ባርሴሎና ባለፈው በቻምፒዮንስ ሊጉ ሮም ኦሎምፒክ ላይ ከሮማ ጋር 1-1 በተለያየበት ጨዋታ ሊዮኔል ሜሲ በቀዩ እና ሰማያዊው ማልያ 100ኛ የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታውን ፈፅሟል፣ አርጀንቲናዊው በውድድሩ 80 ጎሎችን ካስቆጠረው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ቀጥሎ በ77 ጎሎች ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
አራት ጊዜ የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ያነሳው የ27 ዓመቱ ሜሲ የመጀመሪያ ድሉ በ2009 በሮም ኦሎምፒኮ ያሳካው ነበር፣ በጨዋታው ሊዮኔል ከዣቪ ኸርናንዴዝ የተሸጋገረለትን የአየር ላይ ኳስ ወደ ጎልነት ለውጦ ቡድኑን አሸናፊ አድርጓል፤ ጨዋታውም 2-0 ተጠናቅቋል፡፡
በ2011 ባርሴሎና ማንችስተር ዩናይትድን 3-1 በረታበት ጨዋታ ሜሲ አንድ ጎል አስቆጥሯል፣ በዌምብሌይ ኳስ እና መረብን ያገናኘው አጭሩ አጥቂ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ቡድኑ በተመሳሳይ ጁቬንቱስን 3-1 ሲያሸንፍ ጎል ማስቆጠር አልቻለም፡፡
ሊዮ ባርሴሎና በ2006 በፓርክ ደ ፕሪንስ አርሰናልን 2-1 አሸንፎ ከ1992 በኋላ ታላቁን ዋንጫ ሲያነሳ የቡድኑ አባል የነበረ ቢሆንም በግማሽ ፍፃሜው በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ሳይሰለፍ ቀርቷል፡፡
የአራት ጊዜ የወርቅ ኳስ ተሸላሚው የሆነው ኮከብ በቻምፒዮንስ ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የመሰለፍ ዕድል ያገኘው ዲሴምበር7 2007 ባርሴሎና በዶኔስክ ከሻክታር ጋር ባደረገው ጨዋታ ነበር፣ አሰልጣኝ ፍራንክ ራይካርድ ቀድሞ ከምድብ ማጣሪያ ማለፉን ያረጋገጠውን ቡድን በቋሚ ተሰላፊዎች ከመጠቀም ይልቅ አዳዲስ ፊቶችን ለመመልከት በነበረው ፍላጎት ሜሲን ከተጠባባቂ ወንበር አንስቶ ለማጫወት እቅድ ነደፈ፣ የካታላኑ ክለብም በጨዋታው 2-0 ለመሸነፍ ተገደደ፡፡
ሊዮ በቻምፒዮንስ ሊጉ የመጀመሪያ ጎሉን ያስቆጠረው ኖቬምበር 2/2005 ነበር፣ በኑካምፕ ባርሴሎና የግሪኩን ፓናቲናይኮስን 5-0 በረታበት ጨዋታ ሶስተኛውን ጎል አግብቶ በታላቁ መድረክ የጎል አካንቱን ከፈተ፡፡
በቻምፒዮንስ ሊጉ 100ኛ ጨዋታውን የፈፀመው የግራ እግሩ አጥቂ በውድድሩ አምስት ጊዜ ኮከብ ጎል አግቢ ሆኖ ሲፈፅም 48 ጎሎችንም አስቆጥሯል፤ ይህ በሁለት ጨዋታ አምድ ጎል የማስቆጠር ያህል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
በአንድ ጨዋታ ሁለት ጎሎችን ያስቆጠረባቸው ጨዋታዎች 16 ደርሰዋል፤ በሶስት አጋጣሚዎች ሃትሪክ ሰርቷል፡፡ ከምንም በላይ በ2010/11 የውድድር ዘመን ግማሽ ፍፃሜ ሪያል ማድሪድ እንዲሁም በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ባየርን ሙኒክ ላይ በኑ ካምፕ ያስቆጠራቸውን ሁለት ጎሎች መቼም ቢሆን አይዘነጋም፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ ተጨማሪ የማይረሳቸው አጋጣሚዎች ተከስተዋል፡፡ በ2011/12 የውድድር ዘመን ሁለተኛው ዙር ላይ ባርሳ ባየር ሌቨርኩሰን ላይ ሰባት ጎሎችን ሲያስቆጥር (ጨዋታው 7-1 ተጠናቅቋል) ሜሲ አምስት ጎሎችን አግብቶ ነበር፣ ባለፈው ዓመት የሻክታር ዶኔስኩ አጥቂ ሉዌስ አድሪያኖ በባቴ ቦርሶቭ ላይ ተመሳሳይ የጎል መጠን እስኪያስቆጥር ድረስ የባርሴሎናው ልጅ ሪከርዱን በብቸኝነት ይዞ ነበር፡፡
በ2009/10 የውድድር ዘመን በቻምፒዮንስ ሊጉ በአንድ ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ በርካታ ጎሎችን ያስቆጠረበት ወቅት ነበር፡፡ በኢምሬትስ ከአርሰናል ጋር 2-2 የተለያየው ባርሳ በኑካምፕ የሰሜን ለንደኑን ክለብ 4-1 ሲያሸንፍ የላ ሜሲያው ግኝት የተጋጣሚ ቡድን ተከላካዮችን እጅግ በጣም አሰቃይቶ አራቱንም ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡ ይህንን ሲፈፅም እግርኳስን ተንከባክቦ እና ውበትን ጨምሮ ተጫውቷል፡፡
‹‹ሊዮኔል በእያንዳንዱ ጨዋታ ላይ መሰለፍ ይፈልጋል›› ይላል ከ2008-2010 ድረስ በባርሴሎና አብሮት የተጫወተው አጥቂው ቲዮሪ ሆንሪ፣ ‹‹በኮፓ ዴል ሬይ ከመጀመሪያው ዙር ጀምሮ እስከ ፍፃሜው ድረስ መጫወት ይሻል፡፡ በልምምድ ሜዳ ላይ እንኳን ማሸነፍ እንጂ ሽንፈት አይፈልግም፡፡ በአንድ የጨዋታ እንቅስቃሴ ጥፋት ከተፈፀመበት ከራሱ ግብ ጠባቂ ኳስ እንዲሰጠው በትህትና ጠይቆ ከፊቱ የሚገኙትን ተጨዋቾች በሙሉ አልፎ ኳስ እና መረብን ማገናኘት ይፈልጋል፡፡ ተጋጣሚው ጎል በማስቆጠር በድጋሚ ጨዋታውን ሲጀምር ድንገት ኳስ ይነጥቅና ተጨማሪ ጎል ያገባል፣ የእርሱ ቡድን እስኪያሸንፍ ድረስ ይህንን ደጋግሞ ይፈፅማል፡፡ የዚህ አይነት ተጨዋች ከዚህ ቀደም ገጥሞኝ አያውቅም››
በእርግጥም ሜሲ የእግርኳስ ‹‹ሊቅ›› ነው፣ ኧረ እንዲያውም በህይወት ዘመን አንድ ጊዜ የሚገኝ ታላቅ ተጨዋች መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ብቃቱ ማቆሚያ ያለው አይመስልም፣ እርሱን የሚያውቁ ይህንን ይመሰክራሉ፣ ነገሩ የተጋነነ አይደለም፣ የተጋነኑ የሚመስሉ አስተያየቶችን መስጠትም ፍትህን ማዛባት አይሆንም፡፡
‹‹የፕላኔታችን ምርጡ ተጨዋች›› የሚል ማሞካሻን ያገኘው እንዲሁ አይደለም፣ እስካሁን በነበረው የእግርኳስ ህይወት የነበረው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እና ሪከርዶቹ ከግምት ውስጥ ገብተው ነው፣ የዚህ ሁሉ ምስጢር ምን ይሆን?
‹‹ሪከርዶቼን ወደ ኋላ መለስ ብዬ አልመለከትም፤ አሁንም ድረስ እግር ኳስን እየተጫወትኩኝ የምገኘው ለዚህ ነው፡፡ እርግጥ ነው በእኔ ቦታ ላይ የሚጫወት የትኛውም ተጨዋች ጎሎችን ማስቆጠር ይሻል፤ የእኔ ቀዳሚ ግብ ዋንጫዎችን ማንሳት ነው፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን የሚያነሳሳኝ ዋንጫ ነው፤ ዋንጫዎችን ማንሳት ተነሳሽነት ይፈጥርብኛል፤ እንደ ቡድን ከዚህ የተሻለ ነገር ማግኘት አይቻልም›› ይላል፡፡
በዚህ ደረጃ የሚገኝ ተጨዋች ከግል ሽልማት ይልቅ በቡድን ለሚገኝ ስኬት ቅድሚያ ሲሰጥ መመልከት ያስደስታል፡፡ ተጨዋቹ በ90ሺ ወይም 90 ተመልካቾች ፊት ቢጫወት ሁልጊዜም ቢሆን ቅድሚያ የሚሰጠው ዋንጫዎችን ለማንሳት ነው፡፡
‹‹ተነሳሽት ለማግኘት አልቸገርም፤ እግርኳስን መጫወት እወዳለሁኝ፤ በልምምድ ሜዳ ላይ መገኘት ያስደስተኛል፡፡ በዚህ አይነት መልኩ በየዕለቱ የማሳልፈው ነገር ደስታ ይሰጠኛል፤ አንድ ስኬት ስታገኝ ተጨማሪ ድሎችን ደጋግመህ ማሳካት ትፈልጋለህ›› የሚል አስተያየትን የሚሰጠው ኮከብ ‹‹ልምምድም ይሁን ጨዋታ አልያም ዋንጫዎችን ማንሳት ያስደስተኛል፡፡ ምርጡ ህይወቴ እነኚህ ናቸው፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን ከቡድኔ ጋር ዋንጫዎችን ማንሳት እፈልጋለሁኝ፤ በቃ ይኸው ነው›› ይላል፡፡
‹‹ወርልድ ክላስ›› ተጨዋቾችን ከሌሎች መደበኛ ተጨዋቾች የሚለያቸው የድል ረሃብ ስሜታቸው ነው፤ በየጊዜው ዋንጫዎችን ለማንሳት ያላቸው ፍላጎት በድል ላይ ድል እንዲደግሙ ያስችላቸዋል፡፡
እርግጥ ነው 2014 ለሜሲ አስደሳች አልነበረም፡፡ በላ ሊጋው የመጨረሻ ጨዋታ አትሌቲኮ ማድሪድን የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ የገባው ባርሴሎና 1-1 ተለያይቶ በመጨረሻም ዋንጫውን ተነጥቋል፤ በቻምፒዮንስ ሊጉ በዲያጎ ሲሞኒ ቡድን ሩብ ፍፃሜ ላይ ሽንፈትን አስተናግዶ ረጅም ርቀት መጓዝ አልቻለም፣ በዓለም ዋንጫው ደግሞ አርጀንቲና በፍፃሜው ጨዋታ በጀርመን 1-0 ተሸንፋ ከ1986 በኋላ ይህንን ዋንጫ ለማንሳት የነበራት ዕድል ሳይሳካ ሲቀር ሊዮ በግሉ ከፍ ያለ ትችት አስተናግዷል፡፡
2015 ዓመት ግን የእርሱ ነበር፡፡ በግልም ሆነ እንደ ቡድን ከፍ ያለ ስኬትን አስመዝግቧል፡፡ ‹‹በዓለም ዋንጫ ለፍጻሜ ቀርቦ ሽንፈትን ማስተናገድ ጥሩ የሆነ ስሜትን አይፈጥርም፣ ለአገሬ ታላቁን ዋንጫ ማስገኘት እፈልግ ነበር፡፡ ነገር ግን እንደ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋች ከመጥፎ አጋጣሚ በማገገም ወደፊት መጓዝ ተገቢ ነው›› የሚል አስተያየትን ሰጥቶ ‹‹እንደ እግርኳስ ተጨዋች ሽንፈትን ካስተናገድክ በኋላ በቀጣይ የሚገጥምህን ፈተና በብቃት በመወጣት መጥፎውን አጋጣሚ መርሳት ምርጥ አማራጭ ነው፤ የዓለም ዋንጫው መጥፎ አጋጣሚ ጥሩ ስሜት እንደማይፈጥር ግልፅ ነው፡፡ ነገር ግን ብስጭቱ ለድል ያነሳሳይል፡፡
ሊዮ የተናገረውን ነገር በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በሚገባ ተግባራዊ አድርጓል፡፡ የላ ሊጋውን ዋንጫ ለማንሳት ባልተቸገረው ባርሴሎና ሜሲ በርካታ ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡ የኮፓ ዴል ሬይ ዋንጫን ለማንሳት አልተቸገረም፡፡ ከምንም በላይ በበርሊን ጁቬንቱስን 3-1 አሸንፎ ሻምፒዮን ሆኗል፤ በእነኚህ ድሎች የአጭሩ ኮከብ አስተዋፅኦ ከፍ ያለ ነበር፡፡
ለባርሴሎና ያለፈው ዓመት አስደሳች ነበር፤ ለሁለተኛ ጊዜ የሶስትዮሽ ዋንጫ ባለቤት በመሆን በስፔን ብቸኛው ክለብ ሆኗል፡፡ በ2009 በፔፕ ጋርዲዮላ እንዲሁም ባለፈው ዓመት በሉዊስ ኤንሪኪ ይህንን ስኬት ሊጎናፀፍ ሊዮ የሁለቱም ቡድን መሪ ተዋናይ ነበር፡፡
እርግጥ ነው በባርሴሎና ያለፈው ዓመት ታሪካዊ ስኬት አርጀንቲናዊውን ብቻ አጉልቶ መጥቀስ ሌሎቹን መናቅ ይሆናል፤ ሉዊስ ሱዋሬዝ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ታላቅነቱን አስመስክሯል፡፡ በቻምፒዮንስ ሊጉ የፍፃሜ ጨዋታ ጭንቀት ላይ ለነበረው የካታላኑ ክለብ ኳስ እና መረብን አገናኝቶ ቡድኑን ከጭንቀት መገላገሉ እንዴት ይረሳል? ሶስተኛውን ጎል አግብቶ የቡድኑን አሸናፊነት ያረጋገጠው ኔይማርስ እንዴት ይዘነጋል?
ሶስቱ አጥቂዎች ባለፈው ዓመት በሁሉም ውድድሮች በጋራ 119 ጎሎችን አስቆጥረዋል፡፡ ይህ አስገራሚ ሪከርድ ነው፤ በላ ሊጋው 81 ጎሎችን አግብተዋል፡፡ ባየርን ሙኒክ በተመሳሳይ ወቅት በቡድን ደስ ሊጋው 80 ጎሎችን አግብቷል፤ የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን ቼልሲ 73 እንዲሁም የሴሪ አው አሸናፊ ጄቬንቱስ 70 ጎሎችን አስቆጥረዋል፡፡
‹‹በጣም ዕድለኛ ነኝ›› ይላል- ሊዮ፣ ባለፈው ዓመትም ከታላቅ አጥቂዎች ጎን ተሰልፎ ተጫውቻለሁኝ- ከሮናልዲንሆ ጋር ድንቅ የሆነ መግባባት ነበረኝ፡፡ ከእርሱ በኋላ ደግሞ ከሳሙኤል ኤቶ፣ ቲዮሪ ሆንሪ፣ ፔድሮ፣ ዴቪድ ቪያ እና አሌክሲስ (ሳንቼዝ) ጎል ተሰልፌ በመጫወት አስደሳች ጊዜያትን አሳልፌያለሁኝ፡፡
‹‹ከምንም በላይ ከኔይማር እና ሱዋሬዝ ጋር የፈጠርኩት ጥምረት የተለየ ነው፤ ሁለቱ አጥቂዎች የብቃታቸው ጫፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ በጋራ የተጫወትነው ለአንድ ዓመት ብቻ ቢሆንም ጥምረታችን በጣም ይገርማል፡፡ በቀጣይ ከዚህ የተሻለ ጥምረት መፍጠር እንደምንችል አልጠራጠርም፡፡ ቅድሚያ የምንሰጠው ለቡድን ሥራ ነው፡፡ ኔይማር ባለው ኳሊቲ፣ የኳስ ንክኪ እና አካል ብቃት የዓለማችን ምርጡ ተጨዋች መሆን ይችላል፡፡ ሉዊስ (ሱዋሬዝም) ተመሳሳይ ነው፤ የኳስ ቁጥጥሩ፣ እይታው፣ እንቅስቃሴው፣ ደሙ ነፍሳዊ አጨዋወቱ በአጠቃላይ የማይታመን ነው፡፡ ሁላችንም የተለያዩ ግብአቶችን እናበረክታለን››
ምናልባት አሁን ባለው ሁኔታ ከሜሲ ቀድመው ሊቀመጡ የሚችሉት ፔሌ እና ዲዮጎ ማራዶና ብቻ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከ2003 ጀምሮ ለባርሴሎና መሰለፍ የጀመረው ይህ ኮከብ ዕድሜው ገና 27 መሆኑን አምኖ መቀበል ያስቸግራል፡፡
ስኬቱን ልዩ የሚያደርገው ዘመናዊው እግርኳስ በአካል ብቃቱ ረገድ ወደላቀ ምዕራፍ መሸጋገሩ፣ ታክቲካዊ ጉዳዮች ትኩረት የሚሰጣቸው መሆኑ፣ ክፍተቶችን ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱ እንዲሁም መከላከል ላይ ማተኮሩ ነው፡፡ ያም ቢሆን ሁሉም ነገር ለዚህ ተጨዋች ከባድ አልሆነም፡፡
በዚህ ዘመን ለፈጣሪ ተጨዋቾች ከፍተትን ማግኘት ፈታኝ ቢሆንም ሜሲ ግን ሳይቸገር የሚፈልገውን ነገር በመፈፀም ላይ ይገኛል፡፡ ኧረ እንዲያውም ከእያንዳንዱ ጨዋታ ስኬት አልፎ አራት ጊዜ የወርቅ ኳስ በማግኘት በግሉ ሪከርዱን በእጁ አስገብቷል፡፡
ባለፉት 11 ዓመታት ለባርሴሎና እና አርጀንቲና በጋራ 311 ጨዋታዎች ፈፅሟል፤ በስድስት ትልልቅ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ ሆኗል፡፡ በእነኚህ ጊዜያት 591 ሺ 626.4 ማይል ተጉዟል፤ በአራት የተለያዩ አህጉት 1061 ሰዓታት በርሯል፡፡ በአጠቃላይ 44 ቀናት በጉዞ አሳልፏል፡፡ በሌላ አነጋገር መሬትን 23.9 ጊዜ ዞሯል፡፡
‹‹የብራዚሉ ሮናልዶ የልጅነት አርአያዬ ነበር፣ ለባርሴሎና እና ብራዚል የማይታመን ነገር ሰርቷል፡፡ ከእርሱ የበለጠ ተሰጥኦ የታደለ አጥቂ አልተመለከትኩም፣ የሚገርም ተሰጥኦ ባለቤት ነው፤ ሁሉም ሰው ይህንን መመልከት ይችላል፣ ከምንም ነገር ተነስቶ ጎሎችን ያስቆጥራል፣ የሚያደርጋቸውን ሙከራዎች አስገራሚ ነበሩ፡፡ ከሜዳ ውጭም ቢሆን ድንቅ ሰው ነበር፤ ዚኔዲን ዚዳንንም መጥቀስ አለብኝ፤ እርሱ ሲጫወት መመልከት ያስደስተኝ ነበር፡፡ የፈረንሳውያን ጀግና ነው፤ ከሜዳ ውጭም ቢሆን በአስደናቂ ስብዕና አለው›› የሚለው ሜሲ ነው፡፡
በኤንሪኬ ዘመን ሜሲ የቦታ ለውጥ አድርጓል፡፡ ወደ ኋላ ተመልሶ በአማካይ ቦታ ላይ እስከመሰለፍ ደርሷል፤ ሜሲን ወደፊት በአማካይ ቦታ ላይ ለመጫወት እቅድ አለህ? የሚል ጥያቄን ስታነቡበት ‹‹አዎን፤ ይህ እንደሚቻል ይሰማኛል፤ በርካታ ተጨዋቾች ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ ወደኋላ ተመልሰው ይጫወታሉ፤ በቀጣይ ወደ ኋላ ተመልሼ የአማካይ ስፍራ ተጨዋች እንደምሆን ይሰማኛል፤ ከወዲሁ በአማካይ ቦታ በመጫወት በአማካይ ቦታ ላይ በመጫወት በርካታ ቦታዎችን አካልያለሁኝ፤ እንደ አጥቂ በፊት መስመር ላይ መጫወት ያስደስተኛል፤ በርካታ አጥቂዎች በጥልቀት ወደኋላ ተመልሰው በአማካይ ቦታ ላይ በመጫወት የእግር ኳስ ህይወታቸውን ያራዝማሉ፤ ሁልጊዜም በሩጫ ላይ የተመሰረተ አጨዋወት መከተል አይቻልም የሚል ምላሽ ይሰጣል፡፡
ከላ ሊጋ ክለቦች ሊዮ የፔፕ ጋርዲዮላውን ባየርን ሙኒክ መመልከት ያስደስተዋል፤ ‹‹ፔፕ ሁልጊዜም አዳዲስ ነገሮችን ይሞክራል፤ ይህ ለእግርኳስ አስደሳች ነገር ነው፤ በአውሮፐ አዳዲስ ነገሮችን መፍጠር በጣም ያስደስታል›› የሚል አተያየትን ሰጥቶ ‹‹እርሱን በተቃራኒ ወንበር ላይ ሲቀመጥ መመልከት የእንግዳ ስሜትን ይፈጥራል፤ በእግርኳስ ህይወቴ ስሜትን ይፈጥራል፤ በእግርኳስ ህይወቴ ላበረከተው አስተዋፅኦ በጣም ላመሰግነው እወዳለሁኝ፤ ሆኖም የእርሱን ቡድን በተቃራኒ ስገጠም የማስበው ማሸነፍን ብቻ ነው›› ይላል፡፡
የሜሲ ተሰጥኦ የዳበረው በልምምድ እንደሆነ ግልፅ ነው፤ ከባርሴሎና ተጨዋቾች መሀከል በልምምድ ሜዳ ላይ ታታሪው ማነው? የሚል ጥያቄ ስታስተከትሉበት ‹‹ይህንን መናገር ይከብዳል፤ ሆኖም ዣቪ እና ኢንዬስታን ማስቀደም አለብኝ፤ ለረጅም ዓመታት የዚህክለብ ልብ ሆነው ቆይተዋል፡፡ በልምምድ ሜዳ እንደ እነርሱ አይነት ታታሪ ተጨዋቾች አልተመለከትኩም›› በማለት ይመልሳል፡፡
The post Sport: ሜሲ!!! የእግርኳሱ መሲህ appeared first on Zehabesha Amharic.