በኢትዮጵያ የሚገኘው የፍትህ ስርዓት ራሱን እንደ ካሮት ቁልቁል ማሳደግ ከጀመረ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ የፍትህ ስርዓቱ ዋነኛ መገለጫ በሆኑ ፍርድ ቤቶች ዳኞች ውሳኔ የሚሰጡባቸው ጉዳዩች ‹‹ፍትህ››መሳቂያ መሳለቂያ መሆኗን በገሃድ እያሳዩን ይገኛሉ፡፡
በእነ ኤልያስ ክፍሌ የክስ መዝገብ ስሟ ሰፍሮ በ2004 በቁጥጥር ስር የዋለችው ወይዘሮ ሂሩት ክፍሌ የፍትህ ስርዓቱ ወደለየለት ውርደት ውስጥ ለመዘፈቁ የቀረበባት ክስ አይነተኛ ማሳያ ተደርጎ ሊጠቀስ ቢችልም በዚህ ዝቃጭ ክስ ከልጇ ተነጥላ 19 ዓመት የተፈረደባት መሆኑ ግን ያሳቅቃል፡፡
ከሀዋሳ የተያዘችው ሂሩት አሜሪካን አገር ከሚገኘው ጋዜጠኛ ኤልያስ ክፍሌ ትዕዛዝ በመቀበል ‹‹በቃ››የሚል ጽሁፍ በማጻፍ በከተማው ውስጥ ለማሰራጨት ስትዘጋጅ ተይዛለች››የሚል ክስ ቀርቦባት ፍርድ ቤቱ ይህ ሽብር ነው በማለቱ 19 ዓመት በይኖባታል፡፡
አስገራሚው ነገር ሂሩት ላይ በምስክርነት የቀረቡ ሰዎች ‹‹በቃ››የሚል ጽሁፍ በኮምፒውተር እንዲጻፍላት ከጠየቀች በኋላ ትታዋለች››በማለት መናገራቸው ነው፡፡አስባ ትታዋለች በተባለ ሁለት ፊደል የተነሳ አቃቤ ህግ የኤልያስ ክፍሌ ተባባሪ ናቸው ካላቸው ጋዜጠኛ ርዕዩት ዓለሙ፣ውብሸት ታዬና ዘሪሁን ገ/እግዚአብሄር ጋር በአንድ የክስ መዝገብ ስሟን አስፍሯል፡፡
ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ለንባብ ባበቃው ‹‹የነጻነት ድምጾች››መጽሐፉ እርሱና ዘሪሁን ሂሩትን ለመጀመሪያ ግዜ የተዋወቋት በማዕከላዊ ግቢ ውስጥ አሻራ እንዲሰጡ በተጠሩበት ወቅት መሆኑን በማስታወስ በወቅቱም ሂሩት በመገረም ‹‹ታውቁኛላችሁ፣ኤልያስ ክፍሌ የሚባለውስ ሰው ምን አይነት ነው››በማለት እንደጠየቀቻቸው አስፍሯል፡፡
ሂሩት ክፍሌ በአስቂኙ ፍርድ ቤት የተጣለባትን የፍርድ ውሳኔ በአሁኑ ወቅት በቃሊቲ ወህኒ ቤት በማሳለፍ ላይ የምትገኝ ሲሆን ሁለቱ ስዊዲናዊያን ጋዜጠኞች የይቅርታ ጥያቄ ባቀረቡበት ወቅትም ሂሩት ምንም እንኳን ወንጀል የተፈጸመባት እርሷ ብትሆንም ፎርሙን በመሙላት አሳሪዎቿ ስህተታቸውን የሚያርሙበት ዕድል እንዲያገኙ ብታደርግም ጥያቄዋን ውድቅ በማድረግ በፍትህ ላይ በድጋሚ ተሳልቀዋል፡፡