Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Art: አማኑኤል ይልማ –ከታዋቂ ድምፃዊያን ጀርባ ያለ ታላቅ የሙዚቃ ሰው

$
0
0

amanuel & Aster
ዘርፈ ብዙ የኪነ ጥበብ ባለሙያ ነው፡፡ የሙዚቃ አቀናባሪ፣ የግጥምና ዜማ ደራሲ፣ የሙዚቃ ፕሮዲውሰር፣ የቪዲዮ ክሊፕ ፕሮዲውሰርና የፊልም ተዋናይ! አማኑኤል ይልማ፡፡
ለጌዲዮን ዳንኤል፣ ኃይልዬ ታደሰ፣ ሸዋንዳኝ ኃይሉ፣ አለማየሁ ሂርጶ፣ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ ማዲንጎ አፈወርቅ፣ ብርሃኑ ተዘራ፣ ጸሐይ ዮሐንስ፣ ኤፍሬም ታምሩ፣ ማቲያስ ተፈራ፣ ጥበቡ ወርቅዬ፣ ግርማ ተፈራ፣ አቦነሽ አድነው፣ ፋሲል ደመወዜና ሌሎችም በርካታ ድምፃዊያን በአልበማቸው ውስጥ በግጥም፣ በዜማና በቅንብር ተሳትፎ አለው፡፡ እንዲሁም የተለያዩ ድምፃዊያንን ሙሉ አልበም አቀናብሮ ፕሮዲውስ አድርጓል፡፡ በቅርቡ ‹‹ዜማ አማን›› በሚል ኃይለየሱስን፣ ትዕግስትን፣ ህብስትን፣ ብዙአየሁን፣ ግርማ ተፈራን፣ ገረመውንና ፀጋዘአብን ያካተተ ኮሌክሽን አልበምም በፕሮዲውሰርነት አቅርቧል፡፡ በሚዲያዎች ራሱን ለማስተዋወቅ እንብዛም ግድ የሌለውን አማኑኤል ይልማን አነጋግረነዋል፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- በኢትዮጵያ ሚሊኒየም ጊዜ የነበረውን በአል ለማክበር ከ50 በላይ ድምፃዊያን የተለያዩ ሙዚቃዎችን አውጥተው ነበር፡፡ ነገር ግን ከሁሉም ጎልተው የወጡት አንተ ያቀናበርካቸው የቴዲ አፍሮ ‹‹ጊዜ ለኩሉ›› እና የብርሃኑና ማዲንጎ ‹‹አንበሳው አገሳ›› ነበሩ፡፡ ያ እንዴት ሊሆን ቻለ?
አማኑኤል፡- እንዳልከው የ2000 በአልን ለማክበር ህዝቡን ለማንቀሳቀስ ብዙዎች ዘፈኖችን ሰርተዋል፡፡ በዚያ አጋጣሚ አንዱ ሆኜ እንደዜማ ደራሲና እንደ አቀናባሪ ተሳትፌ ነበር፡፡ ዕድለኛ ያደረገኝ እኔ የሰራሁት ዘፈን ህዝቡ የተቀበለው ሆነ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የቴዲ አፍሮ ‹‹ጊዜ ለኩሉ›› ወይም ‹‹አበባ አየህ ወይ›› የሚለው ዘፈን ሲሆን፣ ከዛ በመቀጠል ‹‹አንበሳው አገሳ›› የሚለው በብርሃኑ ተዘራና ማዲንጎ አፈወርቅ የተዜመው ነው፡፡ በጊዜው በታዋቂ ድምፃዊያን ጭምር የተሰሩ ብዙ ዘፈኖች ውድድሩ ውስጥ ነበሩ፡፡ ከእነዛ ውስጥ ግን በተለይ ‹‹አበባአየህ ወይ›› በአንድ ጊዜ ሒት ሆኖ ወጥቷል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የምነግርህ ያኔ ከቴዲ ጋር ብዙ አብረን ስንጓጓዝ ‹‹ቴዲ አትዘፍንም ወይ?›› እያሉ ይጠይቁት ነበርና በጣም የተጨነቀበት ወቅት ነበር፡፡ ምን ይዤ ልምጣ? ብሎ በተጨናነቀበት ወቅት ሌሎች ስራዎችን ስንሰራ ቆይተን አበባአየህ ወይን ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ነበር የጀመርነው፡፡ ወደ 11፡00 ሰዓት ላይ ጨረስነው፡፡ ከዚያ በኋላ ምንም ግጥም አልጨመረም፡፡ ድጋሚም አልዘፈነውም፡፡ አንዴ ስቱዲዮ ውስጥ የተሰራ ስራ ነው፡፡ ዜማና ግጥሙ የቴዲ አፍሮ ነው፡፡ ቅንብሩ ከእነሚክሲንጉና ማስተሪንጉ የእኔ ነው፡፡ ከዛ በኋላ የብርሃኑና የማዲንጎ ‹‹አንበሳው አገሳ›› ወጣ፡፡ (ዜማው የህዝብ፣ ግጥሙ የመሰለ ጌታሁን ሲሆን ቅንብሩ ሙሉ በሙሉ የእኔ ነው) ሁለቱም ላይ የሰቀሉ ዘፈኖች ነበሩ፡፡ እኔን የሚሊኒየሙ ዕድለኛ ያደረገኝ ሁለቱም ዘፈኖች ዓመት በዓል በመጣ ቁጥር የምንሰማቸው ማለትም ድሮ ከነበሩት ከእነጥላሁን ገሠሠ፣ ከእነ ብዙነሽ በቀለ የአመት በአል ዘፈኖች ጋር በማይተናነስ መልኩ እየተሰሙ ዘመን ተሻጋሪነታቸውን በማስመስከራቸው ነው፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- በተለይ የቴዲ አፍሮን ‹‹ጊዜ ለኩሉ›› ቢዮንሴ አዲስ አበባ መጥታ በሰራችው ኮንሰርት መድረክ ላይ ተጫውተው ደንሳበታለች፡፡ ያ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ብታጫውተኝ?
አማኑኤል፡- በወቅቱ እኔም እዚያው ሚሌኒየም አዳራሽ ነበርኩ፡፡ እና ሰርፕራይዝ ያደረገች ጊዜ እንደማንኛውም አድማጭ ደንግጫለሁ፡፡ በጣም አሪፍ ነበር፡፡ ሙዚቃውን የመረጠችው ሳውንድ ማኗ ናት የሚል ነገር በኋላ ሰምቻለሁ፡፡ እርግጥም በዚያን ጊዜ የሳውንዱ ግሩቭ (Groove) በጣም ሒት ነበረ፡፡ ብዙ ጊዜ እንደ አጋጣሚ ሆኖ እንደዚያ አይነት ሚክሲንግ አልተሰራም ነበር፡፡ በመሆኑም ሳውንድ ማኗ ወደደችው፡፡ በሳውንድ በኩል በጣም ብዙ የሚጠበቅብን ነገር ያለ ቢሆንም በወቅቱ ግን ያ ሳውንድ በቂ እንደነበረ አምናለሁ፡፡ በተጨማሪም ያን ጊዜ በመላው ኢትዮጵያ ይለቀቅ የነበረው ይህ ዘፈን ነበር፡፡ ህዝቡ ያብድበት የነበረ በመሆኑ የቴዲ አዘፋፈንም ምርጥ ስለነበረ መርጠውታል፡፡ በአጠቃላይ በዚያ የሚሌኒየም ወቅት ለቢዮንሴ ይመጥን የነበረ ሙዚቃ ስለሆነ ነው ብለን ብንወስደው ደስ ይለኛል፡፡
amanuel & ephrem Tamru
ዘ-ሃበሻ፡- ብዙ ጊዜ በግጥምና ዜማ ስራዎችህ ላይ እውነተኛ ታሪኮችን ወደ ሙዚቃ እየቀየርክ እንደምታቀርብ ይሰማል፡፡ ይህን ስታይል የመረጥከው ለምንድን ነው?
አማኑኤል፡- ይሄን ጥያቄ ለመመለስ ትንሽ ወደኋላ መለስ ብዬ ልጀምርልህ፡፡ ከያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት የተመረቅኩበት መሳሪያ ደብል ቤዝ ይባላል፡፡ ፒያኖ ማይነሬ ሲሆን፣ በባህል መሳሪያ ማሲንቆን ተጫውቻለሁ፡፡ ማሲንቆ በጣም ዜመኛ ያደርጋል፡፡ ከዚያ ውጭ ደግሞ የአዝማሪ ግጥሞችን መስማት በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ረጅም ጊዜ እየሄድኩኝ የእነሱን ስራዎች እከታተላለሁ፡፡ አንድ የአዝማሪ ስራንም ፕሮዲውስ አድርጌያለሁ፡፡ እንደነዚህ አይነት በድሮ ጊዜ የሚሰሩ ነገሮች ሪያሊቲ አላቸው፡፡ ለምሳሌ ከድሮ ድምፃዊያን የማደንቀው የጋሽ ባህሩ ቀኜ ግጥሞችን ነው፡፡ በዚህ ዘመን ‹‹አንጣላ›› ብሎ የሚዘፍን የለም፡፡
ልቤን ጅብ በበላው ባወጣው አጥንቱ፣
ተጣልቶ መታረቅ አይሆን እንደ ጥንቱ፡፡
የመሳሰሉ ግጥሞች ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ቀድመው የሚነግሩህ ናቸው፡፡ እንደዚህ አይነት ፍልስፍና ውስጥ ስትገባና ይህን እያዳበርከው ስትሄድ፣ ላይፍን ወደ ሙዚቃ አምጥተህ የሰውን ታሪክ ስትፅፍ ከዛ የበለጠ ቀድመህ ሁሉ መድሃኒት ታዘጋጃለህ፡፡ እኔ ደግሞ ፊት ለፊት ያሉኝን ችግሮች ወደ እውነተኛ ታሪክ ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ ለምሳሌ በአንድ ዘመን እሰራቸው የነበሩት ስራዎች በአብዛኛው አፍቅሮ የተጎዳ ሰው ላይ ያመዝን ነበር፡፡ የተወሰኑትን ብጠቅስልህ ‹‹እንዳረከኝ አድርገኝ፣ ሳታመሀኝ ብላ፣ ኋላ እንዳይቆጭሽ፣ በአይኔ ላይ ዋልሽሳ በአይኔ፣ የማታ ማታ…›› ሌሎችም አሉ፡፡ በሴት ደግሞ የነፃነት አየለ ‹‹ላያገባኝ›› አለ፡፡ ማለትም እንዴት ይሄ ሁሉ ጊዜ አልፎና ዛሬ ከእኛ አልፎ ለሰው ተርፎ፣
ለካ ይሄን ሁሉ ጊዜ እያለፋኝ ነበረ ለካ
ሳያገባኝ እያለች የምትጫወተው ማለት ነው፡፡
ይህም አንዲት ሴት ረጅም ዓመት አንድ ወንድ ይዟት ሄዶ ጊዜዋን ሁሉ ገድሎ በመጨረሻ ሳያገባት ሲተዋት ያመላክታል፡፡ የብዙ ሴቶችን፣ ችግር ያሳየሁበት ነው፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- በጎሳዬ ተስፋዬ የተዘፈነውን ‹‹ሳታመሀኝ ብላ›› ግጥም የፃፍከው ከእውነተኛ በምታውቀው ሰው ላይ ከደረሰ አጋጣሚ ተነስተህ መሆኑም ይነገራል፡፡
አማኑኤል፡- ልክ ነህ፡፡ ‹‹ሳታመሀኝ ብላ›› ትልቅ ታሪክ ነው፡፡ በአንድ የቅርብ ጓደኛዬ የደረሰ ታሪክ ነው፡፡ አንድ ሰው የሚወደውን ጓደኛውን በምን መንገድ እንደሚያጣው፣ ሚስቱን ደግሞ በጓደኛው እንዴት እንደሚያጣ የሚገልፅ ነው፡፡ የክሊፑ አለመሰራት ዘፈኑን በውስጥ ደረጃ አስቀረው እንጂ ትልቅ ታሪክ ያለው ነው፡፡
የሚገርምህ ከዚህ ዘፈን ጋር በተያያዘ ብዙ ገጠመኝ አለኝ፡፡ ለምሳሌ ‹‹እንዴት ሰውን ጅብ ትላለህ?›› ያሉኝ ሰዎች ነበሩ፡፡ እኔ ግን ‹‹ጅብ›› ስል በልመናና በጨዋነት ነበረ የገለፅኩት፡፡
አንቺም ትዳሬ ነሽ እሱም ጓደኛዬ፣
ጥፋቱ የማን ይሆን ስሄድ አንችን ጥዬ፣
አወይ ክፉ ዘመን ልቤ አዘነብሽ
እሱም ተሳሳተ የእኔ እናት አንቺም አልታመንሽ
ታማኝ ያንቺ ገላ ያለኔም አያውቅም
ምነው ደከመሳ አነሰው ወይ አቅም
ስደተኛ ታርገኝ ደሞ ብላ ብላ
ጅብ ረሃብ አይችልም ብለህ ወንድሜ ሳታመሀኝ ብላ
አየህ ‹‹ወንድሜ›› ነው ያልኩት፡፡ ጭካኔ የለውም፣ ግን መልዕክቱ ሃያል ነው፡፡ በጓደኛዬ ላይ የደረሰው ህመም ነው ያንን እንድፅፈው ያደረገኝ፡፡ ብዙዎች ይህ የእኔ ስራ መሆኑን ሲያውቁ የኔ ታሪክ መስሏቸው ደውለው ሀዘናቸውን የገለፁልኝ አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ‹‹የእኔን ታሪክ ነው የሰራህልኝ›› ያሉኝም አሉ፡፡
amanuelዘ-ሃበሻ፡- አንተ በጥሞና ዜማውን የሰራኸውና ኤፍሬም ታምሩ የተጫወተው ‹‹ኋላ እንዳይቆጭሽ›› ሙዚቃም እውነተኛ ታሪክ ነው አይደል?
አማኑኤል፡- ኋላ እንዳይቆጭሽ እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡ በአንድ ጊዜ የሰራሁት ስራ ነው፡፡ ታሪኩን በዝርዝር ባልነግርህም የዚያን ጊዜ የተፈጠሩት ‹‹ኋላ እንዳይቆጭሽ››፣ የጌዲዮን ዳንኤል ‹‹እንዳደረግከኝ አድርገኝ››፣ የፀሐዬ ዮሐንስ ‹‹ፍቅርሽ እንደ ጥላ፣ አንድ በይኝ…›› ወዘተ እውነተኛ ታሪክን መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- አማን አንተ ሌላ የምትታወቅበት ‹‹ለታናሿ ልስጋ›› በሚለው የሙዚቃ ቪዲዮ ነው፡፡ ይህንን ቪዲዮ ግጥምና ዜማ ሰርተህ ከማቀናበርህም በላይ ራስህ ፕሮዲውስና ዳይሬክት አድርገህ ያቀረብከው መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ለመሆኑ ይህን ስራ ለማቅረብ እንዴት ተነሳሳህ? ከአድማጭ ያገኘኸው ምላሽስ?
አማኑኤል፡- የምር ለመናገር ደራሲ ስትሆን፣ በሰው ችግር ውስጥ ማለፍ ስትጀምር፣ ዘፈኖችን ወደ ሪያሊቲ ስታመጣና ወደ እውነተኛው በሄድክ ቁጥር አርቱም ይሳካልሃል፡፡ የምትፅፈው ነገር ይሳካል፡፡ ዳይሬክት የምታደርገው ነገር ሁሉም ወደ እውነት ይቀርብልሃል፡፡ ከቅንነት ከተነሳህ ማለት ነው፡፡ እና የሚገርምህ ነገር በቡና ቤት ሴቶች ላይ፣ በጎዳና ተዳዳሪዎች ላይ፣ በአላቻ ጋብቻ ላይ እንደዚህ አይነት ነገሮችን ለመስራት እያሰብኩ ባለሁበት ሰዓት ወደ ገጠር ውስጥ እየሄድኩ፣ በቀንም በማታም ያለውን ሁሉ እያየሁ እየቀረብኩ እፅፍ ነበር፡፡ እና በዚህን ወቅት አንዲት ልጅ በጣም አዝና አየሁኝ፡፡ ያቺ ልጅ በሀዘን አገጯን የያዘች፣ ከንፈሯ የሚንቀጠቀጥ፣ እንባ ያቀረረችና ደንግጣ የተቀመጠች ነበረች፡፡ እኔም የፃፍኩት ያንኑ ነው፡፡ ግጥሙንም ስፅፈው፤-
እንባ አዝሎብኝ አይኖቿ፣
መዳፏ አልፎ ከጉንጮቿ
እንባዋ ይፈሳል ሳያባራ
ብቻውን ያወራል ከንፈሯ
እያልኩ ጀመርኩት፡፡ ከዚያ ይህችን ህፃን ሊድሯት፣ ቤተሰቦቿም ፈረዱባት፣ እያልኩ ዘፈኑን እየሰራሁት ይህን ዘፈን በደንብ ሊጫወተው የሚችለው ማነው? የሚለው ውሳኔ የኔ ነበር፡፡ ጎሳዬን መረጥኩት፡፡ እንደውም ለጎሳዬ ክፍያ ስከፍለው ‹‹እንዴት እንደዚህ አይነት አይዲያ?›› ሲለኝ ግድየለህም ብዬ አስጀመርኩት፡፡ ከዚያ ቡሬ አንድ ጥጃ አጠገቧ ስለነበረች ‹‹ቡሬ ቡሬ ቀናችን አይደለም እኔና አንቺ ዛሬ፣ አለጊዜው ታርደሽ አለጊዜው ተድሬ›› የሚለው በመስታወት አራጋው ተቀረፀ፡፡ ታገል ሰይፉም ገባበት፡፡ በእንደዚህ አይነት ተቀረፀ፡፡ ዘፈኑን ከቀረፅን በኋላ የዚህን እውነተኛ ታሪክ ሰው ጭፈራ ይመስለዋል፡፡ ምክንያቱም ሲሰማው እንደዘፈን የሚያደምጠው ነው፡፡ ስለዚህ ክሊፑን በመስራት መልዕክቱን ህዝቡ እንዲረዳው ማድረግ ያስፈልግ ነበር፡፡ የዚህንም ሪስክ ወስጄ ወደ 50 ሺ ብር በማውጣት ክሊፑን አሰርቼዋለሁ፡፡ እዛ ውስጥ ያለ ሁሉ ድምፃዊ፣ አንባቢ ተከፍሎታል፡፡ ይሄ ሁሉ አልፎ እስካሁን ከሰራኋቸው በርካታ ስራዎችና ሙዚቃዎች በላይ በየሄድኩበት ዓለም ሁሉ ‹‹ለታናሿ ልስጋ›› ነው የሚሉኝ፡፡ ምክንያቱም በህዝብ ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት ያገኘሁበት በዚህ ስራ ነው፡፡ እንደምታውቀው የአላቻ ጋብቻን በተመለከተ ብዙ ወረቀቶች፣ ብዙ ወርክሾፖች፣ ብዙ ስብሰባዎች ተደርገዋል፡፡ ግን በሰባት ደቂቃ አንድ የሙዚቃ ክሊፕ ብዙ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል መሆኑን ብዙዎች መስክረውለታል፡፡ ሰውን እያዝናና ለቀጣዩዋ ለታናሿ ደግሞ ይታሰብበት በሚል መንገድ የቀረበ በመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓም፣ በአሜሪካም፣ በካናዳም አውስትራሊያም፣ አረብ አገር ጭምር ያሉት የወደዱትና እንዲዘፈን ደጋግመው ያዩት ክሊፕ ሊሆን ችሏል፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- በቅርቡም ሌላ ይህን መሰል ክሊፕም ሰርተሃል? ይህኛውስ?
አማኑኤል፡- አዎ፣ በቅርብ ጊዜ ድጋሚ ከጎሳዬ ጋር ሰርቻለሁ፡፡ ያቀናበረው አበጋዝ ነው፡፡ ግን ዜማውም ግጥሙም የእኔ ነው፡፡ ‹‹ፍጥረትን እንደቀላል›› የሚል ነው፡፡ ይህኛው ደግሞ ህፃናቶችን ብዙ ጊዜ ከገጠር እያመጡ ዘመድ ጋ ይቀመጡ በሚልና በተለያየ መንገድ በማምጣት ትልልቅ ስራ ከአቅማቸው በላይ ያሰሯቸዋል፡፡ እኔም የሰራሁት ያንን በመቃወም ነው፡፡ ይህም ስራ አስተማሪ፣ ትልቅ ተቀባይነት ያገኘና ማህበረሰቡን የሚነካ፣ ለውጥና ዕድገትን የሚያመጣ የህፃናትን ኃላፊነት እኛ መውሰድ እንዳለብን የሚያስገንዘብ ሆኗል፡፡ እንደ አጋጣሚ ይህን ያሰራኝ አንድ ድርጅት ነው፡፡ ለታናሿ ልስጋን አይተው በዚያ መንገድ እንዲሰራላቸው ፈልገው ጠይቀውኝ ቦታው ድረስ ሄጄ፣ እንዴት ሽመና እንደሚያሸምኗቸው እህል እንዴት እንደሚያስፈጯቸው ከባባድ ስራ ሲያሰሯቸው አይቼ በጣምም እንዳይከፉ አድርጌ ቀለል አድርጌ የሰራሁት ነው፡፡ ግን ያለው ሁኔታ በዚህ መንገድ ብቻ የሚገለፅ ሳይሆን ሁለትና ሶስት እጥፍ የበለጠ መገለፅ የሚችል ነው፡፡ እኔ ግን የማምነው ማንኛውንም አይነት ችግር ነገሮችን በማቅለል ማህበረሰቡ በሚረዳበት መንገድ ማስተማርና ማዝናናት እንዳለብን ነው፡፡ በመሆኑም ያቀረብኩት በዚህ ሁኔታ ነው፡፡ ከሁለቱ ስራዎቼ በተጨማሪ በቀጣይነት እንደዚህ አይነት ስራዎችን ማለትም ማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ችግር እየፈለፈልኩ የማውጣት አቋም አለኝ፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- እስቲ ስለዜማ ላሰታስ ባንድስ እናውራ፡፡ እንዴት ተቋቋመ? እንዴትስ ሊፈርስ ቻለ?
አማኑኤል፡- እኔ ዜማ ላስታስ ባንድ ለሙዚቃ ዕድገት አንድ መሰረት ነው ብዬ የማምንበት ነው፡፡ ከያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት የተመረቅን ልጆች ማለትም ኤልያስ መልካ፣ ሁንአንተ ሙሉ፣ ሚካኤል መላኩ፣ ምስጋናውና እኔ ሆነን ያቋቋምነው ሲሆን፣ ስንጀምር ድምፃዊዎች ትዕግስት በቀለ፣ ሚካኤል በላይነህ፣ እዮብ መኮንን፣ ኃይሌ ሩትስ ባንዱ ውስጥ ነበሩ፡፡ ባንዱ ትልቅ የሳውንድ ለውጥ ይዞ የመጣና አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነበር፡፡ ባንዱ ሊፈርስበት የቻለው ዋንኛ ምክንያት ሁላችንም ወደየስራችን ስቱዲዮ መበታተናችን ነው፡፡ መጀመሪያ ኤልያስ መልካ፣ ቀድሞን የራሱን ስቱዲዮ ሲከፍት ሁንአንተ ተከተለው፡፡ ከዚያ እኔም ወደ ስቱዲዮ ገባሁ፡፡ ከዚያ የየራሳችንን የስቱዲዮ ስራ ስንሰራ ወደ ባንዱ ለመስራት ስላልቻልን ሊፈርስ ችሏል፡፡ ይሁንና ባንዱ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የዓለማየሁ እሸቴ፣ የባህት ገ/ህይወት፣ የፍቅር አዲስና የመሳሰሉትን የድሮ ሙዚቃዎች አምጥተን በጥሩ ሁኔታ ቀርፀን ሰው በሚገርም ሁኔታ ተቀብሎታል፡፡ በዚያ ሳውንድም ባንዱ በጣም አሪፍ ከሚባሉት ባንዶች ስሙን አስቀምጦ ለማለፍ ችሏል፡፡
amanuel teddy afro and maritu legesse ዘ-ሃበሻ፡- አንተ በሙዚቃ ስራ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ለመዞር የቻልክ ነህ፡፡ የአቡጊዳ ባንድ ውስጥ ተካተህም ከቴዲ አፍሮ ጋር ብዙ መድረኮች ላይ መስራትህን አውቃለሁ፡፡ የሙዚቃ ጉዞህን በተመለከተ እናውራ?
አማኑኤል፡- የሚገርምህ ከታዋቂ ድምፃዊያን ጋር ወደ ውጭ አገራት ከመሄዴ በፊት ከያሬድ ት/ቤት እንደተመርቅኩኝ አንድ ‹‹ፎርኤቨር ያንግ›› የሚል የባህል ቡድን አቋቁሜ ነበር፡፡ ከዚያ ቡድን ጋር ሀኖቨር የባህል ኤክስፖ በተዘጋጀበት ወቅት ከዛሬ 13 ዓመት በፊት በመሄድ ጀምረን በተከታታይ ለአንድ 6 ዓመታት የተለያዩ ቦታዎች ሰርተናል፡፡ ከዚያ ስቱዲዮ ከመግባቴ በፊት ከእነፍቅር አዲስ፣ ኃይልዬ፣ ይርዳው፣ ህብስት ቴዲ አፍሮን ጨምሮ ራሴ ፕሮሞተር እየሆንኩኝ ከአገር ውስጥ እስከ አረብ አገሮች እሰራ ነበር፡፡ የመጨረሻ ጉዞዬን ያደረግኩት ደግሞ ከቴዲ አፍሮ አቡጊዳ ባንድ ጋር በመቀላቀል ነው፡፡ ከአቡጊዳ ጋር ከ24 ሾው በላይ ሰርቻለሁ፡፡ ይህም በመላ አውሮፓ፣ አረብ አገራት፣ እንዲሁም አሜሪካና ካናዳ ዞሬያለሁ፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- ምንም አልበም ሳይኖረው በመላው ዓለም ታዋቂ ለመሆን የበቃው ጃኪ ጎሲ (ጎሳዬ ቀለሙ) ከዚህ ቀደም በዚሁ ዘ-ሃበሻ ጋዜጣ ቃለ ምልልስ ሲያደርግ አንተን አመስግኗል፡፡ ከስኬቱ በስተጀርባ ያለህ ቁልፍ ሰው መሆንህንም ተናግሯል፡፡ ለመሆኑ ከጃኪ ጋር የነበራችሁ የስራ ግንኙነት ምን ይመስላል?
አማኑኤል፡- ጃክ ከጥቂት ዓመታት በፊት እኔ ጋር ሊሰራ በአጋጣሚ ወደ ስቱዲዮ መጥቶ ነበር፡፡ ይዞት የመጣው ስታይልም ትንሽ ወጣ የሚል ነው፡፡ ማለት ከአማርኛ ሙዚቃዎች ወጣ ያለና እንደ ሒፕ ሆፕ አይነት ነገር ነበር፡፡ እና የሒፕ ሆፕ ስታይሉን በሚያሰማኝ ጊዜ ልጁ አንድ ቃናና በጣም የሚገርም ድምፅ እንዳለው ተረዳሁ፡፡ ይሄን ድምፁን ደግሞ በእርግጠኝነት የሌላ ዜማ ስታይል ቢሰራበት ጥሩ ይሆናል በሚል ትንሽ ደቂቃ ተነጋገርን፡፡ ልጁም ጥሩና ቅን ስለሆነ ወዲያው ተመለሰ፡፡ ምክንያቱም የዜማ ደራሲ ስትሆን የመጀመሪያው ነገርህ ሰው መፍጠር ነው፡፡ አንድን ድምፃዊ አምጥቶ መስራት እንደማለት ነው፡፡ እንደፊልም ለዚህ ተዋናይ ይህን ካራክተር ብሰጠው ይዋጣለታል ብሎ መቅረፅ ነው፡፡ ስለዚህ በዚያ መንገድ የመጀመሪያውን ‹‹ጭራሽ›› የሚለውን ሰራሁለትና ይዞት ወደ አገሩ ሄደ፡፡ እዛ ከለቀቀ በኋላ አቀባበሉ የሚገርም ሆነ፡፡ እኔ መልዕክቱንም ስፅፈው ውጭ አገር ስላሉ ሰዎች በመለያየትና በመነፋፈቅ ውስጥ እንዴት እንደሚተሳሰቡ በሚያደርግ ስሜት ነበር፡፡ በመሆኑም ውጭ አገር ያሉ ሰዎች በጠቅላላ ወደዱት፡፡ ከዚያ ከስድስት ወር በኋላ ደወለልኝና ‹‹ዘፈኑ በጣም ቡም ብሏል›› አለኝ፡፡ አላመንኩም፡፡ ‹‹እውነትህን ነው?›› አልኩና ዩቲዩብ ላይ ሳየው ደነገጥኩኝ፡፡ የሚገርምህ ወደ 2 ሚሊዮን 800 ሺ ህዝብ አይቶለታል፡፡ በደወለልኝ ጊዜ ሌላ ዘፈን እንዳዘጋጅለት በጠየቀኝ መሰረት ‹‹ደሞ አፌን›› ሰራሁለት፡፡ የመጀመሪያው የባህል ዘመናዊ ሲሆን ይህ ግን ችክችካ አይነት ለመድረክ የሚሆን ነው፡፡ ከዚያ፣ በየኮንሰርቶች ተመራጭ ለመሆንና ለመስቀል ቻለ፡፡ ቀጥሎ ‹‹ሰላ በይ›› የሚለውን በሌላ ስቱዲዮ መጥቶ ሰራው፡፡ እሱም ውጤታማ ሆነለት፡፡ ይሄ ልጅ የተሾመ አሰግድን ‹‹የእኔ አካል›› የሚለውን ድጋሚ በመዝፈን አንድ ዘፈን ጨምሮ በአራት ዘፈን በዓለም ላይ እየተዘዋወረ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
እኔ ለጃክ የመጀመሪያውን ሙዚቃ ግጥምም ዜማም ቅንብርም ስለሰራሁለት ሊያመሰግነኝ ቢችልም፣ እኔ ደግሞ በጣም ብልህ ልጅ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ለምን ብትል በደራሲ ያምናል፡፡ የድሮዎቹን ትልቅ ደረጃ የደረሱት እነ ኤፍሬም ታምሩን ብትመለከት ለረጅም ጊዜ የሰሩት ደራሲዎችን ይዘው በመምጣታቸው ነው፡፡ ልጁ በዚሁ ከቀጠለ ታዋቂዎቹ የደረሱበት ቦታ የማይደርስበት መንገድ የለም፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- ብዙውን ጊዜ የድሮ ድምፃዊያንን በተለያዩ መንገዶች ታነሳለህ፡፡ ለምንድን ነው?
አማኑኤል፡- ያለጥርጥር እኔ የድሮዎቹ ድምፃዊያን አድናቂ ነኝ፡፡ ከ50ዎቹ ጀምሮ የነበሩት በተለይ ባህሩ ቀኜ፣ አሰፋ አባተ፣ ወደዚህ ስትመጣ ጋሽ ይርጋ ዱባለ በጣም ድምፃዊ ናቸው፡፡ በዚያን ጊዜ የሚያገኙት ግጥምም ሆነ ዜማ ያስገርመኝ ነበር፡፡ በተለይ ጋሽ ባህሩ የሚፈጥረው ዜማና ግጥም በጣም ለኢትዮጵያ ሙዚቃ መሰረት የነበረና ለረጅም ዓመት የተደመጠ ነው፡፡ ወደዚህ ስንመጣ ደግሞ የእነ ጥላሁን፣ የእነ ብዙነሽ፣ የእነ ሒሩት ዘመን አለ፡፡ ሲቀጥል ሮሀ ባንድ፣ በ70ዎቹ እነ ኤፍሬም ታምሩ፣ ሙሉቀን መለሰ፣ ቴዎድሮስ ታደሰ፣ አስቴር አወቀ እያልን መዘርዘር እንችላለን፡፡ እነዚህ ሰዎች ሙዚቃን ለ40 እና 30 ዓመታት ያሻገሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ እንደቀላል አይታዩም፡፡ አሁን የእኛ አገር ሙዚቃዎች ለሶስትና ለአራት ወር ተሰምተው ሲቆዩ እንደትልቅ ነገር የምናይበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ስለዚህ እኔ የዚያን ጊዜ ሰዎች በምን መንገድ ቢሰሩት ነው ቴክኖሎጂ በሌለበት ሰዓት፣ በአናሎግ ሲስተም እየቀዱ፣ ኮምፒውተር ሳያግዛቸው፣ ላይቭ እየቀዱ፣ ወጣቱ በእነሱ ዘፈን እየተማረከ እኛ እንዴት እንደነሱ መስራት አቃተን? የሚሉ ጥያቄዎች ስላሉኝ ያኛው ትውልድ ይበልጥብኛል፡፡ ይሄ የእኔ ብቻ ሳይሆን፣ የአድማጭ፣ የህዝብና የአርቲስቱ ጥያቄ ይመስለኛል፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- የዚህ መፍትሄው ምንድን ነው ትላለህ?
አማኑኤል፡- አንደኛው ነገር ራሳችንን እየሆንን አይደለንም፡፡ ራሳችንን መሆን መቻል አለብን፡፡ ሁሉም በየፊናው የተለያየውን ዓለም ሙዚቃ ይሰራል፡፡ አይስራ አልምም፡፡ በስታይሉ ውስጥ ደግሞ ስራውን በማቅለል ደረጃ በአንድ ሞኖ ስቱዲዮ (ሆም ስቱዲዮ) ውስጥ በመሰራቱ አንድ ሰው ሙዚቃውን እንደፈለገው ማድረግ ጀመረ፡፡ ድምፃዊያኑም ስለቀለለው ገባ፡፡ መአት ድምፃዊያን ተፈጠሩ፡፡ ግን ከዚያ ውስጥ ምን ያህሉ ድምፃዊ ነው? ብለህ ብታስብ ሁሉም አይደሉም፡፡ ስለዚህ ህዝቡንም አሰለቸነው፡፡
እኛ የእኛነት የምትለው ነገር የለም፡፡ ሬጌው ምን ያህል በኢትዮጵያ ሄዷል? ብትል የለም ገና መጀመሩ ነው፡፡ ሒፕ ሆፕ አለ ወይ? ብትል ሒፕ ሆፕ የሚባል ሙዚቃ የት አለ? ሌላው ዓለም መጥቶ ሲሰማን በጣም ያዝንብናል፡፡ በየስቱዲዮው ነጮቹ ጥቁሮቹ መጥተው አይተው የተሰማቸውን ስሜት አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በዚህ ትውልድም እንደድሮው የራሳቸውን ቀለም ይዘው መስራት እንዳለባቸው ይሰማኛል፡፡ ኢንዱስትሪው እንዲያድግና አድማጭ እንዲሰማን ከፈለግን ጥሩ ዜማ፣ ለግጥሙም መጨነቅ፣ ለአሬንጅመንቱም መጨነቅና ጥሩ ድምፃዊም መስራት ያስፈልገናል፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- የሙዚቃ አቀናባሪ፣ የግጥምና ዜማ ደራሲ፣ የሙዚቃ ቪዲዮ ክሊፕ ዳይሬክተር ፕሮዲውሰር ስለመሆንህ እስካሁን በነበረን ቆይታችን ስናወራ ቆይተናል፡፡ አሁን ደግሞ በፊልሙ ዓለም ስላለህ ተሳትፎ እናውራ፡፡ እንችላለን?
አማኑኤል፡- ይቻላል፡፡ ስለፊልም ካነሳን የመጀመሪያው ‹‹የማያልቀው መንገድ›› ነው፡፡ እንኳን እኔ ኢትዮጵያ ውስጥም ፊልም ገና እየገባ በነበረበት ከዛሬ 10 ዓመት በፊት ነበረ፡፡ የያኔው ከነበረው ሁኔታ አንፃር ጥሩ ነው፡፡ ወደ አሁኑ ዘመን ስንመጣ ‹‹ፔንዱለም›› እና ‹‹ከመጠን በላይ›› የሚሉ ፊልሞች ላይ ሰርቻለሁ፡፡
የፔንዱለም ፕሮዲውሰር ቶማስ ጠርቶ ሲፈትነኝ ሌሎች ዳይሬክተሮችም ይዞ ነበር፡፡ ከተፈተንኩ በኋላ የተቀረፅኩትን በቪዲዮ ስመለከተው እውነቴን ነው የምልህ ጠላሁት፡፡ እናም ‹‹እኔ መግባት የለብኝም፡፡ እኔ አልሆናችሁም›› አልኳቸው፡፡ ግን ዳይሬክተሩ ለዚህ ቦታ አማን ይሆናል ብሎ ከወሰነ ሪስኩን ይወስዳል፡፡ ስለዚህም ‹‹ይህን ልጅ እለውጠዋለሁ፣ በዚህ አይነት ፎርም አመጣዋለሁ›› ብሎ ስላሰበ ዳይሬክተሩንም አምኜ ገባሁበት፡፡ እውር አሞራ እንደማለት ነው የማታውቀው ነገር ውስጥ መግባት፡፡ በዚህ መንገድ ሰራሁ፡፡ ፊልሙ እስኪያልቅ ድረስ ስቱዲዮ ዘግቼ ነው የሰራሁት፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- የፔንዱለም ፊልም ምርቃት ከተማውን ሁሉ በነቀነቀ ሁኔታ ነበር የተከናወነው፡፡ በዚህ ረገድ የአንተም ወሳኝ ድርሻ እንደነበረበት ሰምቻለሁ፡፡ እውነት ነው?
አማኑኤል፡- ፊልሙ ከተጠናቀቀ በኋላ በአንዳንድ ቦታዎች ማስታወቂያውን ሰማሁ፡፡ ያኔ ለፕሮዲውሰሩ ቶም ደወልኩለትና መተዋወቅ ያለበት በዚህ አይነት መንገድ አይደለም አልኩት፡፡ ምክንያቱም እንደ አበባዮሽ አይነት እን ደጃኪ አይነት ስዎች ጎልተው ሲወጡ ደስ ይለኛል፡፡ ዘፈን ከተሰራ ጎልቶ መውጣት አለበት፡፡ ፊልምም ቢሆን እንደዚያው ነው፡፡ ስለዚህ የሚዲያውን ስራ ሁሉ ጠቅልዬ ያዝኩት፡፡ እንደውም የማልረሳው ለሳውንድ ትራኩ ብዙአየሁ ብዙ ብር ጠየቀ፡፡ እኔ ‹‹በቃ ራሴ እገዘዋለሁ›› ብዬ አሰራሁትና ጨርሼ ቶምን ሰራሁት፡፡ ቶምም ሲሰማው ዘፈኑን ሳላጋንን ከ30 ጊዜ በላይ ቆሞ ሰማው፡፡ ፊልሙን ግልፅ አድርጎ የሚያሳይ በመሆኑ ዘፈን ይሄን ያህል ፓወር አለው ወይ? ብሎ ደነገጠ፡፡ ከዚያ ተጀመረ፡፡ ቶም ሁሉንም ወጪ አወጣለሁ በማለቱ ወደ ሚዲያ መጥተን ሬዲዮኑን ተቆጣጠርነው፣ ጋዜጦችን ተቆጣጠርን፡፡ ቀጥሎ የሚሊኒየም አዳራሽ ሀሳብ መጣ፡፡ ቀይ ምንጣፍ ታሰበ፡፡ እኔ ወደ ባንድ መጣሁኝ፡፡ ሔለን በርሄ ገባች፡፡ በዚህ ጊዜ ሰዎችን ሳማክር ‹‹እናንተ እብድ ናችሁ ወይ፤ እንዴት ዘፈንና ፊልም አንድ ላይ ይታያል? በዚያ ላይ ሚሊኒየም አዳራሽ›› ብለው አልተቀበሉኝም ነበር፡፡ ግን ነገሮችን ትልቅም ትንሽም የምታደርገው አንተ ነህና በውጥናችን ገፍተንበት በስተመጨረሻ 14 ሺ ሰው መጥቶ ፊልሙን ሊያየው ችሏል፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- ለዚሁ ፊልም ማጀቢያነት ሔለን በርሔ የተጫወተችውን ሙዚቃ በግጥምም በዜማም በማቀናበርም ሰርተሀል፡፡ ይሄ ሙዚቃዋ ደግሞ ከፊልሙም በኋላ በተለያዩ ሚዲያዎች ሲደመጥ ይታያል፡፡ ሙዚቃውን ስታዘጋጅላት ከፊልሙም ውጭ ይደመጣል ብለህ አስበህ ነበር?
አማኑኤል፡- ይኸውልህ አንድ ምሳሌ ልንገርህ፡፡ ‹‹ለካ ለካ ያንተ ዓለም፣ ወዲህ ወዲያ ፔንዱለም›› የምትለዋ የዘፈኑ ግጥም ኤዲት ሲደረግ ነበርኩኝ፡፡ እና ያኔ ‹‹በናታችሁ ልብስ ስለካ እዚህች ቦታ አስገቡኝ›› አልኩ፡፡ ፊልሙ ላይ የምሰራው ልብስ ሰፊ ሆኜ ነው፡፡ እና ለካ፣ ለካ ማለት ልብሱን ለካ እንደማለት ነው፡፡ በፊልሙ ላይ ግን ዝም ብለህ ፊልሙን ባታየውም ደግሞ ‹‹ለካ ከእኔ ጋር አልነበርክም›› የሚል ትርጉም ይሰጥሃል፡፡ የውጪዎቹን ስራዎች እያደነቅንና የእነሱን ተሞክሮ እየቀሰምን መሄድ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ታይታኒክ ፊልም ለእኔ ምርጥ ፊልም ነው፡፡ የፊልሙን ማጀቢያ ሙዚቃ የሰራችው ሴሊንዲዮን ናት፡፡ ይህ ማጀቢያ ሲሰራ ስሎው ነው፡፡ ከፊልሙ ጋር ልክክ ብሎ ገብቶ እንዳትወጣ አድርጎ ዘፈኑን በሰማህ ቁጥር ብዙ የፍቅር ትውስታ እንዲኖርህ ያስችላል፡፡ ይሄ ዘፈን ቴክኖና ሐውስ ሆኖ ወጥቷል፡፡ ወደ ጭፈራ ዘይቤ ሆኖ ቀርቧል፡፡ እኔ የሄለን በርሔንም ሙዚቃ እኔ አንዳንዴ ሲጨፍሩበት አያለሁ፡፡ ጥሩ ነው፡፡ ይሄ ከፊልም ማጀቢያ ሙዚቃ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው መነሳሳትን የሚፈጥር ይመስለኛል፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- ከሰሞኑ ‹‹ዜማ አማን›› በሚል ርዕስ አዲስ አልበም በፕሮዲውሰርነት አቅርበሃል፡፡ በዚህ አልበምህ ካመጣኸው ድምፃዊያን ኃይለየሱስ አንዱ ነው፡፡ ኃይለየሱስ ከሙዚቃው አካባቢ ጠፍቶ ነበርና የት አገኘኸው?
አማኑኤል፡- የኃይለየሱስ ነገር እንደማንኛውም አድማጭ እኔንም ይቆጨኝ ነበር፡፡ ተማሪ ሆኜ ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት እያለሁ እሱን ለማየት ለመስማት ስል ኤግዚቢሽን ማዕከል ድረስ እሄድ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ያንን የመሰለ ድምፅ ይዞ ጠፋ፡፡
‹‹ይለፍ ዕድሜ፣ አንችን ስል ቆሜ›› የሚለው ወረድ ብሎ ጀምሮ በኋላ ላይ በጣም ከፍ የሚል ነው፡፡ ሀይለየሱስን ውስጤ ሁሌም ስለሚያስበው በቀጥታ እሱ ነው ይህን የሚዘፍነው ብዬ ወስኜ ደወልኩለት፡፡ እሱም ለረጅም ጊዜ ይፈልገኝ ነበርና ተነጋገርን፡፡ ዘፈኑን ሰጠሁት፡፡ በአጭር ጊዜ ይዞት ሰራው፡፡ አድማጭም በጣም የእሱን ዘፈን ወዶታል፡፡ ኃይለየሱስ የሚገርም ድምፃዊ ሲሆን፣ አብሬው በመስራቴ ደስተኛ ነኝ፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- በአልበምህ የተካተቱት ድምፃዊያን በአሜሪካና በኢትዮጵያ የሚኖሩ ናቸውና እነሱን ማሰባሰቡና መጠበቁ አላስቸገረህም?
አማኑኤል፡- በጣም ተስፋ የሚያስቆርጥ ደረጃ ያደርሳል፡፡ አንዳንዴ ምን ውስጥ ነው የገባሁት? እስከማለት ደርሼ ነበር፡፡ ሙዚቃ ግን ከገባህበት አይለቅህም፡፡ አንዳንዴ ፈተና ቢበዛብ ህም በእልህ ተስፋን ሰንቄ ለአድማጭ ላበቃው ችያለሁ፡፡ ወደ አምስት ዓመት ያህል የፈጀብኝም ለዚህ ነበር፡፡S


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>