Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

በፍቅር ቀንን ለገዥዎቻችን ቀይ ካርድ

$
0
0

ከጌታቸው ሽፈራው

የቫላንታይን ዳይ አብዛኛው ወጣት ቀይ ይለብሳል፡፡ በዚህ ቀን ታዲያ ለምን ይህን ቀይ ምልክት እንደ ቀይ ካርድ ተጠቅመን ምልክት አናደርገውም? በዚህ ቀን ቀዩን የታሰሩትን፣ የሚበደሉትን፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ከፍቅር የነጣጠለ ስርዓት ላይ ምልክት አድርገን አንጠቀመውም?

Valentine day1
በቅርብ አመታት ውስጥ በአገራችን ‹‹Valentine’s Day›› በተለይ በወጣቱ ዘንድ መከበር ጀምሯል፡፡ ካፌዎች፣ ሆቴሎችና ሌሎች መዝናኛዎች ቀኑን በስፋት ለገበያ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ ሆኖም አብዛኛዎቹ ወጣቶች ‹‹ፋሽኑን›› ከማሯሯጥ ያለፈ ትርጉሙን አውቀውት ነው የሚያከብሩት ለማለት ይከብዳል፡፡ የውጭ ባህል ከሆነ ባናከብረው ይመረጣል፣ ፍቅር ምን ባህልና አገር ያስፈልገዋል? ከተባለ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ብናደርገው የተሻለ ነው፡፡

ቅዱስ ቫላንታይን የታሰረበት፣ ከዛም የተገደለበት ዋነኛው ምክንያት በሮማውያን ዘመን እንዲያገቡ ያልተፈቀደላቸውን ወታደሮች አጋብቷል ተብሎ ነው፡፡ ይህ ለእኛ አገር ጠቃሚ ተምሳሌት ነው፡፡ የእምነት አባቶች ለተከታዮቻቸው ማድረግ ያለባቸውን እምነታዊ ተግባር መፈጸም ግዴታቸው ቢሆንም ከመንግስታት ጥቅም ጋር በተጋጨ ጊዜ ሲያስሩና ሲገድሉ ተስተውለዋል፡፡ ቫላንታይን የዚህ ጥቃት ሰለባ ነው፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን እሱ የሚከተለው እምነት በመንግስት ጣልቃ ገብነት ውስጥ ወድቆ ነበር፡፡ ይህ የእኛ የወቅቱ ትክክለኛ ገጠመኝ ነው፡፡

ከወራት በፊት መጅሊስ በቀበሌ ተመርጧል፡፡ በእምነታችን ጣልቃ አትግቡ ያሉት ሙስሊም ወንድሞቻችን እስር ቤት ውስጥ ታስረዋል፡፡ በእድሜ ጠገቡ የዋልድባ ገዳም የሀይማኖት አባቶች አጽም የተቀበረበት ቦታ ሳይቀር ለሸንኮራ አገዳ ማምረቻ ተከልሏል፡፡ በእምነታችን ጣልቃ አትግቡ ያሉት ሙስሊምና የማህበረ ቅዱሳን አባላት ‹‹በጽንፈኛነት›› እየተከሰሱ ነው፡፡

ቅዱስ ቫላንታይን የተከለከሉት ወታደሮቹን እንዳያጋቡ ነው፡፡ በዛን ዘመን ወታደሮቹ ትዳርን ጨምሮ በርካታ ተፈጥሯዊ መብቶቻቸውን እንዳይጠቀሙ ተከልክለው ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባለች አገር መሳሪያ ከያዙትም በላይ ለህዝብ ጥቅምና ለአገር መብት ወታደር ሆነው የሚያገልግሉት አክቲቪስቶች፣ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ እነሱ ወታደርም ብቻ ሳይሆኑ እንደ ቫላንታይን በየ መስካቸው ቄሶች ሆነው ከህዝብ ጎን የቀሙ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ህዝብ ዴሞክራሲያዊና ተፈጥሯዊ መብቱን በተነጠቀበት ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኞቻችን፣ አክቲቪስቶቻችንና ፖለቲከኞቻችን ልክ እንደ ቅዱስ ቫላንታይን እጣቸው እስር ቤት ሆኗል፡፡ በመሆኑም ይህን የ‹‹ፍቅር ቀን›› ስናከብር በርካታ መቶ አመቶችን ወደኋላ ተጉዘን ሳይሆን አሁን ቃሊቲና ቂሊንጦ፣ ማዕከላዊ እንዲሁም በየ ቦታው ታጉረው የሚገኙትን የእኛዎቹን ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች፣ የእምነት መሪዎች፣ ፖለቲከኞችና ህዝብ ብናስታውስ ምን አለበት?

ይህን ቀን ወደ ጾታ ፍቅር እናቅርበው ካልንም የውጭ ባህል፣ የውጭ ታሪክ፣ የቆየ አባባል ከምናስታውሰው ይልቅ ለእኛው ነባራዊ ሁኔታ ቅርብ ነው፡፡ መቼም አገር ሰላም ካልሆነች፣ ህዝብ በሰላምና በፍቅር ካልኖረ የፍቅር ጓደኛሞች፣ የባለ ትዳሮች…..ፍቅር ፍቅር ሊሆን አይችልም፡፡ በአገራችን ባለፉት አመታት ‹‹ብሄር›› የሚሉት መከፋፈያ ባልና ሚስት አፋትቷል፡፡ ወጣቶች ቢዋደዱ እንኳ ቤተሰቦች ‹‹ብሄሯ/ሩ ምንድን ነው?›› የሚል አስቀያሚ ጥያቄ ማንሳት ጀምረዋል፡፡ የጓደኛ፣ የዘመድ አዝማድ ምክርም ተመሳሳይ ሆኗል፡፡ በአጠቃላይ በብልሹ ፖለቲካችን፣ በከፋፋይ ፖለቲከኞቻችንና ፓርቲዎች ምክንያት ሁለት የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪዎች በፍቅር የማይኖሩበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡

ይህ ብቻ ግን አይደለም፡፡ በዚህ 23 አመት ህወሓት/ኢህአዴግ አገሩን የሚጠላ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በመወለዱ የሚያፍር፣ ‹‹ጎሳ›› እንጅ ዜግነት እንደሌለው የሚያስብ ወጣት ለመፍጠር ታትሯል፡፡ ሮማውያኑ ፖለቲከኞች ወታደሮች ትዳር እንዳይዙ እንጅ ሮማን እንዳይወዱ አላደረጉምና ከእኛው ስርዓት በእጅጉ የተሻሉ ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን አገራቸውን እንዳይወዱ አንዴ ‹‹ቅኝ ገዥ›› ሌላ ጊዜ በዝባዝና ጨቋኝ….ተብለው የፈጠራ ታሪክ ሲማሩ አድገዋል፡፡ እናም ይህን የፍቅረኞች ቀን ፍቅረኞች የተወለዱባትን፣ የሚኖሩባት ኢትዮጵያን እያሰብን፣ ስለ አገር ፍቅር እየተነጋገርን፣ አገራችንን እንድንጠላ የሚያደርጉትን ‹‹ቀይ ካርድ!›› እያሳየን ብንውል ትልቅ ቁም ነገር ይመስለኛል፡፡

እስኪ አሁን ደግሞ የፍቅርን ቀን ወደ ጥንዶች እናውርደው! ይህን ቀን ‹‹የፍቅር ቀን›› አድርጎ ለማክበር መጀመሪያ ሰላም መሆን ያስፈልጋል፡፡ ጓደኛዋ/ባሏ የታሰረባት፣ አገሩ ውስጥ ስቃት በዝቶበት የተሰደደበታ፣ ከዚህም አለፍ ሲል በእግፍ የሞተባት ወጣት ይህን ቀን ‹‹በፍቅር›› ቀንነት ልታከብረው አይቻላትም፡፡ በተመሳሳይ ቀኑ ሚስቱ/ጓደኛው ለታሰረችበት፣ ፤ተሰደደችበትና ለተገደለችበት ወጣትም ‹‹የፍቅር ቀን›› ሊሆን አይችልም፡፡ እነዚህ ወጣች የቀድሞውን ቄስ ከማስታወስ ይልቅ ስለ እውነት መስዋት የሆኑትን ጓደኞቻቸውንና ይህ መከራ የተንሰራፋባትን ኢትዮጵያን እንዲያስታውሱ ይገደዳሉ፡፡ ይህን መከራ ያደረሰውን፣ ከጓደኞቻቸው የነጠላቸውን አካል ሊያወግዙ፣ ሊቃወሙና ምልክት (ቀይ) መስጠት ሊኖርባቸው ነው፡፡

የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጓደኛና ባለቤት ባይታሰር፣ ባይሰቃይ፣ ባይሰደድና ባይሞትም ነገ እንደማይፈጠርበት እርግጠኛ ሊሆን ግን አይቻልም፡፡ ምንም ያህል በ‹‹ፍቅር ቀን›› ደስተኛ መሆን ቢቻል ነገ ወንዱ እንደ ርዕዮት ሚስቱ እንደማትታሰርበት እርግጠኛ ሊሆን አይችልም፡፡ ሴቷም ባሏ ልክ እንደ አንዱ ዓለም፣ አቡበክር፣ እስክንድር፣ በቀለ፣ ውብሸት ….ቧላ እንደማይታሰር እርግጠኛ የምትሆንበት ስርዓት የላትም፡፡ እናም በ‹‹ፍቅር ቀን›› እውነትን በመናገራቸው፣ በእምነታቸው በመጽናታቸው፣ አገራቸውን በመውደዳቸው ከባልና ሚስቶቻቸው፣ ፍቅረኞቻቸው ብቻ ሳይሆን ከልጆቻቸው ተነጥለው የዋሉትን ኢትዮጵያውያን ማስታወስ ሊኖርብን ነው፡፡ የ‹‹ፍቅር ቀን››ን ልታከብሩ ያሰባችሁ! እስኪ ፍቅረኞቻችሁንና የትዳር ጓደኞቻችሁን እነዚህ ካለ ፍትህ የታሰሩ ኢትዮጵያውያን አድርጋችሁ እሰቡ?

እውነት የቀኑ ትርጉም ከገባን፣ ስለ ፍቅር ከተጨነቅን ስለ ኢትዮጵያ፣ አገሩን እንዳይወድ፣ እርስ በእርሱ እንዲናቆር ስለተደረገው ህዝብ፣ ስለ ጋዜጠኞቻችን፣ ስለ ፖለቲከኞቻችን፣ ስለ አክቲቪስቶቻችን….ስለ እኛ ስለ ኢትዮጵያውያን እያሰብን ልናከብረው ይገባል፡፡ መከራ ፈጣሪውን ስርዓት፣ ህዝብን የሚያናቁረውን ፓርቲና ፖለቲከኞች፣ አገርን የከፋፈለውን አካል፣ ፍቅረኛና ባለትዳሮችን ያለ ፍትህ የነጣጠለው ህወሓት/ኢህአዴግ ልንወቅስ ይገባል፡፡ ቀኑን የምንወክልበትን ቀን መለዮ ሁሉ የቀይ ካድር ምልክት ልናደርገው ይገባል፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>