ከሠሎሞን ታምሩ ዓየለ
ክፍል 1
ከአጻጻፍ ስልት የአብረሃም ደስታ አጻጻፍ ልቤን ይሰርቀዋል:; የቃላት አመራረጡ፤የአረፈተ ነገሮቹ አጭር መሆን፤ የቃላት ፍሰቱ አንዳንዴም የአማርኛው ከትግርኛ አነጋገርና አነባብ ጋር ሲደመር ፈገግ ያደርጋል:: ለምሳሌ መቶን ሞቶ ብሎ ሲጥፋት:፡ አብረሃም የሕዝብ ልጅ ነው። ሲጥፍም ሕዝባዊ ነው። የአብረሃም ቃላቶች የሁለዜ ቌንቌ ናቸው። የአብረሃምን መጣጥፍ ሳነብ ትዝ የሚለኝ የአንደኛ ደረጃ የአማርኛ ቌን ቌ መማሪያ መጽሃፍቶቼ “አረንጓዴው ጉዋደኛዬ”ና “ተንኮለኛው ከበደ” ናቸው:: በተጨማሪም የ4ተኛ ክፍል የኅብረት ትምህርት” አገራችን “መጽሀፍ ትዝ ይለኛል:: ሁሉም ቢያነባቸው ደህና አድርጎ ይረዳቸዋል:: ተማሪ ሆኚ የጻፍኴቸው ድርሰቶች ትዝ አይሉኝም:: ነገር ግን ከማኅበራዊ ሕይወቴ ሁናቲ ወላጅ አባቴና ታላቀ ወንድሜ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ የሃዘን እንጉርጉሮ በግጥም ጽፌአለሁ:: በተጨማሪም የግብርና ሳይንስ ባለሙያ በመሆኔ የአገሬን አርሶ አደር የሰብል ምርት በመስክና በጎተራ ለጥፋትና ብክነት የሚያደርጉትን ተባዮች ለመከላከልና ለመቆጣጠር ምርት አድን የሆኑ የቴክኒክ የመስክ ረፖርቶች ለቅርብ አለቆቼ ጽፌአለሁ:: በተቻለኝ መጠን እንደ አብረሃ መጣጥፌ ግልጥ እንዲሆን እሞክራለሁ::የምጽፈውም የ20ዎቹን የመጀመሪያ ዕደሜዬንና በሁዋላም የ30ዎቹን ዕደሜዬን ያሳለፍኩበትን የአገሬን አርሶ አደር ማሳዎቹን ሳስስ ያየሁትን፤ ያስተዋልኩትን መሰረት በማድረግና በተጨማሪም በትምህርት ጊዜ ያገኘሁትን ዕውቀትም በመጨመር ነው:: ፍርዱን ለአንባቢዎች ትቻለሁ:: መጣጥፉ ለሁላችንም የኢትዮጵያ ልጆች ነው። ብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች የሚል ቃል አልወጣኝም :: የመልዕክቴ መዳረሻም የአገራችን ትልቅ ችግር ግን ተገቢውንና ትክክለኛ መልስ ያልተሰጠውን በምግብ ሰብልና እንስሳት ሃብታችን ተጠቃሚ ያልሆንበትንና የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ በያዝነው የቀንድ አውጣ ያህል ጉዞ የትም እንደማያደርሰን ሁላችንም አውቀን በአንድ ድምጽ መሪዎቻችንን መዘውሩን እንዲያስተካክሉ ለማስረዳት የመጀመሪያ ሙከራ ነው።
ብሔራዊ ውርደት የሚለውን ቃል አስከምን ድረስ እንደሆነ ምርምርና ጥናት አላደረኩም:: በመሆኑም ይዘቱን፤ስፋቱን፤ግዝፈቱን፤ጥልቀቱን ይሄን ያህል ነው ብዬ ለመናገር ይከብደኛል:: የብሔራዊ ውርደት ነገርም ከየት ተነስቶ የት አንደሚደርስም አላውቅም። ነገር ግን በቅርቡ በአረመኔው የሳውዲ መንግስትና ጋጠ ወጥ የኅብረተሰቡ ክፍሎ ች በሰደተኞቹ የኢትዮጵያ ልጆች ላይ ያደረሱትን በደል ብሔራዊ ውርደት ነው ብለን በመቃወም ጩኀታችን ለዓረቡና ለዓለም ኅ/ሰብ አሰምተናል:: እኛ ብሔራዊ ውርደት ያልነውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩን ቴዎድሮስን አንድ ቀን ብቻ እንቅልፍ ሲነሳቸው ጠ/ሚኒስቴሩ ደግሞ ጉዳዩን አሳንሰው ሰብዓዊ ቀውስ ብለውታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ በዓለም መገናኛ ብዙሃን ቁጥሩ ከ 3 ሚሊዮን በላይ የሚገመት የአገረችን ሕዝብ ለከፋና ሥር ለሰደደ የምግብ ችግርና እጦት መጋለጡ ተገለጠ:: የሚገርመውና የሚደንቅው በመንግስት የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ላለፉት 7ና 8ንት ተከታታይ ዓመት 8በመቶ ዕድገት አሳየ ተብሎ ከተለፈለፈ በኈላ መሆኑ ነው:: በተጩማሪም በ 5ቱ ዓመት የትራንስፎርሜስን እቅድም (በሚከጥለው ዓመት ይጠናቀቃል) መሰረት ይህንኑ ክፍለ ኢኮኖሜ በእጥፍ ለማሳደግም ታሣቢ ተደርጎ ነበር። ይቺ ናት ጨዋታ አለ ጥላሁን ገሰሰ ዘፈኑም ነገሰ። ቁጥር ስልጣኔና የሁነቶችን ደረጃን ማሳያና መለኪያ መሆንዋ ቀርቶ በአገራችን የማይጨበጥ የርዕዮተ ዓለም ብቻ መገለጫ መሆንዋ እጅግ ያሳዝናል። መደመርና መቶኛን በመፈለግ ብቻ ግዜያችንን ከምናጠፋ የቁጥሩ ትርጉም ካልገባን የሂሳብ ባለሞያዎችን እርዳታ መሣት አያስነውርም። ለማንኛውም ለማስታገሻ እንዲሆንም ታሥቦ ይመስላል ክ388635 ሜትሪክ ቶን በላይ የምግብ እህል፤ ጥራጥሬ፤ የቅባት እህልና ዓልሚ ምግቦች እንደሚያስፈልጋት ተገምቶላታል። ለመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቈጥር ክ95 ሚሊዮን በላይ እንደሚገመትና ከዓለምም የ13ተኛ ደረጃን መያዛችንን ተረድተናልን? ከፍሊፒንስ በታች ክቭየትናም በላይ። በ1960ዎቹ እኢአ አጋማሽ ጥቈት ፈሪ የ6ተኛን ክፍል ብሔራዊ የኅብረት ትምህርትን ፈተና ለማለፍ ስናጠና ያን ጊዚ የኛ የሕዝብ ቁጥር ግምቱ 26 ሚሊዮን ነበር:: ታዲያ እያረጋገጥን ያልነው በርግጥ የምግብ ዋስትናን ነው ወይስ የምግብ ኢዋስትናን? የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ማለት በሺህ እና በአስር ሲዎች የሚቆጠሩትን የገዢ ፓርቲ አባላትንና አገልጋዮቹን ከርስ መሙላት ማለት አይደለም። አነርሱማ በወፍራም ደሞዛቸውና በሙስና በሚያገኙት ገንዘብ አቅማቸውን አፈርጥመው የምግብ ፍላጎታቸውን ያሙዋላሉ። በርግጥ የምንከተለው ፖሊሲና ስትራቴጂ ይሄ ቁጥሩ እጅግ እየተንደረደረ የሚመጣውን ሕዝብ የምግብ ፍላጎትና አቅርቦት ለሟሟላት የሚያስችልና በቈ ዝግጅት የተደረገበት ነውን? በፖለቲካ መሪዎች ፍላጎትና መሪ ቃል ብቻ የተዘጋጀ አሰራርና እሩጫ ችግሩን ከማባባስና ከማፋጠን ውጪ የትም አያደርስም። ለመሆኑ የሕዝብ ቁጥር አወቃቀሩ ማለትም በጾታ፤በዕድሜ፤በስራ ዓይነት፤በሚኖርበት ስፍራ፤በትምህርት ደረጃ፤በሚከተሉት ሃይማኖትና በሌሎች መለኪያዎችም ጭምር የሚገለጡት ትርጉም አገሪቷን በሚያስተዳድሩት አካላቶች ተገቢውን መረዳት አግኝቶ ይሆን?
በምግብ ሰብል ምርት ራሷን ችላ ለዜጎቹ ብቁ፤ደህንነቱና ጥራቱን የተጠበቀ ምግብ የምታቀርብ አገር ምንኛ የታደለች፤የተከበረች፤የታፈረችና የኮራች ለመሆና ከራሳችን ሌላ ምስክር አያስፈልገንም:: በተቃራኒው ዜጎቿን ከሌሎች አገሮች በምታገኘው እርዳታና እርጥባን ጠብቃ የምታስተዳድር አገር ደግሞ ለዜጎቿ ሁሌም ማፈሪያና የብሔራዊ ውርደትና የቅሌት መለኪያ ሚዛን እንደምትሆን አሌ የማይባል ሀቅ ነው:: የምግብ ፍላጎቱና አቅርቦቱ የተሟላለት ሕዝብ ጤነኛ፣ አካሉና አእምሮው የዳበረና የበለጠገ ስለሚሆን ሁልጊዜ ምርታማ ነው:: የተራበና ጠኔ ያንገላታው ሕዝብ ደግሞ ሁልጊዜ በሽተኛ ስለሚሆን ለመንግስትም ቢሆን ከፍተኛ የጤና ጥበቃ በጀት እንዲመድብ ይገደዳል:: በመሆኑም ባሁን ሰዓት ለመከላከያና ለደህንነት ተብሎ የተመደበውን ከፍተኛ በጀት ገዢውን መደብ ለመጠበቅ ቀውስ ውስጥ ይገባበታል።
አንደ ፈረንጆቹ አባባል “የራበው ሰው ቁጡ ሰው ነው” ይባላል:: የተራበ ሕዝብ የበዛበት አገርም ሰላም የራቀው ነው። አገሩም ደህንነቱ አስተማምኝ አይሆ ንም:; አንዴ ከተነቃነቀ መመለስው ቀላልም አይደለም። ለመፈራረስም ያለው እድል ከፍተኛ ነው። ፕሮፊሰር መራራ አንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር። “ የራበው ሕዝብ መረዎቹን ይበላል”። ነገርግን መሪዎቹን በአንድ ሆነ በሌላ ምክንያት ካልበላ በመጨረሳም በርግጠኝነትና በሥነ ሕይወታዊ መንገድ ካየነው የራበው ሰው የሚበላው መልሶ ራሱን ነው። ራስን መብላት ምንኛ አሰቃቂና አስቀያሚ እንደሆነ በኅብረ መቅርጽ (ቴለቪዥን) መስኮት የተራቡ ኅጻናት፤እናቶች፤ስማግሌዎች፤አረጋዊያንና ወጣቶች የተመለከትንና በአካልም በአጋጣሚ በአይናችን ያየን ፍርዱን ለናንተው።
የምግብ ዋስትና ለአንድ አገር ዕድገትና ልማት ዋነኛ መሳሪያው ነው:: ይህንንም በማረጋገጥ ለሎች የኢኮኖሚ ዘርፎችን መነቃቃትንና መነሳሳትን ይፈጥራል። ለመሆኑ የምግብ ዋስትና ማለት ምንድነው? ይህንን ቃል ፖለቲከኞች፤የመንግስት ሱሞች፤የአርሳና የጤና አንዲሁም የምግብ ሳይንስ ጠበብቶች፤ጋዜጠኞችና ለሎችም የኅ/ ሰብ ክፍሎች ይጠቀሙበታል።ምን ያህል ቃሉን በአግባቡ ተጠቅመውበታል? የታወቀ ነገር የለም:: አንደ ተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሳ ድርጅት ትርጉም ከሆነ የሚከተለውን ፍቺ ይሰጣል። ሁሉም ሰዎች በማንኛቸውም ጊዜ አካላዊና ምጣኔ ሃብታዊ ተደራስነት ኖሮአቸው ለኑሮአቸው በቂና ደህንነቱ የተረጋገጠ ለሰውነታቸው ዕድገትና ጥንካሬ አስፈላጊ የሆኑ ዓልሚ ምግቦችን እንደ ፍላጎታቸውና ምርጫቸው ተሟልቶላቸው የተነቃቃና ጤናማ ሕይወት ሲመሩ ነው።(ትርጉሙ እኔው እንደተረዳሁት ነው)
የምግብ ዋስትና ዋና ምሰሶዎች ተብለው የሚታወቁት የሚከተሉት ናቸው። እነሱም በአጭሩ። 1ኛ፡ የምግብ ምርት አቅርቦት፤ሥርጭትና ልውውጥ (ትንተናውን በሌላ መጣጥፍ) 2ኛ፡ ለምግብ ሸቀጦች ያለው ተደራሽነት ከመግዛት አቅም አንጻር 3ኛ፡የምግብ አጠቃቀም፤የምግብ በአግባቡ መዘጋጀትን፤የምግብ በሰውነታችን ውስጥ መላምን፤የምግቡን ጤንነትና ደህንነትን ማረጋገጥን ይጨምራል።4ኛ፡በተከታይና ካለማቋረጥ ተመጣጣኝ ምግብን በተፈለገ ጊዜ ማግኘትን ይይዛል።
አንድ ነገር ለማከል የምፈልገው ደግሞ የምርት መጨመርም ሆነ የምርት ግብዓት (ምርጥ ዘር፤ የመሬት ማዳበሪያ፤ ጸረ ተባይና ሌሎች) ማሰራጨት ብቻውን ዋነኛ የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ አድርጎ ማቅረብም ስህተት ላይ ይጥላል። ምርት መጨመሩ ድርሻ የለውም ማለት ሳይሆን ሰዎች ሁሉ የተመረተውን ምርት አቅም ኖሮአቸው ገዝተው ከምግብ ጠረጴዛቸው ላይ እስካላገኙት ድረስና የምግብ ፍላጎታቸውን እስካላሟላ ድረስ ስለ ምግብ ዋስትና አፍን ሞልቶ መናገር አይቻልም። ሕዝቡ የምግብ እህሎችንና ሌሎችም የምግብ ሸቀጦችን ገዝቶ የመጠቀም አቅሙ ከፍ ማለት አለበት። ስለ ምግብ ዋስትና ስናወራ በገጠር ብቻ የሚገኘውን የሕዝብ ክፍል ብቻ ሳይሆን በከተማ ሸምቶ የሚኖረውን ሕዝብ ይጨምራል። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ዋነኛ ኢኮኖሚያቸው በግብርና ላይ ስለተመሰረተ ይኽው ክፍለ ኢኮኖሚ ለዋስትናቸው ወሳኝ ነው። ለዚህም ነው ግብርና የጀርባ አጥንት፤ የማዕዘን ድንጋይ፤ምሰሶና መሰረት ነው እየተባለ የሚነገረው። ለማስታወስም ለግብርና ኢኮኖሚ ምንም ዓይነት የረባና ምቹ የሆነ የተፈጥሮ ሃብት ሳይኖራቸው የምግብ ዋስትናቸውን ያረጋገጡ አገሮችም እንዳሉ መገንዘብ አለብን። ለምን ቢሉ ምግብና የምግብ ውጤቶችን ገዝተው የመጠቀም አቅማቸው ከፍተኛ በመሆኑ ነው።
የተለያዩ መለኪያዎችና ሚዛኖችም ተሰርተውለታል፦ የምግብ ዋስትና! (ዝርዝር ውስጥ አሁን አልገባም) ነገር ግን በቅርቡ አንድ አገርኛ መስፈሪያ ወይም ሚዛን የተገኘ ይመስላል። ይኀውም ቀመር “ቁምራ”፦ ቁርስ፤ ምሳና እራት በአንድ ጊዜ ባንድ ላይ። ጨዋታና ቀልድ ትመስላለች በውስጧ እውነትነት ያላትና የቀመሯ ባለቤት ኢትዮጵያዊ የሆነች። የትኛው ተመራማሪ እንደ ግኝት አረጋግጦ ያስመዝግባት ይሆን? አንዳንድ የሰለጠኑት አገሮችማ የምግብ ዋስትናን በቤተሰብ ደረጃ መጠይቅ በመላክ ጥናትና ክትትል በየጊዜው ያደርጋሉ። የኟዋ አገር ይሄንን ትስራ አትስራ አስረጂ የለኝም።
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የምግብ ዋስትና የሚረጋገጠው በጋዜጣዊ መግለጫ፤ ቁጥር በመደርደርና በቃለ መጠይቅ ወቅት ወለፈንዲ መልስ በመስጠት ሳይሆንና በመሪዎች መልካም ምኞትም አይደለም ( የጠ/ሚኒስተር መለስን የአንድ ወቅት ቃለ መጠይቅና ምኞት አንባቢያን አስታውሱልኝ) ተፈጥሮ የሰጠችንን ሃብትና ጸጋ በተገቢው መንገድ በመረዳትና በዕውቀትና በሕዝብ ፍላጎት ላይ ብቻ በተመሰረተ የግብርና ፖሊሲና ይህንንም መሰረት ያደረጉ ሕጎች፤ አዋጆች፤ ደንቦች፤ መመሪያዎች፤ ትዕዛዞች፤አሰራሮች፤ አደረጃጀቶች፤አፈጻጸሞች፤የክትትል ስልቶችና ሌሎችም ግልጥ የመልካም አስተዳደር መገለጫዎችን ስናዘጋጅ ብቻ ይሆናል። ከሕዝብ ፍላጎት ውጭ የሆነ ፖሊሲማ በደርግ ጊዜ ታይቶ ተፈትኖ ማለፍ አቃተው (ማልባ፤ወልባ፤ወላንድንያስታውሷል)። የደርጉ ጊዜ ለአምራቾች ኅብረት ሥራ ማህበራት ልዩ ትኩረትና አድልዎ የሚል መመሪያ ክዶክተር ገረመው ደበሌ ነበረን (ነፍስ ይማር ብያለሁ)። ታዲያ ዛሬም ለምን እንደግመዋለን። እነሆ በአንድ ዓይነት ዜማና ቅኝት ለ40 ዓመት ተጓዝን። አልተሳካልንም። አካሄዱን እንቀይር። ከበሮ መቺው አመታቱን ሲቀይር ዳንኪራ መቺዎቹም ዳንሱን እኮ እንደሚቀይሩ ከመድረክ ላይ ብዙ ያየን መሰለኝ።
የባላገሩ አይዶል አዘጋጆች እባካችሁ አንድ “የምግብ ዋስትና ዜማና ቅኝት “ውድድር አዘጋጁና ተወዳዳሪዎቹም ከገዥው ፓርቲ፤ከፓርላማ ሰዎች፤ከግብርና ሚንስቴር፤ከእርሻ ምርምርና ኮሌጆች፤ከአደጋ መከላከልና ዝግጁነት፤ከመንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ሌሎችንም ጨምራችሁ በውጤቱም “አልተሳካም” በሉ። ካልተሳካ ደግሞ ጨዋታውን አካሄድ መቀየር ለተወዳዳሪዎቹ የሚበጅ ይመስለኛል።
ለዛሬው ላብቃ በክፍል ሁለት ጠብቁኝ እመለሳለሁ። ቸር እንሰንብት!!!
አሜን!!!!