(ፍኖተ ነፃነት) አንድነት ፓርቲ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ድርጅት “አኬልዳማ” በሚል ርዕስ ያቀረበው ዶክመንተሪ ፊልም የፓርቲያችንን ስም ያጎደፈ ነው በሚል የከፈተው ክስ በሂደት ላይ እያለ ዶክመንተሪ ፊልሙ በድጋሚ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መታየቱን በማውገዝ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት የፃፉትን የግል አስተያየት ተከትሎ “በፍርድ ቤቱ ላይ ዘለፋ” ሰንዝረዋል በሚል ለእስር መዳረጋቸው ፖለቲካዊ አንድምታ እንዳለው ተጠቆመ፡፡
የአቶ አስራት የህግ ጠበቃ አቶ ተማም አባ ቡልጉ በትላንትናው ዕለት ጥር 30 ቀን 2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት በቅድሚያ የስነ -ስርአት ጥያቄ ለማቅረብ እንዲፈቀድላቸዉ በመጠየቅ የሚከተለዉን የስነ-ስርአት ጥያቄ አቅርበዋል “ደንበኛዬ የተጠሩበት መንገድ ላይ የስነ-ስርአት ጥያቄ አለኝ ፡፡ በችሎት ያልነበሩ ሰውን በሌላ ቦታና መጽሔት በሰጡት አስተያየት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 480 ሊጠየቁ አይገባም” ብለዋል ፡፡ አስከትለውም የተጠቀሰውን አንቀፅ ቃል በቃል በማንበብ በአንቀፁ ሊጠየቁ የሚገባቸው በችሎት ተገኝተው የፍርድ ቤቱን ሂደት ያወኩ እንደሆነ ብቻ መሆኑን በማስመር “የኔን ደንበኛ ከውጪ ተጠርተው መጠየቅ አይችሉም፤ ደንበኛዬ ብዚህ ችሎት ተማጋች አይደሉም በስፍራውም አልነበሩም፤ ጥፋት ሰርተዋል ቢባል እንኳን በዚህ አንቀፅ ሊጠየቁ አይገባም ፡፡” በማለት ተከራክረዋል፡፡
ሆኖም የጠበቃውን መከራከሪያ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ፍርድ ቤቱ ባለመቀበሉ አቶ አስራት ስለተጠሩበት ጉዳይ ጠበቃ ተማም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በምላሻቸውም “ደንበኛዬ ይህን ችሎት በተለየ በሚመለከት አልፃፉም፤ አቶ አስራት የገለፁት አጠቃላይ እውነታን ነው፡፡ ኢህአዴግ ስላቋቋማቸው ፍርድ ቤቶች ነው በአጠቃላይ የጻፉት፡፡ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 29 መሰረት ስለፍርድ ቤትም ሆነ በማንኛውም ጉዳይ ላይ መጻፍም ሆነ አመለካከት የማበጀት መብት አላቸው፡፡” በማለት ምላሻቸውን አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ውሳኔውን በ8፡30 እንደሚያቀርብ ቀጠሮ ሰጠ፡፡
ከሰአት በኋላ በችሎቱ ቀጠሮ መሰረት የቀረቡት አቶ አስራት ጣሴ ባልተጠበቀ ሁኔታ ጥፋተኛ ተብለው ለቅጣት ውሳኔ ከሰባት ቀናት በኋላ እንዲቀርቡ እስከዛውም በእስር እንዲቆዩ ተወስኖባቸዋል፡፡
ከውሳኔው በኋላ ለፍኖተ ነፃነት አስተያየታቸውን እንዲሰጡ የተጠየቁት የአንድነት ፓርቲ ተቀዳሚ ፕሬዝዳንት አቶ ተክሌ በቀለ እስሩ ፖለቲካዊ እንድምታ ሊኖረው እንደሚችል ተናግረው፣ “አቶ አስራት ጣሴ ፓርቲዎችን በማቀራረብ ረገድ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ኢህአዴግን አስደንግጦታል እስሩም የአስራትን አስተዋፅኦ ለመገደብ የተደረገ ይሆናል፡፡” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አያይዘውም በቅርቡ በአንድነት ብሔራዊ ምክር ቤት ና ስራአስፈፃሚ የፓርቲዎችን የውህደት ድርድር እንዲመሩና የፓርቲውን አማካሪ ምክር ቤት እንዲያቋቁሙ ኃላፊነት እንደተሰጣቸውም ተናግረዋል፡፡
ምንጭ፡ ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ