Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

‘‘የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ ገዥ እንጂ መሪ አግኝቶ አያውቅም’’ ፕሮፌሰር በፍቃዱ ደግፌ

$
0
0

ፕሮፌሰር በፍቃዱ ደግፌ

prof, Bekadu Degife

ፕሮፌሰር በፍቃዱ ደግፌ

ባለፈው እሁድ ሰማያዊ ፓርቲ ባዘጋጀው የመወያያ መድረክ ላይ ቀርበው ታዳሚዎችን የመሰጠና ያወያየ ኃሳብ አንሸራሽረዋል። በፓርቲው ጽ/ቤት የተገኙ ወጣት ምሁራንም የፕሮፌሰሩን ኀሳብ በሌላ ኀሳብ በመሞገት ምሁራዊ አስተሳሰቦችና ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ጥልቅና ማራኪ ውይይት ተደርጓል።

ፕሮፌሰር በፍቃዱ በመወያያ መድረኩ ላይ ቀርበው የመነጋገሪያ ኀሳቦችን ያቀረቡት ፓርቲው በወጣቶች የሚመራ በመሆኑ አቅጣጫ የሚጠቁሙ ኀሳቦችን ለማሳየት ነበር። ጎን ለጐንም ሀገራዊ ርዕሰ ጉዳዮች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል። ፕሮፌሰሩ በዋናነት የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ማነቆዎች ላይ የመንግስትና የሕዝቡ ሚና ምን መሆን እንዳለበት የራሳቸውን የመፍትሄ ኀሳቦች ሰጥተዋል። ከሁሉም በፊት ግን ፕሮፌሰሩ የሰሞኑ ወቅታዊና አነጋጋሪ ጉዳይ ስለሆነው የኃይማኖት ጉዳይ የተናገሩትን እናስቀድም። ፕሮፌሰሩ በኢትዮጵያ ክርስትናና እስልምና ምን ያህል መስተጋብር ፈጥረው እየኖሩ መሆኑን ከራሳቸው የቤተሰብ አወቃቀር በመነሳት የተናገሩት የታዳሚውን ቀልብ ያሳበ ነበር።

‘‘የእኔ ቅድመ አያት ሙስሊም ናቸው። እናቴ ጌጤ ትባላለች። አያቴ ደግሞ ብሩ ይባላሉ። ቅድመ አያቴ መንሱር የሚባሉ ሲሆን፤ የመንሱር አባት ደግሞ በፈቃዱ ይባላሉ። እኔ በቅድመ አያቴ ስም ነው የምጠራው። ስሜን ያወጡልኝ አያቴ ናቸው። ቀኝ አዝማች ብሩ ይባላሉ። በፍቃዱ ሙስሊም ነው ያገቡት፤ ሰባት ልጆች ወልደው ነበር። ሦስቱ ሙስሊም ሲሆኑ አራቱ ክርስቲያን ሆነዋል። ከነዚህ ውስጥ ሴቷ ሙስሊም አግብታ አብራ ኖራለች። አብረን ነው የምንበላው አብረን ነው የምንኖረው’’ በማለት ለሀይማኖቶች መቀራረብ ከዚህ የተሻለ ማነፃፀሪያ የለም ብለዋል።

ፕሮፌሰሩ ወደ ዋናው ነጥባቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሲመለሱ መነሻ ያደረጉት የሀገሪቱን የድህነት ደረጃ በመጥቀስ ነበር። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በአለም ላይ ማሊ ከምትባል ምዕራብ አፍሪካዊት ሀገር ብቻ ነው የምትሻለው ብለዋል።

‘‘ሀገሪቷ የገበሬና የገጠሬ ሀገር ናት። ስለዚህ ግብርና ትልቁ ስራ ነው። የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ምንጭ ግብርና ነው። ግብርናው ወደ ኢንዱስትሪ አድጎ ብዙ ሰራተኛ መቀጠር አለበት። ሰራተኛው ከግብርናው ወደ ኢንዱስትሪ መምጣት አለበት’’ ያሉት ፕሮፌሰሩ አሁን ግን ገበሬው ከራሱ አልፎ ከተማን መመገብ ብቻ ሳይሆን የእራሱም ህልውና አደጋ ላይ መውደቁን ነው የጠቀሱት።

‘‘ኢትዮጵያ ባት የሌለው ገበሬ ነው ያላት። ባት የሌለውም ማለት እግሩ አጥንት ነው። የዚህ ሀገር የግብርና ስራ ጉልበት በጣም የሚፈልግ ቢሆንም ገበሬው አቅሙን ያጣ ነው። ይሄ ሀገር እራሱን መመገብ ስላልቻለ በፈረንጅ ቸርነት ያለ ሀገር ነው’’ ሲሉ የጠቀሱት ፕሮፌሰር በፍቃዱ ‘‘ከተሞችም የድህነት መሸሸጊያና መጠለያ ሆነዋል’’ ብለዋል።

ገበሬው የተጎዳ በመሆኑና በቂ ምርት የማያመርት ስለሆነ የኑሮ ውድነት መከሰቱን የጠቀሱት ምሁሩ የኑሮ ውድነቱ ምስጢር አይደለም ብለዋል። የሰራ አጥነት በከተሞች የተስፋፋው ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሰውና ድህነትን የሚሸሸው ሰው ስለበዛ ነው። ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት የተመረቁ ተማሪዎችንም እንደሚያካትት በመግለፅ ከተሞች የሰራ አጥነት ማዕከል ለመሆን በመገደዳቸው የችግር ቋት ሆነዋል።

በአሁኑ ወቅት ያለውን የሀገሪቱን ችግር ለመፍታት አንድ ትውልድ መስዋዕት መሆን እንዳለበትም ጠቅሰዋል። በተለይ አሁን ያለው ትውልድ የድሎት ኑሮ ለመኖር ያለው ዕድል የጠበበ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

የሀገሪቱ ሁኔታ ለመቀየር ግብርና ብቸኛው አማራጭ መሆኑንም የጠቀሱት ፕሮፌሰር በፍቃዱ፤ አሁን ሀገሪቱ የምትመካበት ምንም ሀብት ወይም ጥሪት የላትም ብለዋል። ‘‘ሀገሪቱ ቤንዚን የላትም። በእርግጥ ቤኒዚን ሌሎች ሀገሮችን ሲያባልግ አይተናል። ኢትዮጵያ ቤንዚን ከማግኘቷ በፊት ሕዝቡ በጥረቱ መልማት እንደሚችል ማመን አለበት። ከቤኒዚን በፊት የስራ ዲሲፕሊን መቅደም አለበት። ጥረቱ ካለ ቤንዚን ብቻ ሳይሆን ዩራኒየምንም ሆነ ወርቁንና ፕላቲኒየምን አውጥቶ መጠቀም ይቻላል። ጥረቱ መጀመር ያለበት ደግሞ ከግብርናው ነው’’ ብለዋል።

የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ከግብርናው መጀመር አለበት ከተባለ የሀገሪቱ የመሬት ስሪትና ይዞታ መታየት እንዳለበት ነው የገለፁት። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ገጠሩ በአንድ አካባቢ ታፍኖ እንዲቀመጥ በመደረጉ ገበሬዎች የሚያርሱት የመሬት ስፋት በከፍተኛ ደረጃ እያነሰ ነው። በመንግስት ስታስቲክስ መሰረት በኢትዮጵያ ከአንድ ሄክታር በታች የሚያርሱ ገበሬዎች ወደ 11 ሚሊዮን ገበሬዎች ናቸው። ከሁለት ሄክታር በታች የሚያርሱ ወደ 14 ሚሊዮን ናቸው። ይሄ ደግሞ ገበሬው ምን ያህል ውልቅልቁ እንደወጣ ያሳያል’’ ብለዋል። በመፍትሄነትም የመሬት ጥበትን የሚቀንሱ አማራጭ የገቢ ምንጮች በመፍጠር መሬቱ ላይ በውርስም ሆነ በሌላ መንገድ የሚደረገው እየቆራረጡ መከፋፈል መቆም አለበት ብለዋል። በመሆኑም አንድ ገበሬ ቢያንስ ሦስት፣ አራት ወይም አምስት ሄክታር በመያዝ ትርፍ ሊያመርት ይገባል። ለዚህ ደግሞ በሀገሪቱ እንደገና የመሬት ክፍፍል ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል። ገበሬውም ለሚወልዳቸው ልጆቹ መሬት እየቆረጠ የሚሰጥበት አካሄድ አንድ ቦታ መቆም አለበት። ልጆቹ ወደ ሌሎች አማራጭ የስራ ዕድሎች መሰማራት አለባቸው ብለዋል። ገበሬው ትርፍ ባመረተ ቁጥር አነስተኛ ኢንዱስትሪ በማስፋፋት ግብርናን ከኢንዱስትሪው ጋር ማመጋገብ ተገቢ እንደሆነም አስረድተዋል።

ግብርናውና ኢንዱስትሪው ከተመጋገበ በኋላ ገበያ መፍጠር ወሳኝ መሆኑንም ፕሮፌሰሩ በገለፃቸው ላይ አፅንኦት ሰጥተውታል። ‘‘የሀገር እድገት መሰረቱ ብዙ ማምረት ነው። በብዛት ያላመረተ ሀገር የኢኮኖሚ እድገት አለ ለማለት አይቻልም። እድገት ያለ ገበያ ደግሞ አይሳካም። በአሁኑ ወቅት የገበያ አማራጭ ሁለት አይነት ሲሆን የውጪና የሀገር ውስጥ ገበያ ነው። የውጪውን ገበያ ለመወዳደር የምርት ጥራት በቂ ነው’’ ያሉት ፕሮፌሰሩ ኢትዮጵያ ካለችበት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ አንፃር ለመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ገበያ ጥሩ ዕድል ያላት መሆኑን ጠቅሰው፤ ‘‘የሰው ኃይላችንን ወደ መካከለኛው ምስራቅ ከምንልክ የግብርና ውጤቶችን ብንልክ የተሻለ አማራጭ ነበር’’ ብለዋል።

መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ ስለሚኖረው ሚና

‘‘በፕሮፌሰር በፍቃዱ እምነት በአሁኑ ወቅት ትልቁ ቀጣሪ መንግስት ነው። መንግስት የሀገሪቱ ግዙፍ ተቋም ነው። በዚህ ሁኔታ መንግስትን ከኢኮኖሚው ማስወጣቱ ተገቢ አይደለም። ተወደደም ተጠላ መንግስት መንገድ፣ ግድብ፣ ትልልቅ ፋብሪካዎችን ካልገነባ ማን ሊገነባው ነው?’’ ሲሉ የሚጠይቁት ፕሮፌሰሩ ከመንግስት ውጪ ያለው ኢኮኖሚ የጉሊት ኢኮኖሚ ነው። የኢትዮጵያን እድገት በኃላፊነት ለመያዝ የሚችል የግል ክፍለ ኢኮኖሚ የለም። ስለዚህ መንግስት የግሉን ሴክተር መፍጠር አለበት። በ1959 ዓ.ም ኮሪያ ከእኛ እርዳታ የምትቀበል ሀገር ነበረች። ሲንጋፖር ብትሄዱ ‘‘የኢትዮጵያ አደባባይ’’ የሚባል ቦታ አለ። በችግራቸው ጊዜ እርዳታ ስለላክንላቸው ነው። ኮሪያም ዘምተናል እና ይሄ ሀገር ትልቅ ሀገር ነበር። ‘‘ትልቅም ነበር ትልቅ እንሆናለን’’ የሚለው አባባል እውነት ነው። ነገር ግን ትልቅ ነበርና ትልቅም እንሆናለን ማለት አሁን ግን ትልቅ አይደለንም ማለት ነው። የምስራቅ ኢሲያ ሀገሮች የኢኮኖሚ ተሞክሮ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ መሆኑንም በ1959 ዓ.ም ጀኔራል ቹንኪ ፓርክ የኮሪያን መንግስት ገልብጦ ስልጣን ከያዘ በኋላ የሀገሪቱን የፊውዳል ሐብታሞች ሰብስቦ የግሉን ሴክተር መፍጠር ችሏል። እነ ሳምሰንግ ዘዩናድይ ወዘተን ሊፈጠሩ ችለዋል። በእኛም ሀገር መንግስት ጠንካራ የግል ሴክተር መፍጠር አለበት። መንግስት የግል ሴክተር ይፍጠር ሲባል አሁን እንዳለው መንግስት የግሉን ሴክተር ተክቶ ይስራ ማለት አይደለም ብለዋል።

ጃፓኖች ከድህነት አዘቅት የተነሱት አፄ ቴዎድሮስ በሞቱበት እ.ኤ.አ 1868 ዓ.ም ወደስልጣኔ ማምራት የጀመሩበት ዘመን እንደነበር ያወሱት ፕሮፌሰሩ በዚያን ጊዜ አፄ ቴዎድሮስም ሀገሪቱን ወደ ኢንዱስትሪ የመቀየር ራዕይ የነበረው ንጉስ ነበር ብለዋል። በመሆኑም መንግስት የሀገሪቱን ኢንዱስትሪ ለመቀየር የቅድሚያ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል። ኢንዱስትሪ ሲባል ግዙፍ ፋብሪካ ማቋቋም ብቻ ሳይሆን የመንደር ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋትና የምርት ሰንሰለትን መመጋገብ መፈጠር አለበት ብለዋል። ለምሳሌ ጥሬውን ጤፍ ከገበሬው ይዞ ወደ ከተማ ከማምጣት እዛው ወፍጮ ቤት በመትከል ኢንዱስትሪ መጀመር ይቻላል። ከወፍጮ ቤቱ ጎን ለጎን ለጤፍ መያዣ ጆንያ ፋብሪካ ማቋቋም ይቻላል፤ ጆንያውን ለማምረት ደግሞ የቃጫ ፋብሪካ እያሉ ምርት የማመጋገብ የምርታማነት ሰንሰለት በመፍጠር ኢንዱስትሪን በመንደር ደረጃ መጀመር እንጂ ግዙፍ ፋብሪካን በማሰብ ሊሳካ አይችልም ብሎ ተስፋ መቁረጥ አይገባም ብለዋል።

ሀገሪቱን ለመለወጥ የትምህርት ስርዓቱም መለወጥ አለበት ያሉት ፕሮፌሰር በፍቃዱ በአፄ ኃይለስላሴ ጊዜ ትምህርት የምንማረው፤ ለልማት ሳይሆን ቋንቋ ለመተርጎም ነበር። በዚያን ጊዜ ወደ ሀገሪቱ የገባው ትምህርት የአርስቶክራት ትምህርት ነበር። የመደብ (class) ትምህርት ነው። ለስነ-ፅሁፍና ከፈረንጆች ጋር ለመግባባት ነበር። አሁን ግን የትምህርት ስርዓቱ ወደ ዳቦ የሚቀየር መሆን አለበት። ነገር ግን እየተሰጠ ያለው ትምህርት እውቀት እንጂ ስኪል የለውም። በአሁኑ ወቅት 27 ከመቶ የዲግሪ ተመራቂዎች ስራ የላቸውም። ዩኒቨርሲቲዎች የስራ አጥ ማምረቻ ሆነዋል። ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡት የተለዩ የነጠሩና የሳይኒስትነት ደረጃ ያላቸውን እንጂ ሁሉንም በጅምላ እንዲገቡ ማድረጉ ኪሳራ ነው። ጥራት ያላቸውን ወደ ዩኒቨርሲቲ እያስገቡ የቀረውን ደግሞ ስኪል እናስተምረው ብለዋል። የትምህርት ስርዓቱ ሰው ሰርቶ ለመብላት የሚያስችል እውቀት እንዲኖረው በሚያስችል መልኩ መከለስ አለበት ሲሉም ገልፀዋል።

በዕለቱ ከነበሩ ወጣት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና የፓርቲው አባላት ለፕሮፌሰር በፍቃዱ ልዩ ልዩ ጥያቄዎች አቅርበውላቸው ነበር። ከነዚህም ጥያቄዎች መካከል ሀገሪቱ የፖሊሲ ሳይሆን የብሔራዊ ስሜት ማጣት ዋነኛ ችግሯ መሆኑ ተጠቅሶ ነበር። ፕሮፌሰሩ ግን የሀገሪቱ ብሔራዊ ስሜት ሙሉ በሙሉ አለመሞቱንም ይልቁኑ በዚህኛው ትውልድ እየተነሳ መሆኑን ከገለፁ በኋላ ‘‘ሐገሪቷ ያጣችው ብሔራዊ ስሜት ሳይሆን ብሔራዊ መሪ ነወ። የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ ገዥ እንጂ መሪ አግኝቶ አያውቅም። ልማት በሕዝብ ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ ስሜት ባለው መሪ ሊረጋገጥ ይችላል’’ ሲሉ መልሰዋል።

‘‘በተጨማሪም የሀገሪቱ ብሔራዊ ስሜት በአሁኑ ጊዜ በወጣቱ እያንሰራራ ነው።’’ ያሉት ፕሮፌሰሩ ለብሔራዊ ስሜት መጎዳትም ኦነግን ተጠያቂ አድርገዋል። ‘‘በዚህ ሀገር ከመንግስቱ ኃይለማርያም ቀጥሎ ወንጀል የፈፀመው ኦነግ ነው። ኦነግ በሁለቱ ትላልቅ ሕዝቦች መካከል በአማራና በኦሮሞ መካከል ክፍተት እንዲፈጠር ጥረት አድርጓል። በክፍተቱም ወያኔ እንዲገባ አድርጎ ተገዥ አድርጎናል። ወያኔ ደግሞ ያጠፋው ነገር የለም። እኛ ዝም ብለን እየተገዛንለት ነው’’ ብለዋል።

ሰፈራ በተመለከተ የሕዝብ እንቅስቃሴ አስፈላጊ መሆኑን በመግለፅ የሰፈራ ፕሮግራም ደጋፊ መሆናቸውንም ተናግረዋል። ነገር ግን ሰፈራው በዋናነት የሚሰፍረውን ሕዝብ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ማረጋገጥ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ‘‘ኮንዶሚኒየም የከተማ ሰፈራ ነው’’ ያሉት ምሁሩ፤ ሰፈራ የሕዝብን ቅድሚያ ጥቅም በሚያረጋግጥና ልማትን በተለይም ግብርናን በሚያፋጥን መልኩ ቢፈፀም ችግር እንደሌለው ነው የገለፁት። ለሁሉም ግን ይቻላል፤ እንችላለን ብለን ልንንቀሳቀስ ይገባል ብለዋል።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>