ሙስሊም ወንድሞቻችን ሁለት አመት ለሚጠጋ ጊዜ እየተገደሉ ነው። በጽናት፤ በጀግንነትና በብልሀት እናም በመስዋእትነት የመብት ትግላቸውን ቀጥለዋል። በለተ – አውዳመት ኢድ አልፈጥርም የመስዋእትነት ደማቸውን፤ …ኢትዮያን የተቆጣጠራት የትግራይ ዱር አራዊት መንጋ አፍሷል። የሞቱትን ሁሉ አላህ በጀነት ነፍሳቸውን ያኑር ከማለት በቀር ምን ይባላል ? ለሁሉም ወገኖቻችን ለቤተሰቦቻቸው፤ ለዘመዶቻቸው አላህ ጥናቱን ይስጥ እላለሁ። በከንቱ ለፈሰሰ ደማቸውም እሱ በማያልቅበት ስልጣኑ ፍርዱን ይስጥ። ሳይውል ሳያድር።…አላህ ሁ አክባር!!!
አፋር ለብቻው እየተቀጠቀጠ ሀብቱን ንብረቱን እየተቀማ እየተዘረፈ ነው። ኦሮሞ ለብቻው እየተቀጠቀጠ ሀብቱን ንብረቱን እየተቀማ እየተዘረፈ ነው። ሶማሌ ለብቻው እየተቀጠቀጠ ሀብቱን ንብረቱን እየተቀማ እየተዘረፈ ነው። አማራው እየተቀጠቀጠ ሀብቱን ንብረቱን እየተቀማ እየተዘረፈ ነው። ደቡቡም ቤኔሻንጉሉም…ሁሉም! ድፍን ኢትዮጵያ….
የኢትዮጵያ ሳተላይት ሬዲዮና ቶሌቪዥን ከተመሰረተ ወዲህ፤ ይህ ህዝብ፤ አንዱ ባንዱ ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ መከራና ግፍ ሌላው ሳይሰማ ቀርቶ አይደለም፤ ከዳር እዳር ለአመጽ ያልተነሳው። አንዱ ላንዱ ለመድረስ ሳይፈግ ቀርቶ ሳይሆን፤ አንድ ሆኖ የጋራ ጠላቱን ህውሀትንና የየክልሉን ባንዳዎች አምርሮ የሚታገልበት ድፍረቱ የጠፋው ነው የሚመስለው። ከየቋንቋው ተናጋሪ፤ ዛሬን ኖረን እንሙት ብለው በቆረጡ የጥቅም ምርኮኞች ወያኔ ያዋቀረው የስላላ መረብ፤ የማያፈናፍን በመሆኑም ሊሆን ይችላል ህዝቡ ከየአቅጣጫው መነሳት ያቃተው። የህውሀት ሰላዮች አብዛኛዎቹ የትምህርት ደረጃቸውና የስራ ልምዳቸው የማያስገኝላቸውን ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ወገኖቻቸውን አሳልፈው የሚሰጡ፤ ይህ ስልጣን ላይ ያለው ቡድን ንቅንቅ የማይል ነው ብለው የሚያምኑ ናቸው። ህልውናቸውን ከስር አቱ ጋር ስላቆራኙት ተግተው ወገኖቻቸውን ሁሉ ያስበላሉ። ይህ ፍርሀት በያንዳንዱ ሰው ልብ ውስጥ ነግሶ ይሆን ? ከሁሉም በላይ ግን ሁሉንም አንድ ላይ መጨፍለቅ የሚችለው የህዝብ ቁጣ ነው። ለምን ይሆን የዘገየው የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጣ ?
መልካሙ ነገር ወያኔ በመላው ኢትዮጵያ ከትግራይ ክፍለሀገር ጨምሮ የጠላቶቹን ቁጥር እያበራከተ መሄዱ ነው ። ይህም በመሆኑ የሚወስደው እርምጃ ሁሉ የውስጥ ፍርሀቱንም ጭምር ይገልጻል። የሚፈራውም አንድ ቀን፤ ከአንድ ጥግ፤ ወይ ከመሀል የሚነሳ የተንቀለቀለ ቁጣ ማእበሉ በሚያስገርም ፍጥነት በመላ ሀገሪቱ ተስፋፍቶ፤ ወያኔ ለወሬ ነጋሪ እንኳ እንዳይተርፍ ሊያደርገው ይችላል። አንባገነኖች አፈናውንና ጭቆናውን እያበዙት በሄዱ ቁጥር፤ የፍርሀታቸውም መጠን እየጨመረ መሄዱ የማይቀር ነው። የፍርሀታቸው መጠን በጨመረ ልክ፤ በህዝብ ላይ የሚፍጽሙትም ግፍ እየከፋ ይሄዳል። በሙስሊም ወንድሞቻችን ላይ የሚያካሂዱት ጭፍጨፋ ይህንኑ ያመለክታል።
ባንድ አጋጣሚ መብቱንና ነጻነቱን ለማይረቡ ደካሞች አሳልፎ የሰጠ ህዝብ፤ በውዴታ ወይም በክብር መልሶ ነጻነቱን ሊያገኝ ከቶም አይቻለውም። በቁጣ እና በሀይል ነው ከጅ ያመለጠ ነጻነት የሚገኘው። በተደራጀ ሀይልና በቆራጥ ትግል ነው ከጅ ያመለጠ ነጻነት የሚገኘው። ወያኔዎች በተቀናጀ የፖሊስና የጦር ሀይል ህዝብን በማሸበር ስራ ላይ ተሰማርተው ህዝቡን አሸባሪ ይሉታል። ህዝቡን እየገደሉት ተገደልን ይላሉ። ባንዲራ ቀደው እያራገቡ ህዝቡን ባንዲራ ቀደደ ይሉታል። ዘጠና ሚሊዮን ህዝብ ይህችን ምድር ትቶላቸው ወዴት እንዲጋዝ አስበዋል? አዎ ይህን ህዝብ አሸንፈውታል። ጥለውታል። ፈሪ ከጣለው ላይ አይነሳም እንዴ?… ፈሪ ግልግል አያውቅም እንዴ? ካንድ መንደር የተውጣጡ ወሮበሎች ይህን ህዝብ በሀይል ጸጥ አድርገው እየገዙ እንድሚዘልቁ አምነዋል? እኛስ እየተረገጥን ተገዝተን መኖር እንዳለብን አምነን ተቀብለናል?
ምን ጊዜም የአንባገነኖች ብርታትና ጥንካሬ የህዝብ ፍርሀትና መንበርከክ ነው። የኛ ችግር ደግሞ ከፍተኛ ፍርሀት በልባቸው ውስጥ መኖሩን አውቀን መድፈር አለመቻላችን ነው። እነሱ ይህን ስልጣን ተነጥቀው በጃቸው ያስገቡትን የሀገሪቱን ሀብት እንዳያጡ ይፈራሉ። እኛ ደሞ ከሞቱት በላይ ከነሱ በታች አድርጋ የምታኖረንን ኩርማን እንጀራ እንዳናጣ እንፈራለን። እየፈራንም ድንገት ባላሰብነው ሁኔታ ያቺን የምንፈራላትንም ጥቅም አሳጥተውን እንደምንወድቅ አሳይተውናል። ስንት ሺ ህዝብ ነው በማያውቀው ምክንያት ከስራ የሚባረረው? ብረት የተሸከመው መለዮ ለባሽ ሳይቀር ስንቱ ሺ ስንት ጊዜ ከሰራዊቱ ተባረረ? መፍራቱ፤ አቤት ወዴት እያለ ለነሱ መታዘዙ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ለኑሮና ለህይወት ዋስትና ነው ብሎ የሚያምን ይኖር ይሆን?
ሀይሌ ገብረስላሴ እግራቸው ስር የወደቀው ፕሬዚደንት እሆናለሁ እያለ መለፍለፍ የጀመረው ሀብቱን ንብረቱን ሊዘርፉት እንደሚችሉ ጠንቅቆ በመረዳቱ ይመስላል። የሚወደውን የኢትዮጵያ ህዝብ ጠልቶ አይመስለኝም እነሱ ስር መለጠፍ የፈለገው። ጨካኝ ወንጀለኞች መሆናቸው አስፈርቶት ነው። ስልጣኑ አይደለም አንባገነኖችን ጨካኝና ጨፍጫፊ የሚያደርጋቸው። ጥቅሙ ነው። ያን ጥቅም የማጣት ፍርሀት ነው ክፉ የሚያደርጋቸው ። ጥቅሙ የሚገኘው ስልጣኑን ተከትሎ ነውና።
የሰው ልጅ በተፈጥሮው የሚገባውን ሰባዊ መብት አላውቅም፤ አልቀበልም፤ አላከብርም፤ ብሎ በህዝብ ላይ ያሻውን እየፈጸመ ለመኖር የቆረጠ የህገወጦች ቡድን ሁሉን በተቆጣጠረበት አገር ውስጥ፤ እርግጥ ፍርሀት የህብረተሰብ የለትተለት ህይወት ሊሆን ይችላል ። እንዳንታሰር መፍራት፤ እንዳንገደል መፍራት፤ በእስር ቤት የቁምስቃይ እንዳይደርስብን መፍራት፤ ልጄን ወንድሜን ይገሉብኛል ብለን መፍራት፤ ስራዬን አጣለሁ ብለን መፍራት፤ ያለኝን ሀብት ነጥቀው ያደኽዩኛል ብለን መፍራት፤ አዎ ባሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ መሰረት ያለው ፍርሀት ነው። አንካካድም። እንዲህም ሆኖ ግን የሚደርስባቸውን ሁሉ እያወቁ፤ ለህይወታቸውም ለንብረታቸውም ቅንጣት ሳይሳሱ፤ በግላቸው ለመጠቀም ሳይሆን፤ ኢትዮጵያውያን መብት ነጻነትና ዲሞክራሲ ያስፈልገናል ብለው፤ እነእስክንድር ነጋ፤ እነ አንዷለም አራጌ፤ ወያኔ እስር ቤት የታጎሩት የነጻነት ታጋዮች በሙሉ፤ የሙስሊም ወንድሞቻችን መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ብሎም መላው ኢትዮጵያዊ ሙስሊም በሙሉ፤ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው እየጮሁ ይህን የነፍሰገዳዮች ቡድን ሲሞግቱ፤ አብሮ ለመነሳትና ለመከተል ወኔ ማጣታችን ነው ከሁሉም የከፋ ፍርሀት። የመጣው ይምጣ ብሎ ጀግና ተነስቶ ይህን አራዊት ቡድን ሲጋፈጥ እያዩ ቶሎ ተነስቶ ከጎኑ መቆም ያለመቻል ነው አደገኛው ፍርሀት።
የቱኒዚያው ለውጥ የመጣው አንድ ወጣት እራሱን በማቃጠሉ፤ ከዳር እስከዳር የሀገሪቱ ሰው ሁሉ ተነቃንቆ፤ በጥቂት ቀናት ነገሩን ሁሉ ቀየረው። በኢትዮጵያ ውስጥ ጀግናው የኔ ሰው ገብሬ ለፍትህ ሲል ራሱን አቃጠለ። ወያኔ በህዝቡ ላይ የጫነው የፍርሀት ድባብ በልጦ ነው መሰለኝ የተንቀሳቀሰ ሰው አልታየም።
በማናቸውም ስርአት ውስጥ ኢትዮጵያ ጭቆናን፤ አንባገነንነትን፤ ዘረኝነትን፤ የሚቃወሙ ጀግኖች ሞልተዋታል። ቀድመውን የተነሱትን ፈጥኖ የመከተል ወኔ ነው የጎደለን። ሰማያዊ ፓርቲ አዲስ አበባ ውስጥ በቅርቡ በጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ከሶስት መቶ ሺህ ህዝብ ያላነሰ ወቷል። የቀረው እቤት ውስጥ ምን ያደርግ ነበር ?.. ሙስሊም ወንድሞቻችን ሁለተኛ አመታቸውን ይዘዋል ድምጻችን ይሰማ፤ የሀይማኖት ነጻነታችን ይከበር፤ ህገመንግስቱ ይከበር እያሉ ሲጮሁ፤ ሲገደሉ፤ ክርስቲያኑ ምን እያደረገ ነው ? እስላም መንግስት ሊሆንብህ ነው ብሎ ወያኔ የሚያወራው ውሸት ለኢትዮጵያዊው ክርስቲያን የመዝናኛ የመሳቂያ ቀልድ ነው። ከወንድሞቹ ጋር መነሳት ያቃተው፤ ለራሱ ነፍሱ በፍርሀት ብትቀጥን ነው እንጂ። ( በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች ሲደብራቸው ወያኔ ዛሬ ምን ውሸት አወራ? ቴሌቪዥን ያየ አለ? ማለት በየቤቱ የተለመደ ሆኗል ይባላል) እርግጥ የሀገር ቤቷ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በወያኔ ተማርካለች፤ የሀይማኖት መሪዎች፤ የወያኔ ባንዳና ቅጥረኞች ሆነዋል። የሙስሊሙን ቅጥረኛ መጅሊስ ምእመኑ እንቢ እንዳለ፤ የክርስቲያኑም ምእመን ያንኑ አቁዋም ይዞ ከወንድሞቹ ጎን መታየት ነበረበት። በሙስሊም ወንድሞቹ ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ ኢትዮጵያዊውን ክርስቲያን እያሳመመው እያንገበገበው ነው። ይሄ ምንም የሚያጠራጥር ነገር የለውም። ሙስሊሙ በየመስጊዱ ያደረገውን ክርስቲያኑ በየ ቤተክርስቲያኑ ለማድረግ ግን ዘግይቷል። ጊዜ ግን ምንጊዜም አለ። ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችም ተነሱ!
ዊንስተን ቸርችል ተናገሩት ተብሎ ከተጻፈ ጥቅስ እንዲህ የሚል አየሁ “….ታያላችሁ እነዚያን በተደላደለ መሰረት ላይ ተደላድለው የተቀመጡ አንባገነኖች? በወታደሮቻቸው አፈሙዝ ተከበው፤ በፖሊሶቻቸው ቆመጥ ተከበው….ግን በልባቸው ውስጥ ለመግለጽ አዳጋች የሆነ ፍርሀት አለባቸው። …መልካም አስተሳሰቦችን ይፈራሉ። ጠንካራ ቃላትን ሳይቀር ይፈራሉ። ስለ ስርአታቸው ስለሁኔታቸው ከውጭ የሚወሩ ነገሮችን ይፈራሉ። በሀገር ውስጥ የሚንሸራሻሩ ትክክለኛ ሀሳቦችን ይፈራሉ። ስለሚያስፈሯቸውም ሀሳቦችን ያግዳሉ። ያፍናሉ። ሰው ሀሳቡን እንዳይገልጽም ይከለክላሉ። እነሱ ከሚያስቡት የተለየ ኢምንት አስተሳስብ በሀገር ውስጥ ሲንቀሳቀስ ካዩ በፍርሀት በድንጋጤ ይርዳሉ….”
የህውሀት ሰዎች የኢትዮጵያን ህዝብ ለማፈን የሚደክሙት ለምንድነው? የሽብርተኛ ህግ አውጥተው የሚቃወማቸውን ሁሉ፤ ጋዜጠኛውን ሁሉ እስር ቤት የሰበሰቡትና ድፍን ያገሪቱ ህዝብ እነሱ የሚዋሹትን እንጂ እንዳይሰማ ለማድረግ ባለመታከት የሚጥሩት ለምንድነው? መልሱ ከላይ ዊንስተን ቸርችል ከተናገሩት ውስጥ አለ። እኛ የተጎዳነው ፈሪዎች መሆናቸውን ማወቅ አቅቶን ደፍረን እነሱን ለማንበርከክ አለመተጋገዛችንና አለመነሳታችን ነው።
ከደቡብ አፍሪካው አፓርታይድ ጋር ይፋለም የነበረው የነማንዴላ ድርጅት እንደ አወሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር በ1949 ዓም ላይ አመታዊ ጉባኤውን ሲያካሂድ ህዝቡን በማንቀሳቀስ ተግባራዊ የሚሆን የሰላማዊ ትግል እርምጃዎችን አቅዶ ነበር። እነዚያም እቅዶች ቦይኮት፤ የስራማቆም አድማ፤ እቤት የመዋል አድማ፤ ከመንግስት ጋር ያለመተባበር፤ ዘረኛ ለሆኑ ህጎች ያለመገዛት፤ ባጠቃላይ ሀይል ያልተቀላቀለበት አመጽ፤ እንቢታ የመሳሰሉት ነበሩ።
በ1951 መጨረሻ ላይ ይህንኑ የትግል ስልት በተግባር ሊጀምሩ፤ የኤ-ኤን-ሲ መሪዎች ተሰበሰቡና አግባብነት የሌለውንና አፓርታይድ ህዝቡን ለማፈን ያወጣውን ህግ ባደባባይ ጥሰው በማሳየት፤ ለመታሰር የሚፈልጉ በጎ ፍቃደኞችን ማሰባሰብ ቀጠሉ። በሀገራችን ወያኔ እንደሚጠቀምበት የሽብረተኛ ህግ ማለት ነው። በ1952 መጀመሪያ ላይ ወደተግባር ሲሻገሩ በበጎ ፍቃደኝነት ህግ ጥሰው ለመታሰር የወሰኑ በርካታ ሰዎች ተሰለፉና ነጮች ብቻ መዘዋወር የሚችሉበት አካባቢ ጥሰው መግባት፤ ለጥቁሮች ያልተፈቀዱ ሁቴሎችና መዝናኛዎች ጥሰው መግባት፤ ለነጮች ብቻ በተፈቀደ የማመላለሻ አውቶብሶችና ባቡሮች ላይ ሆ ብለው መግባት፤ ለጥቁሮች ከተፈቀደ ሰአት ውጭ ማምሸት ተግባር ላይ እያዋሉ ሆን ብለው በብዛት ወደ እስር ቤት ይገቡ ጀመር። ይህ የመጀመሪያው የእንቅስቃሴ ክፍል ሲሆን በሁለተና ደረጃ የተነደፈው በመላ ሀገሪቱ ባንድ ጊዜ አንድ አይነት ሰላማዊ እርምጃ መውሰድ ነበር። ያም ብሄራዊ እንቢተኝነትና ብሄራዊ የስራ ማቆም አድማዎች ነበሩ።
ጁን 26 1952 ህግን የመጣስ ተቃውሞ በያለበት ተጀመረ። ህዝቡ በነቂስ ወቶ በጎ ፍቃደኞቹን እያበረታታና እየዘመረ ድጋፉን ሰጠ። ጥቁሮች እንዳይደርሱ በህግ የተከለከሉባቸውን ቦታዎች እየጣሱ በሀይል በመግባት በጅምላ ወደ እስር ቤት መጋዝ ጀመሩ። በርካታ የኤ-ኤን-ሲ መሪዎችም ቡድኖችን እየመሩ አብረው ታሰሩ። ፖሊስ ያሰረውን ህዝብ በሙሉ ፍርድ ቤት እያመላለሰ በመክሰስ ስራ ላይ ተጠመደ። “ሁላችንንም እሰሩን” እያለ ህዝቡ፤ “ማንታስሮ ማን ይቀራል” እያለ፤ በፉክክር መንግስቱን ፈተና ላይ ይጥለው ጀመር። በመጀመሪያዋ የአመጽ እለት 250 በላይ በጎ ፍቃደኞች ህግ ጥሰው ታሰሩ። በተካታታይ በተካሄደ የአምስት ወር ዘመቻ 8500 ሰዎች በበጎ ፍቃድ ህግ የመጣስ ዘመቻ ተካፍለው እስር ቤት ገቡ። የህክምና ዶክተሮች፤ የህግ ጠበቃዎች፤ የፋብሪካ ሰራተኞች፤ የዩኒቭርስቲ መምህራንና ተማሪዎች ባጠቃላይ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ፍጹም ወደር በሌለው አንድነትና መተባበር ያንን መንግስት እስከመጨረሻ ሊታገሱት እንደማይችሉ አረጋገጡለት። ህዝቡ ይዘምር ነበር የባለስልጣናቱን ስም እየጠራ “ ክፈቱት.. ክፈቱት በሩን፤ የእስር ቤቱን…እንፈልጋለን መግባቱን..” እያለ።ይህን ህዝባዊ ሰላማዊ አመጽ ያቀደውና የመራው የማንዴላ ድርጅት ኤ-ኤን-ሲ በህዝቡ ዘንድ እጅግ ትብብርና ድጋፍ በማግኘቱ፤ ባንድ ጊዜ የአባላቱ ቁጥር ከ20‹000 ወደ 100‹ 000 ተተኮሰ።
ከዚያ በፊት የደቡብ አፍሪካ ህዝብ በዘረኞቹ ገዢዎች አንጻር፤ አንድ መሆኑን ያረጋገጠበት አጋጣሚ ነበር። ነሀሴ 1943 ዓም ላይ ንብረትነቱ የነጮች የሆነ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ኩባንያ የአውቶብስ አገልግሎት ዋጋ ከአራት ሳንቲም አንድ ሳንቲም ጨምሮ ከፍ አደረገ። እነማንዴላ ህዝቡ ባውቶብሶቹ እንዳይሳፈር አድማ ጠሩ ( ቦይኮት ) ዘጠኝ ቀን አውቶብቹ ሰው የሚባል አጠገባቸው አልደርስ አለ። ኩባንያው ተሽመድምዶ ቁጭ አለ። ጠባቂውና ተንከባካቢው ዘረኛው የነጮች መንግስት ህዝቡን ደብድቦ ባውቶሶቹ እንዲገለገሉ ማድረግ አልቻለም። ዘሮቹን አጽናንቶ ከባጀቱ ለኪሳራው ማካካሻ ከመስጠት በቀር። የህዝቡን መቁረጥ የተረዳው ኩባንያ መጀመሪያ በሚያስከፍለው አራት ሳንቲም ስራውን ቀጠለ። አገልግሎቱን ለመስጠት ተገደደ። ህዝብ እንዲህ ለአንድ አላማ በአንድ ድምጽ በአንድ አቋም ጸንቶ እርምጃ ከወሰደ፡ ካልተንጠባጠበ፤ ማናቸውንም የአመጸኞች ስርአት የማንበርከክ ሀይል አለው። አንድ መሆን ያቃተው ህዝብ ግን ዝንተአለም እየተረገጠ ሲገዛ ይኖራል።
ኢትዮጵያን ዳግም በልጆቿ አንድነት ተነሳለች!
ሞት ለወያኔ
lkebede10@gmail.com