(updated) የፊታችን እሁድ በባህርዳር መኢአድ እና አንድነት በጋራ የፊታችን እሁድ የካቲት 16 ቀን 2006 ዓ.ም በጠሩት የተቃውሞ ሰልፍ ሕዝብ ወጥቶ ድምጹን እንዲያሰማ ለመቀስቀስ ዛሬ በባህር ዳር አደባባዮች መኪና እና በትልቅ የድምጽ ማጉያ ሲቀሰቅሱ የዋሉ የድርጅቱ አባላት በፖሊስ ወከባ ሲደርስባቸው፤ ሲታሰሩ መዋላቸውን የድርጅቶቹ ቃል አቀባዮች ለዘ-ሐበሻ በላኩት መረጃ አመልክተዋል።
“ብአዴን አማራውን የመምራት ብቃት የለውም” በሚል መፍክር እያሰሙ ሲቀሰቅሱ የዋሉ የሁለቱ የተቃዋሚ ድርጅቶች አባላት በፖሊስ ታግተው ቅስቀሳውን እንዳያደርጉ ቢስተጓጎልም፤ በፖስተር፣ በበራሪ ወረቀት፣ በስልክ ቴክስት፣ በፌስቡክ፣ በትዊተርና በኢሜሎች በሚደረጉ የተቃውሞ ሰልፍ ቅስቀሳዎችን የባህርዳር ሕዝብ በንቃት እየተከታተለ እንደሚገኝ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላማዊ ትግል አማራጫችን ነው፤ አንድም ጥይት ሳይተኮስ ኢሕአዴግን ለማውረድ እንታገላለን የሚሉት አንድነት እና መኢአድ እሁድ በባህርዳር የጠሩት የሰላማዊ ሰልፍ አገዛዙን እጅግ እንዳስነገጠው ከሚወስዳቸው እርምጃዎች መረዳት ይቻላል ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።
በተጨማሪም፡
ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ በባህርዳሩ ሰልፍ ቀስቃሾችና በእሁዱ ሰልፍ ዙሪያ የሚከተለውን ዘግቧል።
የፊታችን እሁድ አንድነትና መኢአድ ለሚያደርጉት ሰላማዊ ሰልፍ የቅስቀሳ ስራ በመስራት ላይ የነበሩት ወጣቶች በፖሊስ ተወስደው ከክልሉ አስተዳደር የተጻፈ ወረቀት እንደቅድመ ሁኔታ ተቀብለው እንዲወጡ ተነግሯቸዋል፡፡ወጣቶቹ ግን ቅድመ ሁኔታውን አንቀበልም በማለት በህጋዊ መንገድ በአሁኑ ሰዓት በመከራከር ላይ ይገኛሉ፡፡
ቅድመ ሁኔታው ‹‹ባስገባችሁት የሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ደብዳቤ ቅስቀሳ የምናደርገው በባህርዳርና አካባቢዋ ለሚገኝ ህዝብ ነው ብላችኋል፡፡በደፈናው ባህር ዳር አላችሁ እንጂ የየትኛው ቀበሌ፣ወረዳና ሰፈር ህዝብን እንደምትቀሰቅሱ አልጠቀሳችሁም ከዚህ ባሻገር የአቅራቢያው ህዝብ የትኛው እንደሆነ አላብራራችሁም ስለዚህ ቀበሌዎቹን፣ወረዳዎቹን፣ሰፈሮቹንና አካባቢውን በመዘርዘር በድጋሚ ደብዳቤ እንድታስገቡ ››የሚል ነው፡፡
ተጨማሪ መረጃ እንደደረሰን እንመለሳለን።
ለባህርዳሩ ሰልፍ አንድነት እና መኢአድ በዩቲዩብ የለቀቁት ማስታወቂያም የሚከተለው መልክ አለው።