ከሥርጉተ ሥላሴ
ይድረስ ብለናል ከወደ ሲዊዘርላንድ ዙሪክ እኔና ብዕሬ ለሞገደኛው ብዕረ ተክሌ ….
ጭራሽ ተበዳይ ብዙኃኑ ተወቃሽ ሆነ? ይገርም! ጡር የሚባል ነገር አለ። በፈጠረህ ጡር ፍራ የስሞተኛው ብዕር …..
እንደምን አለህ ሞገደኛው ተክሌ? ደህና ነህ ወይ? ጠፍተህብኝ ጭንቅ ብዬ ሳለ የወጣት ጃዋር ዶክተሪን በመቃወም ከሰሞናቱ ፊርማ የማሰባሰብ ዘመቻን ተከትሎ ብዕርህን ብቅ አደረገችህና ደስ አለኝ። የእውነት ናፍቆትህ ግድል አድርጎኝ ነበር። እኔማ የኦሮሞና የአምራ ትዳር ፈርሶ የነገ ሀገር ተረካቢዎች እንዲበተኑ፤ እንዲሁም ከሁለት ብሄረሰብ የተወለዱ ወገኖች ጥግ አጥተው ሜዳ አደር እንዲሆኑ ሲታወጅባቸው፤ ያው በትንሹም በትልቁም የምታብጠለጥለው ብሄረሰብ ቁምጥና መላያው ተደርጎ ሲቀጠቀጥ፤ አንድ ታላቅ ማህበረሰብ ሞትና መፈናቀል ሲታወጅበት፤ መዲናች ተለቃ የንጹኃን አንድትሆን ሰባት አንቀፆች ያሉት ድንጋጌዎች ሲተረተረ፤ ኃያሉ ሚኒሊክ ሃውልታቸው ፈርሶ ፈረሱ ወደ ኦሮሚያ ሲጫን፤ ክብራቸው ትብያ ሲለብስ፤ የወሎይቱ ወርቂቱ አፄ ቴውድሮሰን አነጣጥራ የገደለች ስለመኋኗ ሲነገርላት፤ አፄ የኋንስም ጥላሸት ሲቀቡ፤ ተዋህዶ ተዘቅዝቆ ሲንጠለጠል፤ ብዕርህ ሃግ ትላለች ብዬ ሳሰብ እቴ እሷ አብራ ከበሮ ስትደልቅ ሰነባብታ ይሁን አይታወቅም፤ ብቻ ከመሼ ብቅ አለች። እኔማ እህትህ ሰርግና መልሱ፤ ቅልቅሉ አላዳርሳት ብሎ ይሁን ጣል ጣል ያደረገችን በጤና? ብዬ ነበር።
አሁን መልካም ሆነ ዕድሜ ለዘሃበሻ ከወደ ቶረንቶ ብቅ ማለታችሁ አስደሰተኝ። እጅም ነሳን ለጥ ብለን አደግድገን።
ግን ደህና ናችሁ? ብርዱና በረዶው እናንተን አልደረሰባችሁም …. ሞቅ ብሏችኋል „የፍቅር ጉዞ መደናቀፍ በደሌ ማዕቀብ እያጣጠምን ነው … ብሎን ነበር ወጣቱ …. ከፌስ ቡኩ ወደ ዘሀበሻ በተሻጋገረው ቅምሻ …
እኔ እንኳን ካንተው ከወዳጄ ጋር እንጂ በዛ ዙሪያ ምን መስራት እንዳለብኝ ስለማውቅ ቅጭጭም አይለኝ …. ቡጢ መግጠም አያስፈልግም። ሙያ በልብ … ይላል የጎሪጥ የምታዬው የጎንደር ሰው …
ለነገሩ ጎንደር ላይ ሆነ ጎጃም ላይ ስለነበረው የኦሮሞ ወራራስ ምን ይሰማህ ይሆን? የወተር የበደኖ የአርባጉጉ የጉራፈረዳ ጎሽ! ነው ወይንስ ሰቅጠጥ …. መሆን የማንችለውን የፈለገ ጫና ቢፈጠረም ማንነታችን ገላጫችን ነው – ኢትዮጵያዊነት። መወረድ የአባት አይደለም። ተግባባን? …. ጎሳ ከቤተሰብ ቀጥሎ ያለ ያላደገ የማህበረሰብ እስቤ በመሆኑ በግሌ ለእድሌም አላሳዬው። ሁኜም አላወቅም። መሆንም አልችልም። ሌላ የሚያርመጠምጠኝ መጠነ ሰፊ ሀገራዊ ጉዳይ አለብኝ። የሆነ ሆኖ ብዕራችን ጉጉስ ትጋጠም ዘንድ ወደደኩ። ደስ ስለምትለኝ ….
ዘሃበሻ ላይ ከአንተ ጹሑፍ ሥር የተሰጡ አስተያዬቶችን ሳነብ ደግሞ ጎሽ! ሞገደኛው ተብለኃል። ሜጫው አንተን ዘለል
አድርጎ ሽልማት ቢጤ ልታገኝ ስበሰባ ላይ መቀመጣቸውን አነበብኩ። ድምጽም ሰጡህ። ለነገሩ ወገኖቼ እውነት ብለዋል። እንዲህ ሁሉንም ፍላጎት በእኩልነት የሚስተናገድ ሚዲያን ነፃ ሊያሰኘው ስለመቻሉ በተግባር መገኘቱ ዘሃበሻ እኔም ምርቃቴ ይድረሳቸው እላለሁ። እኔንስ እኩል አድርገው ባለወግ አድርገውኝ የለ። ይባረኩ። በአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚፈስ ወንዝ ውበቱ እንብዛም ነው … ህግጋትን ካልተላለፈ …. ትውልድን ለመናድ ካልተንጠራራ፤ ለዬት ያሉ አወያይ ሃሳቦች ጉልበት ይሰጣሉ። ቀዳዳም ይሸፍናሉ፤ ያልታዬትን ያስጎበኛሉ። እራስን ያርቃሉ። እንዲህም ያነጋግራሉ …
አንድ ትውስታ አለችኝ። ልጅ ተክሌ አንተ የኢሳት መደበኛ አዘጋጅ በነበርክበት ጊዜ አብዝቼ አደምጠው የነበረው „እፍታና የእሁድ ወግ„ ዛሬ የለሁበትም። ስለምን? አንተ በነበርክ ጊዜ የራስህን ዕይታ ይዘህ ከች ትልና አንተና ሲሳይ ማህል ዳኛው ደረጃ ስትፋተጉ፤ ሃሳብን በሃሳብ ስታፈጩ ትቆዩና ከዛም በሌላ ፕሮግራም ላይ ደግሞ በጋራ ማዕደኛ ስትሆኑ ገነት ነበር ለእኔ ለመንፈሴ። ምክንያቱም የእኔ ሃሳብ የእኔ ነው። እኔ ዬእምፈልገው እንደ አንተ ያለውን ወጣ ያለ የእኔን የማይመስለውን ስለነበር ጓጉቼ እታደም ነበር። የእውነት ውበት ነበረው። አዎን ዛሬ ዛሬ ግን የእኔን ሃሳብ ወይንም ዕይታ ደግሜ ለመስማት መታደሙ አላስፈለገኝም ማለት ቀርተህብኛል። የዛሬው ጹሑፍ ደግሞ ዋው! እራሰህን ያነበበው ሸጋ ነው። ማለፊያ ነው። አጋድመህ ከመጻፍ ግን እኔም ብሆን ብለህ ደፈር ብትል ማጣቀሻ ምሳሌዎችን ተረተረት ነገር ከምትነገረን የጭብጡን ተዋናይ አንተን አድርገኸው ቢሆን ገላጭ፤ ተራኪና ትዕይንታዊ በሆነ ነበር። እንዴት ባመረ ነበር። ካልጎሼ አይጠራም። የጠራ ደግሞ ጤና ነውና …. ከራስ መነሳት ደግሞ … አብነትነት ነው ….
ከቶ …. ወንድምዬ ብልህ ይሻልኃል ወይንስ ታናሼ …. በሞቴ በሥርጉት ሞት እንዲህ ካለ የአንድ ሀገር ምስረታ ታሪክን ከናደ ጠቀራ ሂደት ጋር ዶር. ኦባንግ ኢትዮጵያን ማነካካትህን አልወደድኩትም። እሙት ወንድምዬ የምር ክፍት ነው ያለኝ። “በኢትዮጵያዊነታችን ያጣነው ነገር ስላለ ብቻ ኢትዮጵያዊነታችን ይሰረዛል ማለት አይደለም”። „ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ“ እንዲሉ እንዳይሆን …። ምን ባደረገ …. ዶር. ኦባንግ እኮ ንጹህ ግን ብልህ ሰው ነው። ተቋማችንም ነው። ሞት ካወጀ ጋር ማዳበለህ ይቀፋል እሺ! ያው የፈረደበት ግንቦት ሰባት በትንሹም በትልቁም ጥርስ መፋቂያህ፤ ማጠቀሻህ፤ ማጣፈጫህ ስለሆነ አሁን ደግሞ አምጥትህ ማህል ላይ ድንቅር አደረከውም። ፍቅሩ ገደለህ አይደል የግንቦት ሰባት?!! …. ከትክት …. መስጠት ነበረበት ነው ማለም ነበረበት … እሱም እኮ ስደተኛ ነው የማከበርህ። ሥልጣን ኑሮት የነሳው ሲኖር ያን ጊዜ ቢተች …. በቀጠሮ …. ካለ ግንቦት 7 ብዕርህ ውቃቤዋ አይነሳም አይደል?
ከእርእስህ መነሳት ግድ ነው። „የእኛ ነገር የተሸነፈ ርእዮትናሀገር ገፊ ፖለቲካ“ የጹሑፍ ሆድ እቃ እንደ አመለከተኝ ከሆነ ኢትዮጵያዊነት ተሸንፎ አያውቅም ለወደፊቱም አይሸነፍም። ሀገረ ኢትዮጵያም በታሪኳ ስታሸንፍ እንጂ ስትሸነፍ ተሰምቶም ታይቶወም አይታወቅም። ጠላቶቿም አይመሰክሩባትም። እውነት እናትዬ ሞገደኛው ዬትኛው ፕላኔት ላይ ይሆን የከተምከው? ይህ የብሄር የምተለውም ፍትኃዊ ሥርዓት ስንገነባ ነው ተጠያቂነቱ …. „የተሸነፈ ርዕዮትናሀገር?!“ ይህ ታሪክን የመግደል ዕይታ የጤና ወንድምአለም? እርእሱ አራሱ እኮ ገዳይ ነው። አተጋፋት ሀገርህን ….
„ገፊ“ ለሚለውም ከሌላ ዕይታ አንጻር አቅርበኸው ቢሆን ሊያስማማን ይችል ነበር። አቅማችን በመሰብሰብ እረገድ ብትመጣ፤ ወይንም ይህ ሥልጣን በሚሉት ተወዳጅ አዚመኛ ብቅ ብትል ስምምነት በወረደ። ምን የመሰለ ድፎ ዳቦም በተቆረሰ። አንተ ላነሰኸው ነጥብ ግን የተገፋ ነገር አልበረም። በራሱ ጊዜ አጎጠጎጠ፤ በራሱ ጊዜ በቀለ፤ በራሱ ጊዜ ጥፋትን አወጀ፤ በቀለን ዘራ …. ለዛውም ብዙዎቻችን ዝም ብለን ነው እያየን ያለነው። የተማገዱት ጥቂቶች ናቸው … ፊት ለፊት ወጥተው „ኢትዮጵያዊነት“ ሲጠቃ … ዋቢ የሆኑት። ለነገሩ እንቅልፍ ሊኖረን ባልተገባ ….
ምንድን ነው የምትለን? ምን ሁኑ ነው የምንባለው? ከዛ በላይ ወጣቱ የፖለቲካ ተንታኝ፤ አክቲቢስት፤ የሰብዕዊ መብት ተሟጋች ምን ያልተባለው ነገር አለና? እኔ ከእሱ ይልቅ ጋዜጠኛ ሳዲቅ ቀልቤን ሳብ ያደርገው ነበር። ብቻ ከቁንጮጯችሁ ላይ ተሸክማችሁት ሂዱ ተብለን ነበር የታዘዝነው። ይገርምኃል እኔ እህትህ ሳይሞቀኝ ሳይቀዘቅዘኝ ጠርዝ ላይ ሆኜ እመለክት ነበር። በኋለም በዛ አጣብቂኝ ጥያቄ ከመንበሩ ዝቅ ማለት ሲጀምርም ኖርማል ነበር ለእኔ። ሰው ይወጣል ይወርዳል። በቃ!
ትእግስት አጣን ለምትለው ግን ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ላላ ምን ቆራጣ ጊዜ ያስፈልገዋል ብለህ ነው። ይቅናው። መንገዱንም ጨርቅ ያድርግለት …. ከእኛ ተነጥሎ ህይወቱ አልባብ ባልባብ ሲሆን ይድላው … አይተናል ኤርትራን … ሚሊዮን ወጣቶች በርኃ ላይ ሲረግፉና ሲንጋፖር አፍሪካ ቀንድ ላይ ሲገነባ …. ከትከት!
ሌላው ግን ይህን አክቲቢስት የሚባል ሹመት አብዝቼ እታዘበው ነበር። መቼ እንደሚያቆምም እያነፈቀኝ ነው …የተያዘ የተረዘዘው ሁሉ „አክቲቢስቲ“ ሲባል የአውቶብስ ትኬት እንደ መግዛት ነው የቆጠርኩት። እንደ ወያኔ ሹሞች ዶክተሬትነት ….. ሳር ቅጠሉ ሁሉ ሆነ። ለነገሩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ካለ ከፍተኛ ድግሪ ፍንክች አልልም ብሎ መልዕክት ልኳል አሉ?! ነጋሪትም ጎስሟል ይላሉ። ወይኔ! ሥርጉተ ብጣቂ ምንም የለ ከነፃነት በኋላ አስኮባ ማግኘትሽን እንጃ እያለ መንፈሴ ያጣድፈኛል። አንተ ድነሃል አሉ …. የእውነት ነውን? ቀለሜዋ ሳትሆን አትቀርም … በፈርንጅኛው ቃለ ምልስህን አዳምጬ ነበር። እኔ ስሜን መጣፉ አልሆነልኝም ….
ለማንኛውም የእኔ እናት ዘረኝነት በሽታ ነው። ጎጠኝነት ዲዲቲ ነው። ተመስጥሮ የተያዘ በሽታ ሲያዳልጥ በራስ ጊዜ ያፈናቅላል። ከእቅፍ …. አፈንጣሪው ንዑድ መንፈስ የማታውቀው እንደሆን ልንገርህ ወንድምዬ ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረው ሚስጢር „ኢትዮጵያዊነት“ ነው …. አሁን ደግሞ ከመቼውም በላይ በራሳቸው ቋንቋና የዕምነት ዶክተሪን ተሰልፈው የሚሟገቱለትን አፈራ። ልጆቹን እዬሰበሰበ ነው … ጎራ በልና በተቃራኒው በኩል ያሉትን ሲቢሊቲና ደብተራ ሩሞችም ሰንበት ላይ ሆነ በአዘቦት ታደምና ልኩን እወቅ። ልክን ማወቅ ከልክ ያደርሳል – አሁንም ጎንደሬ ይላል።
የከፋን፤ የኢሊባቡርን፤ የጋሙን፤ የሲዳሞን፤ የባሌን የሀረርን ወጣቶች በተለያዬ ኮርስ ምክንያት በቤተሰብ ደረጃ አውቃቸዋለሁ። ንጹህ ናቸው። በነገራችን ላይ አርሲን አወቀዋለሁ። ሮቤን በሙሉ። የጢቾ የአምኛ የሴሩ የዲክሲስ ቁርጡ ወተቱ ገንፎው ጭኮው ፍቅሩ ስስቱ ናፍቆቱ ከቶም ልክ የማይወጣለት ኢትዮጵያዊነቱ፤ እንግዳ ተቀባይነቱና አክባሪነቱ፤ ወደር የለሽ ናፍቆቴ ነው። አሁን አንተና ብዕርህ ጥብቅና የቆምክለት ዬሜጫም ፖለቲካ ያን ደግ ህዝብ ሊወክል የማይችል፤ በአብሮነትና በጨዋነት የሚኖር ስለሆነ …. ብጣቂ ስጋት የለኝም። ማን ወልቆ እንደሚቀር ፈጣሪ ያወቀዋል። እኔ ስዛውር ለአንድ ሳምንት ሥራ የገባ አንድም ሰው አልነበረም። ፍቅር ነው። ነፍሶቼ ናቸው እሺ!
የፈረደበትን ዲያሰፖራ ለማተራመስ ወያኔ በሙሉ ኃይሉ የሰራበት ዘመቻም እሳት የላሱ የእስልምና የተዋህዶ ኦሮሞዎች ሆኑ የሌላ ብሄረስብ አባላት ሁሉ እጅ እጅ ያላቸውን የጃዋር ዶክተሪን ፊት ለፊት እዬተዋጉት ነው። የምሥራቹ ደግሞ እንደምታወቀው በተዋህዶ ትንሳኤን ያበሰራቸው ቅድስት መግዳላዊት ናት። አሁን ደግሞ ሞገዱ የሴቶች ኃይል በመሆኑ ወዬ! ነው … እዬገፋህ ከማልፈልገው ነጥብ ጋር አለካለከኝ እግዚሩ ይይልህ። የእኔ አቅጣጫ ፈጽሞ ሌላ ነበር። የሚገርምህ ጆኖሳይድ ሩም ሲከፈት በተረጋጋ ስሜት ነበር የተቀበልኩት። „ኢትዮጵያዊነትን“ በሚመለከት ባላቤት የሌለው ስለሆነ በዚህ ዙሪያ ብዙ መስራት እንዳለብን ብቻ መንፈሴን አዘጋጀሁት። አሁን እንዲያውም በራሳቸው ጊዜ ጎርቦ የነበረው እብጠት ፈናዳ፤ የዋሆቹ ደግሞ ወደ ጡታቸው እናታቸው ተመለሱ ደስ አይልም? የምስራቹ ይህ ነው።
ትንሽ ከተረተረት የወጣውን የሰሞናቱን የሃቅ አናት መስማት ያሰኝኃልን? በምስክርነት ትንሽ ልበልለት
እንዲህ ሆነልህ …. ታናሼዋ …. „ሞት ለወያኔ“ በሚል ፓል ስም የምትታወቀው ዬእስልማና እምነት ተከታይ ብሄረሰቧ ኦሮሞ፤ ሀረር ተወልዳ ያደገች ብርቅዬ ውብ በ15.01.2014 ደብተራ ሩም ላይ እንዲህ አለችን። „ እኛ ተሰይፈን ሳናልቅ እናንተ ዘንድ አይደርሱም። አስተውል „እኛ ተሰይፈን ሳናልቅ“ እኛን ሳይጨርሱን ከእናንተ ዘንድ ድርሽ አይሉም። ቁምጥና በሽታ በመሆኑ ሀረር ላይም ድውያኑም ሆስፒታሉም አለ“ በማለት አብራ ቆመች ከማንነቷ ጋር አርበኝት።
… በ26.01.2012 ዛሬ ደግሞ ሲቢሊቲ በአባ መላ ሩም 1000 ታዳሚ ነበር። ቃለ ምልልስም ከዶር ጌታቸው ጋር ነበር። „ አጼ ሚኒሊክ ከወገኖቼ ጋር አገናኙን። እኔ የምጠይቀው በእሳቸው ዙሪያ የጀግኖች ሀውልት እንዲሰራ ነው። ከኢትዮጵያዊነታችን አንድ ኢንች ፈቀቅ አንልም።“ ድንቅ ውሳኔ! ሌላዋ እህቴም ሳራ አብዱ ትባባለች። እሷም „ጃዋር እኛን አይወክልም። ምን አለ የእስልምና ሊቃናትን አምጥታችሁ ቃለ ምልልስ ብታደርጉ። በኢትዮጵያዊነቴ እኮራለሁ።“ ሳርዬ ደግሞ የጉራጌ ብሄረሰብ አባል ናት። ለአምስት ዓመት አውቃት የነበረችው ናፍቆቴ አምርትዬ ደግሞ የሰላሌ አንበሲት „በረት ገልባጭ ጀግና ስትሉ ያሳፍራል። ቀመር ዮሱፍ ወይንም አገሪ ቱሉ ሽፍታ የነበረ በረት ገልባጭ ነው። 90 በመቶው ኦሮሞ እስልማና ነው ሲል ጃዋርን አዳመጥኩት። እኔስ የተዋህዶ ልጂት የት ልጣል ነው?! በሃይማኖቴ ቀልድ የለም። እሰዋለሁ። ለነገሩ የድርጅቱ የኦሮሞ ከፍተኛ መሪዎች እኮ ከ10 ጋሻ መሬት በላይ የነበራቸው አስገባሪዎች ነበሩ። አባቴን ጨምሮ፤ ዛሬ እነ አቶ ሌንጮ ስንት ደም አስፈስሰው ሀገር ሊገቡ ነው። እጅግ ያሳዝናል። መጀመሪያ እኔን ኦሮሞዋን ያሳምኑ። አባል ነበርኩ በድርጀቱ“ ሌላው እጅግ ድንቅ ነገር ዲነግዴ መቼም መብራት ነው። ከትናንት ወዲያ በ25.01.2014 ጋዲሳ በሚል ስም የሚጠሩ ፕሮፌሰርና ዳኛ ህይወት ሰጡን ብል ይቀላል። ዛሬ ደግሞ „ መምህሮቼ ስሄድ ይነሱልኛል ነበር ያከብሩኛል። በጀርባዬ ሀገሬ ኢትዮጵያ አለችና።“ አሉን ዘመናትን በትንግርት ያነገረ ሚስጢር ይሉኃል ይህ ነው። ክቡርነታቸው ደግሞ የጥቁር አንበሳ አንባ ጎሬ ላይ እትብታቸው የተቀበረ … ናቸው። ይህን ዘለቅ ብለህ ገባ እያልክ ዛቅ። ሥነ ጥበብ ከማህበረሰቡ ጓሮ ይታፈሳል። ምርት ደግሞ ከሃቅ አውድማ!
ማመሳካሪያዎችህን አብረን ….
1. ወይኔ! ይህ ማጣቀሻ ከሆነ „አከራዩ ደግ አማራ ሴት፤ ለጃዋር ምግብ ሰጥታ፤ እሳት አንድዳ እያሞቀችዉ፤ ከላዩ ላይ ጋቢ ደርባ “ለምን እስኪመሽ ቆየህ አሁን ከመንገድ አንድ ጋላ ቢያገኝህና አንገትህን ቢልሀስ” አለችው፡፡ የዚህን ልጅ ስሜትና ምላሽ ለመረዳት ኦሮሞ መሆን አያስፈልግም፡፡ ራስን በሱ ቦታ ማስቀመጥና ነገሩን የራስን ጎራ ያለስስት በመተቸት ፈቃደኝነት ማሰላሰል እንጂ፡፡”
1. “ልክ ጅሁርና ጋይንት፤ ቢቸናና አንኮበር እንደምትኖር አንዲት አማራ ኢትዮጵያዊት፤ ይህቺ ሴት ክፋት እንደሌላትና የንግግሩዋን ፖለቲካዊ አንድምታ፤ በዚህ ልጅ ቀጣይ ማንነት ውስጥ የሚኖረውንም ፋይዳ እንደማታውቅ አሳምሮ መገመት ይቻላል፡፡ ይሄንን አጋጣሚ የነገረን ጃዋር ግን የሚለው፤ ይህቺ የዋህ ሴት የኢትዮጵያ ገዢ መደብ አካላት ያሰራጩትንና ለገዢ መሳሪያነት የተጠቀሙበትን የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍልን ዝቅ የማድረግ አመለካከት፤ ሳታውቀው ከነፍሱዋ አዋህዳዋለች ነው፡፡ ስለዚህም፤ በቀጥታ ይሄንን የተወሰነ ብሄርን ዝቅ የማድረግ ባህል በመፍጠርና በመቅረጽ ባትጠየቅም፤ የዚህ ባህል በረከት ተቁዋዳሽ በመሆንና አውቃም ሳታውቅም ይሄንን ባህል እድሜ በመስጠት ተሳታፊ ነች ሲል ተከራከረ፡፡ በላይኛው ጽሁፍ ላይ ሰፈርኩትን የኦባንግን ገጠመኝ ጨምረን ካየነው፤ የጃዋር መከራከሪያ ስሜት ይሰጣል፡”
ወይ ፈጣሪዬ! …. ስሜት ከሰጠህ የጆዋር ዶክተሪን መጠቃለል ምን ችግር አለው። በነፃነት ሀገር ልመና ዬለ … ፕሮቶኮል ሲናሪዮ ብሎ ነገር የለ ደጅ ጥናት የለ። አማረም ከፋም ፈርጆዋን በውልብልቢት ከማጣቀስ ዋና መልካም ነው …. ለነገሩ ቀዘፋ ታውቃለህን? ኧረ አስነካው ወንድም ጋሼ!
የገረመኝ የአማራር ብሄረሰብ ከቤንሻጉል ሲፈናቀል „አማራ ብሄረሰብ“ አይባልም ብለህ ሲሳይን የሞገትክ ጀግና አሁን አንተ የብሄረሰቦች ተቆርቋሪና አስታራቂ ሆነህ ጉብ ስትል ትዝብት ነው። …. እዬረሳኸው ይሆን? የሚመከት ነገር ጠፍቶ ይመስልኃልን? አይመስለህ። ሥልጡን ዕያታ ነው ያሳደገን ኢትዮጵያዊነት። ይህ በነጋ በመሼ ምክንያት እዬቆነጠርክ እያጣጣልክ የምትዘልፈው የተዋህዶ ሃይማኖት ሆነ መስጥረህ በጥርስህ የያዝከው ብሄረሰብ የወያኔን ማንፌስቶ የፈጠረ ስለሆነ ጎራው የት ላይ ሊያሰርፍ እንደሚችል ስለሚታወቅ አይደንቀንም ….. መሬትም ባለቤትም ጥግም አልባ ሆኖ የሚንከረተተው ድሃ …. ወገን። „የደላው ገንፎ ያላምጣል አሉ“ ብጣቂ አዘኔታ የለህም እኮ!
„አማራ ብሄረሰብ“ ለማለት አንደበትህ አልደፈረም። ከላይ ያነሰኃት ቅን ሴት የሰው ልጅ ከነነፍሱ ገደል ሲጣል በቅርብት የሰማች ናት …. በሙሉ መፈረጀህ ደግሞ እጅግ አሳዛኙ ገጠመኝ ነው። እኔ እኔን አውቀዋለሁ። በድፈረትም የመናገር አቅሙም ሆነ ብቃቱ አለኝ። ያሳደገኝ ማህበረሰም አሳምሮ ኢትዮጵያዊነትን አጠጥቶ በእሱ አቁርቦ ነው። ይህ ነው የጃዋር ዶክተሪን መሰረት …. የአንዲት ሴት ቀንጣ ዕይታ ታሪክና ሀገርን ለመበተን ያስነሳው። አንተም የምታጅበለት? አልተደመጠም? ምን? ሞትን ነው ማደማጥ የነበረብን ወይንስ 18000 ፊርማ ተሰብስቦ „የፍቅር ጉዞ መታገዱ“ …. እስኪ የበለጠህን ቴዲ ከአዲስ አድማስ ጋር የሰጠውን ቃለ ምልስ ከልብህ ሆነህ እንደ ለመድከው ምስባክ ገፋ አድርገህ ሂድበት ለቤትህ ቀናተኛ ነህ ብዬ ነው የማስበው። የትውልዱ መንፈስ ተነግሮኃል። „እግዚአብሄር በአንድም መንገድ በሌላም ይነገራል ሰው ግን አያስተውለውም“ ይላል አካል የሌለው የመዳህኒዓለም አገልጋይ ቃለ ወንጌል። ከአንተ ያነሰው ቴዲ ዘመኑን – የሚመራን ትእዛዝ ከአምላኩ ተላከለት። ለእኛ አቀበለን …. ካበቀልከው። የዕድሜ አቻውም ወጣቱ ጃዋር ካደመጠው ድህነቱ ከዛ ላይ አለለት …. ቂም በቀል ቋሳ የሌለበት የተረገጋ ንዑድ መንፈስ ….
2. “ወዳጄ ገረሱ ቱፋም፤ እንዲሁ ልጅ ሆኖ ሳለ፤ ጾም መሆኑን ረሳና፤ ወተት ጠጣ፡፡ እናቱ ወደንስሀ አባታቸው ላኩት፡፡ ቄሱ ቃል በቃል ምን ብለው እንደመለሱለትና ልቡን እንዳደሙት የነገረኝን በደንብ አላስታውሰውም፡፡ ብቻ፤ “ኤድያ ደግሞ፤ የጋላ ጹዋሚ ብሎ ነገር የለም” ብለው መለሱለት፡፡ “ለጋላ ንስሀ አባት ዲያቆን መች አነሰው” አይነት የሚለውን፤ የተለመደውን ክብረ-ነክ ተረት የሚያጠናክርና የሚያናንቅ መልስ ነው፡፡ በወቅቱ ገረሱ የሱ ጣፋት መስሎት ነበር፡፡ ነፍስ እያወቀ ሲመጣ ግን የሱ ጥፋት ሳይሆን ልክ እንደጃዋር ቀላቢ፤ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ፤ በቄሱ ውስጥ የተተከለውን የሱን ብሄር ዝቅ የሚያደርግ ገዢው መደብ የፈጠረው ንቀትና ጥላቻ ተገለጸለት፡፡ ከአመታት በሁዋላ፤ እነሆ በገረሱ ነፍስ ውስጥ አብሮ የሚኖርና ዘወትር ቄሱ ስለወጡበት ህብረተሰብ ሲያስብና እኛ ጋር ክርክር በገጠመ ቁጥር ትዝ የሚለው መርዝ አጋጣሚ ሆነ፡፡ እንደውም ኢትዮጵያ ስትባል፤ የኚህን ቄስ ጋቢ የደረበች የአማሮች ፈጠራ መስላ ታየችው፡፡ጉርሶ አይደለም አንተን የጎረበጠህ” ኢትዮጵያ ስትባል የኚህ ቄስ ጋቢ የደረበች የአማሮች ፈጠራ መስላ ታዬው”
ሎቱ ስብኃት! ጉርሶ አይደለም አንተን የጎረበጠህ” ኢትዮጵያ ስትባል የኚህ ቄስ ጋቢ የደረበች የአማሮች ፈጠራ መስላ ታዬው” እግዚአብሄር ይቅር ይበልህ። ለምን እራስህን ማወረድ አስፈለገህ? ማንነትህ እኮ አለ “ኢትዮጵያ” ከምትባል ሀገር። ደፈጠጥከው። ሃዘን ቢጤ እኮ ፈለሰበት …. እናትዬ …. አቤት አቤት ማረን!
…. መጀመሪያ አፍሪካዊ ወይስ ኢትዮጵያዊ?
1. “ባለፈው ሰሞን፤ አልጀዚራ ላይ በቀጥታ ስርጭት ይመስለኛል፤ ጃዋር ፖለቲካዊ አጣብቂኝ ውስጥ የሚከተውን ጥያቄ ተጠየቀ፡፡ “መጀመሪያ ኦሮሞ ነህ፤ ኢትዮጵዊ?” የሚል፡፡ የሚቀጥለው ምሳሌ መቶ በመቶ ላይመሳሰል ይችላል፡፡ የተወሰነ መመሳሰል ግን አለው፡፡ አንድ ሰላሳ አመት ካናዳ ወይም አሜሪካ ውስጥ የኖረ ኢትዮጵያ፤ ወይንም እነዚህ አገር ውስጥ የተወለደ ናይጄሪዊ ይህንን ጥያቄ ቢጠየቅና፤ መጀመሪያ ናይጄሪያዊ ነኝ ብሎ ቢናገር፤ አሜሪካኖችን ወይንም ካናዳዎችን የሚያስቆጣ አይመስለኝም፡፡ ጃዋር ከኢትዮጵ በፊት መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ ብሎ ሲናገር ግን ብዙዎች አኮረፉ፡፡ ንትርክ ተጀመረ፡፡ የነቁና የበቁ የሚመስሉ የአንድነት አቀንቃኞች ራሱ ተቆጡ፡፡ አሁን በእመብርሀን ይሄ ምኑ ያበሳጫል? በዚህ መደንገጥም መቆጣትም የለብንም፡፡ ማድረግ ካለብን መጠየቅ ብቻ ነው፡፡ ችግሩ፤ እንድንሸመድድ እንጂ፤ እንድንጠይቅ በሚያበረታታ ባህል ውስጥ አላደግንምና፤ ከመጠየቅ ይልቅ፤ ልጁን ወደመዘልዘሉ ዘለልን፡፡”
አንደኛ፤ ከአገሬ በፊት ብሄሬን ነኝ የሚለው መልስ እንደየአመለካከታችን ትክክል ሊሆን ይችላል፡፡ በርግጥም ሰው ከአገሩ በፊት ብሄሩን ነው፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ መጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ነህ አፍሪካዊ ቢባልና መጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ ቢመልስ፤ ምንም ብዙ ቁጣ የሚቀሰቅስ አይመስለኝም፡፡ጥምር ዜግነት የሚሉትን ጽንሰሀሳብም ማስታወስ አይጎዳም፡፡ ኢትዮጵያዊ መሆንም ሙሉ በሙሉ የስራችንና የምርጫችን ውጤት ሳይሆን፤ የትውልድና የሕግ ጉዳይ ነው፡፡”
“ከሰደበኝ መልሶ የነገረኝ እንዳልባል እንጂ፤” አልከን ነገርከን እናመሰግንኃለን – ። ይህን ምሳሌ ዳር ዳር ከምትለው እኔ ብሆን ብለህ እንቅጩን ለምን አትነግረንም ነበር?! በብዕርህ ያለን ፍቅር እርሙን አውጥቶ ቦታ ፍለጋ ሊዝ ይገዛ ነበር። እርፍ ባልንም ነበር። እንዲህ በሺህ ምሳሌ ድርድር ከምታባካነን …. አናሳዝንህም ከቶ? … አንተም ወቅተህን፤ ወያኔም ቀጥቅጦን፤ … ዘረኛውም ደንፍቶብን – ዝቶብን – ቁምጥናችን ታቅፈን። ፈረደብን —- በህግ አምላክ!
„…. ነፍስ እንደዜግነት በህግ አትገደድም፡፡ ነፍስ ዜግነቱዋን ወይም ማንነትዋን ትመርጣለች እንጂ፡፡ ነፍሱ ማንነትዋን መረጠች፡፡ የኛ ስራ መሆን ያለበት፤ መናደድ ወይም ማበድ ሳይሆን፤” ማን ነው የተናደደው? ማን ነውስ ያአበደው? ሀቅ ላይ ተሁኖ … ንዴትም ማበድም የለም። በተከታታይ የወጡትን የኔን ጹሑፎች ስለማንነት አንብባቸው። እንኳንም ሩሙን ከፈቱት። ምን ያህል ምርት እንዳታፈሰ ጥንግ ገበሬዎች የተግባር ጀግኖች ያወቁታል። ይልቅ ያበደ ካለ አንተ የምታውቀው የቆምክለት ስሜትን አስረህ አስጠምቀው አንተው በነካ አፍህ …. “ ኢትዮጵያዊነት” የተረጋጋገ መንፈስ የረበበት ማንነት ነው። እሺ ወንድም ጋሼ! ተገፈቶ የማይገፋ ተንቆ የማይንቅ ገናና ተፈሪ ማንነት!
1. “እነዚህ ወጣቶችም ሆኑ የፖለቲካ ንስሀ አባቶቻቸው፤ በዚህ በአልጀዚራ ላይ የሰማነውን አይነት፤ ኢትዮጵዊነትን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ፤ ለኛ ለመቀበል የሚያስቸግረን ንግግር ሲናገሩ፤ የቆሰለውና እንዲህ ወዳለው ስሜት ውስጥ የሰነቀራቸውን ፖለቲካዊ ሕመም በማከም ፈንታ፤ እንደጠላት የሚፈርጅ አካሄዳችንና ራሳችንን የኢትዮጵያ አንድነት ጋሻዣግሬዎች አድርጎ የመሾም ባህላችንን ነው፤ እነዚህን ሰዎች ወደጽንፈንነት የሚመራቸው፡፡ ያ ደግሞ ለኛም ለኢትዮጵያም አይበጅም፡፡ በዚህ ረገድ ይሄን ያህል አመት በኢህአዴግ መበለጣችን ሁሌም ይገርመኛል፡፡ ምክንያቱም፤ ኢህአዴግ ለነጃዋር፤ የአንድነቱ ሀይል ለመቀበል የሚያዳግተውን፤ ኦሮሚያ የሚባል ክልል/ካርታ፤ ሙሉ ነጻነት ባይኖረውም በራሱ ቁዋንቁዋ የሚተዳደር መንግስት ሰጥቶዋቸዋልና፡፡ ስለዚህ ከአንድነት ሀይሉ ውግዘት ጋር ሲወዳደር ብቻ ሳይሆን፤ ራሱን ችሎም፤ ኢህአዴግ ለብሄር ፖለቲከኞች የሰጠው ፖለቲካዊ ገጸ-በረከት፤ ልብ የሚማርክ ነው፡፡”
ለነገሩ ባለፈው „ወያኔ ቀማን ሰልፋችን“ አልከን ዛሬ ደግሞ ወያኔ በለጠችሁ ትለናለህ …. ሀገር በማፈረስ፤ በመሸጥ በመለወጥ፤ ሰው በማጨረስ ጎሳና ጎሳ በማዋጋት፤ ሃይማኖት ሃይማኖትን በማጋጨት፤ በማፈን በመግደል በማሰረ አዎን በረኃብ በመቅጣት። ይበልጠናል። እኛ ስለ አብሮነት ስለ አንድነት ስለ ፍቅር ስለ ነፃነት ነው የሚያንገግበን … ከቶረንቶ ሽልማት ቢጤ ላክ አድርግለት ለሙጃው ወያኔ … ማንነትህን ለመቀማት እዬተጋለህ ነው።
1. “አማሮችና ትግሬዎች እየተፈራረቁ ይህቺን አገር መርተዋል፡፡ አሁን ደግሞ እኛ እንምራ ነው ነገሩ፡፡ በትግሬ ታኮ ወይንም በአማራ ጥላ ስር ሳይሆን፤ በራሳችን መታወቂያ፡፡ አገሪቱን መምራት ካልቻልንም፤ ቢያንስ የራሳችንን እጣ ፈንታ እንወስን ነው፡፡ የኛ ምላሽ …. “
እንዴት ከት ብዬ እንደሳቅኩኝ። ለመሆኑ መቼ ነው አማራ ብቻ ሀገር መርቶ የሚያውቀው? የትኛው ዘመን ላይ ነው ያለኸው? “ወያኔን” አዎን እያዬን ነው …. ይበቃኝ …. ናፍቆቱ ሳያባትለኝ ከች በልልኝና ምን አልባት ዳግም እንፋለም ይሆናል። …. በናፍቆት ይጠበቃል ቀጣዩ ዘላፈህ ደግሞ … “ችኮ” “ማነው ምንትስ” አለ ጋሼ ጸጋዬ “ማመናጨቅቅ” ቅብጥርስ የምትለው ፖለቲካና ፖለቲከኞችን፤ …. ለነገሩ … እስኪ ወኔው ካለህ ዘሀበሻን ጠይቃቸው ስጡት እላቸዋለሁ ኢሜሌንና ዲቤት ማደረግ እንችላለን። አንተ ሙሑር ነህ እኔ ግን መሃይም …… ደግመህ አንበበው። ጽንሰ ሃሳቡን ብቻ ተከተሎ አጠቃላይ እይታ ማቅረቡ ተመራጭ ነው …. ወደ ቀድሞዋ ውበት መልሳት ብእርህን በፈጠረህ። እኔ ለቀለማም ብዕር አብዝቼ ስስታም ነኝና።
ውዶቼ ይህ ኮበሌ እኮ አደከመን። በሉ ለነበረን መልካም የብዕር የጉጉሥ ትዕይንት በጎውን ሁሉ ተመኘሁላችሁ። መንፈሳችሁን ስለሸላማችሁኝ ወደድኳችሁ። አሁን ደግሞ በተክሌ ብዕር በነካ እጅ የተክሌ ደጋፊውች ውቁኝ። ይመቻችሁ ….
ልቦና ይስጠን። አሜን! ማስተዋልን እንደ ሰጠን እንጠቀምበት ዘንድ አዕምሯችን አምላካችን ያብራ። አሜን!
ኢትዮጵያዊነቴን የሰጠኝ አምላክ ክብሩ ይስፋ! ማህተም አለበት – የጸጋዬ ድህረ ገጽና ራዲዮ!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።