(ዘ-ሐበሻ) የኢትዮጵያ መንግስት የደህነነት መስሪያ ቤት ባለፈው እሁድ ኦገስት 11 ቀን 2013 በአዲስ አበባ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሁለት ተቀጣጣይ ባዕድ እቃ የያዙ ሁለት ሲሊንደሮች መገኘታቸውን አስታወቀ። የኢትዮጵያ መንግስት የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎትና የፌዴራል ፖሊስ የጋራ የፀረ ሽብር ግብረ ሃይል በመንግስት ሚዲያዎች ላይ ባሰራጩት ዜና እንደገለጹት ሲሊንደሮቹ በአውሮፕላን ማረፊያው የመንገደኞች መነሻ አከባቢ እንደሚገኙ ጥቆማ ያደረሱት የፅዳት ሰራተኞች ናቸው ብሏል።
የመንግስት ሚድያዎች እንደዘገቡት የፈንጂ አምካኝ ባለሙያዎች ሲሊንደሮቹ ተቀጣጣይና በቀላሉ በእሳት በመያያዝ ጉዳት ማድረስ የሚችሉ መሆናቸውን መረጋገጡን እና ሲሊንደሮቹ የያዙት ተቀጣጣይ ንጥረ ነገር ባህሪም እየተጣራ ነው።
መንግስት ይህን ተቀጣጣይ ሲሊንደር በአዲስ አበባ ኤርፖርት ማን እንዳስቀመጠው ባይገልጽም አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ግን መንግስት ከዚህ ቀደም ካለው ባህሪ አኳያ ራሱ ሲሊንደሩን አስቀመጦ በአንድ ድርጅት ላይ ለማላከክ ነው ይላሉ። አስተያየት ሰጪዎቹ ጨምረውም ከዚህ ቀደም መንግስት ኦነግን ለማስጠላት የትግራይ ሆቴልን ጨምሮ የተለያዩ ቦታዎችን በማፈንዳት ኦነግን በአሸባሪነት መፈረጁን፣ ይህን ሆቴል አፈነዱ ተብለው በቴሌቭዥን የቀረቡት ሰዎች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በሌላ ጊዜ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ መገነታቸውን፤ በግንቦት 7 ላይም አኬልዳማ ድራማን ለመሥራት የጠቀመውን በማስታወስ አሁን በአዲስ አበባ ኤርፖርት ተቀመጠ የተባለውን ተቀጣጣይ ሲሊንደር ከመንግስት ውጭ ሌላ ሰው ያደርገዋል የሚል እምነት እንደሌላቸው አስታወቀዋል።