እየተካረረ የመጣው የሚኒሶታው ደብረሰላም መድሃኔዓለም ቤ/ክ ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት ማምራቱ ተገለጸ። ዛሬ ጃንዋሪ 2 ቀን 2014 ዓ.ም እንደወትሮው ምዕመናን ከቅዳሴ በኋላ ስብከት ሳይሰማ የጠበቆች መልዕክት ብቻ ተሰምቶ ህዝቡ ወደ እቤቱ ተመልሷል።
ባለፈው ሳምንት በቤተክርስቲያኑ በሁለቱም ወገኖች ማለትም “ወደ ሃገር ቤቱ ሲኖዶስ መጠቃለል አለብን” በሚለው እና “በሃገር ቤት እና በውጭ ያሉት ሲኖዶሶች አንድነት እስኪፈጥሩ ድረስ በገለልተኝነታችን መቆየት አለብን” በሚሉት ወገኖች መካከል የተነሳው አለመደማመጥ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አተካሮ ፈጥሮ እንደነበር የተለያዩ ሰዎች በዘ-ሐበሻ ድረገጽ ላይ በጻፏቸው አስተያየቶች ለንባብ መብቃቱ ይታወሳል።
ዲሴምበር 15 ቀን 2013 በሚኒሶታው ደብረሰላም ቤ/ክ በተጠራ ጠቅላላ ጉባዔ ቤተክርስቲያኑ በነበረበት በገለልተኛነቱ እንዲቆይ መወሰኑ የሚታወስ ሲሆን፤ ወደ ሃገር ቤት ሲኖዶስ እንዲጠቃለል የሚፈልገው ወገን “ምርጫው ኮረም አልሞላም፤ ውሳኔውም ህጋዊ ስላለሆነ አንቀበልም” በማለት አለመግባባቱ እየተካረረ መምጣቱን ሁለቱም ወገኖች በዘ-ሐበሻ መድረክ ላይ በጻፏቸው አስተያየቶች መረዳት ይቻላል። ይህን ተከትሎም የቦርዱ ሊቀመንበር “የቦርድ አባላቱ የሕዝቡን ውሳኔ አናስፈጽምም በማለታቸው ጠቅላላ ጉባኤ እስከሚጠራ ድረስ ማንኛውንም ስብሰባና ቦርዱን ማገዳቸውን” በቤተመቅደሱ ውስጥ የተናገሩ ሲሆን ባለፈው እሁድ ቦርዱ አዲስ የቦርድ ሊቀመንበር በመምረጥ የቀድሞው ሊቀመንበርን በድምጽ ብልጫ ከስልጣናቸው አውርጃለሁ ማለቱና ይህም ደብዳቤ በዘ-ሐበሻ መነበቡ አይዘነጋም።
ከሁለቱም ወገኖች ያሉ ጠበቆች ዛሬ ከቅዳሴ በኋላ ለሕዝቡ ከዚህ በፊት ከቅዳሴ በኋላ ይደረጉ የነበሩ እንስቃሴዎች እንዳይደረጉ መታገዱን የገለጹ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ፍርድ ቤት የቀድሞውን ሊቀመንበርም ሆነ፤ አዲሱን በቦርድ የተሾሙትን ሊቀመንበር እንደማይቀበል፤ ቦርዱ ምንም ዓይነት ስብሰባ እንዳያደርግ መከለክሉን፤ ሁሉም ውሳኔ በፍርድ ቤት እስኪሰጥ ድረስ የቤተክርስቲያኑ አካውንት ውስጥ ያለ ገንዘብ እንዲታገድ መደረጉን ለምዕመናኑ ገልጸዋል። በዚህም መሠረት ዛሬ ስርዓተ ቅዳሴ የተካሄደ ሲሆን፤ እንደወትሮው ከቅዳሴ በኋላ ስብከት ሳይሰጥ ምእመኑ ወደ ቤቱ መመለሱን በሥፍራው የነበሩ የዘ-ሐበሻ ዘጋቢዎች ገልጸዋል። ሆኖም ግን ለቤተክርስቲያኒቱ ቆሞስ አባ ኃይለሚካኤል ከቅዳሴ በኋላ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴዎች እንዳይደረጉ የፍርድ ቤት ወረቀት የደረሳቸው ቢሆንም ሕዝቡ ከተበተነ በኋላ መዘምራኑ መዝሙር ዘምረው መለያየታቸውን የደረሰን መረጃ ጨምሮ አመልክቷል።
የደብረሰላም መድሃኔዓለም ቤ/ክ ጉዳይ የፊታችን ማክሰኞ ወይም ረቡዕ በፍርድ ቤት መታየት እንደሚጀመር የሚጠበቅ ሲሆን ዘ-ሐበሻ ጉዳዩን ተከታትላ ለሕዝብ ለማድረስ ትሞክራለች።
በአሁኑ ወቅት በሚኒሶታው ደብረሰላም መድሃኔዓለም ቤ/ክ የባንክ አካውንት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር እንዳለ በተደጋጋሚ የተገለጸና በሕዝብ መነጋገሪያ የሆነ ጉዳይ ሆኗል።
ዘ-ሐበሻ ከዚህ ቀደም በሁለቱም ወገኖች ላሉ ኢትዮጵያውያን ሰላም እንዲፈጥሩ እና ቁጭ ብለው በመነጋገር ችግሩን ሊፈቱት እንደሚገባ ስትመክር የቆየች ቢሆንም ጉዳዩ እየተካረረ ሄዶ እዚህ መድረሱ ጉዳዩን ከውጭ ሆነው ለሚከታተሉ አሳዛኝ ክስተት ሆኗል ተብሏል።