Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

በጎንደር ሰማያዊ ፓርቲ ለድንበር መከበር፤ የቅማንት ማህበረሰብ የማንነት መብቱ እንዲከበር በተመሳሳይ ቀን ሰልፍ ሊወጡ ነው

$
0
0

“በጥይት ትመታላችሁ፣ መትረየስ ጠምደን እንፈጃችኋለን እያሉ እያስፈራሩን ነው”

- የቅማንት ማህበረሰብ የማንነት መብት ጥያቄ ሰልፍ አስተባባሪዎች

በዘሪሁን ሙሉጌታ (የሰንደቅ ጋዜጣ ሪፖርተር)

በመጪው እሁድ ጥር 25 ቀን 2006 ዓ.ም በጎንደር ከተማ ሰማያዊ ፓርቲ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር መካከለል ጉዳይ ለሕዝብ ግልፅ አለመሆኑን በመቃወም ሰልፍ የጠራ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ቀን በጎንደር ዙሪያ የሚኖሩ የቅማንት ብሔረሰብ አባላት ማንነታችን አልተከበረም በሚል ሕገ-መንግስታዊ ጥያቄአቸውን ለማቅረብ የሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄ አቅርበዋል።

የጎንደር ከተማ (ፎቶ ፋይል)

የጎንደር ከተማ (ፎቶ ፋይል)

ለጎንደር ከተማ አስተዳደር ሁለቱም ወገኖች የሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄ ቢያቀርቡም፤ ለሁለቱም ወገኖች ለሰላማዊ ሰልፉ መካሄድ ማረጋገጫ አለማግኘታቸውን እየተናገሩ ነው። ሰማያዊ ፓርቲ ሰልፉን ለማስተባበር ወደስፍራው የላከውን የፓርቲውን አመራር ጨምሮ ሌሎች የፓርቲው አስተባባሪዎች ታስረው መፈታታቸውን ገልጿል። ሆኖም ሰልፉን ለማካሄድና የማሳወቂያ ደብዳቤ ለከተማው አስተዳደር ቢያቀርቡም አስተዳደሩ ደብዳቤውን ባለመቀበሉ ጠረጴዛ ላይ ትተው መውጣታቸውን የፓርቲው ሕዝብ ግንኙነት አስታውቋል። እስካሁን የከተማው አስተዳደር ምንም አይነት ምላሽ ያልሰጠ በመሆኑ ሰላማዊ ሰልፉ እንደተፈቀደ በመቁጠር ሰልፉን ለማካሄድ በዛሬው ዕለት 12 የአመራር አባላት ያሉት ቡድን ወደ ጎንደር እንደሚሄድ አስታውቋል።

በሌላ በኩል በበርካታ ጊዜያት የቅማንት ብሔረሰብ የቋንቋ፣ የባህልና የማንነት መብቱ አልተጠበቀም የሚሉ ወገኖች በተመሳሳይ ቀን (ጥር 25 ቀን 2006 ዓ.ም) ጥያቄአቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ለመጠየቅ ሰልፍ መጥራታቸውን የቅማንት ብሔረሰብ የማንነት የራስ አስተዳደር ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ አበራ አለማየሁ ለሰንደቅ ጋዜጣ አስታውቀዋል።

የኮሚቴው ሊቀመንበር የጎንደር ከተማ በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር ጥረት ማድረጋቸውን ገልፀዋል። አስተዳደሩም የእነሱ ጥያቄ ሕገ-መንግስታዊ እንጂ የፖለቲካ አይደለም። ነገር ግን እናንተ ጥያቄ ካቀረባችሁ በኋላ ሰማያዊ ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ ጠይቋል በማለት አጀንዳችሁ ተመሳሳይ ነው የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው አጀንዳችን የተለያየ መሆኑን ብንገልጽም፤ “በጥይት ትመታላችሁ፣ መትረየስ ጠምደን እንፈጃችኋለን” እያሉ እያስፈራሩን ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ጥር 4 ቀን 2006 ዓ.ም በጅልጋ ወረዳ አይከል ከተማ ላይ ከ70 ሺህ በላይ ሕዝብ የተገኘበት ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸውን ያስታወሱት አቶ አበራ፤ በዚያን ጊዜም “በመትረየስ እንፈጃችኋለን” ቢሉንም ሕዝቡ ነቅሎ መውጣቱን ተናግረዋል። አሁንም በጎንደር ከተማ ከሰማያዊ ፓርቲ ቀድመው ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ቢዘጋጁም በየቀበሌው ሕዝቡን በስብሰባ በመጥራት ወደ ሰልፉ እንዳይወጡ ቅስቀሳ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም ያለውን ጫና ተቀቁመው ሰልፉን ለማካሄድ ወደኋላ እንደማይመለሱ ተናግረዋል።
እንደ አቶ አበራ ገለፃ፤ እነሱ የሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄ ተቀባይነት ያላገኘው በተመሳሳይ ቀን ሰማያዊ ፓርቲ በሌላ አጀንዳ ሰልፍ በመጥራቱ እኛም ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር አብረን እንደምንሰራ ተደርጎ ታይቶብናል ብለዋል። ይሁን እንጂ የእኛ ጥያቄ ሕገ-መንግስታዊ እንጂ የፖለቲካ ወይም የድንበር አይደለም ብለዋል።

የቅማንት ብሔረሰብ በአማራ ክልል በጎንደር የተለያዩ ወረዳዎች የሚኖር ሕዝብ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አበራ፤ የሕዝብ ብዛቱም አንድ ሚሊዮን እንደሚሆን፣ የቋንቋው ተናጋሪዎችም ከ20 ሺህ በላይ እንደሚሆኑ ገልፀው፤ ሕዝቡ እራሱን በቻለ ዞን ለመተዳደር ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል ብለዋል። በያዝነው ዓመት መስከረም ወር ጥያቄውን ለፌዴሬሽን ም/ቤት አቅርቦ ውሳኔ አለማግኘቱንም ተናግረዋል። የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ጌትነት አማረን በስልክ አግኝተን በዚሁ ጉዳይ ላይ የአስተዳደራቸውን አቋም እንዲያብራሩልን ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>