ብአዴን እና አመራሮቹን በመቃወም እሁድ የካቲት 16 በባህር ዳር ከተማ በአንድነትና በመኢአድ ለተጠራውን የተቃውሞ ሰልፍ የአንድነት ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴና የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት ለመቀስቀስ ዛሬ ወደ ባህር ዳር ማቅናታቸውን የአንድነት የዜና ምንጮች ለዘ-ሐበሻ በላኩት መረጃ ላይ አስታውቀዋል። እንደ አንድነት የዜና ምንጮች ገለጻ እሁድ ለሚደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ቅስቀሳው በሰፊው የቀጠለ ሲሆን በኢሕአዴግ በኩል የሚፈጸምባቸው ትንኮሳም በዛው ልክ በሰፊው ቀጥሏል ብለዋል።
“በረዳት አንስፔክተር ክንፈ ሀይሌ ጉልላት የሚመራ የፖሊስ ሀይል በተለምዶ ከአባይ ማዶ በሚባለው አካባቢ የመኪና ላይ ቅስቀሳ እናዳይደረግ ማይክራፎን መበስበር ጭምር ሙከራ ማድረጉን” የገለጹት የአንድነት የዜና ምንጮች የከተማዋ ነዋሪዎች ግን የፖሊሶቹንና የትራፊኮቹን ህገወጥ ድርጊት በማስቆም ተባብረዋል ብለዋል። አካባቢው “ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም” በሚለው ዜማ መድመቁን የገለጹት እነዚሁ የዜና ዘጋቢዎች ፖሊሶቹ ከህጉ ይልቅ ለአለቆቻቸው ታማኝነታቸውን እያረጋገጡ መሆናቸው ትዝብት ውስጥ ጥሏቸዋል ብለዋል። ህዝቡ የመኢአድ እና የአንድነት ደጋፊ የሆኑት ቀስቃሾቹ ሊነኩ አይገባም በማለት ተቃውሞውን ሲያሰማ ረዳት ኢንስፔክተሩ ተጨማሪ ሀይል እንዲመደብላቸው ትዕዛዝ ቢያስተላልፉም በህዝቡ ጫና የቅስቀሳ ቡድኑ ስራውን ቀጥሏል፤ ይህም የሚያኮራ ተግባር ነው ተብሏል።
ዘገባዎቹ እንደጠቆሙት በባህር ዳር የአንድነትና የመኢአድ አባላት ጫማ በማውለቅ በብአዴን ላይ ተቃውሟቸውን በመግለፅ ቅስቀሳቸውን የቀጠሉ ሲሆን፤ ይሄም በቅርቡ አቶ አለምነው መኮንን የአማራውን ሕዝብ ለመሳደብ የተጠቀሙበትን ቃል ለማስታወስና ምላሽ ለመስጠት እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ። በዛሬው እለት 14/06/2006 ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ የአንድነትና የመኢአድ አባላት በሞንታርቦ በመቀስቀስ ላይ ሲሆኑ በራሪ ወረቀት የሚያድሉ አባላት በፍፁም ቁርጠኝነት የብአዴኑ ባለስልጣን የተናገሩትን በመቃወም በባዶ እግራቸው በከተማዋ በመዘዋወር ለህዝቡ ግንዛቤ እየፈጠሩና በራሪ ወረቀቶችን እያደሉ ሲሆን የከተማው ነዋሪ በቁጭት አጋርነቱን እየገለፀ ይገኛል፡፡
በባህርዳር አቶ አለምነው መኮንን አማራውን ከተሳደቡ ወዲህ ብአዴን ከፍተኛ የሆነ ደጋፊ እንዳጣ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።