የወጣችሁትን ተራሮች ጥላችሁ
የሮጣችሁትን ሜዳዎች ትታችሁ
አፈር ሳር ቅጠሉ እየናፈቃችሁ
በምኞት በተስፋ ቀን እንዲያልፍላችሁ
በረሀ አቋርጣችሁ የተሰደዳችሁ
ከዘመድ አዝማዱ በመለየታችሁ
ባይተዋርነቱ ናፍቆት ሳያንሳችሁ
በሰው አገር ደግሞ ኑሮ እንዳይከፋችሁ
ያገር ቤቱን እድፍ ከልብ አጥባችሁ
ንጹሕን ልበሱ እናንተም ታጥባችሁ
ተባይ ተከትሎ ጤና እንዳይነሣችሁ።
ዘመንና ትውልድ የማያስተምረው
ተመክሮም ተምሮም እጁን የማያጥበው
ከእድፍ እንዳይጠራ አዚሙ የያዘው
አውቆ የለገመ ይነግሣል መከራው።
ከእግዜር በተሰጠ የማሰብ ፀጋው
ራሱ ንጹሕ ሆኖ ሰው መርዳት ሲገባው
በሽታ ያረባል ወይ በገዛ ሆዱ ሰው?
ነግቶ እሰከሚጠባ አፈር ለሚሆነው
ለቁርሱ ለጉርሱ የሚያደላ ሰው
ከመንደር ቡችዬ በምን ተሻለው?
የወደቀ ሥጋ አፈር ያነሣል
እንዳገኙም መብላት አይቀርም ይጎዳል
ሰው ለነገ ጤናው ቢያስብ ይሻለዋል።
አንጀራ ከመሶብ በእጅ መቁረስን ረስቶ
እንዴት ሰው ይበላል ከመሬት አንሥቶ?
አይሰቀጥጥም ወይ አያሳፍረን?
አይጠዘጥዝም ወይ እንዴት አያመን?
እንዴት ይሸከማል መዥገር ገላችን?
እንዴት በራስ ተባይ ይበከል ባህላችን?
በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን
በእንዝህላልነት ኮሶ ተጣብቶን
የሚያሽር መድሐኒት መምረጥ አቃተን።
በአንድ አምላክ ሥር ሆነን በሰብአዊነት
እንድንፈቃቀር ተሰጥቶን እርስት
ታሪካችን ሆኖ የሰው ልጅ ሥርየት
ደም መጣጭ የሆነ የጉያ ጠላት
ምነው ማምለካችን ጥቃቅን ጣኦት?
በሽታ ካልጠፋ ከየመንደራችን
ሰላም የት ይገኛል በመካከላችን።?
በሽታ ከረባ ምን ሰላም ያገኛል?
ባገር ላይ ተስቦ ለጥፋት ይነግሣል፤
እየተላለፈ ሁሉንም ይፈጃል።
በወረርሽኝ ገብቶ እየተስፋፋብን
ያገር ቤት በሽታ ደግሞ ተከትሎን
ባለንበት ሁሉ እንዳያጠቃን
ገና ያልታመምነው ተራ እስከሚደርሰን
መጠበቅ ሳንሻ ዳግመኛ ሰንፈን
የዘር ነው ተብሎም ሳይተረትብን
እንደሌላው ዓለም እኛም አስተውለን
ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም ተንብየን
ጤናማ ሆድና ሳንባ ልብ ይዘን
ዞሮ መግቢያችን ቤት እንዲፀዳልን
እንከላከለው እናጥፋው ተባብረን፤
እኛ ለኛው እንሁን ተፈጠሮ እንደሰጠን፤
ሰላምና ጤና እንዲሰፍንልን።
“መልካም አስጀምሮ እንዲያስጨርሰን”
“አልፋና ኦሜጋን ተስፋ አድርገን”