- የአ/አበባ ጎልማሶችና ወጣቶች ማኅበራት ኅብረት ተቃውሞውን ያስተባብራል
- ለተቃውሞው፣ በሰባት ቀናት ከ100 ሺሕ በላይ የድጋፍ ፊርማዎች ተሰባሰቡ
- የጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እንዲወስንበት ለማድረግ ታቅዷል
- “በማስረጃ ተደግፎ የሚቀርብ ነገር ካለም እርምት እንወስዳለን” /የጣቢያው ሓላፊ/
(ምንጭ: አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፮ ቁጥር ፰፻፳፤ ቅዳሜ መስከረም ፳፪ ቀን ፳፻፰)
![tao logos and kale awadi]()
![Begashaw and Assegid]()
በኢትዮጵያን ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (EBS) ቴሌቪዥን በሚተላለፉት “ታዖሎጐስ” እና “ቃለ ዐዋዲ” በተሰኙት የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አቀንቃኝ ፕሮግራሞች ላይ ሰሞኑን ከፍተኛ ተቃውሞ ተነሣ፡፡ ፕሮግራሞቹ እንዲዘጉና በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም እንዳይጠቀሙ ለመጠየቅ የሚያግዝ የሕዝባዊ ተቃውሞ ድጋፍ ፊርማም እየተሰባሰበ ነው፡፡
በ7 ቀናት ከ100ሺሕ በላይ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች መፈረማቸውን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ወጣቶች እና ጐልማሶች ማኅበራት ኅብረት ሰብሳቢ ፌቨን ዘሪሁን ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡
“ኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ ዕውቅና ለሌለው አካል ፈቃድ እየሰጠ ጥንታዊቱንና የተከበረችውን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዶግማ እና ቀኖና እንዲኹም ያሬዳዊ ዝማሬን እያንኳሰሱ ይገኛሉ፤” ያሉት ወ/ሮ ፌቨን፤ “ይህ ትውልድን ከመተካት እና የቀናችውን ሃይማኖት ከማስቀጠል አንጻር ትልቅ አደጋ አለው፤” ብለዋል፡፡
የአገራችን ሕገ መንግሥት ማንኛውም ሰው ወይም ተቋም የፈለገውን ሃይማኖት የመከተልና የሀገሪቱ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት የእምነቱን አስተምህሮ ማስተማር እና ማስፋፋት እንደሚችል ያስታወሱት ሰብሳቢዋ፤ ነገር ግን የሌሎችን የእምነት ተቋማት ስም በማናለብኝነት በመዝለፍ በሃይማኖቱ ስም ስብከትም ኾነ ትምህርት በብዙኃን መገናኛ ማስተላለፍ ወንጀልም ኃጥያትም ነው፤ ሲሉ ኰንነዋል፡፡
“ታዖሎጐስ” እና “ቃለ ዐዋዲ” የተባሉት የጣቢያው ፕሮግራሞች፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሥርዐት እና ደንብ የተዘጋጁ መኾናቸውን ቢገልጹም የሚተላለፉት መልእክቶች ግን ከኦርቶዶክሳዊ ትምህርት፣ ሥርዐት እና ትውፊት ፈጽሞ የሚቃረኑና የቤተ ክርስቲያኗን ክብር የሚጋፋ በመኾናቸው ፕሮግራሞቹን ለማዘጋት በበርካታ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በመዘዋወር ከ100 ሺሕ በላይ ምእመናንን ማስፈረማቸውን ወ/ሪ ፌቨን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ “በነዚኽ መርሐ ግብሮች አፋቸውን የሚያላቅቁት ጥቂት የማይባሉ ሰባክያን ነን ባዮች ኦርቶዶክሳዊ ያልኾነ ኑፋቄ ሲጽፉና ሲያስተላልፉ የነበሩ ውስጠ ሌላዎች መኾናቸው በግልጽ ይታወቃል፤” ብለዋል ሰብሳቢዋ፡፡
ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እና ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጋር ግንኙነት አላችኹ ወይ? ፊርማውንስ አስባስባችሁ ስትጨርሱ ለማን ነው የምታቀርቡት? በሚል ላነሣንላቸው ጥያቄ፤ ወ/ሪት ፌቨን ሲመልሱም፤ “አኹን እንቅስቃሴውን እያደረጉ የሚገኙት ከምእመናን ጋር እንደኾነ ገልጸው፤ ውሳኔውን ግን በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በኩል ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቀርብ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ ከዚያ በፊት ግን ከቅዱስ ሲኖዶስ በታች በተዋረድ ካሉ ጽ/ቤቶች ጋር እንነጋገራለን፤” ብለዋል፡፡
ለኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን ቅሬታ አቅርበው እንደኾን የተጠየቁት ሰብሳቢዋ፤ “የጣቢያው ባለቤቶች ስሕተት እንደሚሠራ በርግጠኝነት ያውቃሉ፤”ካሉ በኋላ የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰቡን በ10 ቀናት ውስጥ በአፋጣኝ አጠናቀው ጥቅምት ላይ የምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ ለሚቀመጠው ቅዱስ ሲኖዶስ ለማቅረብ እየተጣደፉ መኾኑን ጠቁመዋል፤ ከዚያም በላይ ለጣቢያውም ጥያቄ እናቀርባለን፤ ብለዋል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ ምላሽ ለማግኘት በአዲስ አበባ ለሚገኘው የኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን ተወካይ ኢንኮም ትሬዲንግ ደውለን፤ እነዚህ ፕሮግራሞች ፈቃድ የሚያገኙት አሜሪካ ከሚገኘው ዋናው መሥሪያ ቤት ስለኾነ በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ ነግረውናል፡፡
አሜሪካ ከሚገኙት የጣቢያው ሥራ አስፈጻሚዎች አንዱ፤ አቶ ነቢዩ ጥዑመ ልሳን፤ ለአዲስ አድማስ በስልክ እንደተናገሩት፤ ከቅዱስ ሲኖዶሱም ኾነ ከሌሎች የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ ተቋማት በይፋ የደረሳቸውና በአካልም ቀርቦ ያመለከተ ባይኖርም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚካሔደውን እንቅስቃሴ ተረድተነዋል፤ ብለዋል፡፡ በማስረጃ ተደግፎ የሚቀርብ ነገር ካለም አስፈላጊውን እርምት እንደሚወስዱም አስታውቀዋል፡፡
* * *
“ታዖሎጎስ” እና “ቃለ ዐዋዲ” በተባሉ የኢ.ቢ.ኤስ ቲቪ ፕሮግራሞች በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም እንዳይጠቀሙ ስለ መጠየቅ፤
Petition Background (Preamble):
የሀገራችን ሕግ መንግሥት ማንም ሰው የፈለገውን ሃይማኖት የመከተል መብት እንዳለው በግልጽ አስቀምጧል:: ስለዚህ ማንም የፈለገውን ሃይማኖት ያለተጽዕኖ እና ግፊት መከተል ይችላል፤ የሚያምንበትንም ሃይማኖት፣ የሀገሪቱ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት ለማስተማርና ለማስፋፋት የሚከለክለው የለም፤ ነገር ግን የሌሎችን የእምነት ተቋማት ስም በማናለብኝነት በመዝለፍ እና በዚያ እምነት ስም ስብከትም ኾነ ትምህርት በብዙኃን መገናኛ ማስተላለፍ ግን ወንጀልም ኃጥአትም ነው::
ለዚኽም መነሻ የኾነን፣ በኢ.ቢ.ኤስ ላይ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ስም የሚተላለፉ “ታዖሎጎስ” እና “ቃለ ዐዋዲ” የተባሉ የቴሌቪዝን መርሐ ግብሮች ናቸው:: እኒኽ መርሐ ግብሮች፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ደንብ መሠረት የተዘጋጁ እንደኾኑ ይገልጻሉ፤ የሚተላለፉት ዝግጅቶች ግን፣ ከኦርቶዶክሳዊ ትምህርት አንጻር ከፍተኛ ጥያቄ የሚያሥነሱና የብዙውን ኦርቶዶክሳዊ ምእመን ግንባር የሚያስቋጥሩ ናቸው:: በነዚኽ መርሐ ግብሮች የሚራቀቁት ጥቂት የማይባሉት ሰባክያንም ኦርቶዶክሳዊ ያልኾነ የኑፋቄ ትምህርት ሲጽፉና ሲያስፋፉ የነበሩውስጠ – ሌላ ሰዎች መኾናቸው በተለያዩ ሚዲያዎች በስፋት ተዘግቧል፤ እየተዘገበም ነው::
በቅርቡ በኢ.ቢ.ኤስ በሚተላለፈው የቴሌቪዥን መርሐ ግብርም ላይ በግልጽ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዘመን ጠገብ ያሬዳዊ ዜማዎች እና የተከበሩ ዘማርያንን “መንደርተኛ” ብለው እስከ መዝለፍ ማለት ደርሰዋል:: ይህ በሃይማኖት ነጻነት ስም የሚደረግ ጠብ አጫሪነት በጊዜ ካልተፈታ በኋላ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ እና ሀገራዊ ችግር መፍጠሩ አይቀርም::
ስለዚህ እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን ጥያቄዎቻችንን ከዚህ በታች አቅርበናል፡-
1. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ራሱን የቻለ ሃይማኖታዊ እና አስተዳደራዊ መዋቅር አላት:: ማንኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱን ስም ይዞ የሚወጣ የአየር ፕሮግራም የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕጋዊ ፈቃድ ወይም ይኹንታ ማግኘት አለበት:: የቤተክርስቲያኒቱ ሕጋዊ መዋቅር ውስጥ ያለ አካል መኾን ይኖርበታል:: ቤተ ክርስቲያኒቱ ያላከችው ማንም አካል ግን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶን ስም ይዞ መንቀሳቀስ አይችልም::
በዚኽም መሠረት “ታዖሎጎስ” እና “ቃለ ዐዋዲ” የተሰኙት መርሐ ግብሮች ከቤተ ክርስቲያኗ ሕጋዊ ፈቃድ እስካልተሰጣቸው ድረስ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያንን ስም መጠቀም አይችሉም:: ስለዚኽም ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ሕጋዊ ማስረጃ ካላመጡ በስተቀር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ስም መጠቀም እንዲያቆሙ ቴሌቪዝን ጣቢያው አስፈላጊውን ርምጃ እንዲወስድልን እንጠይቃለን::
2. በነዚሁ የቴሌቪዝን መርሐ ግብሮች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ስም የቤተ ክርስቲያኒቱን ቀኖና በሚጥስ መልኩ የሚተላለፉ መልእክቶች እና ድርጊቶች እየተበራከቱ መጥተዋል:: ይህም የአንድን ሃይማኖት ክብርና ልዕልና የሚነካ ነው:: በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ስም የሚከናወኑ ኢ – ኦርቶዶክሳዊ የኾኑ ስብከቶች እና ድርጊቶች የሃይማኖቱ ተከታዮች ላይ የሞራልና የሥነ ልቡና ጫና እያስከተለ ነው:: ሕዝቡ ወደ ሕጋዊ ጥያቄ ከመሔዱ በፊት የኢ.ቢ.ኤስ አስተዳደር አስፈላጊውን እርምት እንዲሰጥልን እንጠይቃለን::
3. በነዚኹ ሰባክያን፣ በነዚሁ የቴሌቪዥን መርሐ ግብሮች ላይ በዐደባባይ “መንደርተኛ” በሚል የተዘለፈው የቤተ ክርስትያኒቱ ዘማሪ ይልማ ኃይሉ በይፋ ይቅርታ እንዲጠየቅ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮም ኾነ መምህራን ላይ ተመሳሳይ ዘለፋ እንዳይከናወን አስፈላጊውን መመርያ እንዲሰጥልን የኢ.ቢ.ኤስን አስተዳደር በኢትዮጵያዊ እና ክርስቲያናዊ ትሕትና እንጠይቃለን::
4. በመጨረሻም እነዚሁ ስብስቦች ለቲቪ ፕሮግራሞቻቸው ማስፈጸሚያ ይኾኑ ዘንድ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ስም የሚያደርጓቸው የስፖንሰር ጥያቄዎችና ልመናዎች በአስቸኳይ እንዲታገዱ እንጠይቃለን::
በዚሁ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደርም፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም ስለሚተላለፉት መርሐ ግብሮች ግልጽ መግለጫ እንዲሰጥ እንጠይቃለን:: ከኹሉም በላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖና እና ታሪክ ከመጠበቅ እና ከማስጠበቅ አንጻር በዚኽ ጉዳይ ላይ ሰፊው ምእመን ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ እንጠይቃለን፡፡
Source:: haratewahido