የዞን9 ማስታወሻ
በእነ ሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው ከአንድ አመት በላይ እየተጓተተ ከሚገኙት አራቱ የዞን 9 ጦማርያን ለነሀሴ 13/2007 ዓ.ም ለብይን ተቀጥረዋል፡፡
ዛሬ ሐምሌ 22 ቀን 2007 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛ “ፍርድ ቤት” ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት ጦማርያኑ በተከታታይ ቀጠሮ በተሰጠበትና እልባት ባላገኘው ‹ተከሳሾች መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ ይሰናበቱ ወይስ ይከላከሉ› በሚለው ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ፍርድ ቤቱ ሌላ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
መዝገቡ ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው የአቃቤ ህግ የደረጃ ምስክሮች ቃል ከመቅረጸ ድምጽ ተገልብጦ በጽሁፍ ከመዝገቡ ጋር መያያዙን ለመጠባበቅ ነበር፡፡ በዚህም ፍርድ ቤቱ የምስክሮቹ ቃል በጽሁፍ ተገልብጦ ከመዝገቡ ጋር መያያዙን በመግለጽ መዝገቡን መርምሮ ተከሳሾች መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ ይሰናበቱ ወይስ መከላከል ያስፈልጋቸዋል የሚለውን ለመበየን ለነሀሴ 13/2007 ቀጠሮ ይዟል፡፡
የተሰጠው የቀጠሮ ጊዜ ረዘመ በሚል ቀጠሮው አጭር እንዲሆን የተከሳሾች ጠበቃ ቢጠይቁም ፍርድ ቤቱ ‹‹ከተያያዘው የመዝገብ ብዛት አንጻር ከነሀሴ 13/2007 በፊት አይደርስልንም›› በማለት የተሰጠው ጊዜ ምክንያታዊ እንደሆነ ለማስረዳት ሞክሯል፡፡ ጠበቃው በበኩላቸው ‹‹መዝገቡ ብዙ ቢመስልም የተጠቀሰውን ያህል ጊዜ ሊወስድ አይችልም ብለን ስለምናምን አጭር ቀጠሮ ይሰጠን፤ በሌላ በኩል ክሱ ከተቋረጠላቸው ሰዎች ጋር በተያያዘ መዝገቡ እንደቀነሰ እናምናለን›› በማለት መዝገቡ ከተባለው ጊዜ በፊት ተመርምሮ ብይን ሊሰጥ ይገባል በሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ሆኖም ግን ፍርድ ቤቱ ከነሀሴ 15/2007 ዓ.ም በኋላ እንደማይሰየም በመግለጽ፣ ከዚያ በፊት ነሀሴ 13/2007 ዓ.ም ብይኑን ለማድረስ፣ ካልተቻለ ደግሞ እስከ 15/2007 ባሉት ሁለት ቀናት ለመጨረስ እንደሚሞክር በመግለጽ ቀጠሮውን በነሀሴ 13/2007 ዓ.ም አጽንቷል፡፡
በዛሬው ውሎ ከቂሊንጦ እስር ቤት በፍቃዱ ኃይሉ፣ አጥናፍ ብርሃኔ፣ አቤል ዋበላና ናትናኤል ፈለቀ የቀረቡ ሲሆን አሁን በክስ ላይ ከሚገኙት ውስጥ አንደኛ ተከሳሽ የሆነችው ሶልያና ሽመልስ በሌለችበት ጉዳያቸው ለአጭር ጊዜ ታይቷል፡፡
የዞን9 ማስታወሻ
የዞን9 ጦማርያንን የፍርድ ቤት ሂደት በማጓተት ያልተሰራ ወንጀልን መፍጠር አይቻልም፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ጉዳየዮን ማንጓተቱን ያቆም ዘንድ የመንግስት ስራ አስፈጻሚ አካላት በጉዳዬ ላይ ውሳኔያቸውን በአፋጣኝ እንዲሰጡልን ለመጠየቅ እንወዳለን፡፡