Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

በበዓል የረሃብ አድማ!! –ርዕዮት ምን ልትነግረን ነው?

$
0
0

ከዳዊት ሰለሞን (ጋዜጠኛ)

በብሄራዊ በዓላት ቀን በአብዛኛው ከወደ እስር ቤት የሚሰማው ዜና አስደሳች ነበር፡፡ይህንን አጼዎቹ ፣ሰው በላው የደርግ ስርዓትና ብሶት ወለደኝ ያለን ኢህአዴግ ሲያደርጉት ቆይተዋል፡፡በዘንድሮው አዲስ አመትም የመንግስትን ይቅርታ በማግኘት ከወዳጅ ዘመዶቻቸው የተቀላቀሉ ስለመኖራቸው ተሰምቷል፡፡በአዲሱ ዓመት ይቅርታ ከተቸራቸው እስረኞች መካከል ታዋቂ ፖለቲከኞች፣አክቲቪስቶችና ጋዜጠኞች አለመኖራቸው ተፈቺዎቹ በደረቅ ወንጀል ታስረው የነበሩ መሆናቸውን ለመናገር ብዙ መድከም አይጠይቅም፡፡
መንገስት ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ሂሩት ክፍሌና ዘሪሁን ገ/እግዚአብሄር አቅርበውት ለነበረ የይቅርታ አቤቱታ የእምቢታ ምላሽ መስጠቱም ይቅርታ የሚገባውና የማይገባው በመንግስት ማውጫ ውስጥ ስለ መኖሩ ማሳያ ነው፡፡የይቅርታው ጉዳይ ለጊዜው ይዘግይልንና በጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ ላይ በበዓል ቀን ስለ ተፈጸመ ግፍ ላካፍላችሁ፡፡

 ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ

ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ


ጋዜጠኛዋን በበዓሉ ዋዜማ ለመጠየቅ ወደ ቃሊቲ አምርተን ነበር፡፡በመጠየቂያ ሰዓት መድረስ የቻልን ቢሆንም ጥበቃዎቹ ‹‹ርዕዮት የምትጠየቀው በዋናው በር ሆኗል፡፡ስለዚህ ወደ ዋናው በር ሂዱ›› አሉን፡፡ዋናው በር ፈጣን ተራማጅ በ10 ደቂቃ የሚደርስበት በመሆኑ ሰዓቱ እንዳይረፍድና እንዳንከለከል በማለት መሮጥ ጀመርን፡፡
ዋናው በር ግብረ ገብነት አልያም ፖሊሳዊ ስነ ምግባር በዞረበት ለሰላምታ እንኳ አግኝቷቸው የማያውቁ የሚመስሉ ጠባቂዎች ‹‹በዚህ በኩል እስረኛ አይጠየቅም ሂዱ ››አሉን፡፡ግትር ብለን በዚህ በኩል ግቡ ተብለናል አልን፡፡ሰዓቱ እየሄደ ፖሊሶቹም በአቋማችን የበለጠ በመበሳጨት እየዛቱ ነው ፡፡በመካከሉ የርዕዮት ታናሽ እህት እስከዳር አለሙና እጮኛዋ ስለሺ ሀጎስ ከግቢው ውስጥ እየተጣደፉ ወጡ፡፡
ስለሺ አንገቱን አቀርቅሮ እጆቹን እያወናጨፈ ብቻውን ያወራል፣እስከዳርን በሙሉ አይን ማየት ያስፈራል፡፡ ፊቷ በርበሬ መስሎ በእንባ ጎርፍ እየታጠበች ነው፡፡አብሮኝ የነበረው ሰውና እኔ ለመግባት እናደርግ የነበረውን ትንቅንቅ በመተው ሁለቱን ለማጽናናት እና ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ መወትወቱን ተያያዝነው፡፡
ርዕዮት ቤተሰቦቿን እንዳገኘች‹‹ያለሁበት ሁኔታ አስቸጋሪ ነው፣ችግር ውስጥ ነኝ››ትላቸዋለች፡፡በዚህ ወቅት በዙሪያዋ የነበሩ ሴት ፖሊሶች ጋዜጠኛዋ ላይ በመጮህ ‹‹ስለ ራስሽ ብቻ አውሪ››ይሏታል፡፡
‹‹የነገረችን እኮ ስለ ራሷ ነው››የእስከዳር ምላሽ ነበር፡፡በዚህ መሃል በጊዜያዊነት የሴቶች ዞን ሃላፊ የሆነች ፖሊስ ‹‹እናንተ አቅማችሁ ጋዜጣ ላይ ነው ከፈለጋችሁ ሂዱና እንዳንጠይቃት ተከለከልን በሉ፡፡››በማለት በዚህ ቦታ ለመጥቀስ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት የሚያቅበንን የስድብ መዓት በስለሺ ፣በርዕዮትና በእህቷ ላይ ታወርዳለች፡፡

ርዕዮት ሁኔታውን መቋቋም ተስኗት ሃላፊዋን ለምን እንዲህ አይነት በደል እንደምትፈጽምባት ለመጠየቅ ስትሞክር እየገፈታተሩ ወደ ውስጥ እንድትገባ በማድረግ እነ ስለሺን ግቢውን እንዲለቁ ያደርጋሉ፡፡
በንጋታው መስከረም 1/2006 ነው፡፡የመንግስት ሃላፊዎችና የሃይማኖት አባቶች የቴሌቭዥኑን መስኮት በአዲስ አመት ቀና መልዕክት አጨናንቀውታል፡፡አዲስ ቀን አዲስ ገጠመኝ እንደሚፈጥር ተስፋ ያደረጉት የርዕዮት ቤተሰቦች ከቃሊቲ አልቀሩም፡፡ነገር ግን የሰሙት ነገር በቀኑ እንጂ በአስተዳደሩ መካከል ለውጥ ወይም ዕድሳት አለመኖሩን ነው፡፡ለካ የአዲስ አመት በጎ መልእክት የሚያስተላልፉልን መሪዎቻችን ያሉት‹‹በድሮው ቀን ነው፡፡››
ርዕዮትን እንዲጠይቁ የተፈቀደላቸው ‹‹እናቷ፣አባቷና የነፍስ አባቷ ብቻ ናቸው››እነ ስለሺ ከቃሊቲ ሃላፊዎች ዛሬ ያደመጡት መንፈስ ሰባሪ ቃል ነው፡፡የህግ ባለሞያው አቶ አለሙ ጌቤቦ ድርጊቱ ህገ መንግስታዊ ጥሰት እንደሆነ በመግለጽ ቃሊቲ ደርሰው ልጃቸውን ሳይጠይቁ ተመልሰዋል፡፡ወላጅ እናቷ ያመጡትን ምግብ ለማስገባት ቢሞክሩም ርዕዮት በቃሊቲ የሴቶች ዞን ጊዜያዊ ሃላፊ እየደረሰባት የሚገኘውን ህገ ወጥ ድርጊት ለመቃወም የርሃብ አድማ በመጀመሯ እናት ያመጡትን ምግብ የሚቀበላቸው አላገኙም፡፡
ወዳጄ ስንቶቻችን ነን አዲሱ ዓመት በጾም ቀን ዋለ ብለን የተከፋን?ይህው እንግዲህ በዓሉን ርዕዮት በርሃብ አሳልፋዋለች፡፡
የርዕዮት የርሃብ አድማ መልእክቱ ግልጽ ነው፡፡አቅም ያላት በራሷ ላይ በመሆኑ ራሷን በመቅጣት ህገ ወጦችን እምቢ አለቻቸው በዚህ ሰላማዊውን ታጋይ ማህተመ ጋንዲን መሰለችው፡፡ሰዎቹ እየበሉ በርሷ ላይ የሚፈጽሙት በደል እየተራበች በምታስተላልፈው መልእክት የህሊና ርሃብተኞች መሆናቸውን ይነግራቸዋል፡፡
ከቃሊቲ ውጪ ያለንም ምግብ ወደ አፋችን ባስጠጋን ቁጥር ርዕዮት የቃሊቲ አጥር ሳይበግራት ትመጣብናለች፡፡በምግብ ብቻ በማይኖርባት አለም በምግብ ብቻ ለመኖር ለምናደርገው ከንቱ ሩጫም ርሃቧ ትልቅ ደወል ይሆንብናል፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>