ከዚህ በታች ላቀረብኩት ፅሑፍ የመረጥኩት ርዕስ ዶ/ር መረራ ጉዲና “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትግል ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ እስከ ኢህአዴግ” (2006 2ተኛ ዕትም) በሚል ርዕስ ያቀረበውን መፅሐፍ ከዳር እስከዳር በማሰስ ላይ የተመሰረተ አይደለም። ይህ ርዕስ የሚመለከተው ደራሲው በመፅሐፉ ገፆች በመደዳውና አልፎ አልፎም እየተመለሰ ስሜን በማንሳት የዛሬ ሰላሳ አምስት ዓመት ገደማ በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ይመራ የነበረው መንግሥት በጅባትና ሜጫ አውራጃ ጥቁር እንጭኒ በሚባል አካባቢ በመላው ኢትዮጵያ ሶሺያሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) አባላት ላይ ከፈፀመው አረመኔያዊ ግድያ ጋር ከማነካካት ያለፈ የ”ክህደት” (የመረራን ቃል ለመጠቀም) ወንጀል ፈፅመሃል በሚል እጅግ ምሬትና ብሶት ባልተለየው አንደበት በመረጃ ያልተደገፈና ሊደገፍም የማይችል በርካታ ክሶች በመቃወም መልስ ለመስጠት ነው። ስለዚህም በዚህ ግለሰብ የቀረበውን በጎ ትውስታዎችም ሆነ የሕይወት ምስቅልቅሎቹን በሰፊው ለመገምገምና አስተያዬት ለመስጠት አልተነሳሁም። ከኔ ይልቅ ይህ መዘክር ምን ያህል ብስለትና ተመክሮን የተላበሰና በአንደበቱም ሆነ ባቀራረቡ አንባቢን ለመማረክ የቻለ ሥራ ለመሆኑ ለመናገር ብቃቱ ያላቸው ይመለሱበታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ባለፉት 30 እና 40 ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ በየትኛውም ርዕዮተ ዓለማዊና ድርጅታዊ አካባቢ ለነበሩ፣ላለፏና አሁንም በመሰላቸውና ባመኑበት ተሳትፎ ላላቸው ሁሉ ከበሬታን ያዋደደ ሙገሳም ሆነ ነቀፌታ በማቅረብ ምን ያህል እንደተዋጣለት የሚፅፉና የሚያወያዩ ወገኖች ብቅ ብቅ ማለታቸውን ያየሁ በመሆኑ እኔን በሚመለከተው ጉዳይ ላይ ብቻ በማተኮር ምላሽ አቀርባለሁ።
ከሁሉ አስቀድሞ የዛሬ ሰላሳ አምስት ዓመታት ገደማ በጅባትና ሜጫ፣ በጫንጮ፣ በሲዳሞም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች በድርጅቱ አባላት ላይ የደረሰውን እልቂትና ጭፍጨፋ ሳናነሳውና “እከሌ መረጃ ሰጥቶ ነው እከሌ ደግሞ ተዝረክርኮና ተባብሮ ወይም ጠቁሞና ክህደት ፈጽሞ ነው” በሚል የርስ በርስ መካሰስ ውስጥ ሳንገባና ወደዚያ እጅግ መሪርና አሳዛኝ ታሪክ ሳንመለስ አፈር እንደለበሰ መካነ መቃብር ሳንነካካው እንዳለና እንደተከበረ ብንተወው የተሻለ ነበር እስከማለት እደፍራለሁ። ምን እንደተከሰተና ምን በመሳሰሉ በርካታ ምክንያቶች ያንን የመሰለ እልቂት ሊደርስ እንደቻለ ለመናገር ድፍረቱ እንኳ ቢኖረን የዚያኑ ያህል ደግሞ በተለይ በጊዜው የግለሰቦችን ሚና በሚመለከት በትክክልና እርግጠኛ ሆነን ልንናገርባቸው የማንችልባቸው በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን በመገንዘብና ቋሚ ምስክር ሊሆኑ የሚችሉትም ሰዎች ከሞት ተነስተው ሊመሰክሩ እንደማይችሉ በማወቅ ይህንን ታሪክ በተመለክተ ጥንቃቄና ሃላፊነት የተሞላው አቀራረብ መምረጥ በተገባ ነበር። ከሁሉም በላይ የምንቀሰቅሰው የኛን ስሜት ብቻ አለመሆኑን በማሰብና ሌሎችንም ብዙ ሰዎች መልሰን ወደዚህ ጉዳይ ውስጥ በማስገባት እንደገና ደግመን ልናሳዝናቸው እንደምንችል በማስተዋል ያንን አስከፊ ታሪክ በዚህ መልክ ባንነካካ የተሻለ ነበር። ወደዚህ ዘመን እንመለስ ያልንም እንደሆነ ዓላማችን ርስ በርስ የመካሰስን ባህል ከሰላሳና አርባ ዓመታትም በኋላ መልሶ ነፍስ እንዳይዘራ ተጠንቅቀንና በአሳማኝ መረጃ ተደግፈን ከሁሉም በላይ ላለውና ለመጭው ትውልድ ምን ሊያስተምር እንደሚችል አስበን ይመስለኛል። በታሪካዊው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በ ’ረዳት ፕሮፌሰር’ ደረጃ የሚታወቅ ምሁር ይህንን የመሰለ ከበሬታ ያለው ማዕረግ ላይ የደረሰው መረጃዎችን በሚገባ በማጥናትና በርካታ አመሳካሪ ሊሆኑ የሚችሉ ተጨማሪ መረጃዎችን በማከል ወደ እውነት የቀረበ ሥራ ለማቅረብ ያለውን ችሎታ አስመስከሮ እንጂ ባቋራጭ ሊሆን እንደማይችል የታወቀ ነው። ራሱ የተሳተፈበትም ታሪክ ቢሆን ስሜቱን ዋጥ በማድረግ፤ ትዝታውን በጥናት አጠናክሮ ለመጨረሻው አንባቢ (audience) ለማቅረብ ሲወስን ላለውና ለመጭው ትውልድ ምን ሊያስተምር እንደሚችል የሚመዘንበትና ምርምር ለሚጠይቀው ኤትካል መርህ ላሳየው ተገዥነት የሚመሰከርለት እንጂ የሚመሰከርበት እንዳይሆን ተጠንቅቆ ይመስለኛል። እኔ በተማርኩበትና ለ13 ዓመታት ባስተማርኩበት አገር ባለ ዩኒቨርስቲ በተራ ማህበራዊ ጉዳይ ላይ እንኳን የግለሰብን ስምና ታሪክ ያለበቂ መረጃ ያዋረዱ የዩኒቨርስቲ መምሀራንና ፕሮፌሰር ድረሰ የደርሱ ሰዎች ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው ከሳሽ ሳይቀርብባቸው ዩኒቨርስቲው ራሱ በራሱ የኤቲክ ኮሚቴ እንዲከሰሱ በማድረግ ዲስፕሊነሪ ቅጣት ብቻ ሳይሆን መምሀራኑን ከሚወክለው የሙያ ማህበር ለተውሰኑ ዓመታት እንዲታገዱ ያደረገበት ሁኔታ እንዳለ መረራ እንዲያውቀው እፈልጋለሁ። በዚህ መለኪያ የሄድኩ እንደሆነ መረራ ጉዲና ከመንደር ትምህርት ቤት መምህር ያነሰ ሰው ሆኖ አግኝቼዋለሁ። የታዩኝና ያሳዘኑኝ የሱ ተማሪዎች ናቸው። እኔም አልገፋሁበትም እንጂ ለነገሩ ያህል የፖላቲካል ሳይንስ ተማሪ ነበርኩ። መረራ ምን እንደተማረና እንዳነበበ ተማሪዎቹንም ምን እንደሚያስተምር ግራ የሚያጋባ ሆኖብኛል። የዚህ ሰው አመለካከትና ግንዛቤ ከዛሬ ሰላሳና ዓርባ ዓመታት ንቅንቅ አለማለቱ ከመጽሐፉ የተሻለ አስረጅ አይገኝም።
በቅደሚያ መረራ ጉዲና የሚባል የመኢሶን ካድሬ በጅባትና ሜጫ አውራጃ አምቦ ከተማ መኖሩን እንጂ ምን ዕልቅና በድርጅቱ ውስጥ ይኑረው አይኑረው የማውቀው ነገር የለም። ይህንን ሰው ከዚያ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ አይቼው አላውቅም ። ስለዚህ ሰው ከርቀት የነበረኝ እውቀት ከሌሎቹ ወጣት የመኢሶን ካድሬዎች ታናሽ ወንደሜን ጨምሮ የተለየ አልነበረም። እሱ እንደሚለው ሳይሆን ለዚህ ሰው በስሙ መልዕክት ልኬበትም ለስብሰባ ጠርቼው አላውቅም። የድርጅቱ የግንኙነት መዋቅር በፈረሰና ባካባቢው የድርጅቱ ተጠሪ የነበሩትና እኛን ወደ ጅባትና ሜጫ የወጣነውን ከድርጅቱ አመራር አካል ጋር አገናኝ የነበሩትና ከመረራ ይልቅ ላመራሩ አባላት ቅርበት የነበራቸው አስፋው ሽፈራውና ሃምሳ ዓለቃ ማህተሙ በኩረ ነበሩ። አስፋው ከተያዘና ያምሳ አለቃ ማህተሙም ጉዳይ አጠራጣሪ ከመሆን አልፎ አቋሙን ቀይሮ ወደ አብዮታዊ ሰደድ ገብቷል የሚል ዜና ከመድረሱ በፊትም ሆነ ክደረሰም በኋላ እኔን ወደ ጥቁር እንጭኒ ከሄደው በዶ/ር ተረፈ ወ/ጻዲቅ ከሚመራው ቡድን ጋር ባንድ በኩልና አዲስ አበባ አካባቢ ህቡዕ ከነበረው ተተኪ የደርጅቱ አመራር አካል ጋር ታገናኝና መልዕክት ታደርስ ትመለስ የነበረችው መክሊት ግርማ የምትባል መረራ በመፅሐፉ ውስጥ ሰለጥንካሪዬዋና መስዋዕትነቷ የሚያወሳትሳት ወጣት ነበረች። እዚያው አሞግሶ እሟሟቷን በሚመለከት ከሁላችንም ቀድሞ ብሎ ከተያዘው አስፋው ሽፈራውና ሃምሳ ዓለቃ ማህተሙ ጋር በማነካካት በ”ይመስለኛል” ያቀረበውን ከእውነት የራቀ ጉዳይ ሌሎች ሰዎች እንዲመለሱበት በመተው ከድርጅቱ የተመደበችልኝም ተገናኝ እሷዋ ብቻ እንደነበርችና ለዚህ ሰው በስሙ መልዕክት ልኬበትም ለስብሰባ ጠርቼውም እንደማላውቅ ላሰምርበት እወዳለሁ። ስለዚህ ሰው የነበረኝ እውቀት ከሌሎቹ ወጣት የመኢሶን ካድሬዎች ታናሽ ወንደሜን ጨምሮ የተለየ አልነበረም። በዚህ መሃል የመኢሶን ድርጅታዊ መዋቅር ሲፍረከረክ መረራ ተወካይ ወይም ተጠሪ ሆኖ ተመድቦ ሊሆን ይችላል። ባነጋገሩም መሰረታዊ ነገሮች ላይ እየታከከ የሚያውቀውንና የሰማውን ከማያውቀውና ካልሰማው ጉዳይ ጋር በማገናኘት “ቀድመው ሊጎዱኝ” ይችላሉ ብሎ በጠረጠርን ሰዎች ላይ እብደትና ቅሌት ባቀላቀለ Paranoia መክሰሱ የራሱን የሕይወት ምስቅልቅልና እስከዛሬ ሊያገግምለት ያልቻለውን የሕሊና ሥቃይ በማተራመስ ያባብስበት እንደሆን እንጂ እውነትን አይናገርም።
በመጽሐፉ ገጽ 84 እኔና ታናሽ ወንድሜ እሱን “ሊጎዳ የሚችል ሪፖርት” ለመጻፍና እኔ ላዘጋጀሁለትም “የረቀቀ ወጥመድ አስፈጻሚ ነበር” በሚለው ወንድሜ ለመጠቀም እንደማልመለስ ያትታል። ለመሆኑ ይህንን ለማድረግ የምነሳበት ምክንያት ምንድነው? መረጃውስ ምንድን ነው? መረራን ሊጎዳ ወይም ሊያጠፋው የሚችል ሪፖርት በወንድሜ መረጃ ሰብሳቢነት ለመኢሶን የበላይ አካልም ሆነ ወደ ውጭ ጉዳዩ ለማይመለከተው ወገን ለመጻፍም ለማውራትም የሞክርኩበት ጊዜ የለም። የሰማሁት ነገር አልነበረም ለማለት ሳይሆን በእርግጠኛነት የማውቀው ጉዳይ ባለመኖሩና ከሁሉም በላይ ላለውም ሆነ ለመጭው ትውልድ የሚሰጠው ትምህርት እንደሌለ ስለማምን ነበር።
በዚሁ ገጽ መረራ ከአብዮታዊ ሰደድ አዲሱ ተወካይ በሚል ካነሳው ሰው ጋር መቻቻሉን ይናገራል። የሚታወቀው የአብዮታዊ ሰደድ ተወካይ ሆነው መኢሶንን ለመተካት በየክፍለ ሃገሩ፤ አውራጃና ወረዳ የተላኩ ካድሬዎች በመኢሶንነት የሚጠረጥሩትን ሁሉ ከማሳደድና ቢቻላቸው ከማጥፋት ካልተቻላቸው ደግሞ ከማሰር ያለተመለሱብት ጊዜ ነበር። ጥቁር እንጭኒ ለግድያ ከተሰማራው ቡድን ጋር አብሮ አንደነበር ሲነገር የሰማነውንና ያንን ያህል አመኔታ የተጣለበትና ከበደ ድሪባም የከርስትና አባቱ መሆኑን የነገረን ሰው ምን እንደገፋፋው ከሞት አስነስተን ልንጠይቀው የማንችለወን ሃምሳ ዓለቃ ማህተሙ በኩረንም በሚመለከት ስለዚህ ሰው የሰማው “እውነትም ይሁን ሃሰት … እኔ እንድሞት ቢንቀሳቀስ ኖሮ ከሞት የምተርፍ አይመስለኝም” ነበር “ የሚል ነው። እንዲያውም በመፅሐፉ ላይ ባንድም ሥፍራ ሃምሳ ዓለቃ ማህተሙን ከግድያው ጋር ሳያነካካ በተጠያቂነት ሳያመለክት አልፎታል። ከዛሬ 10 እና 15 ዓመታት ገደማ መረራ ጉዲናን ጅባትና ሜጫ ለደረሰው ዕልቂት ተጠያቂ በማድረግ ተነስተውበት የነበሩትንና ሃምሳ ዓለቃ ማህተሙ በኩረም “የእናቱ እህት” ነው በሚል ሲከሱት የነበሩትን ወደ ኦነግ የተጠጉ ወገኖችንም በዚህ “ታሪካዊ ትዝታው” አብክሮ ሳይወቅሳቸው ማለፉ አስገርሞኛል። ይህ መብቱ ነው። ምንም ቅሬታ የለኝም።
በዚሁ ገፅ 84 እና 85 እኔ ከዘረጋሁለት “የረቀቀ ወጥመድ ሕይውቱ የተረፈበትን አጋጣሚ” እና ብዙም ሳይቆይ ስለዘረጋሁት “የተንኮል ድር” ይህንኑ የዘረጋሁትን “የከህደት መስመር የሚያንቀሳቅሰለት ሲራክ ተግባሩ የተባለ ታናሽ ወንድም” እንደነበረኝ ያትታል። እኔ የሕዝብ ደርጀት ጽ/ቤት ተቀጣሪም ሆነ በመኢሶን ውስጥ ካድሬ የመሾም የመሻር ሥልጣን አልነበረኝም። ይህንንም በመረጃ ያልተደገፈ ክስ ከየት እንዳመጣው መልስ መስጠት ይኖርበታል።
በዚሁ ገጽ 85 ስለመቀደም ያወራል፡ የተቀደመውስ ምን ለማድረግ ነበር? መልሱን ፍለጋ ሩቅ መሄድ አያስፈልግም። በዚሁ ገጽ 85 መጨረሻ ገደማ “ከመግደል ውጭ አማራጭ አልነበረም” የሚለውን ስመለከት የተቀደመበትን ምክንያት ማሰላሰል አላስፈለገኝም። ይህም የሰው ሕይወት ከማጥፋት የማይመለስ ፍላጎት (INTENT) እንደነበረው ያጠናክራል።
በዚሁ ገፅ 84-85 ዝቅ ብሎም ስሜን በማንሳት “አማረ ብዙም ሳይቆይ የተንኮል ድሩን መዘርጋት ይጀምራል …” ይልና በመቀጠል “በእውነቱ ከኔ የተሻለ አማረን የሚያውቀው ኢዮብ ታደሰ መጠርጠሩ መረጃ ቢኖርኝም … “ (ስርዝ የተጨመረ ገፅ 85) በሚል ይቀጥላል።
እነኚህ ከላይ ስማቸውን የሚጠቅሳቸው ሰዎች አንዳቸውም በሕይወት የሉም። በስም እየጠራ እከሌ ይህንን ማለቱን፤እከሌ ደግሞ ያንን “ማለቱን አስታውሳለሁ” ይላል። እዚያው በዚያው ደግሞ “በቦታው ያልነበረ” እና “በሕይወት ለወሬ ነጋሪነት የተረፈው እሱ ብቻ መሆኑን በመጥቀስ “የቡድኑን ጭቅጭቅ በለማ ፊዳ በኩል ሲከታተል” እንደነበር ይናገራል። ለማ ፊዳን ከሞት አስነስቶ መጠየቅ አይቻልም። “በለማ ፊዳ በኩል ስከታተል ነበር” ብሎ ነገር እንዴት ሊሆን ይችላል? እውነትስ ቢሆን በስለላ ሥራ እንዲሰማራ ያዘዘው ማነው? በበኩሌ ይህ አዲስ ነገር ነው። በመኢሶን ታሪክ አንዱ ሌላውን የመሰለል ሥራ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም። በድርጅቱ አባላት መካከል የ “አግድሞሽ” (horizontal) ግንኙነት ተገቢ እንዳልነበር በመጽሐፉ ውስጥ የሚናገረው ይህ ሰው ለሱ ይህንን የአግድሞሽ ግንኙነት የፈቀደለት ማነው?
ወደ ገጽ 86 እና 87 ስንሄድ አቅጣጫ ለማሳስት ወንድሜን መሳሪያ በማድረግ አንድ በዚያን ጊዜ ስለቻይና አብዮትና ረጅም ጉዞ ከጻፍኩት ጋር አያይዞ እውነት ያልሆነ ነገር ያነሳል። እኔ የነበርኩት ወለንኮሚ ሲሆን እነዶ//ር ተረፈ ያረፉበትን የነመረራ ጉዲናን ዘመዶች ቤት ይቅርና ጥቁር እንጭኒን ደርሼበት አላውቅም። ሲራክም ከመረራ፤ ሃምሳ ዓለቃ ማህተሙና መክሊት በስተቀር እነዶ/ር ተረፈ በየትኛው ሥፍራና መረራ እንደሚለው በየትኛው የነ ”መረራ አጎት ቤት” ቤት እንዳረፉ እንደማያውቅ ለመረራ ጉዲና ከተቀባይ ደረሰኝ ጋር ከላከለትና ለማንም ባላሰራጨው የሚስጥር ደብዳቤ ይነበባል። የዚህ ደብድዳቤ ኮፒም በጄ ይገኛል።
ወደ ገጽ 88 እና 89 ደግሞ መናገሻ አካባቢ የኔ ወንድምና በሌላ በኩል መረራ “ወንድሜና ረዳቱ” በሚላቸው መካከል በሌላ በኩል ተፈጠረ የሚለውን የጥቆማ፤ የደብደባና የግድያ ታሪክ የምሰማውና የማነበው ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ነው። ይህንን የመሰለ ከባድ ጉዳይ ቀርቶ በየቦታው በመኢሶን ደጋፊና ተባባሪ በነበሩ ሰዎች ላይ ይደርሱ የነበሩትን ጉዳዮች ደርግ ጽ/ቤትም፤ ፖሊስ ጣቢያም ወህኒ ቤትም ሆነ ለእኛ አራተኛ ክፍለ ጦር ለነበርነውም በሆነ መንገድ ይደርስ ነበር። በመናገሻ አካባቢ በሌላ አጋጣሚ በእርግጠኛነት የደረሰ ነገር አልነበረም ለማለት አልችልም። መረጃ የለኝም።
የዛሬ 30 ዓመት እ.አ.እ 1983 በጅባትና ሜጫ የነበረውን ሁኔታ በተመለከተ ለድርጅቱ አመራር አካል አንድ እጅግ ዝርዝር ሰነድ አቅርቤ ነበር። በዚህ ሰነድ ታናሽ ወንደሜን ሲራክ ተግባሩን ለመገናኘት የወሰንኩበትን ምክንያት ያስረዳል። እሱም የኔን መልዕክት ይዞ ወደአዲስ አበባ ለመግባት ሲሞክር ገፈርሣን አለፍ ብሎ “ኢያሱ ጠበል” በመባል በሚታወቀው አካባቢ በተዘጋጀው Road Block ሲደረስ ቀድመው እዚያ ሲጠብቁት በነበሩት የደርግ ምርመራ አባላት መያዙን፤ በዚህም ጊዜ ብቻውን እንጂ ማንም እሱን ተከትሎ የሄደ፤ የተያዘ፤ የተደበብደበና እዚያው “እሱን ገድለናል” የተባለና እንደገና ደግሞ ሞትን አሸንፎ “ራሱን ስቶ” እንደነበረ መረራ የሚነግረንና “ወደአምቦ ተወስዶ የተገደለ” የሚለውን ወንድሙን የሚመለከት ታሪክ የማነበውም የምሰማውም በዚህ መጽሐፍ ነው። መረራ ወንድም ይኑረው አይኑረው የምውቀው ነገር የለም። የትም ቦታ ይሙት በመስዋዕትነቱ ሊከበር ይገባል። በተረፈ የወንድሙ ረዳት የሆነ የሆነ ሰው የነመረራን አጎት ቤት አውቆ መምራቱን ከሞት አስነስቶ መጠየቅ አይቻልም። ሲራክ እንደሚለውና ለመረራ በጻፈው ደብዳቤ ያረጋገጠው መረራ ጉዲና የኮማንዶው ቡድን ተባባሪ እንደነበርና አምቦ ከተማ ሲደርሱ ከተደባለቀው ሃምሳ ዓለቃ ማህተሙ ጋር ሆነው ያጎቱን ቤት መርቶ ማሳየቱን፤ ሲራክም እዚያው ግድያው የተፈጸመበት ሥፍራ እንደነበረ ይመሰክራል። ክርክር መግጠም የነበረበት ከኔ ወንድም ጋር ነበር።
ስለእኔ መኢሶንን መክዳት በማያውቀው ጉዳይ ከመዘባረቅ በስተቀር መረጃ አላቀረበም። እውነተኛው ታሪክ ግን እኔ ከእሰር ተፈትቼ ወደ ስዊድን አገር ከገባሁ በኋላ በውጭ ካለው የመኢሶን ድርጅቱ አመራር አካል ጋር በመደባልቅ የድርጅቱ የውጭ ልሣን በነበረችው “አዲሲቱ ኢትዮጵያ” ጋዜጣና የደርጅቱንም ታሪክ ለመፃፍ በተደረገው ሙከራ ተሳትፌአለሁ። በዚህ ሳልቆጠብ ደርግ ወድቆ ኢህአዴግ ሥልጣን እስከያዘበት ዘመን ድረስና ከዚያም በኋላ በድርጅት ከታቀፈ የፖለቲካ ተሳትፎ ራሴን እስካገለልኩበት ድረስ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሠርቼ ያፈራሁትንም ቅርስ ጭምር ለድርጅቱ ሥራ አበርክቻለሁ። ተጨባጭ መረጃዎቸን በሰፊው ማቅረብ ካስፈለገ የነበረንን ግንኙነት የሚመሰክሩ የጽሑፍ መረጃዎችን የማቅረብ ችግር የለብኝም። ለአብነት ያህል ወደ ስዊድን አገር በገባሁበት ዘመን የስደተኝነት ማመልከቻዬን በመደገፍ በድርጅቱ የተጻፈልኝልን ደብዳቤ እዚህ ላይ አባሪ አድርጌአልሁ።
መላ ኢትዮጵያ ሶሽያሊስት ንቅናቄ – መኢሶን
All Ethiopian Socialist Movement (ME’ISONE)
05/08/82
To: The Office of the UNHCR
Stockholm, Sweden
Dear Sir,
It has come to our knowledge that MR. AMARE TEGBARU, born in Addis Ababa, Ethiopia on the 10th of October 1952 has filed an application in order to obtain the status of Political Refugee in the Kingdom of Sweden.
MR. AMARE TEGBARU is a long time militant who has suffered persecution, imprisonment and torture both in the hands of the former regime of Emperor Haile Selassie and the present military government.
A member of the “University Students’ Union of Addis Ababa” from 1969 to 1972, Mr. Tegbaru served as the Secretary General of this militant organization for the year 1971/ 1972. During this period, he was condemned to serve a six months’ prison term and was severely tortured during his detention.
In 1972, Mr. Tegbaru left Ethiopia for France where he joined the local branch of the Ethiopian Students’ Union in Europe. During the 1974/ 1975 he served as the President of the Union and the next year became an advisor of its Executive Committee.
He became a member of ME’ISONE, The All Ethiopian Socialist Movement in 1976 and returned to Ethiopia to become the editor of the organization’s paper, “ADDIA FANA”. When the organization broke with the military regime in August 1977, Mr. Tegbaru was one of those ordered to go underground. A few months later, he was arrested by the government’s security forces and detained at the Headquarters of the 4th Army Division in Addis Ababa.
During his second stay in prison which lasted for over Four (4) years, Mr. Tegbaru was subject to inhuman torture and mistreatment which damaged his health seriously.
We believe that Mr. Tegbaru’s request for Political Asylum in Sweden is justified and hope that his application would be considered favorably by your office.
Yours Sincerely,
DR. NEGEDE GOBEZIE
For the Foreign Mission
ME’ISONE
የኔን መያዝ በተመለከተ በኢማሌድህ ዘመን ከማንም በላይ ውስጠ አዋቂና የማሌሪድ መሪ የነበረው ተስፋዬ መኮንን “ይድረስ ለባለታሪኩ” በሚል በጻፈው መጽሐፍ ታናሽ ወንድሜ “በዚያን ጊዜ 17 ዓመት ዕድሜ ያለው … ወጣቱ ልጅ በመሆኑ ያንዣበበውን አደጋ ሲያይ የወንድሙን መሞት ሊቀበል ይቸገራል። ቀደም ሲል ሀገሩ ሁላ እንደሰማው የእነዶ/ር ከበደን መሞት ሰምቶታል፡ የእነ ሃይሌ ፊዳም መያዝ አስደንግጦታል፡ ስለዚህም ወንድሙንና ራሱን ማዳን ፈለገ ማለት ነው” (ገፅ 255 -256)) በሚል የጻፈውና ሲራክ በቤተሰብ አካባቢ ከዚያም ከ20 ዓመታት በኋላ ባካል ስንገናኝ ከነገረኝና ለመረራ ጎዳና በሚስጥር ከላከለትና ለማንም ባላሰራጨው ደብዳቤ ከገለፀው ጋር አንድ ነው። መረራ ይህንን እውነት ሳያውቅ ቀርቶ ሳይሆን በሱ ቤት ቀድሞ መጉዳቱ ነው።
በገፅ 85 መረራ ሥልጣኔ (civility) ባልጎበኘው ቋንቋው ያነሳው “እግር ማከክ” እና የጤንነት ጉዳይ እሱም ራሱ ሳያውቀው አይቀርም ብዬ የምገምተው ጉዳይ አልተነሳም ለማለት አይደለም። ከሃዘኔታ፤ ቁጭትና እንክብካቤ በስተቀር ምንም ነገር ያላየሁባቸውን ሰዎች በዚህ መልክ “እንልቀቀው” ወይም እሱ በገፅ 85 መጨረሻ ገደማ እንዳመለከተው “ከመግደል ውጭ አማራጭ አልነበረም” ወደሚለው ሃሳብ የሚዘቅጡ ሰዎች አድርጎ ማቅረቡ እነኚህን ሰዎች በራሱ ደረጃ እጅግ ዝቅ አድርጎ መገመቱና ከራሱ ተመክሮና ሞራል ጋር አዳምሮ ማቅረቡ እጅግ የሚያሳዝን ነው። እንደ መረራ ጉዲና ዝቅ ባለ የካድሬ ደረጃ ምን ይደረግ እንደነበር አላውቅም። እሱን የመሳሰሉ በድርጅት ለመገዛት የሚያስቸግሩ፣ ከዕብድ የማይሻሉ ሰዎች በድርጅቱ አልነበሩም ማለት አልችልም። ድርጅቱ ከተመሰረተበት እ.አ.አ 1968 ጀምሮ የድርጅቱ መሥራች አባላት ከነበሩ ጋርና ከዚያም በ1974 የኢትዮጵያ አብዮት ከፈነዳ በኋላ በድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ወስጥ በነበሩ ሰዎች መካከል ልዩነቶች ተፈጥረው እስከመለያየት የተደረሰበትና አንዳንዶችም ድርጅቱን ጥለው የወጡበት ታሪክ ነበር። ከነኚያ ድርጅቱን ጥለው ከወጡ ሰዎች ጋር በግለሰብ ደረጃ የወዳጅነት ግንኙንት ቀጠለ እንጂ አንዱ ሌላውን demonize የማድረግና አንዱ ባንዱ ላይ እየተነሳ የመወነጃጀልና ስም የማጥፋት ዘመቻ ያካሄደ አልነበርም። ስለ”ዕልቅና” ከመናገር በፊት በቅድሚያ የድርጅቱን ታሪክ ማጥናት
የዛሬ 30 ዓመት ገደማ ለድርጅቱ የውጭ አመራርና ወደ አገር ቤትም ተልኮ ከተመረመረ በኋላ በዚያን ጊዜና በዚያ ሥፍራ በትክክል ምን እንደተፈፀመ የማይታወቁ ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው አማረን ባንድም ጉዳይ የሚያስጠይቅ ምንም መረጃ የለም በሚል ከድርጅቱ አመራር ጋር ተደባልቄ አብሬ ለመስራት ካበቃኝ ጽሑፍ ውስጥ በዚያን ጊዜ በመካከላቸን ተነስቶ የነበረውን ችግር እንዴት እንደፈታነው የሚመለከት ለአብነት ሲታወስ የሚኖር ታሪክ እንደሚከተለው አነሳለሁ።
እኛን ከበላይ አካል ጋር ባገናኝነት ከተመደቡልን ሰዎች መካከል አንደኛው ወደኛ በመጣ ጊዜ በመጠጥ ኃይል መድከሙ ብቻ ሳይሆን ለመናገርም ለመንቀሳቀስም ተቸገሮ ባየንበት ሰዓት ይህንን ሰው “አንልቀቀው”፣ “እንሰረው” ወዘተ አላልንም። ለደህንነታቸን አስደንጋጭ እንደነበር ጠፍቶን አልነበረም። የተጠቀምንበት ዘዴ ይህ ሰው ከተሰጠው ሃላፊነት የተገፈፈና የተዋረደ ሳይመስለውና የኛንም ደህንነት compromise በማያደርግ መንገድ፤ ትዕግሥት በተመላው ብልሃት ይህ ሰው ተመልሶ ወደኛ እንዳይመጣ ተደርጓል። ሌላም የነሃይሌ ፊዳን መያዝና የነከበደ መንገሻን መገደል፣ የነዶ/ር ካሣሁን ብርሃኑንና ሃይሉ ገርባባን፣በኢሊባቦርም የነዶ/ር ከድር መሐመድንና አዲሱ በየነን መያዝ ስንሰማ አስደንጋጭ ከመሆኑ የተንሳ በመካከላችን ከነበሩት ኦሮሞዎች አንዱ ከንግዲህ የሚያዋጣው መኢሶንን በመሰለ በመደብ ጥቅም ላይ በቆመ ድርጅት ሥር መታገል አይደለም። የሚያዋጣው በየብሔር ድርጅቶችና ነፃ አውጭ ግንባሮች ውስጥ ገብቶና ተመልምሎ ትግሉን መቀጠል ነው በሚል በመኢሶን ውስጥ ያሉትም ኦሮሞዎች ከነወራቃና ኦነግ ጋር በመደባለቅ ትግሉን መጀመርና በቅድሚያ የየራሳቸውን ብሔር ብሔረሰቦች ነፃ ማውጣት አለባቸው እስከማለት ደርሶ ነበር። ይኸው ሰው በተለይም መኢሶንን በመሰለ በነፍጠኛ ድርጅት ስም በሚከሰስ ድርጅት ውስጥ መቆየት በብሔረሰቦቻችን ዘንድ ተቀባይነት እንዳናግኝ ችግር ይፈጥርብናል በሚል በቶሎ ከመኢሶን ተሰናብቶ ከመሄድ የማይመለስ ጥያቄ እስከማንሳት ደርሶ ነበር። ይህንን ጉዳይ ካነሳው ጋር የረጋ ውይይት ከማድረግና ሃሳቡን በማክበር ሁኔታውና ጊዜው በሚፈቅድ ጊዜ ይህንን ውሳኔ ለመውሰድ የሚከለክለው እንደሌለ ተነግሮት፤ በነበርንበት ሁኔታ ግን ደርግ ማንኛቸንንም የሚምርበት ሁኔታ ስለሌለ ሌላው ቢቀር ለጊዜው በትግል ሕብረት ደርጃ አብረን ልንቀጥል እንችላለን በሚል መስማማት ላይ ደርሰን ነበር። ይህንን ጉዳይ ያነሳውን ሰው “የክህደት ድሩን መዘርጋት መጀመሩ ነው”፣ “አንልቀቀቀው”፤ እንሰርው ወይም ደግሞ መረራ እንዳመለከተው ለክሃዲ አማራጩ በሕይወቱ ላይ እርምጃ መውሰድ ነው የሚል ነገር ያነሳ አንድም ሰው አልነበረም። ይህንን ያነሳውም ቢሆን ከቅንነትና ከመደናገጥ መሆኑን በመረዳት ለማረጋጋት የተደረገው ሙከራ ፍሬ ሰጥቶ በሌላ ጊዜ ሃሳቡን ቀይሮ መኢሶን የነፍጠኛ ድርጅት እንዳልሆነና ያውም ያለበቂ ድርጅታዊ ዝግጅት ከደርግ ጋር ለመቆራረጥ መምረጡ ለሥልጣን የቋመጠ አድርባይ ድርጅት በሚል ሲከሰስበት ለኖረው ጉዳይ ቆራጥ ምላሽ ነው እያለ እስከመከራክር ደርሶ ነበር። በመጨረሻውም በጥቁር እንጭኒ ተሰውቷል። ይህንንና ሌላም እጅግ ዝርዝር ትዝታዎቼን ለማቅረብ ዕድሉና ዕድሜው በሰጠኝ ጊዜ ላሉትም ለሞቱትም አክብሮት ባለው መንገድ ይፋ ለማድረግ እሞክራለሁ። ይህ የሚይሳየው መአኢሶን የተለየ የአመራር ባህል እንደነበረው ሲሆን፣ ርስ በርስ በመጫረስ የትም ሳይደርሱ ከጠፉትም ሆነ የትግል ጓደኞቻቸውን እየጨረሱ የተመኙትንም የፖለቲካ ሥልጣን ሳይጨብጡ ርስ በርሳቸው በመባላት ከጠፉና ለጓደኞቻቸው ሕይወት መጥፋት ከተጠያቂነት ከማይድኑ ወገኖች ከመደመር አድኗል።
መረራ በመፅሐፉ እንደሚገልፀው ይህንን ያህል ድርጅታዊ አመኔታ የተጣለበት ሰው እንደነበርና እኔን የመሳሰሉ ከሃዲዎች ባይገጥሙት ኖሮ እሱን የመሰለ ‘አብዮታዊ ጀግና’ ሌላው ቢቀር የድርጅቱ በዚያ አካባቢ የተሻለ እንቅስቃሴ እንኳን ማድረግ ቢሳነው ያባላቱን ሕይወት ለማዳን ብቃትና ችሎታ እንደነበረው ይናገራል። እስከዚህ ድረስ በዕድሜም ሆነ ተመክሮ ከሁላችንም ወጣት የነበረ ሰው በሥነ ልቦናዊ ቀውስ ካልተነካ በስተቀር ወይም Narcissism ካልሆነ በስተቀር እንዲህ በድፍረት ስለራሱ ለመናገርና ለመጻፍ መድፈሩ የሚገርም ነው። ወይ “ዝም በል የሚለው ሰው” የለም። ወይም ደግሞ ሰውዬው በተፈጥሮው “ደብረ በጥብጥ ነው” ከማለት በስተቀር ሌላ ቋንቋ አላገኝለትም። አንድ ልብ ያላለው ጉዳይ ቢኖር ግን የሚከተለው ነው፡
ከፍ ብዬ እንደገለፅኩት የዛሬ 30 ዓመት ገደማ እኔ የማውቀውንና የማስታውሰውን በዝርዝር እንዳቀርብ በድርጅቱ የበላይ አካል ተጠይቄ ባቀረብኩት ሰነድ ይህንኑ ወደጅባትና ሜጫ ለወጣው ቡድን ደህንነት የሚበጅ ስፍራ በግንባር ቀድምትነት አዘጋጀሁ የሚለው ይህ ሰው በ“ንቃት” ደረጃውና “ዕልቅናው” እየተኩራራ የሚገልጸው ሥፍራ ምን እንደሚመስል የገለፅኩበትን እያሳጠርኩ እንደሚከተለው አቀርባለሁ።
ከጉደር ወጣ ብለው ወደሚገኙ መንደሮች የሄድነው በሁለት ቡድን ተከፍለን ነበር። ለጥቂተ ቀናት ቀድመውን አንድ የገበሬ ማህበር የአብዮት ጠበቃ አባል ቤት የደረሱት የነኢዮብ ቡድን ነበር። ይህም ሰው ዱጋሣ ይባላል። ስለ መኢሶን የሚያውቀው ነገር አልነበረም። የተቀበለንም ጉድታ የሚባል ጉደር አፋፉ ላይ የሚኖር “የ42 ቀበሌ ሊቀ መንበር” አደራ ስላለው ነበር። ዱጋሣ አንድ ጥይት ብቻ ባላት ምንሽር ጠመንጃ መታጠቁን ታጥቋል። እንደአጋጣሚ ጠመንጃው የጎረሰውን አንድ ጥይት ነክሶ ከተቀመጠ መሰንበቱንና ተወርዋሪውም እንደተከፈተ ዝገት እንደበላው ባይናቸን አይተናል። እኔና ዶ/ር ተረፈ ያለንበት ቡድን አቶ ዱጋሣ ቤት ደርሰን ከተደባለቀን በኋላ ከነኢዮብ ጋር አብረን የቆየነው ላንዲት ቀን ብቻ ነበር። በሚቀጥለው ቀን እኛ እዚያው ስንቀር የእነኢዮብ ቡድን ራቅ ብሎ ወድሚገኝ የገበሬ ማህበር አባል ቤት ተዛውረዋል። ይህም ቤት የአቶ ቃበታ ቤት ሲሆን እሱም የገበሬ ማህበር የአብዮት ጥበቃ አባል ነው። ቃበታም እንደ ዱጋሣ መታጠቁን ይታጠቅ እንጂ ትጥቃቸው ለየቅል ነው። እንደጠመንጃ የተሰራውን የቃበታን የዱላ ትጥቅ ባይናቸን አይተናል። ወደእኛ በመጣ ጊዜ አንግቷት ነበር። በሌላም ጊዜ ወደኛ በመጣ ቁጥር የሚያነገትውም ይህንኑ በጠመንጃ ቅርፅ የተሰራውን የዱላ ትጥቅ ነበር። ድጋሣም ሆነ ቃበታ ዕቃ ባደራ እንዲያስቀምጡ ተጠይቀው እንዳስቀመጡ ያህል እንጂ ምንም አይነት አብዮታዊ ንቃትም ሆነ ድርጀታዊ ዕውቀት አልነበራቸውም። ይህ አንዳለ ሆኖ ለሁለት ተከፍለን ገሚሳቸን ከነዱጋሣ ቤት ገሚሳችን ደግሞ ወደቃበታ ቤት ለመሄድ የተወሰነው ሁላችንም ባንድ ቤት ወስጥ መሸሽጉ ከደህንነት አንፃር ተገቢ እንደማይሆንና አንድ ድንገተኛ አደጋ እንኳ ቢያጋጥም አንዱ ወገን በድጋፍ ሰጭነት ወይም ደግሞ አቅጣጫ ቀይሮ ወደሌላ አካባቢ ለመሸሽ ይረዳል በሚል ነበር፡ ከዚህም በላይ አንድ ደሃ የገበሬ ማህበር አባል፥ ከአሮጊት እናቱ፥ ሚስቱ፥ ልጆቹና ሁለት እህቶቹ ጋር የሚኖር ሰው ያንን ያህል ብዛት ያለንን እንግዶች ለማሳረፍ የሚያስችል ቦታ ስላልነበረውና በተለይም ገባ ወጣ ባልንም ቁጥር ያካባቢውን ዓይን ልንስብ እንችላለን በሚል ለሁለት መከፈል ነበረብን። በዚህ መሰረት እኔ፤ ተረፈ፤ አጥናፍ፤ ከበደ ድሪባና ለማ ፊዳ አንድ ቤት ስንቀር ኢዮብ፤ መርዕድ፥ ሽመልስ ኦላናና ስሙን በትክክል የማላስታውሰው የሸዋ ሕዝብ ድርጅት ካድሬና ከበደ ድሪባን በከፊል ሾፌርነት የሚረዳው ምናልባት ስሙ ታደሰ ሳይሆን አይቀርም ብዬ የምገምተው ሰው ከእኛ ራቅ ብሎ በሚገኝ የገበሬ ቤት ነበሩ። መሸትና ላይን ያዝ ሲያደርግ አንዳንድ ጊዜ ተረፈና ከበደ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከበደ ብቻውን እነኢዮብ ወዳሉበት በመሄድ ሲገናኙ አብዛኛውን ጊዜ ግንኙነቱ በወረቀትና በመልዕክተኛ ስለነበር የሚላላክልንም መጠጊያ የሰጠን ገበሬ ዱጋሣ ወይም እህቱ ሶርሴ ነበረች። በዚያች አብረን በዋልንባት ቀን የተነጋገርነው ተረፈ ባንሳው ጉዳይ ላይ ነበር። እሱም ለጠመንጃ ትግል ወደገጠር የወጡ አብዮታውያን ምን ያህል ጊዜ በትግሉ እንደሚቆዩ አወቁም አላወቁም ከመሃላቸው በየቀኑ የሚሆኑትን ጉዳዮች በዲያሪ መልክ የሚይዝ ክሮኒክለር ነበራቸው። አባቶቻችን ሳይቀሩ ወድ ማይጨው ሲዘምቱ አንድ ቀለም የለየ ሰው አብሮ ይዘምትና እሱም በየዕለቱ የሆነውንና የደረሰውን በጽሑፍ እንዲያስቀር ያደርጉ ነበርና አሁንም አንድ ሰው ከመሃላቸን ይህንን ማስታወሻ በዲያሪ መልክ የሚይዝ ያስፈልገናል የሚል ሃሳብ አቅርቦ በዚህ ተነጋግረናል። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ብቻ ሳይሆን እንግሊዝ አገርም አብረን ላጭር ጊዜ አብረን የነበርነው ኢዮብ ታደሰና ከበድ ድሪባ እኔን ኖሚኔት ሲያደርጉ ሌሎችም ይህንኑ ሲስማሙ ተረፈም ቀድሞ በልቡ ይዞ የነበረ የኔን ስም ለመስጠት እንደነበር ገልጾ ያ ስብሰባ በዚያው ተደመደመ። አንድም ጊዜ ሁላቸንም ባንድ ጊዜ ባንድ ቦታ ተገናኝተንና ተቀምጠን የተወያየንበት ጊዜም አልነበረም። ከጥንቃቄም አንጻር ተገቢ አልነበረም። በህይወት የሌሉ ሰዎቸ ለማንኛችንም ምስክር አይሆኑም። ከሳሽ መረራ ጉዲና ነውና መረጃ የማቅረብ ዕዳው ከኔ ይልቅ የሚወድቀው እሱ ላይ ነው።
መረራ ጉዲና ለአማረ ተግባሩ ስፍራ አዘጋጀንለት ወዳለው ወለንኮሚው ታሪክ ስመለስ ደግሞ በየተራ እየተቀባበሉ የደበቁኝ ሃይሉ ጉርሙ የሚባል ቀድሞ አየር ወለድ፤ በወለንኮሚ የንግድ መደብር የነበረውና የኤፒድ ሠራተኛ የነበረቸው እልፍነሽ ደበሌ ነበሩ። መጀመሪያ እንዲቀበለኝ የተጠየቀው ገረመው የሚባል “በድርጅት ተይዟል” የተባለ ሰው ሲሆን እሱ ግን ሊቀበለኝ እንደማይችልና በሥራ ምክንያት ተዛውሮ ወደ መርሐ ቤቴ ለመሄድ ጓዙን በማንሳት መሆኑን ይገልፃል። ወደ ሃይሉ ጉርሙ መደብር ስንሄድ ደግሞ እሱም ሚስት ለማግባት አዲስ አበባ ስለምሄድ ጥቂት ቀናት ጊዜ እንዲሰጡትና እስከዚያ እንደሚዘጋጅ ይነግራቸዋል። እልፍነሽ ዘንድ ስንሄድ ፈቃደኛ ሆና ልትቀበለኝ ቻለች። እልፍነሽና ሃይሉም ቢሆኑ ደጋፊ እንጂ የድርጀቱ አባላት አልነበሩም። እየተቀባበሉ ባስቀመጡኝ ጊዜ ሁሉ ቀን ቀን ቤቱ እየተዘጋብኝ መብራት ሳላበራ መፀዳዳትም ቢያስፈልገኝ እዚያው የምፀዳዳበት ተዘጋጅቶልኝ አሳልፍ ነበር። መብራት የማብራት እድል የነበረኝ ማታ ሃይሉ መደብሩን ሲዘጋ ወይም ደግሞ እልፍነሽ ከሥራ ስትመለስና ሲመሻስ ብቻ ነበር። ይህ ሰው ድርጀታዊ ንቃቱና ብቃቱ በዚያን ጊዜ ይሻል ነበር በሚል ስለራሱ የሚናገር ሰው ያን ጊዜም ሆነ ዛሬ ስለ ድርጅት ጥንካሬና ብቃት ያለው ዕውቀት ጉደር ከደበቁን ገበሬዎች ንቃትና ብቃት ምን ያህል እንደሚሻል አንባቢ እንዲታዘበው እተውዋለሁ።አዘጋጀሁ የሚለው ሥርቻ በመፅሐፉ ውስጥ በልጅነቱ ላምና ጥጃ ከሚጠብቅበት የዘመዶቹ ማሳ ታጭዶ የተወቃ በቆሎና ማሽላ ያስቀምጥ እንደሆን እንጂ ድርጅታቂ ንቃትና ብቃት አለኝ ብሎ የሚኩራራ ሰው ደፍሮ አዘጋጀሁ በሚል በኩራት የሚናገረው ሥፍራ አልነበረም።
መረራ ጥቁር እንጭኒ የደረስውን ዕልቂት እንደሰማ በአምቦ ገጠር ሲባዝን ቆይቶ በመጨረሻ እጅ እንደሰጠና ለምን መስጠት እንደወሰነ ያትታል። የኔ ወንድም ደብዳቤ ደግሞ እሱ ከ2ተኛ ፖሊስ ጣቢያ መረራ ደግሞ “ምርጫ ተሰጥቶኝ” (ለማንም ያልተሰጠ ምርጫ ለሱ ብቻ እንዴት እንደተሰጠው ምክንያቱን የሚያውቀው እሱ ብቻ ነው) በሚል ከተናገረው 6ተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደውና በወታደር ማመላለሻ መኪና (MACK) ተጭነው ከተባለው የኮማንዶ ቡድን ጋር አምቦ ከተማ እንደተወስዱና እዚያም ሲደርሱ ሃምሳ ዓለቃው ተደባልቋቸው ወደ ጥቁር እንጭኒ እንደተወሰዱ ነው። የኔ ወንድም እንደሚለው መረራና ሃምሳ ዓለቃው አምቦ ከተማ ሲገናኙ እሱ በማያውቀው ኦሮምኛ ቋንቋ እያወሩ እነዶ/ር ተረፈንና ቡድኑን ወዳስቀመጡበት ዘመዶቻቸው ቤት መርተው ማሳየታቸውን ይናገራል። እሱም ራሱ (ሲራክ ተግባሩ) ጭምር በዚያን ሰዓት እዚያው ጥቁር እንጭኒ ተወስዶ እንደነበር በማብራራት ግድያው እንዴት እንደተፈፀመ ሲናገር በዚያን ሰዓት መረራ የወንድሜ ረዳት በሚል ያቀረበው ሰው መኖሩን አይናገርም። የሲራክ ትወስታ እነርሱም ተደምረው ለመረሽን ከተደባለቁ በኋላ የግድያው ተሳታፊ በነበረው የወዛደር ሊግና የአብዮታዊ ሰደድ አባሎች ባንድ በኩል በሌላ በኩል ደግሞ ከደርግ ምርመራ ከፍል በተላከው በአንድ መኮንንና የበታች ሹም የሚመራው የኮማንዶ ቡድን መካከል በተነሳው አለመግባባት በመጨረሻዋ ደቂቃ “እኒኚህንም ልጆች ጨምራችሁ ግደሉ አልተባልንም” በሚል ያንደኛው ወገን እሪታ መትረፋቸውንና ጭፍጨፋውን ከፈፀመው ቡድን ጋር እሱም፤መረራ ጉዲናም፤ ሃምሳ ዓለቃውም ተመልሰው ከሃምሳ ዓለቃው በስተቀር እነርሱ በእስር እንዲቆዩ መደረጋቸውን ነው። ሲራክ ተግባሩም ለመረራ ጉዲና በፈረንጅ አቆጣጠር በ2010 የላክውና መልስ ሳያገኝ የቀረው በዲችልና ኢሜል የተላከው ደብዳቤ ይህንን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ለምን ለመረራ ጉዲና ለመፃፍ የተገደደበትንም ምክንያት አብሮ ያነሳል።
“ለማስመሰል ደርግ ጽ/ቤት እንደ እስረኛ” እንደወሰዱኝ የሚናገረውም አንባቢ የሚታዘበውና የሚያሳዝን ነው። መረራ በመጽሐፉ ውስጥ እንደጠቀሰው ‘ምርጫ’ ተሰጥቶት ወደስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ፤ ከዚያም ወደ ወህኒ ቤት ተወስድኩ ሲል ነግሮናል። ለእኔም ሆነ ለሌላ የመኢሶን አባላት ምርጫ ሳይሰጥ እኔ ወደ 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ ከዚያም ወደ 4ኛ ክፍለ ጦር ተወስኛለሁ። እኔም ሆንኩ መረራ ለረጅም ዓመታት የቆየንባቸው እሥር ቤቶች “ለማስመሰል” ሰው የሚታሰርባቸው ቦታዎች አይደሉም። በአንፃራዊ ደረጃ ያወዳደርን እንደሆነ 4ኛ ክፍለ ጦር ያለስንቅ፡ ነፃ ህክምናና እንደልብ ነፋስ ለመቀበልና ለመንቀሳቅስም ሆነ ዘመድ ለጥየቃ ብቅ በማይልበት ማጎሪያ በጥብቅ መታሰርና በወህኒ ቤት ተበላም አልተበላም መንግሥት ስንቅ በሚያቀርበብትና የዘመድ ጥየቃ በማይከለክበት፣ አልፎ ተርፎም ለመንቀሳቀስና ከሌላው እሥራኛ ለመገናኝት ይህን ያህልም ገደብ በሌለበት ቦታ መታሰር መካከል የትኛው እንደሚሻል መረራ ጠፍቶት ነው ለማለት ይቸግረኛል። ከሌላው የመንግሥት ቀለብ ከነበረው እሥረኛ የሚተርፈው ትርፍራፊ በሙሬ ከየሳህኑና ከየወለሉ ላይ እየተሰበሰበ፣ በባሬላ ከተጫነ በኋላና ጠባቂዎቻችን ፈቅደው ወደእኛ እስኪመጣ ድረስ የዝንብ መንጋ ሲተራመስበት ቆይቶ የሚደርስልንን፣ ዘመዶቻችን የሚያቀርቡትን እንደማጣፈጫ አያይዘን ለመብላት ስንጣደፍ ከምግቡ ማነስ የተንሳ ገና እጃችንን ለሁለተኛ ጊዜ ሳንሰድ ቦዶ ከመሆኑ የተነሳ ረሃብ ማለት ምን እንደሆነ ልንገነዝበ በቻለንበት ቦታ መታሰር ምን ማለት እንደነበር ሳስበው ያሳለፍነው መከራን ችግር እስካሁን ዓይኔ ላይ ድቅን ይላል። ይህ ብቻ አይደለም ዝንብ ሲተራመስበት ውሎ የሚመጣልን ትርፍራፊ ያስከትል የነበረውን የሆድ ሕመምና ተቅማጥ ተቆጥረን ከተዘጋብን በኋለ ለመጽዳዳት ስለማይፈቀድለን ቀን በበላንበት ለመጸዳዳት የመንግደድበትን እሥር ቤት ማንም “ለማሰመሰል” ለዘመናት የሚቆይበት እንዳለነበር ሕሊና ላለው ሰው የሚጠፋ አልነበረም። በ4ኛ ክፍለ ጦር እጅግ ዝቅተኛ የሆነው የሰው ልጅ መብት በተገፈፈብት ቦታ የነበሩ ሁሉ ሊታዘቡት እንደሚችሉት በመኢሶን ድርጅት ውስጥ “ዕልቅና” ነበረኝ ከሚል ሰው ይቅርና ከውጭ ወሬውን የሰማ ሰው የማንኛችንንም በየትኛወም ቦታ መታሰር “ለማሰመስል” በሚል የሚፈርጅ ሰው ቢኖር መረራ ጉዲና ብቻ ይመስለኛል። ግራ የሚገባኝ ይህ ሰው ምን እንደተማረና ከሃምሳ ዓመት በላይ በሆነው ዕደሜው ምን ተመክሮ እንዳካበተ ነው። ባጭሩ ይህ ሰው እንዳለ ዜሮ ነው ማለት እችላለሁ።
መረራ ጉዲና በመፅሐፉ ገፅ 89 እና 92-93 ጥቁር እንጭኒ ከወደቁት ጓዶቼ ጋር ባንድ ጉድጓድ ሳልገባ በመቅረቴ የገባውን መቆጨትና ባሰበውም ቁጥር በሞት ከተለዩት ዘመዶቹም ሆነ ለተሰዉት ጓዶች ካለቀሰው የበለጠ የኔን ነገር ሲነሳ ከመዘግነን አልፎ ዕንባው እንደሚፈስ የገለፀውን ስመለከት ከዚህም የተሻለ የሰውዬውን ትምህርት፤የዕድሜ ተመክሮም ሆነ ሥልጣኔ (civility) ያልሞረደውን የጭካኔ (sadistic) አመለካከት የሚያስረዳ ዓረፍተ ነገር አላገኘሁም።
በገፅ 124 – 125 ደግሞ እኔ “የዘመኑ ቀንደኛ ነፍጠኛ የነበረው የደጃዝማች ፀሐዩ ዕንቆ ሥላሴ የእህት ልጅ” መሆኔን በማንሳትና ዝቅ ብሎም በባሌ ተነስቶ ለነበረውና በዋቆ ጉቱ ይመራ ለነበረው የኦሮሞ ገበሬዎች እንቅስቃሴ መደምሰስ ምክንያት አድርጎ ከሚያቀርበው ከሌላው የእናቴ አጎት ጋር በማገናኘት እኔም “ያቀነባበርኩት ክህደት” ከነፍጠኛ” ዘመዶቼ ተነጥሎ እንደማይታይ አድርጎና አያይዞ ማቅረቡ ከአገር ወዳድ ኢትዮጵያዊም ሆነ በሶሺያልስት ንቅናቄ ስም በሚጠራ ድርጅት ላንድ ሳምንት ያህል እንኳን በአባልነት ከታቀፈ ሰው የማይጠበቅ ወራዳ አነጋገር መሆኑን አንባቢ እንዲታዘበው እተወዋለሁ። ይህንን የመሰለ ወደ ዘርና ብሔር የሚዘቅጥ የማነካካት ቋንቋ ወደኦነግ ከተጠጉ አክራሪ ኦሮሞ ብሄርተኞቸ ሰሰማው የነበረ ፀረ አማራ አነጋገር ከዚህ ሰው መስማቴ አስገርሞኛል። መረራ በኦሮሞ ገበሬ ቤተስቦቹና ዘመዶቹ የሚኮራውን ያህል እኔም ከላይ በጠቀሳቸው አጎቶቼ ብዙ የምኮራበት ቅርስ ያለኝና በዚህም የማላፍር ሰው መሆኔን እንዲረዳው እፈልጋለሁ። ማንኛችንም መርጠን ከዚህ ብሄር ወይም ከዚያ ዘር አልተወለድንም። ልንከሰስበትም ሆነ ልንመጻደቅበትም አይገባም።
መረራ ጉዲና በተለይ የደጃዝማች ፀሐዩን ስም በዚያው በጅባትና ሜጫ ግንደበረትና ጥቁር እንጭኒ ይፈፀም ከነበረ አንድ ታሪካዊ ጉዳይ ጋር በማያያዝ ስማቸውን በክፉ እንደሚያነሳ ከታናሽ ወንድሜ በተደጋጋሚ ሰምቻለሁ። ነገር ግን ይህ ተራ ጉዳይ በመሆኑና መረጃም ስለሌለኝ ምክንያቱ ለዚህ ነው ብዬ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ መረራን ለመክሰስ መሞከር እሱን ራሱን መሆን ነው። እርግጥ ደጃዝማች ፀሐዩ የጅባትና ሜጫ አውራጃ ገዥና ከዚያም የሸዋ ክፍለ ሃገር ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ ሆነው በቀዳምዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ባገለገሉበት ዘመን በዚህ በጅባትና ሜጫ አውራጃ በግንደበረትና ጥቁር እንጭኒ አካባቢ በባሪያ ሽንገላ የተሰማሩ የኦሮሞ ባላባቶችንና ከመካከለኛ እስክ ሃብታም ገበሬ ድረስ የሚደርስ መተዳዳሪያ የነበራችወን በዚሁ በባሪያ ንግድ ተሰማርተው የነበሩትን በማሰስና በባርነት የፈነገሏቸውን በነፃ እንዲለቁ ከማስገደድና በዚህ ንግድ አካብተውት የነበርውንም ሃብትና ንብረት በመውረስ፣ ገሚሶቹንም ወህኒ ቤት በማውረድ የባሪያ ንግድ እንዲወገድ አድርገዋል። ይህ ብቻ አይደለም። ከሕዝብ ንብረት በመንጠቅ አላግባብ የበለጸጉ አማሮችን ንብረት ጭምር በመውረስ ንብረታቸው ለተነጠቀው ኦሮሞ ገበሬ በመመለስ ለሕግና ፍትህ የቆሙ ሰው እንደነበሩ ዶ/ር ሥዩም ሐረጎት ከጻፉት መጽሐፍ አንብቦ መረዳት ይቻላል። ይህ ብቻ አይደለም። በዚያን ዘመን ከአውጫጭኝ ለማምለጥ የሞከሩ ባሪያ ሸንጋዮች ከሥርቻ ጥለውት የሄዱትን ከመረራ ብሔር/ብሔርሰብ የሚወለድ ሕፃን ወንድ ልጅ ደጃዝማች ፀሐዩ እንደልጃቸው ወስደው በማሳደግ አርበኞች ት/ቤት በማስገባት፣ ከዚያም ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ውጭ አገር በመላክ በስማቸው የሚጠራ፣ አገራችን ካፈራቻቸው አጅግ ታዋቂ የቀዶ ጥገና ሐኪም ለማፍራት የቻሉ ሰው መሆናቸውን ልነግርህ እወዳለሁ። መረራን ከመሰለ አሳዛኝ ፍጡር “ቀንደኛ ነፍጠኛ” በሚል የማዋረድና አክብሮት የመንሳት አነጋገር በሱ ዙሪያ ያሉትን ያስደስት ይሆናል። ብስለት ያላቸው ወገኖች ግን መረራ ለኦሮሞ ሕዝብ ምን ተጨባጭ ቁም ነገር እንደሰራና ምን ያህልስ ከበሬታ ያለው ተቃዋሚ ፖለቲከኛ እንደሆነ ይጠፋቸዋል ብዬ አላሳብም።
የኔን አጎትች በሚመለከት አገራችን በኢጣልያ ፋሽስት በተወረርችበት ዘመን በዱር በገደሉ በመንከራትተት የሰሩትን ጀብዱና የፈጸሙትን ያርበኘነት ታሪክ መረራ ቢቀር ለብዙ ውድና እውነተኛ የኢትዮጵያ ልጆች የሚያኮራ ቅርስ መሆኑን ላስገነዝበው እወዳለሁ። እንዲሁ በመደዳው (simplistic በሆነ መንገድ) “ነፍጠኛ” በሚል ለማዋረድ የሚሞከር ትምሀርት ቤት ያልገባና ታሪክን፣ በመወለድ ማነንትን፣ በአዲስና ዘመናዊ የፖለቲካ ባህል አእምሮውን ማነፅ ያልተሳካለትና በዘር ላይ የተመሰረተ ጥላቻወን መደበቅ ያልቻለ ከንቱ ሰው ብቻ ነው።
መረራ ጉዲና የባሌው የነዋቆ ጉቱ ትግል ከራሱ ብሔር/ብሔረሰብ ከመጡ ኢትዮጵያዊ ፀረ ፋሽስት አርበኛና ጄነራል እንዳከተመ እዚያው አዲሰ አበባ ዪኒቨርስቲ ካሉት የታሪክ ምሁራን ጠይቆ መረዳት አለመቻሉን ሰመለከት ይህ ሰው በዚያ ዩኒቨርስቲ በጉርብትና ካልሆነ በስተቀር በማስተማርና ምርምር ሥራ ላይ መሰማራቱ የሚያጠራጥር ሆኖ አግቼዋለሁ።
ይህ ሰው ስለራሱ ያለው ግምትና የሚሰጠው ምስክርነት ከየትኛወም ኢትዮጵያዊ አንደበት ተሰምቶ የማይታወቅ ነው። ይህ የበሽታ ካልሆነ በስተቀር ከጤነኛ ሰው የሚጠበቅ አይደለም። የምደመድመው ግን እንደሱ የሚያስጨንቅ የሕሊና ሥቃይና በቅሌት የሚጠረጠር የሕይወት ታሪክ እንደሌለኝ እንዲገንዝብ በመንገር ነው። በራሴ ላይ እምነትና የመንፈስ ጥንካሬ ያለኝ፣ እንደ መረራ በጠባቡ ሳይሆን፣ ካንድ አገር ግዛት ክልልና ብሔራዊ ጥቅም ባሻገር ዓለም ዓቀፋዊነትንና (Internationalism) እና ሰብዓዊነትን (Humanism) የሕይወት ተመክሮዬ በማድረግ ባለም ዙሪያ ያሉትን የሰው ልጆች በተማርኩትና በልምድ ባካበትኩት ቅርስ በማገልገል ላይ እገኛለሁ። ስለዚህም እንደ መረራ ጉዲና ወደዚያ የዛሬ 35 ዓመት ታሪክ ከመመለስና ጊዜ ከማጥፋት ይልቅ ትምህርታዊና ላለውም ሆነ ለመጭው ትውልድ የሚጠቅም በመቻቻልና መከባበር ላይ ለቆመ፣ ዘላቂና ሰላማዊ የፖለቲካና የልማት አማራጭ ሃሳቦች ላይ ማተኮር እንደሚገባ በማሳሰብ ጽሑፌን እደመድማለሁ።