የመብት ጥያቄ ያነሱ የሙስሊሙ ማኀበረሰብ አካላት ላይ መንግሥት እየወሰደ ያለው የኃይል እርምጃ አጥብቀው እንደሚቃወሙት ሶስት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰሞኑን ባወጡት መግለጫ አስታወቁ።
የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ እና የመላ ኦሮሞ ሕዝብ ድርጅት ነሐሴ 5 እና 6 ቀን 2005 በተናጠል ባወጡት መግለጫዎች መንግሥት አለመግባባቱን ለመፍታት እየተከተለ ያለውን የኃይል እርምጃ ተገቢ አለመሆኑን ገልፀዋል።
ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጋር ሰሞኑን ባደረጉት ቃለምልልስ ‘‘ጽንፈኞች’’ ያሏቸውን የመብት ጥያቄ ያነሱ የሙስሊም ማኀበረሰብ አካላት እያደረጉ ያሉት እንቅስቃሴ ፀረ-ሕገመንግስታዊ መሆኑን አመልክተዋል። ‘‘የሃይማኖት መንግስት እንመሰርታለን፣ የሸሪዓ ሥርዓት እናሰፍናለን’’ የሚል አቋም እንደሚያራምዱ የጠቀሱት ጠ/ሚኒስትሩ መንግስት ሃይማኖታዊ ተልዕኮ ያላቸው መስሏቸው ከፅንፈኞች ጋር የሚተባበሩ ተከታዮችን በጅምላ ላለመጉዳት በትግስት ሁኔታውን ሲከታተልና የማሳመን ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል። ጽንፈኞችን ከሌሎች የእምነቱ ተከታዮች ለመለየት የተደረገው ጥረት የተሳካ እንደነበርና መንግስት ሰሞኑን የወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። ከጽንፈኞች ጋር ተቀናጅተው የአገሪቷን ሠላም ለማወክ ይንቀሳቀሳሉ ያሏቸውን የተቃዋሚ ፓርቲዎችንም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አስጠንቅቀዋል። (የሦስቱ ፓርቲዎች ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ተስተናግዷል)
ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ የተሰጠ መግለጫ
‘‘በሙስሊሙ ወገኖቻችን ላይ መንግስት እያካሄደ ያለው እስር፣ ድብደባና ግድያ መንግስታዊ የሽብር ተግባር ስለሆነ አጥብቀን እናወግዛለን፣ በአስቸኳይ እንዲገታም እንጠይቃለን’’
ኢትዮጵያ የምትመራበት ሕገ መንግስት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ኮንቬንሽንን የሕጉ አካል አድርጎ የተቀበለው ሲሆን ከሕገ መንግስቱ አንቀጽ 14 እስከ 29 ያሉት ሕጎችም የዜጎችን የሕይወትና የአካል ደህንነት፣ የሃይማኖት ነፃነትና የሰብአዊ መብት እኩልነት ክብርና እንዲሁም የመልካም ስምን የሕግ ጥበቃ በዝርዝር ይደነግጋል። እነዚህ በአገሪቱ የበላይ ሕግ ውስጥ የተካተቱ መብቶችን መንግስት የማክበርና የማስከበር ግዴታም እንዳለበት ጨምሮ ተደንግጓል።
የኢሕአዴግ መንግስት ግን ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ እነዚህን ሕገ መንግስታዊ መብቶች ሲጥስ ይታያል። የአብዛኛው ሕዝብ ጥያቄ ኢሕአዴግ ራሱ የማያከብረውን ሕገ መንግስት ለምን አወጣው? የሚል ነው። ምክንያቱም ሕገ መንግስቱን መጣስ የዕለት ተዕለት ተግባራቱ እየሆነ መጥቷል፤ እንዲያውም ሕገ መንግስቱን የፃፈውና ያፀደቀው ለይስሙላ በዓለም አቀፍ ማኀበረሰብ ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ያሰፈነ መንግስት ለመምሰል እንጂ ከምስረታው ጀምሮ ዲሞክራሲያዊና ተዓማኒ ሊያሰኘው የሚችል ገፅታ እንደሌለው ግልፅ ሆኗል። የሕዝብን የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች መጣስ የጀመረው ገና ከጅምሩ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ነበር። ለአብነት ለመጥቀስም በንፁሃን የአኙአክ ዜጎች ላይ፣ ቅሬታቸውን በሠላማዊ መንገድ ለመግለፅ በወጡ የአዲስ አበባ እና የሐዋሳ ነዋሪዎች ላይ በአሳሳ፣ በዶዶላና በገርባ ሙስሊም አማኞች ላይ የፈፀማቸው የግድያ ወንጀሎች ጉልህ ማሳያዎች ናቸው። በነዚህ የግድያ ወንጀሎች እስከ ዛሬ የተጠየቀ የመንግስት አካል ወይም ባለሥልጣን የለም፤ ዛሬ ዜጎች በግፍ እየተገደሉ ደማቸው ደመ-ከልብ ሆኖ ሲቀር መንግስት የሕግ ጥበቃ ያደርግልናል የሚለው ተስፋ እየተሟጠጠ ሄዷል።
የዓለም የሰብዓዊ መብት ኮንቬንሽን በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት የፀደቁ የዜጎች መብትን በመደፍጠጥ በፀረ ሽብር ሕግ ሽፋን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን ማሰር፣ ማጉላላት፣ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ጣልቃ በመግባት፣ የሃይማኖት መሪዎችን በማሰር፣ የዜጎችን በነፃ አስተያየታቸውን የመግለፅ ሕገ መንግስታዊ መብት ከመጣሱም በላይ በቅርቡ በሃይማኖት ጉዳዮች መንግስት ጣልቃ እንደማይገባ የተደነገገውን በመጣስ መንግስት በሚያስተዳድረው ቀበሌ የሃይማኖት መሪዎችን ማስመረጡ፣ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ ለመግባቱ ጉልህ ማስረጃ ነው። ይህን የተቃወሙትንና ድምፃችን ይሰማ ያሉ ሰላማዊ የሙስሊም የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን በሽብርተኛነት ፈርጆ ማሰሩና አሁን በሐምሌ ወር መጨረሻ አካባቢ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ አርሲ ዞን በኮፌሌና በዶዶላ በአሳሳ እንዲሁም በሌሎችም የኦሮሚያ ዞኖችና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ያለማስረጃ በማሰርና በመደብደብ የግድያ ወንጀልም ፈጽሟል። የታጠቀ የመንግስት ኃይል ባልታጠቀ ሕዝብ ላይ እስራት፣ ግድያና ድብደባ መፈፀም መንግስታዊ የሽብር ተግባር በመሆኑ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከዚህ ኃላፊነት ከጎደለው ሕገ ወጥ ድርጊቱ ሊቆጠብና ሕገ መንግስቱን ሊያከብር ይገባል።
የእስራቱ፣ የብርበራውና የግድያው ዓላማ ሽብርተኛነትን ወይም አክራሪነትን ለማስወገድ መፍትሔ ነው ብለን አናምንም። ይልቁንም መንግስት በሕገ መንግስቱ በተደነገገው መንገድ ብቻ የዜጎችን የእምነት ነፃነት በማክበር ለሙስሊሙ ሕብረተሰብ ሰላማዊና ሕጋዊ ጥያቄዎች አዎንታዊ መልስ ቢሰጥ ኖሮ ይኸ ሁሉ የዜጎች ሕይወት አይጠፋም ነበር እንላለን። አክራሪነትንና ሽብርተኛነትን ምክንያት በማድረግ የዜጎችን ሕጋዊና ሰላማዊ ተቃውሞ ለመደፍጠጥ የተወሰደውን የጭካኔና ሰብአዊነት የጎደለው ተግባር በመሆኑ አጥብቀን እናወግዛለን። መንግስት በታጣቂዎቹ እየታገዘ የሚጽመው እስራትና ግድያ ለአገር ሠላምና ለሕዝብ ደህንነት እጅግ አስጊ እየሆነ ስለመጣ መንግስት ከዚህ ድርጊቱ እንዲገታ እንጠይቃለን። በዚህ አጋጣሚ ሙስሊሙ ሆነ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ የኢሕአዴግን ኢ-ሕገመንግስታዊ ድርጊት በመገንዘብ ትግሉን በሕጋዊና ሠላማዊ መንገድ አጠናክሮ በመቀጠል አንድነቱንና ሠላማዊ የትግል ትብብሩን እንዲያሳይ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
መንግስታዊ የሽብር ተግባር በተባበረ ሕጋዊና ሠላማዊ የሕዝብ ትግል ይገታል!
ከኢዴፓ የተሰጠ መግለጫ
‘‘ውይይትና ድርድር ደከመኝ፣ ሰለቸኝ የማይባልበት ብቸኛው የሰላምና የዴሞክራሲ አማራጭ ነው።’’
የመብት ጥያቄ ያነሱ የሙስሊሙ ማኀበረሰብ አካላትና መንግስት በተለያየ መድረክ መፋጠጥ ከጀመሩ ከአስራ ስምንት ወር በላይ ሆኖታል። በአብዛኛው ከአዲስ አበባና አካባቢዋ የሶላት ስግደት ቀን የማያልፈው የመብት ጥያቄ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንቅስቃሴው እየሰፋና እያደገ በመሄድ በርካታ ሙስሊሞችን ማካተት ችሏል። እንቅስቃሴውን ለመግታት መንግስት በተከታታይ በወሰደው እርምጃ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ የተለያዩ ጉዳቶች ደርሰዋል። በተለይ ደግሞ ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ ግጭቱ በስፋትና በቅርጽ እየጎለበተ በመሄድ ወደ ሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች በመዛመት በበርካታ ዜጎች ዘንድ አነጋጋሪና አሳሳቢ ጉዳይ ለመሆን በቅቷል።
በኢዴፓ እምነት ዜጎች በሃይማኖታዊም ሆነ በፖለቲካዊ አሊያም በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ጥያቄ የማንሳትና ከመንግስትና ከመንግስታዊ ተቋማት ጋር ወይም በተናጠል የመብት ጥያቄዎችን የማቅረብ፣ የመደራደርና መፍትሄ የመሻት መብታቸው ያለአንዳች ገደብ ሊከበር እንደሚገባ አጠንክሮ ያምናል። ኢዴፓ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመቃወም፣ ያለማንም ጣልቃ ገብነት የማምለክና የመሳሰሉ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች እንዳይሸረሸሩ ዘብ የሚቆምላቸው አጀንዳዎቹ መሆናቸውም ይታወቃል።
በሌላ በኩል ኢዴፓ እነዚህ የመብት ጥያቄዎች በስምምነት ካልሆነ በስተቀር የሌሎችን ጥቅምና መብት በማይነኩበትና በሕገ-መንግስቱ ላይ በሰፈረው መሰረት መቅረብ፣ መደመጥና አግባብነት ያለውን ፍትሐዊ መልስ ማግኘት እንዳለባቸው ያምናል። ከዚህም በላይ ዜጎች ጥያቄዎቻችን በበቂ ሁኔታ አልተመለሱም ብለው ሲያምኑ ጥያቄዎቻቸው እንዲመለሱ በሕጋዊ መንገድ ሰላማዊ ሰልፍ፣ የአዳራሽና ሕዝባዊ ስብሰባ በማድረግ በመንግስት ላይ ገንቢ ተጽእኖ በመፍጠር ለጥያቄዎቻቸው መፍትሄ የመሻትና የማግኘት መብታቸው ሊሸረሸርና ሊገሰስ እንደማይገባ ኢዴፓ በጽኑ ያምናል።
መንግስትና ተቋማቱ ዜጎች በሕገ-መንግስቱ ላይ የሰፈሩ መብቶቻቸው ወደ ተግባር እንዲለወጡ ሁኔታዎችን የማመቻቸትና ጥያቄዎቻቸው በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበትን አቅጣጫ የማሳየት፣ የማገዝና ቅራኔዎችን በሰለጠነ መንገድ በትዕግስት የመፍታት ኃላፊነት አለበት። መንግስት በአጣብቂኝ ውስጥም ሆኖ ቢሆን ከዜጎች የሚቀርቡ የመብት ጥያቄዎች እንዳይጨፈለቁ ጥበቃ ማድረግ ይገባዋል። በተለይ ደግሞ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም የሚቀርቡ የመብት ጥያቄዎችን ለማስከበር የሚሄድበት ርቀት የዜጎችን የመብት ጥያቄ ለማስተናገድ የሚኖረውን ቁርጠኝነት የምንለካበት ነው። መንግስት በማንኛውም መለኪያ ዜጎች ጥያቄዎቻቸውን በነፃነት የማቅረብ መብታቸው እንዳይታፈን በማድረግ ቁርጠኝነቱን ማሳየት ይጠበቅበታል። አጀንዳዎቹ ተጠልፈዋል ብሎ ሲያምን የችግሩ ምንጮችን ብቻ ለይቶ በማውጣት ቀሪው ዜጋ ጥያቄውን የማስተጋባት መብቱ እንዲቀጥልና መፍትሄ እንዲያገኝ በማድረግ ሕገ-መንግስታዊ ግዴታውን መወጣት አለበት። መንግስት በዚህ የመብት ጥያቄ ሂደት ውስጥ መብታቸውን በአግባቡ መጠቀም ያልቻሉ ዜጎች ቢገኙ እንኳን በዜግነታቸው ተገቢውን ሕጋዊ ጥበቃና እንክብካቤ ሳያጓድልባቸው ሕግ ፊት በማቅረብ ሳይፈረድባቸው የመወንጀል ሕገ-መንግስታዊ መብታቸውን በማስከበር ዋስትና መሆኑን ማረጋገጥ አለበት።
ኢዴፓ ‘‘መብቶች ሁሉ ግዴታ ያዘሉ መሆናቸው’’ የምናምነውን ያህል የመብት ጥያቄዎች በቅድመ ሁኔታዎች መጨናገፍና መጨፍለቅ እንደሌለባቸው ደግሞ በጥብቅ የምንታገልለት ፍልስፍናችን ከመሆኑም በላይ ስህተት ሊሰራበት የማይገባ ጉዳይ መሆኑን ግልጽ ማድረግ ይፈልጋል።
ከላይ በዝርዝር ያነሳናቸው የሰብአዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች በመርህ ደረጃ እንደተጠበቁ ሆነው። ካለፉት አስራ ስምንት ወራት ወዲህ በሙስሊሙ ማኀበረሰብ ውስጥ የተነሳውንና እስከ አሁንም የዘለቀውን የመብት ጥያቄ መፍትሄ ሳያገኝ በእንጥልጥል መቆየቱና ከነአካቴውም ስፋት እያገኘ መምጣታቸው መንግስት በተናጠል በሚወስደው የእመቃ እርምጃዎች ጥያቄዎቹ ሊፈቱ እንደማይችሉ ጠቋሚ ምልክቶች ናቸው። አሁን ለመገንዘብ እንደተቻለውም የመብት ጥያቄዎቹ መልስ ሳያገኙ ለበርካታ ወራት መዝለቃቸው ቅራኔው እየሰፋና መልኩን እየለወጠ ወደ አልተጠበቀ አቅጣጫ እየተገፋ ዜጎቻችንን ለሞት፣ ለአካልና ለንብረት ጉዳት እየዳረገ መሆኑን ኢዴፓ በሃዘኔታ ለመታዘብ ችሏል።
በተለይ ደግሞ በሙስሊሙ ማኀበረሰብ የኢድ አልፈጥር በዓል ላይ የታየው ፍጥጫ፣ ድብደባ፣ መጠነ ሰፊ እስርና እንግልት በማንኛውም መስፈርት ሃይል የተቀላቀለበት ፈጽሞ ያልተገባ እንደነበረ ኢዴፓ ያምናል። በዚህ አጋጣሚም በእለቱ ጉዳት ለደረሰባቸውና ለታሰሩ የሙስሊሙ ማኀበረሰብ አባላትና ቤተሰቦቻቸው የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን መግለጽ ይወዳል። መንግስት የመብት ጥያቄ ያነሱ የሙስሊሙ ማኀበረሰብ አባላትን በየበዓላቱ ቀኑ የመብት ጥያቄዎቻቸውን በመያዝ ማብቂያ በሌለው አዙሪትና ፍጥጫ ውስጥ ገብተው ለሃይል እርምጃ እንዳይጋለጡ ማድረግ እንዳለበት እናምናለን። መንግስት አሁን በእስር ላይ የሚገኙት ሙስሊሞች ያሉበትን ሁኔታ ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ ኢዴፓ ጥሪውን ያስተላልፋል።
ይህ ሳይሆን ቀርቶ ጥያቄዎቹ ከዚህ በላይ እየተገፉ ከሄዱ የጉዳዩን ጥልቀት በመረዳትም ሆነ ባለመረዳት ወይም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ላልተፈለገ ግጭትና አለመረጋጋት በር መክፈቱ አይቀሬ ነው። በዚህም ምክንያት በጉዳዩ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በሚመለከታቸው ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊና የሃይማኖት ተቋማት አማካኝነት አጀንዳውን ወደ ውይይት መድረክ መመለስ ጉዳዩ መፍትሄ እንዲያገኝና በቅራኔ የተወጠሩ አካሄዶች እንዲረግቡ መንገድ እንደሚከፍት ኢዴፓ ያምናል። በፍጥጫና በውጥረት ውስጥ ያለን የሕዝብ ጥያቄ ማፈን ጊዜ ከመግዛት ያለፈ ፋይዳ የማይኖረው ከመሆኑም በላይ ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ የአጠቃላይ ማህበረሰቡ ጣልቃ ገብነትን መጋበዙ አጠራጣሪ አይደለም።
ከዚህም በላይ እጅግ አደገኛ የሆነው መንገድ ይህንን ክፍተት በመጠቀም በክርስትያንና በሙስሊሙ ማኀበረሰቡ መካከል ልዩነትን የሚፈጥሩና ለቁርሾ የሚዳርጉ አደገኛ ዝንባሌዎች ከየአቅጣጫው እየተደመጡ መምጣታቸው የጉዳዩን አሳሳቢነትና አደገኛነት እንድንገነዘብ የሚረዳ ሆኖ አግኝተነዋል። በኢዴፓ እምነት እንደዚህ ዓይነቶቹ አደገኛ ዝንባሌዎች ምንጫቸውና ባለቤታቸው ማንም ይሁን ማን በሁላችንም የተባበረ ድምጽ ሊወገዙ እንደሚገባ ያምናል።
በመንግስት በኩል በተደጋጋሚ የሚነሳው ስጋት የመብት ጥያቄው የአክራሪ ሃይሎች ሰለባ ሆኗል የሚል ነው። ኢዴፓ ይህ ጥያቄ አሳሳቢ መሆኑን ቢያምንም፤ በተጋነነ ሁኔታ የቀረበ መሆኑን ለመረዳት አዳጋች አይደለም። ኢዴፓ፣ ኢትዮጵያዊያን የዓለም ማኀበረሰብ አካል እንደመሆናችን መጠን የጐረቤት ሃገሮችን ጨምሮ አንዳንድ ሃይሎች የውስጥ ጉዳዮቻችንንና ተፈጥሮ ልዩነቶቻንን አላግባብ በመለጠጥና በማራገብ የስግብግብ አጀንዳቸው ማራመጃ አድርጎ ለመጠቀምና ሃገራችንን ከአደገኛ ሁኔታ ጋር ለማላተም የሚተጉ ሃይሎች የሉም የሚል የዋህ እምነት ያለው ድርጅት አይደለም። ይህም ሆኖ እያለ ለእንደዚህ ዓይነቱ አደጋ አጋልጦ ወይም አመቻችቶ የሚሰጥን ምዕራፍ የሚከፈተው ውስጣዊ ችግሮቻችንን በመደማመጥና በመግባባት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለን አቅም ሲዳከም ብቻ እንደሆነ ኢዴፓ ለማሳሰብ ይወዳል።
ከዚህ መሰረታዊ ሃሳብ በመነሳት የመብት ጥያቄ ያነሱ የሙስሊሙ ማኀበረሰብ አባላትን ጉዳይ መንግስት እንደገና ወደ ውይይትና ድርድር መድረክ በማምጣት መልስ እንዲገኝ ጥረት እንዲያደርግና የተጀመረውን ፍጥጫን ቅራኔ የሚያረግቡ እርምጃዎችን እንዲወስድ ጥሪያችንን እናቀርባለን። የመብት ጥያቄ ያነሱ የሙስሊሙ ማኀበረሰብ አካላትም ጥያቄዎቻቸው መልስ እንዲያገኙ ወደ ውይይትና ድርድር መድረክ መመለሱ ወደ ውጤት የሚወስደው ብቸኛ መንገድ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ፍጥጫዎቹንና ግጭቶቹ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያልተገባ ዋጋ እንዳይከፍሉ የድርድርና የውይይቱን መንገድ በቁርጠኝነት እንዲገፉበት ኢዴፓ ጥሪውን ያስተላልፋል። የሃይማኖት ተቋማት፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሙያ ማኀበራትና ማኀበራዊ ተቋማት ይህ ጉዳይ የራሳቸው ጉዳይ መሆኑን ከወዲሁ ተረድተው ቅራኔውን ተቀራርቦ በመወያየት መፍትሄ እንዲያገኝ ገንቢ ግፊትና ጥረት እንዲያደርጉ ኢዴፓ ጥሪውን ያስተላልፋል።
ሰላምና ሕብረ ብሔራዊነት ዓላማችን ነው
የኢዴፓ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ከመላ ኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
‘‘ኢህአዴግ የኢትዮጵያን ሕዝበ ሙስሊም ጥያቄ በኃይል፣ በጠመንጃ መፍታትን ያቁም’’
ኢህአዴግ የሕዝበ ሙስሊም ጥያቄን በኃይል፣ በጠመንጃ ለመፍታት መሞከር ችግሩን አባባሰው እንጂ ሊፈታው ስላልቻለ ኢህአዴግ ያሰራቸውን ሕዝበ ሙስሊም በአስቸኳይ ፈቶ የኢትዮጵያ ሕዝበ ሙስሊም ጥያቄ በዲሞክራሲያዊ ውይይት እንዲፈታ ጥሪአችንን እናቀርባለን።
በአዲስ አበባ ከተማ በአወሊያ ት/ቤት የተቀሰቀሰው ጥያቄ ዛሬ ተስፋፍቶ በአገሪቷ ላይ ሊፈታ ወደማይችልበት እድገት ሊደርስ የቻለው የገዥው ፓርቲ ‘‘ኢህአዴግ’’ የኃይል የጠመንጃ አፈሙዝ እርምጃ በመሆኑ በአስቸኳይ በቶሎ እርምት ተወስዶ ወደ ዲሞክራሲያዊ ውይይት እንዲመለሱ ጥሪአችንን እናቀርባለን።
ኢህአዴግ በሺ የሚቆጠር ሕዝብ ኢድአልፈጥር የበዓል አከባበር ተንተርሶ ያሰራቸውን ሁሉ እንዲፈታም ጥሪአችንን እናቀርባለን። ዛሬ ‘‘የኢህአዴግን’’ የኃይል እርምጃ ምክንያት በማድረግ ብዙ ሕዝብ አገሩን ለቆ ወደ ሌላ አገር በመኮብለል ላይ ስለሚገኝ ገዢው ፓርቲ ስህተቱን በአስቸኳይ በማረም ወደ ዲሞክራሲያዊ ውይይት እንዲመለስ እንጠይቃለን።
ኢህአዴግ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄም ሆነ የጐረቤት አገር ጥያቄን በዲሞክራሲያዊ ውይይት የማይፈታ ከሆነና ወደ ኃይል እርምጃ የሚዞር ከሆነ በአሁኑ ጊዜ እየተሰሩ ያሉት ትላልቅ የልማት ስራዎች ስለሚደናቀፉ ‘‘ኢህአዴግ የአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ መንገድን ይዞ አገሪቷን እንዲመራ ጥሪአችንን እናቀርባለን።’’n
ምንጭ ሰንደቅ ጋዜጣ