Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የሰማዕቱ ቅዱስ አቡነ ጴጥሮስ ድምጽ

$
0
0

ሐምሌ 22 ቀን 1928 / ሰማዕትነት የተቀበሉበት ቀን

በሰላሌ አውራጃ ፍቼ ከተማ የተወልዱት አቡነ ጴጥሮስ ገና በለጋ እድሜአቸው ወደ ደብረ ሊባኖስ በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርታቸውም በመከታተል ያደጉ ቅዱስ አባት ናቸው። ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ትልቅ ሰው አንዱ የሆኑት አቡነ ጴጥሮስ ላገራችን በሰሩት ስራ ሁሌም ልናስባቸው እና ልናከብራቸው  የሚገባ አባት ናቸው።

Abune Petrosጣሊያን ኢትዮጵያን ሊወር በመጡ ሰዓት ከቤተ መንግስቱ  ቀጥሎ ትልቅ ቦታ የነበራት ቤተ ክህነት ነበረች። ጣሊያንም ይህንን በቅጡ ስለተረዱ ቤተ ክህነትን ካሳመንን  ኢትዮጵያን በቀላሉ መቆጣጠር እንችላለን የሚል ግምት አድሮባቸው መልእክተኛ ወደ አቡነ ጴጥሮስ ይልካሉ። የተላኩት የአገራችን ዜጎች ቢሆኑም ነገር ግን የአገርን ክብር አሳልፎ በመስጠት ለጣሊያን አገልጋይ የሆኑ ባንዳዎች ነበሩ። የጣሊያን ቅጥረኛ በመሆን ዜጋዎችን በማስገደል በማሳደድ ስራ የተሰማሩ የአገር መረጃን አሳልፎ ለጠላት በመስጠት ለሆዳቸው ያደሩ ሆድ አደሮች ናቸው። እነዚህ ባንዳዎች አቡነ ጴጥሮስ ጋር በመቅረብ  ኢትዮጵያ በጣልያን ስር እንድትሆን እንዲስማሙ ይወተውቷቸው ጀመር የመጡት ቅጥረኛ ባንዳዎች ከጣልያኖች የተሸለሙትን ኒሻን በደረታቸው ላይ አንጠልጥለው ነበረ። አቡነ ጴጥሮስም ሁሉንም ከቃኙ በኋላ የአገር ልጅ ሆነው የአገሩን ልጅ በማስገደል እና የአገርን ክብር አሳልፈው ለጠላት በመስጠት የተሰማሩትን….. ትሰማላችሁ አሏቸው ደረታችሁ ላይ ያንጠለጠላችሁት የክብር ኒሻን ሳይሆን የወገኖቻችሁ ደም ነው። የአገርን ክብር አሳልፎ በመስጠት ወንድሞቻችሁን እና እህቶቻችሁን በማስገደል የተሸለማችሁት ኒሻን ነው። ይህንን ኒሻን አውልቁና ጣሉት ካሉዋቸው በኋላ በሉ ሂዱና ለላኳችሁ ጣልያኖች ሃይማኖትን ለሚያጠፋ ህዝቤን በባርነት ለመግዛት ለሚሻ አገሬን አሳልፌ አልሰጥም በሏቸው አሏቸው። መልክተኞቹ የሆነውን ሁሉ ለጣልያኖቹ ነገሯቸው የዚህን ግዜ እንዴት ሃሳባችንን አይቀበልም ብለው ተናደዱ በአደባባይም ሊገድሏቸው ወሰኑ። አቡነ ጴጥሮስን በመግደል ህዝቡ ደንግጦ ይገዛልናል በማለት ሊገድሏቸው ወደ አደባባይ አወጧቸው። አነጣጣሪ ተኳሾች በአስር ሜትር ርቀት ባልሞላ መሳሪያቸውን በመያዝ ተንበርክከው ወደ አቡነ ጴጥሮስ እንዲደቅኑ የጣልያኑ አዛዥ ትእዛዝ አስተላለፈ ተኳሾችም እንደታዘዙት አደረጉ ይህንን አይተው ፈርተው ሃሳባቸውን ይቀይራሉ በማለት ተኳሾችን መሳሪያውን ከአቡነ ጴጥሮስ ላይ እንዲነሳ በማዘዝ አሁን የመጨረሻ እድል እንስጦ ምን ይላሉ አሏቸው።

አቡነ ጴጥሮስም እንዲህ በማለት ተናገሩ፡- አገር አፍራሽ፡ ሃይማኖት ለዋጭ፡ ለሆነው ጠላት አገሬን አሳልፌ አልሰጥም እውነትን በሃሰት ክብሬንም በነውር አለውጥም የሸዋ ህዝብ ሆይ ስማኝ፣ የጎጋም ህዝብ ሆይ ስማኝ፣ የጅማ ህዝብ ሆይ ስማኝ፣ የወለጋ ህዝብ ሆይ ስማኝ፣ የጎንደር ህዝብ ሆይ ስማኝ፣ የሃረር ህዝብ ሆይ ስማኝ የትግራይ ህዝብ ሆይ ስማኝ ሃገርህን ለባእድ አሳልፈህ እንዳትሰጥ  ሃይማኖትህንም ለውጠህ እንዳትገኝ ይህንን ያደራ ቃሌን ስሙኝ በምድር የሰጠኋችሁን አደራ ጠብቁ ብለው በእጃቸው የያዟትን ሰዓት አየት አደረጓት። የቡነ ጴጥሮስ ቃል በእውነት የተሞላ፣ የአገር ወዳድነት ስሜት የተላበሰ፣ ስለ ህዝብ ፍቅር እስከ ሰማዕትነት የደረሰ፣ ጥቅማ ጥቅም ያለወጣቸው፣ እውነትን ተናግረው፣ እውነትን ለብሰው፣ ስለ እውነት የኖሩ፣ እውነትን ይዘው ሰማዕትነትን የተቀበሉ፣ የኢትዮጵያ ብርቅዬ አባት ናቸው።

የጣልያኑ አዛዝም ተንበርክከው ለነበሩት ታጣቂዎች እንዲገደሏቸው ትዕዛዝ አስተላለፉ ተኳሾችም ስምንቱም በመተኮስ አቡነ ጴትሮስ በአደባባይ ስለ አገር ክብር ስለ ህዝብ ፍቅር ብለው ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ/ም የሰማዕትነትን ክብር ተቀበሉ። ከዛች ሰዓት ጀምሮ  በታላቅ ቁጣ ህዝቡ ተነሳ ጣልያንንም ከኢትዮጵያ ምድር ለማጥፋት ሁሉም ህዝብ ውስጥ የጽናት ሃይልን ከአብነ ጴጥሮስ ተቀብሎ ሄዱ ጽናት አስተማሪ እውነተኛ አባት የአባቶችን ድምጽ ሰሚ እውነተኛ ህዝብ በዘመኑ ነበሩና የድሉን ብስራት ጣሊያንን ከኢትዮጵያ በማባረር የአቡነ ጴጥሮስን ቃል ተግብረዋል።

ዛሬም እንደ አቡነ ጴጥሮስ አይነት አባት በእውነት መንገድ ላይ በመቆም ስለ አገሩ፣ ስለ ህዝቡ፣ ስለ ሃይማኖቱ በክብር የቆመ የሃይማኖት አባት ያስፈልጉናል ያባቶችን ቃል ፈጻሚ ባገሩ የማይደራደር፣ በሃይማኖቱ የማይደራደር ለጠላት የማይገዛ እውነተኛ ትውልድ ያስፈልጋል። ህዝቡን ወዳጅ አገሩን የሚወድ ለእውነት የቆመ ትውልድ ያስፈልገናል።

እንግዲህ ሁላችን ወደ ልቦናችን እንመለስ ያኔ ከእውነት ጋር እንገናኛለን፣ ያኔ ስለ አገር እናስባለን ያኔ፣ ያኔ ስለ ሃይማኖት እንኖራለን፣ ያኔም አሸናፊዎች እንሆናለን።

ስለ አገር ክብር  ስለ ህዝብ ፍቅር በእውነት በመቆም የተሰውቱን ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስን ሁላችን በክብር እናስባቸው።

ከተማ ዋቅጅራ

28.07.2015

Email waqjirak@yahoo.com

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles