የካድሬው ወንጀል በማይጨው ሆስፒታል
====================
ብርሃኑ ሃይለስላሴ ይባላል። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ እያለ ጥናቱን ትቶ በካድሬነት ተግባር የተሰማራ እንደነበር አውቃለሁ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የምንማር የትግራይ ልጆችን እየሰለለ ነበር የሚውለው።
ተመረቀና በህወሓት አባልነቱ መሰረት የትምህርት ዉጤቱ ግምት ዉስጥ ሳይገባ፣ ሳይወዳደር (ሌሎች ብቁ ሰዎች እያሉ) በእምባ አለጀ ወረዳ የጤና ጥበቃ ሐላፊ ተደርጎ በፓርቲ በመሾሙ ዓዲሽሁ ከተማ ገባ። በዓዲሽሁ ከተማ ብዙ ሴቶችን ደፈረ። ህዝብ ጮሆ። ሰሚ የለም። ምክንያቱም ሐላፊ ነው።
ሴቶችን በመድፈር ወንጀል ከመክሰስ ይልቅ ሌሎች ሰራተኞች ያላገኙት የማስተርስ ትምህርት ዕድል ተሰጠው። ሴቶች ስለደፈረ ተሸለመ ማለት ነው። በጦላይ ለስልጠና ተልኮ እዛም ሌላ ሴት ደፈረ። የተደፈረች ሴት የሕግ ከለላ አጥታ ከሱ ጋር እንድትታረቅና ክስ ላትመሰርት ተገደደች።
ከስልጠና በኋላ ህወሓቶች የማይጨው ለምለም ካርል ሆስፒታል CEO አድርገው ሾሙት። እነሱ ምን ይሳናቸዋል!? በማይጨው ከአንድ ዓመት ባልበለጠ ግዜ ዉስጥ አስራ አራት ሴቶችን ደፈረ፤ ስልጣኑን ተገን በማድረግ። ሴቶች አቤት ይላሉ። ግን ሰሚ የለም። በማይጨው ሰው በመኪና ገጨ። ራሱ ሰው ገጭቶ ሽፌሩ እንደገጨ ለማስመሰልና ከቅጣት ለመዳን ከሽፌሩ ጋር ተዋዋለ። ክስ ተመስርቶበት፣ በፖሊስ ተይዞ በስድስት ሺ ብር ዋስ ተለቀቀ።
ይህን ሁሉ ግፍ ሲፈፅም የማይጨው ኗሪዎችና የሆስፒታሉ ሰራተኞች ቅሬታ አሰሙ። ረበሹ። ተሰበሰቡ። የሆስፒታሉ ሰራተኞች ተሰብሰበው ከፓርቲ አባልነቱ እንዲወገድ ጠየቁ (ምክንያቱም የገዢው ፓርቲ አባል በመሆኑ ስልጣኑ ተገን አድርጎ ነው ግፍ እየፈፀመ ያለው ከሚል እሳቤ)። ከስራ (ከሐላፊነቱ) ታግዶ በፖሊስ እንዲያዝ ወሰኑ። ቢሮው ታሽጎ ሁለቴ ቁልፍ ሰብሮ መግባቱ ተረጋገጠ። ማንም አልጠየቀውም።
አቶ ብርሃኑ ሃይለስላሴ በሰራተኞቹ ስብሰባ ቀርቦ ሁሉም የተጠቀሱት ወንጀሎች መፈፀሙ አምኖ ይቅርታ ጠየቀ። በተበዳዮቹና ሰራተኞቹ ግፊት በፖሊስ እንዲታሰር ተደረገ። ህዝቡ ተረጋጋ። እኛም “ኮርማው ታሰረ!” ብለን በፌስቡክ ፃፍን። ህወሓቶች ለምን አስራ ስምንት ሴት እስኪደፍር ድረስ ዝም አሉት? ሕግ ለካድሬዎችስ አይሰራም ወይ? ብለን ጠየቅን። የህወሓቶች አድሎአዊ አሰራር ወቀስን። መታሰሩ ግን ጥሩ መሆኑ ጠቆምን።
አቶ ብርሃኑ በፖሊስ ከታሰረ ከሁለት ቀናት በኋላ መለቀቁ ሰማሁ። መለቀቁን አስመልክቼ በፌስቡክ ፃፍኩ። መለቀቁ ግን በሌላ አካል አልተረጋገጠም ነበር።
አሁን ከአስራ ስምንት ሴቶች በላይ የደፈረ ባለስልጣን ምን ቢቀጣ ጥሩ ነው!? አሁን በደረሰኝ መረጃ መሰረት አቶ ብርሃኑ አልታሰረም። ወደ ሌላ የስራ ቦታ ተዛወረ እንጂ። ህወሓቶች አንድ ባለስልጣን ወንጀል ከሰራ ባለስልጣኑ ከመቅጣት ይልቅ ወደ ሌላ የስራ ሐላፊነት ይቀይሩታል። ቅጣት ግን የለም። ሽልማት እንጂ።
አሁን አቶ ብርሃኑ ከዞን (ከማይጨው) ወደ ክልል (መቐለ) የስልጣን እርከን አድጎ በመቐለ የትግራይ ክልል የጤና ቢሮ የHMIS ዲፓርትመንት expert ሁኖ በሙሉ ደሞዝና የተሻለ የሐላፊነት ደረጃ እየሰራ ይገኛል። ይህን ጉዳይ የማይጨው ለምለም ካርል ሆስፒታል ሐላፊዎች አረጋግጠውታል። ለምን የሚል ጥያቄም አስነስተዋል። አሁን በማይጨው ሆስፒታል ሰራተኞች ጥሩ ስሜት የለም።
አሁን እንደሰማነው ግን ከእሰር የተፈታው በህወሓቶች ነው። በክልል ጤና ቢሮ እንዲሰራ ትእዛዝ ያስተላለፈውም አቶ ሃይሉ አስፈሃ የተባለ የደቡባዊ ዞን ዋና አስተዳድሪና የማይጨው ለምለም ካርል ሆስፒታል የቦርድ ሰብሳቢ ነው። የሆስፒታሉ ሰራተኞች ይሁኑ የቦርዱ አባላት ሳይሰበሰቡና ምንም መረጃ ሳይኖራቸው አቶ ሃይሉ አስፈሃ (የቦርዱ ሰብሳቢ) ግን የቦርዱ ዉሳኔ እንደሆነ አድርጎ ደብዳቤ በመፃፍ በክልል ጤና ቢሮ እንዲቀጠር ማድረጉ ለማረጋገጥ ተችሏል።
ባሁኑ ሰዓት በማይጨው ከተማ ኗሪዎችና ለምለም ካርል ሆስፒታል ሰራተኞች በከባድ ቀውስ ዉስጥ እንደሚገኙ ለማወቅ ችያለሁ። የማይጨው ህዝብ በዋና አስተዳዳሪው አቶ ሃይሉ አስፈሃ ከፍተኛ ቅሬታ እያነሳ ሲሆን ህወሓቶች ለህዝብ ያላቸው ንቀት እያሳዩን ነው በሚል የተቃውሞ መንፈስ እንዳለ ከማይጨው ኗሪዎች የደረሰኝ መረጃ ያመለክታል።
አይ ህወሓቶች መቼ ነው ለህዝብ ደህንነት የምትቆሙ? በትግራይ የሚፈፀሙ አስተዳደራዊ በደሎች ቢጋለጡኮ ስንት ጉድ በሰማን ነበር! ይህን ጉዳይ እስከመቼ እንችለዋለን?!
በህወሓት እምነት የለኝም። ከዚህ በላይ ምን ሊያደርገን ይችላል!? እናንተስ?
It is so!!!