እጅግ በጣም ሰፊ መሬት ነው። ኢትዮጵያን እንደምሳሌ በጠቀሱበት ንግግራቸውም የ140 የእግርኳስ ሜዳን የሚያህል ስፋት ያለው የአበባ እርሻ ልማት ውስጥ በርካታ ወጣት ሴቶች በቀን ሰራተኛነት ተቀጥረው በአለም ላይ ያሉ ኬሚካሎችን ሄርቢሳይድ፣ ፈንጂሳይ፣ ኢንሴክቲሳይድ፣ ባክቴሪሳይድ ወዘተ በቆዳቸው በሳንባቸው እየሳቡ ያለ እድሜአቸው የሚረግፉ እንዲሆኑ መገደዳቸውን በመግለጽ የመሬት ቅርምቱ በተለይም በሴቶች ላይ ያስከተለውን አደገኛ ተጽእኖ ለተሰብሳቢዎች ገልጸዋል። ተጋንኖ የሚነገረው የእርሻው ኢንቨስትመንት የስራ እድል ይፈጥራል፣ የምግብ ምርት ያሳድጋል ለማህበራዊ አገልግሎቶች አመቺ እድል ይሰጣል የሚባሉት መደለያዎች ፈጽሞ ከእውነት የራቁ መሆናቸውን ሲገልጹ በመሰረቱ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሰራተኛ ቁጥርን በመቀነሱ እንጂ በስራ እድል ፈጣሪነቱ አይታወቅም ብለዋል። ኢንቨስተሮችም የሀገሬውን ህዝብ የመቀለብም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚሸጥ ምግብ የማምረት ግዴታም የሌለባቸውና እንዲያውም የእርሻ መሬትን በአብዛኛው ለምግብ የሚሆን ሳይሆን ለስኳርና የነዳጅ ዘይት ለማምረቻ የሚጠቀሙበት መሆኑን ገልጸዋል። ኮካኮላ የስኳር ምርቱን በዚህ ጉዳይ ከሚጠቀሱ አምራቾች ባለመግዛት የጥፋቱ ተካፋይ ላለመሆን የወሰደው እርምጃ አበረታች መሆኑንም ለተሰብሳቢው ገልጸው የመሬት ቅርምቱ ለአጭርጊዜም ይሁን ለረጅም ጊዜ ሕዝባዊ ጠቀሜታ እንደሌለው አክለዋል። በመጨረሻም ካናዳም ሆነች የበለጸጉ ሀገሮች በዚህ ጉዳይ ላይ የሚወስዱት አቋም ወቅታዊም አስፈላጊም መሆኑን አበክረው ተናግረዋል።
ሌላው ተናጋሪ ብሩስ ሙር ሲሆኑ የ Canadian Hunger Foundation (CHF) ዳይሬክተር የነበሩና በተለያዩ አንጋፋ ድርጅቶች ውስጥ በቦርድ አባልነት በዳይሬክተርነት ያገለገሉና በአሁኑ ወቅት የ ‘North South Institute’ የቦርድ ሰብሳቢ፣ የ Forum of Democratic Global Governance (FIM) የቦርድ አባል እንዲሁም የ ‘Transparency International’ አባል ናቸው። ብሩስ ሙር በአስከፊው የኢትዮጵያ ድርቅ ወቅት ለውጪ ሰዎች መጓጓዝ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ እስከ ኮረም ድረስ ዘልቀው የችግሩን ስፋትና ክብደት ከተመለከቱ በሁዋላ ለካናዳ መንግስትና ለዐለምም የችግሩን መጠን ያሳወቁ በዚህም ሳቢያ ከፍተኛ እርዳታ ለኢትዮጵያ እንዲደርስ አስተዋጽኦ ያደረጉት ሲሆኑ በዚሁ የመሬት ቅርምትና የለጋሽ አገሮች ሚና በተለይም ካናዳ ሊኖራት ስለሚገባው ፖሊሲ አጠር ያለ ግን ጥልቅና ጠበቅ ያለ አስተያየት ሰንዝረዋል። እንደ እርሳቸው አባባልም የከተማዎች የከፋ ድህነት የገጠሩ ጉዳይ ችላ መባሉን አመልካች ነው በማለት ተናግረዋል። በማከልም ከ 2000 -2010 ዓ ም በሰነድ የሚታወቅ የመሬት ይዞታ ዝውውር 200 ሚሊየን ሄክታር ሲሆን ከዚህ ውስጥ 134 ሚሊየኑ በአፍሪካ ውስጥ ነው። ይህም ጉዳዩ ለ አፍሪካ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ያመለክታል። የምግብ እጥረት ከተከሰተ በሗላ ሳውድአረብያ ከ ኢትዮጵያ ብዙ መሬት ገዝታ ነበር በጣም የሚገርመው በ2009 ዓም ሳውዲ የመጀመርያ ምርቷን ከኢትዮጵያ በወሰደችበትና ሕዝብዋን በመገበችበት ወቅት ወርል ፉድ ፕሮግራም አምስት ሚሊየን የ ኢትዮጵያ ረሃብተኞችን መግቦ ነበር። ይህ የሚናገረው ትልቅ እውነት አለ፣ ይህ የሚያመለክተው ትልቅ ክፍተት አለ በማለት የተሰማቸውን ገልጸዋል።
ሌሎች ተሰብሳቢዎችም አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን ይህ ጥልቅና ውስብስብ ጉዳይ ለፓርላማ አባላት ቀርቦ ካናዳ ልትወስድ ስለሚገባት አቋም በቂ ግንዛቤ ማስጨበጡ እንደ አማራጭ ቀርቧል። በተለይም የግብር ከፋዮች ገንዘብ ለሕዝብ መፈናቀል ተጨማሪ መሳርያ እንዳይሆን ካናዳውያን ኢንቨስተሮችም ይህንን በመረዳት እንደዚህ ያሉ አገሮች ውስጥ የሚደረግ ኢንቨስትመንት የሚያስከትለውን ተጽዕኖና የሚያመጣውንም አደጋ ልብ እንዲሉ እንዲደረግ ሁሉም የድርሻውን እንዲያደርግ በየአቅጣጫው መረባረብ አስፈላጊነቱን ጠቅሰዋል።
በመዝጊያ ንግግራቸው ላይ የ CELADA ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ሮይ በዚህ የመሬት ቅርምት ዙርያ በዚህ ጉባዔ ላይ የተገኛችሁ በጉዳዩም ላይ በቂ እውቀት ያላችሁ ጠበብቶች አላችሁና የኤክስፐርት ምስክርነታችሁን ለፓርላማ አባላት በማቅረብ ይህንን ውስብስብ የሆነ ነገር በማስረዳት እንደምትተባሩ አምናለሁ። በየአቅጣጫው በያዝነው ስራ እንበርታ ለዚህ አንገብጋቢ ችግር መፍትሄ ለማስገኘት የየበኩላችንን እናድርግ በማለት ተሰብሳቢዎቹንና ለዚህ ስብሰባ ስኬት አስተዋጽኦ ያደረጉትን ሁሉ አመስግነው የእለቱ መርሃግብር በዚሁ ተጠናቋል።