Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የአውሮፕላኑ ጉዳይ፡ የረዳት አብራሪው ውሳኔ በውጭ ሚዲያዎች ዓይን

$
0
0

ethio airlines
በፀጋው መላኩ

በበረራ ቁጥር ET702 የተመዘገበውና ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው ቦይንግ 767 አውሮፕላን በረዳት አብራሪው ተጠልፎ የጉዞ መስመሩን በመቀየር ጄኔቭ ኤርፖርት ካረፈ በኋላ በጉዳዩ ዙሪያ በርካታ ዘገባዎች እየተሰራጩ ይገኛሉ። በዚህ ዙሪያ በየድረገፆቻቸው ሰፋ ያለ ዘገባዎችን ካሰራጩት ታዋቂ መገናኛ ብዙኀን መካከል አልጀዚራ፣ ቢቢሲ፣ ሲ ኤን ኤን፣ ፎክስ ኒውስ፣ ዘጋርዲያን፣ ሲ ቢ ኤስ፣ ዋሽንግተን ፖስትና አሶሼትድ ፕሬስ ይገኙበታል። የብዙዎቹ መገናኛ ብዙኀን ሽፋን በእለቱ ድርጊት ዙሪያ ትኩረት ያደረገ ሲሆን፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ከዚያ ባለፈ መልኩ “ረዳት አብራሪው ለምን ድርጊቱን ፈፀመ” ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ሞክረዋል።

በዚህ ዙሪያ ዴቪድ ብለየር በተባለ ፀሐፊው “ረዳት ፓይለቱ ለምን ይሄንን ድርጊት ፈፀመ” ለሚለው ምላሽን ለመስጠት ሞክሯል። ዴቪድ ብለየር በዴይሊ ቴሌግራፍ የአፍሪካ እንዲሁም የመካከለኛው ምስራቅ ዘጋቢ ሆኖ አገልግሏል። ከዚያ በኋላ ቴሌግራፍን በመተው በተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን በተንታኝነት ያገለገለ ሲሆን እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ ወደ ቴሌግራፍ ተመልሶ የተለያዩ ዘገባዎች ከማቅረብ ባለፈ ልዩ ልዩ ሙያዊ ትንታኔዎችን በመስጠት ላይ ይገኛል።

ዴቪድ ብለየር በኢትዮጵያ አየር መንገድ የተካሄደውን ጠለፋ አስመልክቶ “ጠለፋው ለምን ተከናወ” በሚለው ጉዳይ ላይ የራሱን ትንታኔ ለመስጠት ሞክሯል። እንደ ባለሙያው ገለፃ የፓይለቱ የጠለፋና የጥገኝነት ጥያቄ በኢትዮጵያ የተስፋፋው የዜጎች ሀገር ጥሎ መሰደድ አንድ ማሳያ ነው። ባለሙያው በዜጎች ሀገር ጥሎ መሄድ ሁለት ምክንያቶችን ያስቀመጠ ሲሆን፤ እነዚህንም ጭቆና እና ድህነት በማለት አስቀምጧቸዋል። “ሀገሪቱ የአንድ ፓርቲ ሀገርና በጥቂት ሰዎች የምትመራ ናት” ያለው ይሄው ተንታኝ ዜጎች ከሚደርስባቸው ጭቆና በተጨማሪ የነፍስ ወከፍ ገቢያቸውም በዓለም ድሀ ከተባሉት ሀገራት ውስጥ የሚመደብ በመሆኑ ዜጎች ሀገር ጥለው የሚሄዱ መሆኑን ገልጿል።

ባለሙያው በዚህ ትንታኔው የአለም ባንክን መረጃ ዋቢ በማድረግ በሰጠው ትንታኔ 620 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ከሀገራቸው ውጪ የሚኖሩ መሆኑን ገልፆ ከእነዚህም ውስጥ 10 በመቶው የሚሆኑት የዩኒቨርስቲ ዲግሪ የያዙ መሆናቸውን አመልክቷል። ፀሀፊው ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከገበያ ባላንጣዎቹ የገልፍ ሀገራት በኩል እየገጠመው ያለውን የባለሙያ ማስኮብለልንም በምክንያትነት ያነሳል። ከሶስት ዓመታት በፊት 60 የአየር መንገዱ ቴክኒሻኖች በገልፍ ሀገራት አየር መንገዶች በተሻለ ክፍያ ስራ ያገኛሉ። ይህንንም ተከትሎ ባለሙያዎቹ አየር መንገዱን ለቀው ለመሄድ ስማቸውን ለኢሜግሬሽንና የዜጎች ጉዳይ ቢያስተላልፉም ሀገር ጥለው መሄድ እንደማይችሉ ተገልፆላቸው የሥራ እድሉን መከለከላቸውን በመግለፅ ይህንንም መሰል ችግር ለጠለፋው በምክንያትነት ያስቀምጣል። ምንም እንኳን የሚያስከፍለው ዋጋ ከባድ ቢሆንም ይህ ረዳት ፓይለት ከሀገሪቱ ወጥቶ ሊሰራ የሚችልበት ህጋዊ አካሄድ ስለሌለ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ይህን እርምጃ እንዲወስድ ሊገፋፋው እንደሚችል በመግለፅ ፀሐፊው ሙያዊ አስተያየቱን በዴይሌ ቴሌግራፍ ላይ አስነብቧል።

በዚሁ ዙሪያ በትላንትናው እለት ማብራሪያ የሰጡት የኩሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሬድዋን ሁሴን፤ ፓይለቱ የትም ሀገር ሄዶ መቀጠር የሚችልና የቪዛ ችግር የሌለበት ነው በማለት ድርጊቱን ኮንነዋል። ፎክስ ኒውስ በበኩሉ ኢትዮጵያ መንግስት የሂውማን ራይትስ ዎችን ሰብዓዊ መብት ረገጣ ሪፖርትን በማጣቀስ በሀገሪቱ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ፣ የመሰብሰብና በማህበር መደራጀት አለመቻልን በመግለፅና ጉዳዩን ከዚህ ጋር አያይዞ ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ አባላትም የጥቃት ኢላማ በማድረጉ መንግስት በተደጋጋሚ ክስ የሚሰማበት መሆኑንም ዘገባው አመልክቷል።
ከዚህ ውጪ ያሉት ዘገባዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተለያዩ ጊዜያት በተደጋጋሚ የጠለፋ አደጋዎች እየገጠሙት መሆኑን ገልጸዋል። እ.ኤ.አ በ2002 በሀገር ውስጥ የአየር መንገዱ በረራ ሁለት ጠላፊዎችን ቢላዋ፣ ተቀጣጣይ ፈንጂ በመያዝ አውሮፕላኑን ለመጥለፍ ሙከራ ቢያደርጉም በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን የአሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ ያመለክታል። ዘገባው ከዚህም በተጨማሪ እ.ኤ.አ. በ1996 ተጠልፎ በኮሞሮስ ደሴት በህንድ ወቅያኖስ የተከሰከሰውን አውሮፕላን ታሪክም ያስታውሳል።

የረዳት ፓይለቱን ቀጣይ እጣፈንታ በተመለከተ በርከት ያሉት ዘገባዎች ጉዳዩ ወደ ክስ የሚያመራ መሆኑን በመግለጽ ጥገኝነት በመሰጠቱ በኩልም ቢሆን ከበርካታ የአውሮፓ ሀገራት በበለጠ ሁኔታ የሲውዘርላንድ ህግ ጥብቅ መሆኑን ያትታሉ። የኢትዮጵያ መንግስት ድርጊቱን የፈፀመው ግለሰብ ተላልፎ እንዲሰጠው የሚፈልግ መሆኑን በአቶ ሬድዋን በኩል ተገልጿል። እንደ ፎክስ ኒውስ ዘገባ ከሆነ በጣሊያንም ሆነ በሲዊዘርላንድ ሕግ መሰረት አንድ ግለሰብ በሌላ ሀገር በሞት የሚያስቀጣው ወንጀል ከፈፀመ ለዚያ ሀገር ተላልፎ አይሰጥም።

ይህ ጽሁፍ ዛሬ በአዲስ አበባ ታትሚ በተሰራጨው ሰንደቅ ጋዜጣ ላይ ወጥቶ ነበር።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>