ከይርጋ አበበ
ዛማሌኮች በጽናት እስከመጨረሻው በመጫወታቸውና የጊዮርጊሶችን መዘናጋት በመረዳታቸው ጨዋታውን በአሸናፊነት አጠናቅቀዋል፤
የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ከግብፁ ዛማሌክ ጋር ባደረገው ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማግኘት ወይም ግቡን ሳያስደፍር አቻ መውጣት ባለመቻሉ ወደ ቀጣዩ ዙር ሳያልፍ ቀረ።
ትናንት በአዲስአበባ ስቴዲየም 10 ሰዓት ላይ በተካሄደው የመልስ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስና የግብፁ ዛማሌክ ሁለት ለሁለት በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ በጨዋታው በአንድ ግብ ብልጫ አለያም ዜሮ ለዜሮ በሆነ ውጤት ቢለያይ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ይችል የነበረ ቢሆንም ይህንን ውጤቱን ማስጠበቅ ባለመቻሉ አሳዛኝ ተሸናፊ ለመሆን ተገድዷል።
በተለይ ሁለት ለአንድ መምራቱን ማስጠበቅ እንዲያም ሲል ተጨማሪ ግብ በማከል የበላይነቱን ማረጋገጥ ሲገባው በተከተለው የታክቲክ ስህተት ሁለት አቻ በመውጣቱ በሰው አገር ብዙ ግብ ባስቆጠረ በሚለው ስሌት መሠረት ዛማሌክ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ዕድሉን አስጠብቋል።
ጨዋታው በተጀመረ ገና የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የጊዮርጊስ ተከላካዮችን መዘናጋት ተጠቅሞ የዛማሌኩ ተጫዋች አብዱላዬ ሲሴ ዛማሌኮችን መሪ ያደረገች ግብ አስቆጥሯል።
በእዚህ ወቅት ጊዮርጊሶች የነበራቸው አቋም መልካም በመሆኑ በአሥራ አራተኛው ደቂቃ ላይ ሽመልስ በቀለ ከያሬድ ዝናቡ የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብ ቀይሮ አቻ መሆን ቻሉ። የመሐል ሜዳ የበላይነቱ በእንግዳው ቡድን ቢወሰድባቸውም በ43ኛው ደቂቃ በተከላካዩ አይዛክ ኡሴንዴ አማካኝነት ተጨማሪ ግብ አስቆጥረው በስቴዲየም ይገኝ የነበረውንና ጨዋታውን በየቤቱ ይከታተል የነበረውን ስፖርት አፍቃሪ ማስደሰት ችለዋል።
የመጀመሪያው ግማሽ ጨዋታ ብዙም የኃይል አጨዋወት ያልተስተዋለበት ቢሆንም የዛማሊኩ 25 ቁጥር መሐመድ ኢብራሂም የመጀመሪያውን ቢጫ ካርድ ሲመለከት፣ ሌላኛው የቡድን ጓደኛው ኑሬ ሰዒድ በ44ኛው ደቂቃ የማስጠንቀቂያ ካርድ ተመልክቷል።
ከዕረፍት መልስ ጊዮርጊሶች ጫና ፈጥሮ ከመጫወት ይልቅ ኳስን ወደ ኋላ እየመለሱ ሰዓት ማባከንን በመምረጣቸው የጨዋታ ብልጫ ተወስዶባቸዋል። የጊዮርጊሶቹን ወደ ኋላ አፈግፍገው መጫወት የተመለከቱት የዛማሌክ አሠልጣኝ የበለጠ ጫና ለመፍጠር እንዲቻላቸው የተጫዋች ቅያሬ አካሄዱ። መሐመድ ኢብራሂምን አስወጥተው ዘጠኝ ቁጥሩን መሐመድ ፋቲ አብዱል ሳሚርን በማስገባት ይበልጥ ተጭነው መጫወት ጀመሩ።
በአንፃሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ የአንድ ግብ ብልጫውን አስጠብቆ ለመውጣት አጥቂውን ዮናታን ብርሃኔን በተከላካዩ አሉላ ግርማ በመቀየር ይበልጥ ወደ ኋላ ተመልሶ መጫወት ጀመረ። አሉላ ግርማ ተቀይሮ ከገባ በኋላ አስር ደቂቃ ሳይጫወት ተጐድቶ በመስመር አማካዩ ምንተስኖት አዳነ ተቀይሮ ሊወጣ ችሏል። ኮከቡን አዳነ ግርማን በጉዳት ያጣው ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ መስመሩ ጠፍቶበት ታይቷል።
በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ካይሮ እና አዲስ አበባ ላይ የጊዮርጊሱ ሮበርት ኦዶንካራ መረብ ላይ ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው አብዱላዬ ሲሴ ጊዮርጊሶችን አንገት ያስደፋች በአንፃሩ ግብፃውያንን ወደ ቀጣዩ ዙር ያሳለፈች ግብ አስቆጠረ። በጨዋታው ሙሉ ጊዜውን ምርጥ ሆኖ ያመሸው ብቸኛው ጥቁር የዛማሌክ ተጫዋች የቡርኪናፋሶ ዜጋ አብዱላዬ ሲሴ በድምሩ ሦስት ግቦችን በጊዮርጊስ መረብ ላይ በማሳረፍ ለዛማሌክ ባለውለታ ሆኗል።
በቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል አበባው ቡጣቆና አማካዩ ተስፋዬ አለባቸው ጥሩ ሲንቀሳቀሱ ያመሹ ሲሆን፣ በቀኝ መስመር ተከላካይ በኩል የተሰለፈው ቢያድግልኝ ኤልያስና ወጣቱ ዮናታን ብርሃኔ ብዙ ስህተቶችን ሲሠሩ አምሽተዋል።
ጊዮርጊሶች ሙሉ 45 ደቂቃውን ሰዓት በማባከን ውጤት ለማስጠበቅ መሞከራቸው ደግሞ ሌላው የክለቡ ድክመት ሆኖ ታይቷል። ፈርኦኖቹ ሁለተኛውን ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ጊዮርጊሶች በኡሞድ ኡኩሪ እና ሽመልስ በቀለ አማካይነት ሁለት ያለቀላቸው ዕድሎች አግኝተው የበረኛ ሲሳይ አድርገዋቸዋል። በእነዚህ ስህተቶች የተነሳ ጊዮርጊሶች የማለፍ ዕድላቸውን አበላሽተው ወደ ቀጣዩ ዙር ሳያልፉ ቀሩ።
↧
Sport: ቅዱስ ጊዮርጊስ የራሱን እድል በራሱ አሳልፎ ሰጥቷል (አስተያየት)
↧