“ሁሉም ከህግ አያመልጡምና ዜጎች መረጃ በመሰብሰብ የቤት ስራችሁን ስሩ” ኦባንግ ሜቶ
ኦሞት ኦባንግ በዓለም ዓቀፍ ተቋማት ለፍርድ እንዲቀርቡ እየታደኑ ነው
ሰሞኑን አገር ጥለው መኮብለላቸው የተደመጠው የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦሞት ኦባንግ በተለያዩ የዓለም ዓቀፍ ተቋማት ክትትል እየተደረገባቸው እንደሆነ ታወቀ። የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ /አኢጋን/ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ ፍትህ የተዛባባቸው ዜጎች ሁሉ መረጃ በማሰባሰብና ለድርጅታቸው በመላክ የዜግነት የቤት ስራቸውን እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል። አቶ ኦሞትን ፍትህ ደጅ ለማቆም ከ19 ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በኅብረት እየሰሩ መሆናቸውም አመልክተዋል። በሌላም በኩል ኢህአዴግም “ነገር ሳይበላሽ” እያደናቸው እንደሆነ ተሰምቷል፡፡
በ2003 በጅምላ ለተጨፈጨፉና በሺህ ለሚቆጠሩ የአኙዋክ ተወላጆች መሰደድ ከመለስ ቀጥሎ ግንባር ቀደም ተጠያቂ የሚባሉት አቶ ኦሞት፤ ሳምንት በፈጀ ግምገማ ከክልሉ ሊቀመንበርነታቸው መነሳታቸውና የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው መመደባቸው ይታወሳል። “እውነተኛው ወያኔ” እየተባሉ የሚጠሩት አቶ ኦሞት ምንም እንኳ በሚኒስትርነት ደረጃ ቢመደቡም በሙስና ተወንጅለው እንደሚታሰሩ ጎልጉል ምንጮቹን ጠቅሶ መዘገቡ አይዘነጋም።
በሰኔ 10፤2005 ዓም (June 17, 2013) የጎልጉል ዘገባ ላይ እንደተጠቀሰው ከ83 ሚሊዮን ብር በላይ አላግባብ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን፣ እንዲሁም በክልሉ የሚፈጸሙትን የተጭበረበሩ የበጀት አፈጻጸሞችንና ምዝበራዎችን የሚያጋልጡ ሰነዶችን በሚስጥር ተደራጅቶ ለኢህአዴግ የድርጅት ቢሮ ቀርቦ ነበር። የክልሉ የፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ኢሬሳ ከፍተኛ ምስጢር ያላቸውን ሰነዶች በመያዝ ከመታሰራቸው በፊት መሰወራቸውን የጠቆመው ዘገባ “የቢሮ ሃላፊው ይዘው የተሰወሩት መረጃ አቶ ኦሞት የፈረሙባቸው ከፍተኛ የገንዘብ ሰነዶችና ሙስና የተከናወነባቸው የኮንስትራክሽንና የተለያዩ መረጃዎች ይፋ የሚያደርጉ ነበሩ። በወቅቱ “መረጃዎቹ አንድ ቀን ህዝብ ፍርዱን ይሰጥ ዘንድ ይፋ ይሆናሉ” ተብሎም ነበር። የመረጃ ምንጫቸውን ባይጠቅሱም አቶ ኦባንግ “ኦሞትን በተመለከተ ከበቂ በላይ መረጃ አለን፤ ህግ ፊት እናቀርበዋለን፤ በንጹን ደም ተጨማልቆና ህዝብ ላይ ግፍ ፈጽሞ መሰወር አይቻልም” በማለት በስልክ ለጎልጉል ተናግረዋል። አቶ ተስፋዬ ኢሬሳ በድንገት ምሳ እየተመገቡ ከመርዝ ጋር በተያያዘ ህይወታቸው በድንገት ማለፉ ይታወሳል።
ከታህሳስ 23 ቀን 2004 ዓ ም ጀምሮ ሟቹ አቶ መለስ በላኳቸው አስገምጋሚዎች ለሳምንት በተካሄደ አውጫጪኝ አቶ ኦሞት “የአኙዋክ ተወላጆችን አስጨፍጭፈሃል” የሚል መነሻውና ዓላማው ግልጽ ያልሆነ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። በወቅቱ ግምገማው ላይ የነበሩ እንዳሉት አቶ ኦሞት “እኔ በዚህ ጉዳይ ተጠያቂ ከሆንኩ መሳሪያና ወታደር የሰጠኝ መለስም ይታሰራል” በማለት መልስ ሰጥተው ነበር።
በወቅቱ አቶ ኦባንግ ሜቶ የሚመሩት ድርጅት /አኢጋን/ አቶ መለስን በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ችሎት ተጠያቂ ለማድረግ ያቀረበው ማመልከቻ ተቀባይነት ያገኘበትና አቶ መለስ ላይ ክስ እንዲመሰረት ውሳኔ የተደረሰበት ዜና የተሰማበት ነበር። ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ የጋምቤላ ምንጮች “አቶ መለስ አቶ ኦሞትን በጭፍጨፋው ተጠያቂ በማድረግና ርምጃ በመውሰድ ራሳቸውን ጲላጦስ ለማድረግ የወጠኑት አካሄድ እንደሆነ የፌዴራል ሰዎች ነግረውናል። ኦሞትም በሙስና በዘረጋው መዋቅር እስከላይ ድረስ ዘመድና ተቆርቋሪ ስላበጀ መረጃው ደርሶት ነበር” ብለዋል። /በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የተመሰረተው ክስ መለስ ቢሞቱም እስካሁን ክፍት ነው/
በሌላም በኩል ወቅቱ በክልሉ ኢህአዴግ ለልማት በሚሰጠው ርዳታ ዜጎችን ለማፈንና ረግጦ ለመግዛት የሚያስችለውን ሃይል ያደራጅበታል በሚል ተቆርቋሪዎች መረጃ አስደግፈው ባቀረቡት ክስ ዓለም ባንክ አጣሪ የላከበት ነበር። ከዚሁ ጋር ተያይዞ መሬታቸውን፣ የትውልድ ቀያቸውን በአንጋቾች የተነጠቁ ምስኪን ዜጎች ድምጽ ዓለም አቀፍ ትኩረት አግኝቶ ኢህአዴግን ክፉኛ የተፈታተነበት ነበር። ለዚህ ይመስላል ኢህአዴግ በግምገማ በርካታ የክልሉን ሃላፊዎች ወረዳ ድረስ በመዝለቅ በሙስና ሰበብ ሲያባርርና ሲያስር፣ አቶ ኦሞትን ወደ ፌዴራል በማዛወር በቅርብ ይከታተላቸው ነበር። አቶ ኦሞት ወደ ፌዴራል ሲዛወሩ “የቤንሻንጉል ጉምዝ ፕሬዚዳንት በነበሩት አቶ ያረጋል አይሸሹ ላይ የተደረገው ይፈጸምባቸዋል” ተብሎ አስቀድሞ ተተንብዮ ነበር።
ለአብነት ከላይ በተዘረዘሩት መነሻዎችና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ሳቢያ የአቶ ኦሞትና የህወሃት ግንኙነት ማክተሙን የሚናገሩት ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ክፍሎች፣ “ቀደም ሲል ህወሃትን ሲያገለግሉ ኖረው መጨረሻቸው እስር እንደሆነው አራት የቀድሞ የክልሉ መሪዎች፣ ወይም እንደ አምስተኛው ፕሬዚዳንት አቶ ኦኬሎ አኳይ ስደት እጣ ፈንታቸው ይሆናል” የሚል ቅድመ ትንበያ ነበር።
አቶ ኦኬሎ አኳይ በአኙዋክ ተወላጆች ላይ የተፈጸመውን የጅምላ ጭፍጨፋ አስመልክቶ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ክልሉን ወክለው የተዛባ መረጃ እንዲሰጡ ታዘው ነበር። በአቶ አባይ ጸሃዬና ገብረአብ በርናባስ መመሪያ መሰረት ግጭቱ በጎሳ ላይ የተመረኮዘ የርስ በርስ እንደሆነ፣ በግጭቱ 59 ሰዎች ብቻ ሲሞቱ አንድ ቤት መቃጠሉን እንዲናገሩ የተሰጣቸውን መመሪያ ያልተቀበሉት አቶ ኦኬሎ ህይወታቸው አደጋ ላይ በመውደቁ አገር ጥለው መሰደዳቸው ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ በተደጋጋሚ ገልጸው ነበር። ይሁን እንጂ አቶ ኦኬሎ አኳይ በስደት ሆነው በይፋ በዚህ ጉዳይ መግለጫ ለመስጠት አለመድፈራቸው ብዙዎችን ግራ ያጋባ ጉዳይ ሆኗል።
ኦሞት የት ናቸው?
አቶ ኦሞት የክልሉ የደህንነት ሃላፊና ፖሊስ ኮሚሽነር ሆነው ባገለገሉበት ወቅት ፍጹም ታማኝ ስለነበሩ በ2005 የተሰጣቸው የክልል መሪነት ስልጣን ለህወሃት ለሰሩት ውለታ የተከፈለ ወሮታ እንደሆነ ተደርጎ ነው የሚወሰደው። በዚሁ መነሻ ይመስላል አብዛኛው የጋምቤላ ተወላጆች ለአቶ ኦሞት የከፋ ጥላቻ እንደነበራቸው የሚናገሩ ክልሉ ተወላጆች፣ ኦሞት ከአገር ኮበለሉ መባሉ አያስገርማቸውም።
አሁን ጥያቄው ኦሞት ከኢህአዴግ አፍንጫ ስር እንዴት አመለጡ? አሁን የት ናቸው? መጪው እጣ ፈንታቸውስ? የሚለው ነው። አዲስ አድማስ ባለፈው ቅዳሜ እትሙ አቶ ኦሞትን የግምባር ዜና አድርጎ ሲያቀርብ አገር ጥለው መኮብለላቸውን የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ማረጋገጣቸውን አስነብቧል። አቶ ኦባንግ ሜቶ ለጎልጉል እንደገለጹት አቶ ኦሞት ከሁለት ወር በፊት ለስልጠና አውሮፓ ሲመጡ በነበራቸው ቪዛ ከሁለት ሳምንት በፊት ዓርብ ቀን አገር ጥለው እንደወጡ መረጃው አላቸው።
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ /አኢጋን/ ከ19 የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ እየሰሩ መሆናቸውን ያመለከቱት አቶ ኦባንግ ሜቶ “ኦሞት መለስ በህይወት እያለ ቢኮበልል መልካም ነበር። አሁን ከኦሞት የምንፈልገው ችሎት ፊት በወገኖቹ ላይና በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ፣ ቶርቸር፣ እስር፣ ዝርፊያ፣ የመሬት ንጥቂያ፣ ወዘተ አስመልክቶ እንዲናዘዝ ነው” ብለዋል። ኮብላዩ አቶ ኦሞት የት እንደሚገኙ ተጠይቀው “አሁን እዚህ ነው የሚባልበት ደረጃ ላይ አይደለንም። ግን መሰወር የሚችል አይመስለኝም። በደም ተጨማልቆ በስደት ተበዳይ መስሎ መኖር አይቻልም። የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ከመለስ ጋር በተመሰረተው ክስ ላይ ኦሞት የተካተተ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። እኛ እንኳ ዝም ብንል ፍትህ በርዋን አትዘጋም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ጎልጉል ባሰባሰበው መረጃ አቶ ኦሞት አገር ጥለው የወጡት ከሁለት ሳምንት በፊት ሲሆን አንድ ሳምንት ቢዘገዩ ኖሮ እስር ቤት ይገቡ ነበር። አስቀድሞ በደረሳቸው መረጃ መሰረት አቶ ኦሞትን እስር ቤት እንዲወረወሩ የሚያዘው የአስር ማዘዣ የሚቆረጥበት ግምገማ ተዘጋጅቶ ነበር። እሳቸው አስቀድመው አገር ጥለው በመውጣታቸው ግምገማው ተስተጓጉሏል። ግምገማው የዓለም ባንክ አጣሪ ቡድን በትላንትናው ዕለት ኢትዮጵያ ሲገባ በሙስናና በሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ ኢህአዴግ ርምጃ በመውሰድ ዝግጅት አጠናቆ ለመጠበቅ የሚረዳው ነበር። ግን አልሆነም።
በጋምቤላ በኢቨስትመንት ስም መሬት ወስደው ከሚሰሩት መካከል 70 ከመቶ የሚሆኑት የቀድሞ የህወሃት ታጋዮችና የትግራይ ተወላጆች መሆናቸው አቶ ኦሞት የሚደረግባቸውን ክትትል አልፈው አገር ሊወጡ እንደቻሉ ግምት አለ። አሁን “ባለሃብት” የሚባሉት እነዚህ ክፍሎች ባላቸው መዋቅር ሳቢያ አቶ ኦሞትን ሊታደጓቸው እንደሚችሉ ከግምት በላይ የሚናገሩ አሉ።
አቶ ኦሞት ሆላንድ ገብተዋል የሚሉም አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ አውሮፓ ሊገቡ አይችሉም በማለት ግምቱን የሚያጣጥሉ አሉ። እነዚህ ክፍሎች ወደ ማሌዢያ ሄደዋል የሚለውን ምንጭ ይደግፋሉ። በስፋት እንደሚነገረው ከሆነ አቶ ኦሞት ኤዢያ እንደሚሄዱ የሚያጠናክሩ ምልክቶች አሉ። አብዛኛው የኢህአዴግ ባለስልጣኖች በማሌዢያ ባንኮች ገንዘብ አላቸው። አቶ ኦሞትም በተመሳሳይ የማሌዢያ ባንክ ተጠቃሚ ናቸው ተብሎ እንደሚገመት የሚቀርቧቸው ይናገራሉ። በተመሳሳይ በኢንቨስትመንት ስም የተወዳጇቸው ባለሃብቶች በኤዢያ ከለላ ሊሆኗቸው ስለሚችሉ የመጀመሪያ ምርጫቸው ኤዢያ እንደሚሆን ይስማማሉ።
ለጎልጉል ማንነታቸውን ሳይገልጹ መረጃ የሰጡ የኢህአዴግ ሰው እንዳሉት “ኦሞት ርቆ አልሄደም ይያዝል” በማለት ግምታቸውን ሰጥተዋል። ጉዳዩን በቅርብ እንደሚከታተሉ የገለጹት እኚህ ሰው “ኦሞት ብዙ ጉዳዮችን እንዳያበለሽ ጥንቃቄ ሲደረግ ነበር። እንዴት ለጊዜውም ቢሆን ተሰወረ?” የሚለው መነጋገሪያ መሆኑን ግን አልሸሸጉም። ኦሞት በወቅቱ የፈጸሙትን ከ400 በላይ የአኙዋኮችን ጭፍጨፋ፣ የተሳተፉበትን ሙስና፣ የመሬት ነጠቃ፣ ግድያ፣ ወዘተ የወንጀል ምስጢር በማውጣት ኢህአዴግን አሳጥተው ፍርድ እንዲቀልላቸው መደራደሪያ ከማድረጋቸው በፊት ኢህአዴግ የራሱ አደን አጠናክሮ እንደሚገኝ ተጨማሪ ዘገባዎች አሉ፡፡
አቶ ኦባንግ ሜቶ የኦሞት መሰወር አያስጨንቅም ባይ ናቸው። ኦሞትን ፍትህ አሳድዳ ትይዘዋለች የሚሉት አቶ ኦባንግ ትኩረታቸው ወንጀል የተፈጸመባቸው በሙሉ መረጃ በመሰብሰብና ወደ ጋራ ንቅናቄው በመላክ እንዲተባበሩ የመነሳሳታቸው ጉዳይ ላይ ነው። ህወሃቶች ወንጀል አሰርተው፣ መጨረሻ ላይ ፍትህ ወዳድ ለመምሰል በወንጀል ያጨማለቋቸውን ሰዎች ህግ ፊት አቅርበው እንደሚያስፈርዱባቸው ያመለከቱት አቶ ኦባንግ “ሌሎች ከዚህና ከቀድሞው ተሞክሮ ተማሩ። ኦሞትን ፍትህ አደባባይ ለማውጣት የሚሰራው ስራ ወንጀለኞችን ለመፋረድ የምናደርገውን ትግል አንድ ርምጃ ያሳድገዋል። እንደ ኦሞት ያሉት ወንጀለኞች ካሉበት ይለቀማሉ። ይህንን ማድረግ አቅም አለን። በደም ተጨማልቆ በስደት መኖር አይቻልም። ሌሎችም ካሁኑ ንስሃ ግቡ፤ ህብረተሰባችሁን አስቀድሙ” ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ህወሃትም ሆነ ኢህአዴግ በራቸውን መክፈታቸው ወይም ለውጥ እንዲመጣ እንዲፈቅዱ የሚገደዱበት ዘመን መቃረቡን ያመለከቱት አቶ ኦባንግ “ነጻ ውጡና ህዝባችሁን ነጻ አውጡ፣ አዲሲቷ ኢትዮጵያ ለወንጀለኞች ቦታ የላትም፣ ትፋረዳቸዋለች” ሲሉ በድጋሚ ህዝብ በወንጀለኞች ላይ መረጃ በማሰባሰብ የቤት ስራውን በወጉ እንዲሰራ ጠይቀዋል።
Please click the link to read the entire report http://www.goolgule.com/the-hunt-for-omot-obang-olum-continues
I am appealing to each of you to forward it to all your friends. If you do, you will not just be giving a voice to our beautiful people, but you would be doing justice to our humanity. Knowing the truth is overcoming the first obstacle to freedom!
Thanks so much for your never-ending support. Don’t give up. Keep your focus on the bigger picture and reach out to others and listen! Care about those who are suffering. Think about our family of Ethiopians and humanity throughout the world—they are YOU! There is no “us” or “them.” This is at the heart of the SMNE.
For media enquiries, more information including interview requests, contact Mr. Obang Metho, Executive Director of the SMNE. Email: Obang@solidaritymovement.org. SMNE ( www.solidaritymovement.org ), is a non-political and non-violent social justice movement of diverse people that advocates for freedom, justice, good governance and upholding the civil, human and economic rights of the people of Ethiopia, without regard to ethnicity, religion, political affiliation or other differences. The SMNE believes a more open, transparent and competitive market economy, supported by viable institutions and reasonable protections, which provides equal opportunity, will result in greater prosperity to the people rather than keeping it in the hands of a few political elites.